Print this page
Monday, 11 September 2017 00:00

“የበጎ ሰው ሽልማት” አሸናፊዎች - ደስታቸው፣ተስፋቸውና ስጋታቸው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው እሁድ ነሐሴ 29 ቀን 2009 ዓ.ም አምስተኛው ዙር “የበጎ ሰው ሽልማት” ሥነ-ስርዓት በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ
እስከ ምሽት ድረስ ተካሂዷል፡፡ ዘንድሮ ሽልማቱ “ለኢትዮጵያ በጎ ያደረጉ የውጭ አገር ዜጎች” የሚል አዲስ ዘርፍ ያከለ ሲሆን በአጠቃላይ በ10
ዘርፎች ከተመረጡት 30 እጩዎች መካከል አስሩ ተሸልመዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከተሸለሙት መካከል ጥቂቶቹን
አነጋግራቸዋለች፡፡ በሽልማታቸው ዙሪያ፣ስላሳለፍነው ፈታኝ ዓመት፣ ከፊታችን ቆሞ ስለሚጠብቀን አዲስ ዓመት እንዲሁ ስለ አገራቸው
ኢትዮጵያ ተስፋና ስጋታቸውን አጋርተዋታል፡፡ እነሆ


                      “2009፤ መንፈሣዊ ቆፈን የተፈጠረበት ዓመት ነበር”
                        (ዲ/ን ዳንኤል ክብረት፤”የበጎ ሰው ሽልማት” ኮሚቴ ሰብሳቢ)

     የዘንድሮውን “የበጎ ሰው ሽልማት” ስንመለከት በጣም ጥሩ ነበረ፡፡ አንደኛ፤ እንደ ዕድል ሆኖ የተመረጡት ሰዎች በጣም ትልልቅና ለዚህች አገር ብዙ ሰርተው እውቅናና ክብር ያልተሰጣቸው ናቸው፡፡ ዘንድሮ የተካተተው “ለኢትዮጵያ በጎ የሰሩ የውጭ አገር ዜጎች” የሚለውም ዘርፍ፣ በዶ/ር ካትሪን ሀምሊን መጀመሩ ለእኛ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሽልማቱ የተካሄደበት ኢንተርኮንትኔንታል ሆቴልም፣ እንግዶች ያለ ችግር ብዙ ሰዓት፣ በምቾት መቀመጥ የሚችሉበት መሆኑ ደስ ያሰኛል። ሥነ ስርዓቱ በENN የቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት መተላለፉና ብዙ ኢትዮጵያውያን በምስራቅ አፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ ሆነው ፕሮግራሙን መከታተል መቻላቸው ትልቅ ነገር ነው፡፡  በማህበራዊ ሚዲያ መተላለፉም በሌሎች ዓለማት ያሉት ሰዎች እንዲከታተሉት አስችሏቸዋል፡፡ ይሄ ለተሸላሚዎቹ ብቻ ሳይሆን ሸላሚዎቹም በራሳቸው ትልልቅ ሰዎች በመሆናቸው፣ ለእኛ ከፍና ለየት ያለ የሽልማት ስነ-ስርዓት ሆኖልናል፡፡ 2009 ዓ.ም በተለይ በዓመቱ መጀመሪያ፣ አገሪቱ ላይ በነበረው ግርግር፣ የሰዎች ህይወት ማለፉ፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ እሬቻ በዓል ላይ በተከሰተው ችግር፣ የብዙ ወገኖቻችን ህይወት መቀጠፉ፣ በክልሎችም መካከል በድንበርና በተለያዩ ያልተፈቱ ቅራኔዎች ምክንያት ግጭቶች መፈጠራቸው ትርምስ መፈጠሩ --- ያለፈውን  ዓመት፣ በጤና ይጠናቀቃል ብሎ ለማሰብ ይከብድ ነበር፡፡ የ”ቆሼ”ውም አደጋ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ብዙ ሊጠቀሱ የሚችሉ ችግሮች የተከሰቱበት ዓመት ነው፡፡ ይሄ ጉዳይ ደግሞ ከጥናት፣ ከድርሰት፣ ከፅሁፍ ጋር ስናያይዘው፣መንፈሳችንን ስለሚጨብጠው ለስራም ምቹ አልነበረም፡፡ በዚህ የተነሳ “2009፤ መንፈሳዊ ቆፈን የተፈጠረበት ዓመት ነው” ብዬ ነው የምገልፀው፡፡
አዲሱ ዓመት ቢሆን የምመኘው፡- የምንግባባበት፣ ችግሮቻችንን በባህሎቻችን የምንፈታበት፣ ጠንካራና ረጅም ዘመን የቆየ ባህል ስላለን፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የየብሄረሰቡና የሀይማኖት ልሂቆች ሰብሰብ ብለው፣ ለድንበሩም ለግጭቱም ለሁሉም ነገር ባህላዊ መፍትሄ በማምጣት ሰላም ማውረድ እንድንችል ነው፡፡ ይሄን የምለው፣ባህላዊ መንገዱንና መፍትሄውን አልሞከርነው ብዬ ስለማምን ነው፡፡ በአዲሱ ዓመት ሁላችንም የምንኮራባትና የምንጠቀምባት ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ምኞቴ ነው፡፡ ለሁሉም መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ!!

---------------------

                               “የሽልማቴን መታሰቢያነት በቅርቡ ላጣናት ሀኪም አድርጌዋለሁ”
                                   (ዶ/ር መስፍን አርአያ፤ የመንግስት ኃላፊነትን በመወጣት “የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ”)

       በሽልማቱ ክብርና ምስጋና ተሰምቶኛል፡፡ በዚህ ስሜት ውስጥ ደግሞ ራሴን ሳይሆን ሌሎች ከእኔ በላይ የደከሙ፣ነገር ግን ያልታዩና ያልተዘመራላቸው ባለሙያዎችን ነው ያየሁት፡፡ ስለዚህ ክብሩን ለእነሱም በመስጠት ነው የሽልማቱን ስሜት ያጣጣምኩት፡፡ እርግጥ እኔ ከ30 ዓመት በላይ መንግስትና ህዝብን ባገለገልም ሌሎችም ከእኔ እድሜ በላይና በታች ሆነው፣ ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው፣ ህዝባቸውን መንግስታቸውንና አገራቸውን ያገለገሉ ስላሉ፣ ክብሩንና ምስጋናውን እነሱም እንዳገኙት ነው የተሰማኝ፡፡  እነሱም ለዚህ ሽልማት ቢበቁ ደስታዬ ነው፤ምክንያቱም ድምፃቸውን ሳያሰሙ አንገታቸውን ደፍተው ጠንክረው የሚሰሩ ብዙ ኢትዮጵያዊን አሉ፡፡
2009 እንዴት አለፈ ላልሺኝ? እኔ መምህርና ሀኪም በመሆን፣ የህዝብና የመንግስት አገልጋይ ነኝ። በአስተማሪነቴም በሀኪምነቴም ብዙ የሚያጋጥሙኝ ነገሮች አሉ፡፡ ደስታን በተመለከተ የማስተምራቸው ከአንዱ ደረጃ ወደ አንዱ ደረጃ በእውቀታቸው ከእኔም ጭምር እየተሻሉ ሲሄዱ ማየት ትልቅ ነገር ነው፡፡ አንድ መምህር፤ እንደ አንድ ወላጅ፣ ልጁ አድጎ፣ በእድሜም በእውቀትም ጎልብቶ ማየት ይፈልጋልና፡፡ ባለፈው ዓመት በአገራችን የነበረውን አለመረጋጋትና የሰላም መደፍረስ እንዲሁም የተከሰተውን ድርቅ ሳስብ በጣም ያመኛል፡፡ ምክንያቱም በአገራችን ቢያንስ መሰረታዊ ነገሮችን አግኝተን፣ በእኔም ሙያ አስፈላጊው የህክምናና የትምህርት አቅርቦት ተሟልቶልን፣ ወደ ህክምና የሚመጡ ህሙማን፣በቂ ህክምናና መድሀኒት አግኝተው፣ ህመምና ህመምተኛ ቀንሶ ማየት የምፈልግ ሀኪም ነኝና፡፡  በ2009 ዓ.ም ብዙ ውጣ ውረድ ማሳለፋችንን ሳስታውስ፣ ዓመቱ የራሱ የሆነ ጥቁር ነጥቦችን ትቶ አልፏል ብዬ አስባለሁ። ለሀኪም የሚያክመው በሽተኛ፣ህሙም ብሶበት ሲያይ ያመዋል፤ ሲሞትበት ደግሞ ልክ እንደ ሟቹ ቤተሰብ ሁሉ በጣም ያዝናል፡፡ በቅርቡ ደግሞ ትልቅ ህመም የሆነብኝ፣ እኔ ያስተማርኳት አንድ የህፃናትና የአዕምሮ ሀኪም በሞት መለየቷ ነው፡፡ ዶ/ር ብርቄ አንበሴ ትባላለች፡፡ ጎበዝ ሀኪም ነበረች፡፡ በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ የበጎ ሰው ሽልማት ደስታ ቢፈጥርልኝም፣ ይህቺ ብርቅዬ የሆነች ጎበዝ ባለሙያ በሞት መለየቷ ደስታዬን ያደበዝዘዋል፡፡ ምክንያቱም እሷን የመሰለ የህፃናትና የወጣቶች የአዕምሮ ሀኪም ማጣት ትልቅ ኪሳራ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ካገኘሁት ደስታ በላይ ያጣኋት የሥራ ባልደረባዬ ሀዘን ያመዝናል። ያገኘሁትን ሽልማት መታሰቢያነቱን ለዚህች መልካም ባለሙያ አድርጌዋለሁ፡፡
አዲስ ዓመት እንዲህ አይነት አሳዛኝ ነገር የማናይበት፤ ሰላም የሚሰፍንበት፣ ምንም እንኳን ድርቅና ረሀብ በአጭር ጊዜ ይቀረፋል ባልልም፣ ቢያንስ ወገኖቻችን የማይራቡበት፣ ተማሪዎች ውጤታቸውን የሚያዩበት፣ የመንግስት ሰራተኞችም ሆኑ ሌሎች ሰራተኞች፣ ስራቸውን በትኩረትና በታማኝነት የሚሰሩበት፣ በተለይ የህክምና ባለሙያዎች፣ ህሙማን ወደ ተቋማችን ሲመጡ በቅንነት አገልግለን፣ ህመማቸውን በማስታገስ፣ ከዚያም አልፎ ሞትን የምንቀንስበት ዓመት ይሁንልን እላለሁ፡፡ የሚዲያ ባለሙያዎችም ታማኝና ሚዛናዊ ሥራ ለህዝብ የምታቀርቡበት ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡

-----------------------


                               “እንኳን ተሸልመን እጩ መሆናችን በራሱ ሽልማት ነው”
                                  (አቶ ጸሃይዬ ዘሙይ፤” የበጎ ሰው የሥራ ፈጠራ ተሸላሚ”)

     መጀመሪያ በሽልማት ሥነሥርዓቱ ላይ እንድሳተፍ ስጠየቅ፣ብዙም ፈቃደኛ አልነበርኩም። ነገር ግን ብዙ ሰዎች ለምን አትሳተፍም፤ ይሄ መልካም ነገር ነው ብለው ገፋፉኝ፡፡ እኔም በመሃል ወደ ውጭ ሄጄ ነበር፡፡ ስመለስ አገኘኋቸው፡፡ እጩ ሆናችኋል ተባልኩ እንጂ ሌላ የሰማሁት ዝርዝር አልነበረም፡፡ እሸለማለሁ የሚል ሃሳብ በህልሜም በእውኔም የለም፡፡ በቢዝነስ ማህበረሰብ ውስጥ ይሄ ዕውቅና ትልቅ ነው፡፡ በህዝብ ተመርጠሽ፣ ፍትሃዊ በሆነ ዳኝነት ተለክተሽ፣ ሽልማትና ዕውቅና ማግኘት ቀላል አይደለም፡፡
የሽልማት ሥነሥርዓቱ ዝግጅትና ድምቀት፣ ሁሉ ነገር በጣም ትልቅ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ እኔ ፊት ወንበር ላይ ተቀመጥ ሲሉኝ ሁሉ፤ “በፍፁም ከፊት አልቀመጥም፣ ከህዝቡ ጋር አቀመጣለሁ” ብዬ እምቢ አልኩ፡፡ ከፊት ለእጩዎች የተዘጋጀ ቦታ አለ ብለው፣ ከፊት አስቀምጡኝ፤ ይሄ ሁሉ ሂደት ለእኔ አዲስ ነው። ግራ ተጋብቼ ነበር፡፡ እርግጥ ሸዋ ዳቦ ከተቋቋመ ከ60 ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ አንድ የሽልማት ድርጅት፣ የተቋማችንን ስራ ፈትሾ፣ ለህዝብ ዳኝነት አቅርቦ፣ “አይዞህ በርታ” የሚል እውቅና መስጠቱ አስደስቶኛል። እንኳን ተሸልመን እጩ መሆናችን በራሱ ሽልማት ነው፡፡ ከእኔም በላይ የድርጅቱ ባለቤቶችና ሰራተኞች ጭምር ደስተኞች ሆነዋል፡፡ የሽልማት ድርጅቱን እናመሰግናለን፡፡ በሌላ በኩል፤በየዘርፉ ለሽልማት የተመረጡ ሰዎች ትልልቅና ለአገርና ለህዝብ ብዙ ውለታ የሰሩ በመሆናቸው፣ ከእነሱ እኩል መሸለምም ትልቅ ኩራት ነው፡፡
እንግዲህ በሰው በህይወት እስካለ ድረስ ብዙ የሚያስደስቱም የሚያሳዝኑም ነገሮች ይገጥሙታል። እኛ እንደ ሸዋ ዳቦ፤ በሥራችን ደስተኞች ነን፡፡ ሰርቶ መዋሉ በራሱ ትልቁ ነገር ነውና፡፡ እድገትም እያየን ነው ፡ኑሯችንንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደየ አቅማችን እያሻሻልን ነው፡፡
በአገር ደረጃ ያለፈውን ዓመት ስናየው፣ በጎርፍ፣ በቆሼ፣ በሰላም ማጣት፣ በትራፊክ አደጋና በተለያዩ ጉዳዮች፣ ህዝባችን ችግር ውስጥ ነበር፡፡ በተለይ የቆሼው አደጋ ሲከሰት እኔ ውጭ አገር ሆኜ እከታተል ነበር፡፡ ተጎጂዎችን ለማገዝ ተሳትፎ አድርገናል፡፡ ባለፈው ዓመት የተከሰቱት ችግሮች ከማሳዘንም በላይ ነበሩ፡፡ መጪው ዓመት ካለፉት ዓመታት በተሻለ አደጋ የሚቀንስበት፣ በአጠቃላይ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነበት፣ የስኬትና የብልፅግና አመት እንዲሆን እየተመኘሁ፣ ለመላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን መልካም አዲስ አመት እላለሁ፡፡

-------------------------

                                     “የአባቴም ስራ ዘመን ተሻግሯል ማለት ነው እንድል አድርጎኛል”
                                          (“የበጎ ሰው ልዩ ተሸላሚ”፣ የክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ልጅ፣ ታደለ ይድነቃቸው)

      ሽልማቱ ጥሩ ስሜት የሚፈጥር ነው። ያስደስተኝ ልዩ ተሸላሚ መሆኑ ብቻም አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው ሸላሚዎቹ አባቴን አልደረሱበትም፡፡ አንድም በእሱ ዘመን አልተወለዱም፤ ተወልደውም ከሆነ በጣም ለጋ እድሜ ላይ የነበሩ ስለሚሆኑ፣ ስራ ላይ በነበረበት ጊዜ አያውቁትም፡፡ የሸላሚ ድርጅቱ የኮሚቴ አባላትን ማለቴ ነው፡፡ ከነሱ ትንሽ ከፍ የሚለው ዲያቆን ዳንኤል ይመስለኛል፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ እንዲህ አይነት እውቅናና ሽልማት በጣም ደስ ይላል፡፡ የአባቴም ስራ ዘመን ተሻግሯል ማለት ነው ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል፡፡ በቀድሞው  ትውልድ ሲሰራው የነበረው ስራ በጣም ይታወቃል፡፡ በሚዲያም ህዝቡ ይከታተለው ነበር፡፡ በወቅቱ ያልነበረውና ሲሰራ ያላየው ይሄኛው ትውልድ፣ ሲያስታውሰው ደግሞ የተለየ ደስታ ፈጥሮብኛል። ሌላው ደግሞ ነሐሴ 13፣ የሞተበት 30ኛ ዓመት ነበር፡፡ የፊታችን መስከረም 1 ቀን 2010 ዓ.ም ደግሞ 95ኛ ዓመት ዕድሜው ነው፡፡ በነዚህ ነገሮች መሀል ሽልማቱን ማግኘት፣ የልደቱም የሙት አመቱም መታሰቢያም በመሆኑ እስከ ዛሬ ከተሸላማቸው በርካታ ሽልማቶች ለየት ያደርገዋል፡፡ እሱ በሕይወት እያለ ከተሸለማቸው ይልቅ ካለፈ በኋላ የተሸለማቸው ይበረክታሉ። ይሄኛው ግን በጣም ለየት ያለ ነው፡፡ እኔም ተደስቼበታለሁ፡፡ የማከብረው ሽልማትም ነው፡፡
እኔ እንደሚታወቀው፤ አሁን ጡረታ ላይ ያለሁ ነጋዴ ነኝ፡፡ በስራ ዘመኔ ብዙ አላደረግሁም ብዬ የሚፀፅተኝ ነገር የለም፡፡ ብዙ ስራዎችን ሰርቻለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ በዚህ በጡረታ እድሜዬ፣ አሁን ላይ ያዘነበልኩት ወደ ታሪኩ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ብዙ እሰራለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ ላይም ብዙ እሰራለሁ፡፡ በዚህ ላይ ብዙ የተሳኩ ስራዎች ስላሉኝ ደስ ይለኛል፡፡
 እኔ እንደ አገር ዛሬ ሳይሆን ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያን የምመለከተውና የምመኘው፣ የምንነጋገርበት ዘመን  እንዲመጣ ነው፡፡ በሀሳብ መለያየት እንደ ወንጀል የማይታይበት፣ በሃሳብ መለያየት የማያገዳድልበት፣ የሚነጋገርና የሰለጠነ ህዝብ “ቆሼን” አይደለም፣ ድርቅን አይደለም ማንኛውንም ችግር መቋቋም ይችላል፡፡ 2009 ትንሽ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች፣ በህዝቡ ላይ ጫና ፈጥረው ነበር፡፡ በ2010  ደግሞ የምንነጋርበት፣ ከእነ ልዩነታችን ተከባብረን የምንዘልቅበት፣ በማንስማማባቸው ነገሮች ላይ ደግሞ ላለመስማማት ተስማምተን፣ በሰላም የምንጓዝበት ዓመት እንዲሆንልን እመኛለሁ። መልካም አዲስ አመት! ለሁሉም እመኛለሁ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡


-------------------

                                 “አዲሱ ዓመት፤ ሚሊዬነር የምሆንበት እንዲሆን እመኛለሁ”
                                       (“የዓመቱ የበጎ ሰው የኪነ ጥበብና ቴአትር ዘርፍ ተሸላሚ”፤ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ)

       በበጎ ሰው ተሸላሚነቴ የሚሰማኝ ቀደም ሲል ከነበሩት ሽልማቶች በበለጠ የሚዲያ ሽፋን ማግኘቴ ነው፡፡ ተወዳዳሪዎቼ የኔ የቀድሞ ተማሪዎች የነበሩ (ደቀመዛሙርቶቼ ልበላቸው) ናቸው፡፡ ከነሱ ጋር ለመወዳደርና ለመሸለም በመብቃቴ ደስ ብሎኛል፡፡ የኔ እኩዮች የነበሩት እነ ፀጋዬ ገ/መድህን፤ እነ አባተ መኩሪያ ቢኖሩና ከነሱ ጋር ብወዳደር ኖሮ ለየት ይል ነበር፡፡ አሁን ግን እኔን ከተኩትና ወደፊት ተሸላሚ ከሚሆኑት ጋር ተወዳድሬ  ሳሸንፍ፣ ሽልማቱ የእነሱም ጭምር እንደሆነ አስባለሁ፡፡
በግሌ 2009 ዓ.ም ጥሩ ዓመት ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ያሳለፍኩት በደስታ ነው፡፡ ሙሉ በሙሉ የተቃናልኝ ዓመት ነበር፡፡ በዓመቱ መጀመሪያ መስከረም 17 ላይ፣ የማንዴላ መፅሀፍ ትርጉሜን ጨርሼ የተመረቀበት ዕለት ነበር፡፡ የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት፣ ዶ/ር አድማሱ ነበሩ የመረቁልኝ፡፡ በቀጣይ ደግሞ የቤተ ኪነት ጥበባት የነበረው፣ የአሁኑ የባህል አዳራሽ፣ በኔ ስም መሰየሙ ሌላው ደስ የተሰኘሁበት ነው፡፡ ይህ ለእኔ ትልቅ ክብር ነው፡፡ በዚያውም  80ኛ ዓመት የልደት በዓሌም ተከብሯል፡፡ ይሄ ሁሉ ደግሞ በሕይወት እያለሁ መደረጉ በጣም አስደሳች ነው፡፡ እኔ ከሞትኩ በኋላ መደረጉ ምን ትርጉም ይሰጠኛል፡፡ በዚህ እድለኛና ስኬታማ የሆንኩበት ዓመት ነው - 2009 ዓ.ም፡፡
 በአገር ደረጃ ብዙ የተከሰቱ መልካም ያልሆነ ነገሮች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ መፅሀፌን በማስመርቅበትና ልደቴን በማከብርበት የዓመቱ መጀመሪያ፣ በኢሬቻ በዓል ላይ የሰው ህይወት ጠፍቷል፡፡ እንግዲህ ሰው በህይወት ሲኖር ኮሜዲና ትራጂዲ፣ ደስታና ሀዘን፣ ጎን ለጎን የሚሄዱ ናቸው፡፡ ሰርግና ሞት ያሉ ናቸው፡፡ ያንን ተመልክቻለሁ፡፡ በ2009 ዓ.ም ብቻ አይደለም፡፡ በ1997 ዓ.ም እነዛ ህፃናት፣ ጊዮርጊስ ላይ ሲጨፈጨፉ አይቻለሁ፡፡ ከዚያው ጎን ለጎን ደግሞ ኮንደሚኒየም ቤት ይመረቃል። ባቡሩ ይሰራል፡፡ ፎቁ ይገነባል፡፡ ኢንቨስትመንቱ ይጧጧፋል፡፡ እንግዲህ ህይወት ሁለቱንም አይነት መልክ (ሀዘኑንም ደስታውንም) ይዛ ትቀጥላለች፡፡ እኔም በእነዚህ ሁሉት ስሜቶች ውስጥ ነው ዓመቱን ያሳለፍኩት፡፡
እንግዲህ በአዲሱ አመት ከዘጠነኛው ወደ አስረኛው ሲገባ፣ ምንድን ነው የምትመኘው ስትይኝ፣ ከሚሊዮን በላይ ብር እንዲኖረኝ ነው የምመኘው፡፡ ይሄውልሽ፤እዚህ ሽልማት ላይ ካባ ያለብሱሻል፣ ሰርቲፍኬት ይሰጡሻል፣ ዋንጫ ይሸልሙሻል፡፡ ይሄ ሁሉ ግን አይበላም፣ አይጠጣም አይቆረጠምም፡፡ የሚበላው ብር ነው አይደለም እንዴ?! እኔ ደግሞ በ2010 ዓ.ም፣ ሚሊዮን ብር  እፈልጋለሁ፡፡ ከዚያም በላይ ባገኝ ደስ ይለኛል። ሆሆታው … እንኳን ደስ ያለህ፣ ካባውና ሌላው ነገር አይቆረጠምም፤ ብር ያስፈልጋል፡፡ እኔ ከዚህም በፊት መፅሀፍ ፅፌያለሁ፤ ሚሊዮን ብር እንዲያወጣ እፈልጋለሁ፡፡ በቴሌቪዥንም የምሰራው የስኬት ፕሮግራም በደንብ ስፖንሰር አግኝቶ፣ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉኝና፣ ይህ ሁሉ ተደማምሮ፣ ሚሊዬነር እንድሆን ነው- የ2010 ምኞቴ፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ደስታ፣ ጤና፣ ሰላም አግኝቶ በሰላም እንዲኖር እመኛለሁ፡፡ ለሁላችንም መልካም አዲስ አመት!

--------------------

                                “ዓመቱ አንድነታችንን በእጅጉ ተፈታትኖናል”
                                 (ያሬድ ሹመቴ፤ የፊልም ባለሙያና “የዓመቱ የበጎ ሰው ባህልና ቅርስ ተሸላሚ”፣” ጉዞ አድዋ” መሰራች አባል)

      ያለፈው ዓመት፤ በኢትዮጵያዊነታችን፣ በአንድነታችንና በህብረታችን ላይ አደጋ የተጋረጠበት ዓመት ነበረ፡፡ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ባለቁ ወገኖቻችን ያዘንኩበት ዓመት ነው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የአድዋ ድል በዓል ባልተለመደ መልኩ በወጣቶችና በአገር ወዳድ ዜጎች በድምቀት የተከበረበትና መንግስትም ለአድዋ በዓል ትኩረት ሰጥቶ፣ ቀኑን ያከበረበት በመሆኑ፣ ሌላው ተስፋ ሰጪ ነገር ነው፡፡ በሌላ በኩል “ጉዞ አድዋ” በቅርስና ባህል ዘርፍ፣ የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ፡፡ በዚህ ድል በየዓመቱ ከ1 ወር በላይ በእግራቸው እየተጓዙ፣ ውርጭና ፀሀይ ሳይበግራቸው፣ የኢትዮጵያዊያንና የመላው ጥቁሮች ኩራት የሆነው የአድዋ ድል፣ የበለጠ ትኩረት እንዲያገኝ ከማስቻላቸውም በላይ “ጉዞ አድዋ” እንዲሸለምና ለክብር እንዲበቃ በማድረጋቸው ኩራት ተሰምቶኛል፡፡
አዲሱ አመት፤ አንድነታችን፣ ሰላማችን የሚመለስበት፣ መንግስትም ከህንፃና ከግድግዳ ግንባታ ባለፈ በአንድነትና በሰላም ላይ የሚሰራበት፣ብሄራዊ እርቅና መግባባት የሚሰፍንበት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ መታወቂያችን ላይ “ብሄር” የሚለው ቃል፣ “ኢትዮጵያዊ” በሚል እንዲተካ፣ የጀመርነው ጉዞ በስኬት የሚጠናቀቅበት ይሁንልን፡፡ መንግስት ብሔራዊ መታወቂያ እሰጣለሁ ሲል የሰማሁት መሰለኝ፡፡ ያ ተሳክቶ የምናይበት፣ የረሀብ አደጋ ጠፍቶ፣ የተረጋጋ ሰላማችን የሚመለስበት፣ መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልን፡፡  ለመላው ኢትዮጵያዊያን፤መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡

Read 1393 times