Monday, 11 September 2017 00:00

ሶቅራጠስና ዘርዓያዕቆብ፣ አቴንስና አክሱም

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(2 votes)

 ከዛሬ 2400 ዓመታት በፊት ሶቅራጠስ በአቴንስ አደባባዮች ላይ አዲስ የሆነ የማስተማሪያ ዘዴ ይዞ መጣ፡፡ ይሄንንም የማስተማሪያ ዘዴ በኋላ ላይ አውሮፓውያን የሶቅራጠስ መንገድ (Socratic Method) ብለው ሰየሙት፡፡ የሶቅራጠስ መንገድ መሰረታዊ የህይወት ፅንሰ ሃሳቦችን (ለምሳሌ - ፍትህ፣ ውበት፣ ፍቅር፣ እውነት፣ መልካምነት…) ለመመርመርና ለመረዳት እንዲሁም ፅንሰ ሃሳቦቹ ላይ ያለውን ውዥንብር ለማፅዳት የሚጠቅም ዘዴ ነው፡፡ ዘዴው የሌሎች ሰዎችን መኖርና ተሳትፎ ስለሚጠይቅ የውይይት ዓይነት ባህሪ ያለው ሲሆን ግቡም በሐሳቦች ፍጭት አማካኝነት የፅንሰ ሃሳቦች ትክክለኛ ምንነትና እውነት ላይ መድረስ ነው፡፡ ፕሌቶም ይህንን ዘዴ በመጠቀም በርካታ መፅሐፎችን አሰናድቷል፡፡
ዘርዓያዕቆብም አክሱም እያለ ይሄንን የሶቅራጠስ መንገድ (የውይይት፣ የጥያቄና የመልስ መንገድ) ለ4 ዓመታት ተጠቅሞበታል፡፡ በዚህም የተነሳ የዘርዓያዕቆብ ወንበር የውይይትና የክርክር መድረክ መሆን ችሎ ነበር፡፡
ክርክርና ውይይት ደግሞ የሰውን መንፈስ የማበልፀግ ከፍተኛ ጉልበት አለው፡፡ “መንፈስ የሚበለፅገው በመነጋገር ነው” ይላሉ ዶ/ር እጓለም፤
መንፈስ ምንጊዜም ብቻውን አይገኝም፤ ከሌላው መሰሉ ጋር ሲገናኝ ይታያል እንጂ፡፡ ይሄንንም ስራ የሚያከናውንበት አንድ ህግ አለው - ዲያሌክቲክስ የሚባል፡፡ መንፈስ የሚበለፅገው በዲያሌክቲክስ ነው፡፡ ዲያሌክቲክስ ማለት የተቃርኖ፣ የክርክር፣ የውይይት ህግ ማለት ነው፡፡ በክርክር ውስጥ የዓለምና የህሊና ህግጋት የሚታወቅበት መንገድ ጉልህ ሆኖ ይታያል፡፡
ዘርዓያዕቆብ አክሱም ላይ ይሄንን የክርክር መንገድ ሲጠቀም የነበረው በክርክር ውስጥ የተማሪዎቹ ህሊና ይበልጥ እየነቃና እውነትንም እያወቀ እንደሚሄድ ስለተረዳ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ የዘርዓያዕቆብ አካሄድ በኢትዮጵያ የጥንቱ፣ የመካከለኛውና የአሁኑ ዘመን ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንግዳ ነው፡፡ በዚህም ህይወቱን አደጋ ላይ እንዲጥልና በርሃ ለበርሃ እስከመሰደድ አድርሶታል፡፡
ዘርዓያዕቆብ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ 4 ዓመት ቅኔና ሰዋሰው የተማረ ሲሆን የቅዱሳት መፃህፍትን ትርጓሜ ደግሞ 10 ዓመት ተምሯል፡፡ ትምህርቱንም ካጠናቀቀ በኋላ ወደ መምህርነት ስራ ገባ፤ ከ1619-1623 ዓ.ም ድረስም ለ4 ዓመታት አክሱም ላይ መፃህፍትን አስተማረ፡፡ ሲያስተምር ግን በሀገሬው ሁሉ ተሰምቶም ታልሞም የማያውቅ፣ ለህዝቡም ባህል እንግዳ የሆነ የማስተማሪያ ዘዴ ይዞ መጣ — ይሄም አዲስ የማስተማሪያ ዘዴ “ወገናዊ ያለመሆን” መርህ ነው!! ይሄም ለሀገረ አክሱም ዱብ ዕዳ ነው!!
በዚህ መርህ በመመራትም ዘርዓያዕቆብ ሲያስተምር እንዲህ ይል ነበር፡-
ሳስተምርና መፃህፍትን ስተረጉም፣ “በዚህ ጉዳይ ላይ ካቶሊኮች እንዲህ፣ እንዲህ ይላሉ፤ ኦርቶዶክሳውያን ደግሞ እንዲህ፣ እንዲህ ይላሉ“ እላለሁ እንጂ፤ “ይኸኛው ጥሩ ነው፤ ይኸኛው ግን መጥፎ ነው” አልልም፡፡ በዚህም ምክንያት ሁሉም ጠሉኝ።
ይሄም የማስተማሪያ ዘዴ ዘርዓያዕቆብ ላይ ጦስ ይዞበት መጣ፡፡ የዘርዓያዕቆብ የስደቱ ዋነኛ መንስኤም ይሄው ሲከተለው የነበረው “ወገናዊ ያለመሆን” የማስተማሪያ መርህ ነው፡፡ በዚህ መርህ የተነሳ ዘርዓያዕቆብ ላይ የደረሰውን ነገር ዶ/ር ዳኛቸው ከሶቅራጠስ ገጠመኝ ጋር ያነፃፅሩታል፡፡ “ሶቅራጠስ…” ይላሉ ዶ/ር ዳኛቸው፣
ሶቅራጠስ በየገበያውና በየአደባባዩ በሚያነሳቸው እልፍ አእላፍና አደገኛ ጥያቄዎች የተነሳ አቴንስ ልታስተናግደው እንዳልቻለችው ሁሉ፤ ዘርዓያዕቆብም ከወገንተኛነት አስተምህሮ በመውጣቱ አክሱም ልታስተናግደው አልቻለችም።
አቴንስስ ሶቅራጠስን መሸከም ያቃታት በሶቅራጠስ የትምህርት ይዘት እንጂ በሶቅራጠስ የማስተማሪያ ዘዴ አልነበረም፡፡ የማስተማሪያ ዘዴ አንድን ትምህርት ተማሪዎች በቀላሉ እንዲረዱት የሚረዳ መንገድ እንጂ በራሱ ትምህርት አይደለም። የማስተማሪያ ዘዴ መሳሪያ ነው — ትምህርትን ከአስተማሪው ወደ ተማሪው የማስተላለፊያ መሳሪያ፡፡ በመሆኑም በመማር — ማስተማር ሂደት ውስጥ በጣም ወሳኙ ነገር ከማስተማሪያ ዘዴው በላይ የትምህርቱ ይዘት ነው፡፡
ከዚህ አንፃር፣ አቴንስ የሶቅራጠስን ትምህርት መሸከም ቢያቅታት አይገርምም፤ ምክንያቱም የሶቅራጠስ የትምህርት ይዘት ከነባሩ ወግና ልማድ ጋር ስለሚጋጭ፡፡ የአክሱም ግን አስገራሚ ነው፤ አክሱም ገና ከመነሻው መፍረክረክ የጀመረችው በወሳኙ ነገር ሳይሆን በመሳሪያው ነው፤ በዘርዓያዕቆብ የትምህርት ይዘት ሳይሆን በማስተማሪያ ዘዴው እንጂ፡፡
አክሱም በማስተማሪያ ዘዴው እንዲህ የራደች፣ ዘርዓያዕቆብ ምን እንደሚያስብ ብታውቅ ኖሮ ምን ልትሆን ነው!!? ስለዚህ ዘርዓያዕቆብ፣ “እውነቱን ብገልፅላቸው ይገድሉኛል፤ ትልቅም ጥፋት ይሆናል እንጂ ጥቅም የለውም፤” ያለው ነገር እውነቱን ነው፤ ቢያንስ ራሱን በመሸሸጉ አንድ ተማሪ ፈጥሯልና፤ በህይወት በመቆየቱም ፍልስፍናው እኛ ጋ ለመድረስ ችሏልና፡፡ ልክ አርስቶትል እንዳደረገው፡፡ ከታላቁ አሌክሳንደር ሞት በኋላ የአቴንስ ህዝብ አርስቶትል ላይ ማጉረምረም ጀመረ፤ ሊወነጅሉትም ተነሱ፡፡ በዚህ ወቅት ግን አርስቶትል “ሶቅራጠስን በመርዝ በመግደል ፍልስፍና ላይ ወንጀል እንደሰራችው፣ አቴንስ ፍልስፍና ላይ ዳግም ወንጀል እንድትሰራ አልፈቅድላትም፤” በማለት ሁሉን ትቶ ከአካባቢው ሸሸ፡፡
የዘርዓያዕቆብ ክስ ግን ስለ ሃገራችን የትምህርት ሥርዓት የቀድሞ ጉዞና የወደፊት መፃዒ ዕድሉንም የሚያመላክተን ነገር አለው፡፡ ይሄውም ለሺ ዓመታት የቆየው ሃይማኖታዊው የትምህርት ሥርዓታችን፣ የተለያዩ አመለካከቶችን ለማስተናገድ የማይታገስ መሆኑንና ይሄ አስተሳሰቡም ወደፊት በ1966ቱ አብዮት እስኪፈራርስ ድረስ ለመቀጠል ቆርጦ የተነሳ መሆኑን ነው፡፡ እናም የዘርዓያዕቆብ ክስ መጪው ትውልድም ልክ እንደቀደሙት አያቶቹ ሁሉ በአንድ ሳንባ ብቻ እንዲተነፍስ የተፈረደበት የሞት ፍርድ ነው፡፡
“በሀገራችን…” ይላሉ ዶ/ር ዳኛቸውም፡-
በሀገራችን ለረጅም ዘመናት ከሃይማኖቱ ጎን ለጎን ፍልስፍና ወንበር እንዳይኖራት የተደረገችውም ለዚሁ ነው፡፡ ከዋሸራ ጀምሮ ባሉ አድባራት “እኔ መምህር እከሌ ፍልስፍና አስተምራለሁ” ብሎ ወንበር የተከለ መምህር የለም፡፡
የምዕራቡ ክርስትና በመካከለኛው ዘመን በነበረው ሃይማኖታዊ ዕውቀት ውስጥ ለፍልስፍና ወንበር ሰጥቶ ነበር፡፡ አብዛኛዎቹ የመካከለኛው ዘመን ፈላስፎችም ፍልስፍናን የተማሩት በአብያተ ክርስትያናትና በየገዳማቱ ነበር፡፡ በእኛ ሀገር ግን ፍልስፍና፣ አይደለም በሃይማኖታዊ ትምህርት ውስጥ ወንበር ሊኖራት ቀርቶ ገና በመጀመሪያ ሙከራዋ ነበር እንድትከሰስ የተደረገችው፡፡ “ዘርዓያዕቆብ፣ “ወልደ ዮሐንስ ከሰሰኝ” አለ እንጂ፤ የተከሰሰችው ግን ፍልስፍና ነች፤” ይላሉ ዶ/ር ዳኛቸውም፡፡ ከዚህ አንፃር፣  የዘርዓያዕቆብ ሙከራ፣ ለሺ ዓመታት በዘለቀው የሀገራችን ሃይማኖታዊ ትምህርትና ዕውቀት ውስጥ ፍልስፍና ወንበር እንዲኖራት የተደረገ የመጀመሪያ ሙከራ አድርገን መመልከት እንችላለን፡፡
ከዘርዓያዕቆብ የማስተማሪያ ዘዴ ጋር የሚያያዝ ሌላም ትልቅ ነገር አለ፡፡ ይሄውም፣ በማስተማር ስራ ላይ “ወገናዊ ያለመሆን” መርህ ዘመናውያኑ የስነ ትምህርት ሊቃውንትም በፅኑ የሚደግፉት መርህ መሆኑ ነው፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ በ20ኛው ክ/ዘ አበክሮ ሲከራከር የነበረው ጀርመናዊው ሶሲዮሎጂስት ማክስ ቬበር (Max Weber 1864 — 1920) ነው። እንደ ቬበር አመለካከት፣ ማንኛውም መምህር በክፍል ውስጥ ይሄን “ወገናዊ ያለመሆን” መርህ መከተል ያለበት ተማሪዎቹ በመምህራቸው “የግል አመለካከት” ተፅዕኖ ስር እንዳይወድቁ ለመጠበቅ ሲባል ነው፡፡
“አስተማሪ…” ይላሉ ዶ/ር ዳኛቸውም፡-
አስተማሪ ለተማሪዎች የተለያየ የሃሳብ ገበታ የሚያቀርብ፤ እንዲሁም ተማሪዎች እንዴት ነገሮችን መመርመርና መጠየቅ እንዳለባቸው የሚጠቁም እንጂ የራሱን የግል አቋም ይዞ ይሄ ልክ ነው — ይሄ ደግሞ መጥፎ ነው የሚል አይደለም፡፡
ይሄ ማለት ግን መምህሩ የግል አቋም የመያዝ መብት የለውም ማለት አይደለም፡፡ ሆኖም ግን እንደዚህ ዓይነት የግል አቋሞች መንፀባረቅ ያለባቸው ከክፍል ውጭ መሆን አለበት፡፡ “ከማስተማሪያ ክፍል ውጭ ግን…” ይላል ቬበርም፡-
ከክፍል ውጭ ግን ማንኛውም አስተማሪ በፈለገው ቦታ ላይ — በየጋዜጦች ላይ አሊያም በህዝባዊ ስብሰባዎች ላይ ሊሆን ይችላል — የፈለገውን ማንፀባረቅ ይችላል፤ሰይጣን ያቀበለውን ሃሳብም ቢሆን!
ከዚህም ባሻገር፣ በማስተማር ስራ ውስጥ የአንድ ወገንን አስተሳሰብ ብቻ ማስተማር የተማሪዎችን የተመራማሪነት ችሎታቸውን ከማኮላሸቱም ባሻገር፣ የላቀ እውነትና ዕውቀት ለመፈለግ ያላቸውን ተነሳሽነትም ያመክንባቸዋል፡፡ ዘርዓያዕቆብም ሐተታውን ሲዘጋ፡-
ይሄንንና ከዚህም የተሻለ የሚያስተውል ከተገኘ፣ ካስተማረና ከጻፈውም እግዚአብሔር የልቡን ይስጠው።
---ያለው ተማሪዎች ወይም አዲሱ ትውልድ ሁልጊዜ በዕውቀት እየበለጠና እየተሻለ መሄድ አለበት ከሚል አመለካከቱ በመነሳት ነው፡፡ አዲሱ ትውልድ ሁልጊዜ በዕውቀት እየበለጠና እየተሻለ ሊሄድ የሚችለው ደግሞ ትውልዱ በአንድ ወገን አስተሳሰብ ሲቀረፅ ሳይሆን በተለያዩ አመለካከቶችና ትምህርቶች ሲታነፅ ነው፡፡ በዚህ ነገር ላይ ወልደ ሕይወትም በሐተታው ምዕራፍ 17 ላይ ጠንከር አድርጎ ፅፏል፤ እንዲህ በማለት፡-
ትምህርትን በመማር ደካማ አትሁን፤ በመላ የህይወት ዘመንህም አትተዋት፡፡ … ደግሞም በአንድ ትምህርት አትኑር፤ ይህ ስንፍና ነውና፡፡ ልክ ንቦች የተለያዩ መዓዛ ያላቸውን አበቦች እየቀሰሙ ጣፋጭ ማር እንደሚሰሩ ሁሉ፣ አንተም ከተለያዩ ትምህርቶች ሁሉ ጥበብን ሰብስብ፡፡
ከአዘጋጁ፡- (ጸሐፊው፤በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህርና “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” መፅሐፍ ደራሲ ሲሆን በኢ-ሜይል አድራሻው  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል)

Read 767 times