Monday, 11 September 2017 00:00

“መስቀልን በጉራጌ” የባህልና ቱሪዝም ፌስቲቫል ሊካሄድ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

  በየዓመቱ መስከረም ወር ላይ የሚከበረው የመስቀል በዓል ከቀድሞው በተለየና እጅግ በደመቀ መልኩ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን አከባበሩ በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ እንዲሰፍርም  ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡
የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝምና የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ፣ የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበርና ቢአርሲ በጀት አስጎብኚና የጉዞ ወኪል በትብብር በሚያዘጋጁት በዚህ “መስቀልን በጉራጌ” የባህልና ቱሪዝም ፌስቲቫል ላይ የአካባቢውን ባህልና ልዩ የመስቀል አከባበር ሥርዓት የሚያመለክቱ ዝግጅቶች፣ ልዩ የደመራ ሥርዓትና የጉራጌ ባህላዊ ምግብ የሆነውን ክትፎ በስፋት ለማስተዋወቅ የሚያስችል ፕሮግራም የሚቀርብ ሲሆን ባህላዊውን የክትፎ ማቅረቢያ ጣባት በልዩ መንገድ አዘጋጅቶ፣ በዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ለማስመዝገብ ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል፡፡
የቢአርሲ በጀት አስጎብኚና የጉዞ ወኪል ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ቢሻው በላይ፣ የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋ ጎይቴ እንዲሁም የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መንግስት ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍቅረዓለም ከበደ በጋራ በዮድ አቢሲኒያ የባህል ምግብ አዳራሽ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ በጉራጌ ህዝብ ዘንድ በታላቅ ድምቀት የሚከበረውን የመስቀል በዓል ከወትሮው በተለየና እጅግ በደመቀ መንገድ ለማክበር ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡
በዓሉን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለማክበር ወደ አገር ቤት ለሚገቡ ከተለያዩ ቦታዎች ወደ ክልሉ የሚሄዱ መንገደኞች የትራንስፖርት ችግር እንዳይገጥማቸው ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ መሆኑን የገለፁት የቢአርሲ በጀት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢሻው ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጥምረት በመሥራት ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዓሉን በተለያዩ ባህላዊና አዝናኝ ፕሮግራሞች ታጅቦ እስከ በዓሉ ማጠናቀቂያ ድረስ እንደሚዘልቅና የበዓሉ ታዳሚዎች ሁሉ መጪው አመት ደርሶ እስከሚገናኙ ድረስ በናፍቆት እንዲለያዩ በሚያደርግ መልኩ ለማጠናቀቅ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ገልፀዋል። የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ጎይቴ በበኩላቸው፤ የመስቀል በዓልና የጉራጌ ማህበረሰብን አነጣጥሎ  ማሰብ እንደማይቻልና በዓሉ በከተማ በገጠር የሚኖሩ የጉራጌ ቤተሰብ አባላት በአንድ ተገናኝተው የሚመራረቁበት፣ የሚጠያየቁበት፣ ጋብቻ የሚፈፅሙበት፣ የቀጣይ ዓመት የቤተሰብ ዕቅድ የሚፀድቅበት ልዩ በዓል እንደመሆኑ፣ በብሔረሰቡ አባላት ዘንድ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ባህል ነው። በዓሉ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅና የብሔረሰቡ ባህላዊ ምግብ የሆነውን ክትፎ ባለቤትነት ለዓለም የሚታዋወቅበት ልዩ ፕሮግራም ለማዘጋጀት መታቀዱንና ፕሮግራሙ በየዓመቱ መስቀል፣ በቀጣይነት እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡
ቢአርሲ በጀት አስጎብኚና የጉዞ ወኪል ቀደም ሲል “አገርዎን በዱቤ” ይጎብኙ በሚል መርህ፣ በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ በማድረግ፣ ህብረተሰቡ አገሩን የመጎብኘት በዓሉን እንዲያዳብር የሚያደርጉ ሥራዎችን በመሥራት ይታወቃሉ፡፡

Read 489 times