Print this page
Monday, 11 September 2017 00:00

ዋዜማ የት እንሂድ? የት እንዝናና?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   በዘንድሮ የአዲስ ዓመት ዋዜማ፣ በመዲናዋ የትኞቹ ሆቴሎች፣ ቴአትር ቤቶች፣ የምሽት ክለቦች … የሙዚቃ ድግሶችና  የአውዳመት የመዝናኛ ፕሮግራሞች ተዘጋጅተዋል? ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ እንዲህ ቃኝታቸዋለች፡፡

                 
                   “እንቁጣጣሽ ክላሲክ ኮንሰርት” - በካፒታል ሆቴል

     ባለአምስት ኮከቡ ካፒታል ሆቴል፤ በአዲሱ አመት ዋዜማ ከምሽቱ 12፡00 ጅምሮ “እንቁጣጣሽ ክላሲክ ኮንሰርት” የሚል ስያሜ የተሰጠው የሙዚቃ ድግስ አሰናድቷል፡፡ በዚህ ድግስ ተወዳጆቹ ድምፃውያን ሳሚ ዳን፣ ሚካኤል ለማ ደምሰው፣ ፀደንያ ገ/ማርቆስ፣ የባላገሩ አይዶል አሸናፊ ዳዊት ፅጌ፣ አስገኘሁ አሸኮ (አስጌ ዴንዳሾ) ታዳሚውን በዘፈኖቻቸው የሚያዝናኑ ሲሆን ዲጄ ዊሽና ዲጄ ጆ ዋዜማውን በምርጥ ሙዚቃዎች ያደምቁታል ተብሏል፡፡
በሙዚቃ ድግሱ ላይ ለሚታደሙ ከእራት በፊት ለአንድ ሰው 699 ብር፣ እራትን ጨምሮ 1199 ብር፣ ለጥንዶች ያለ እራት 1199 ብር፣ እራትን ጨምሮ 1999 ብር የሚያስከፍል ሲሆን ዝግጅቱ እስከ ሌሊቱ 8፡00 ድረስ እንደሚዘልቅ የሆቴሉ ማርኬቲንግ ሃላፊ፣ ወ/ሪት ተወዳጅ አሰፋ ለአደስ አድማስ ገልፀዋል፡፡


-----------------

                    ልዩ የእራት ፓርቲ-በኢሊሊ ሆቴል

      ባለ አምስት ኮከቡ ኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል ደግሞ በዘመን መለወጫ ዋዜማ ምሽት ልዩ የእራትና የሙዚቃ ድግስ አዘጋጅቷል፡፡ በዚህ ምሽት ኦሮምኛን ጨምሮ የተለያዩ የብሄር ብሄረሰቦች ሙዚቃና ባህላዊ ጭፈራ የሚቀርብ ሲሆን ስታንዳፕ ኮሚዲ፣ የባንድ ሙዚቃና ሌሎችም ዝግጅቶች ተሰናድተዋል ተብሏል፡፡ ጳጉሜ 5 ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት ጀምሮ የሆቴሉ በሮች ለታዳሚያን ክፍት ሲሆኑ የመግቢያ ዋጋው እራትን ጨምሮ (ውስኪ መጠጦችን ለሚጠቀሙ) 1500 ብር፣ ከእራት ጋር የወይን መጠጦችን ለሚወስዱ 1 ሺህ ብር መሆኑ ተገልጿል፡፡ ሆቴሉ ከዚህ በተጨማሪም የሞሀ ለስላሳ መጠጦችን፣ ጊዮርጊስ ቢራና አኳ አዲስ ውሃን በነፃ ያቀርባል፡፡ አምራቾቹ ለበዓሉ ስፖንሰር ማድረገቸውን በመግለፅ፡፡  የመዝናኛ ድግሱ እስከ እኩለ ሌሊት እንደሚቀጥል የሆቴሉ የህዝብ ግንኙነትና ማህበራዊ ሚዲያ ሃላፊ አቶ ታሪኩ ዋሲሁን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡  

-----------------

                     ሀሴት አኩስፒክ ባንድ ከአዝማሪዎች ጋር በጎልደን ቱሊፕ ሆቴል

      ቦሌ ኤድናሞል ጀርባ የሚገኘው ባለ አራት ኮከቡ ጎልደን ቱሊፕ ሆቴል በበኩሉ፤ አኩስቲክ ባንድን ከአዝማሪዎች ጋር በማጣመር ዓለም አቀፍና ባህላዊ ሙዚቃን ለማቅረብ በምሽቱ ከሀሴት አኩስቲክ ባንድ ሚኪያስ ፍሬው፣ አይዳ ሰለሞንና ሌሎችም የሚሳተፉ ሲሆን ከአዝማሪዎች ቱፓክ በሚል ቅፅል ስሙ የሚታወቀው አዝማሪ ናርዶስ ከተሰኘች አዝማሪ ጋር ስራውን እንደሚያቀርብ ታውቋል፡፡
በዕለቱ በባህል ዘፈን ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ሁለት ዘፋኞች ሆቴሉ እውቅና እንደሚሰጥም ተነግሯል፡፡ በዚህ ምሽት ላይ ለመታደም ለአንድ ሰው እራትን ጨምሮ 699 ብር ሲሆን ለጥንዶች እራትን ጨምሮ 1299 ብር እንደሚያስከፍል የሆቴሉ ማርኬቲንግ ኃላፊ መርሀዊት ፀጋዬ ገልፀዋል፡፡

------------------

                         የጥበብ ድግስ - በብሔራዊ ቴአትር

      አንጋፋው ብሔራዊ ቴአትር አዲሱን አመት ምክንያት በማድረግ ለአንድ ወር የሚዘልቅ የጥበብ ድግስ እንደሚያቀርብ አስታውቋል፡፡ ከዛሬ ጀምሮ እስከ መስከረም 28 ቀን 2010 ዓ.ም በሚዘልቀው የጥበብ ድግስ፤ ከመደበኛው ሙዚቃና ልዩ ልዩ የኪነጥበባት ዝግጅት በተጨማሪ የአረጋዊያን የፋሽን ትርኢት፣ የአርበኞች ልዩ ዝግጅት፣ የአንጋፋው አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ የመታሰቢያ ፕሮግራም የ”ሚስ ናሽናል ቴአትር” የቁንጅና ውድድርና ሌሎችም የመዝናኛ ፕሮግራሞች እንደሚቀርቡ ብሔራዊ ቴአትር አስታውቋል፡፡

Read 800 times
Administrator

Latest from Administrator