Monday, 11 September 2017 00:00

የአፍሪካ መንግስታት ዜጎቻቸውን ወደ ጽንፈኝነት ገፍተው እያስገቡ ነው ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የአፍሪካ መንግስታት፣ ሽብርተኝነትንና ጽንፈኝነትን ለመዋጋት በማሰብ የሚፈጽሟቸው ድርጊቶችና የሚወስዷቸው እርምጃዎች፣ በተቃራኒው ዜጎችን ወደ ጽንፈኝነት ገፍተው እያስገቡ እንደሆነ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከትናንት በስቲያ ይፋ ባደረገውና ሶስት አመታትን በፈጀው የጥናት ሪፖርት አስታውቋል፡፡
ተመድ ይፋ ያደረገው የጥናት ውጤት እንደሚለው፣በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጽንፈኛ ቡድኖች አባላት፣ የጽንፈኛ ቡድኖችን አስተሳሰብ በመደገፍ አባል ለመሆን የወሰኑት፣ የየአገሮቻቸው መንግስታት በሚወስዷቸው የጸረ ሽብርተኝነትና ጽንፈኝነት እርምጃዎች ተገፋፍተው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ መንግስታት ቦኮ ሃራምንና አልሻባብን የመሳሰሉ ጽንፈኛና አሸባሪ ቡድኖችን ለመደምሰስ የሚያደርጉት ትግል፣ የአገራቱን ዜጎችና ቤተሰቦቻቸውን ተጎጂ የሚያደርጉባቸው አጋጣሚዎች በርካታ እንደሆኑ የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤ ይህም ዜጎችን ወደ ጽንፈኝነት በመግፋት ያልተፈለገ፣ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡
የጽንፈኛ ቡድኖች አባላት ከነበሩና በጥናቱ ከተካተቱ 500 በላይ አፍሪካውያን መካከል 71 በመቶ የሚሆኑት፣ የአገራቸው መንግስት ጽንፈኝነትን ለመዋጋት በወሰዳቸው እርምጃዎች፣ ቤተሰቦቻቸው ወይም ጓደኞቻቸው መገደላቸው፣ መታሰራቸው አልያም የሌሎች በደሎች ሰለባ መሆናቸው፣ የቡድኖቹ አባል ለመሆን ዋነኛ ምክንያት መሆኑን መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡
በአፍሪካ ባለፉት ስድስት አመታት ብቻ ጽንፈኛ ቡድኖች በፈጸሟቸው የሽብር ጥቃቶችና የጥፋት እርምጃዎች ከ33 ሺህ በላይ የአህጉሪቱ ዜጎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ጽንፈኝነት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አፍሪካውያንን ለመፈናቀልና ለሰብዓዊ ቀውስ መዳረጉንም አስረድቷል፡፡
አፍሪካውያንን ወደ ጽንፈኝነት እንዲገቡ ይገፋፋሉ ተብለው በጥናቱ ከተለዩት ሌሎች በርካታ ምክንያቶች መካከልም፣ ፍትሃዊ ያልሆነ የሃብት ክፍፍል እንዲሁም የትምህርትና የስራ ዕድል ዕጦት እንደሚገኙበትም ዘ ጋርዲያን በዘገባው ጠቁሟል፡፡

Read 1522 times