Monday, 11 September 2017 00:00

የብራዚል የቀድሞ መሪዎች የወንጀል ቡድን አቋቁመው በመዝረፍ ተከሰሱ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የብራዚል የቀድሞ ፕሬዚዳንቶች ሉዊስ ሉላ ዳሲልቫ እና ዲልማ ሩሴፍ፣ ግዙፍ የወንጀለኞች ቡድን በማቋቋም ለአመታት ታላላቅ የወንጀል ተግባራትን ሲያከናውኑ ነበር በሚል ባለፈው ማክሰኞ በአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
የአገሪቱ አቃቤ ህግ ሁለቱን የአገሪቱ የቀድሞ ፕሬዚዳንቶች እና የፓርቲያቸው አባላት የሆኑ ስድስት ግብረ አበሮቻቸው፣ በስውር ባቋቋሙት የወንጀለኞች ቡድን፤ ሙስናንና የህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን የመሳሰሉ የተለያዩ የወንጀል ተግባራትን ሲፈጽሙ እንደነበር በመጥቀስ ክስ መመስረቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
በስልጣን ዘመናቸው በሙስና መልክ ከ480 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ አካብተዋል በሚል ክስ የተመሰረተባቸው የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የሉላ ዳ ሲልቫ እና የአልጋ ወራሻቸው የዲልማ ሩሴፍ ጠበቆች ክሱን መሰረተቢስ ውንጀላ በማለት የተቃወሙት ሲሆን ደንበኞቻቸው ከተባለው የወንጀል ድርጊት ነጻ መሆናቸውን በመጥቀስ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡
የሰራተኞች ፓርቲ በበኩሉ፤ ክሱ የተመሰረተው ያለምንም ተጨባጭ ማስረጃ ነው፣ ህዝቡ ሌሎች የወንጀል ምርመራ ጉዳዮችን እንዲረሳና ትኩረቱን እንዲቀይር ለማድረግ ታስቦ ሆን ተብሎ የተመሰረተ ክስ ነው ሲል አጣጥሎታል፡፡
አሁንም ድረስ ብዙ ደጋፊዎች ያሏቸውና በመጪው የአገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለመወዳደር ያቀዱት የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ፤ ከዚህ ቀደምም የሙስና ክስ እንደተመሰረተባቸው ያስታወሰው ዘገባው፣ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለምርጫ እንዳይወዳደሩ ሊያግዳቸው ይችላል ተብሎ እንደሚሰጋም ገልጧል፡፡
በ2002 ወደ ስልጣን የመጡት ሉላ ዳ ሲልቫ፣ለሁለት የስልጣን ዘመን ብራዚልን ካስተዳደሩ በኋላ መንበረ መንግስቱን ለሩሴፍ ማስረከባቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ሩሴፍ በበኩላቸው የአገሪቱን በጀት በህገ ወጥ መንገድ አስተዳድረዋል በሚል በ2016 ከስልጣን መነሳታቸውን አክሎ ገልጧል፡፡

Read 663 times