Monday, 11 September 2017 00:00

ኦክስፎርድ ዘንድሮም የአለማችን ምርጥ ዩኒቨርሲቲ ተብሏል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  100 የአመቱ ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ዝርዝር ውስጥ አፍሪካዊ የለበትም


       የአለማችንን ዩኒቨርሲቲዎች የጥራት ደረጃ በየአመቱ ይፋ የሚያደርገው አለማቀፉ የዩኒቨርሲቲዎች ሊግ ሰሞኑንም የአመቱን የአለማችን ምርጥ 100 ዩኒቨርሲቲዎች ዝርዝር ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የእንግሊዙ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮም እንደ አምናው በአንደኛነት ደረጃ ላይ መቀመጡን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ለ13ኛ ጊዜ ይፋ በተደረገው የአለማችን የምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ዝርዝር ውስጥ የእንግሊዙ ካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛነት ደረጃን ሲይዝ፣ ባለፈው አመት የአለማችን ሁለተኛው ምርጥ የነበረው የአሜሪካው ካሊፎርኒያ ኢንስቲቲዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ዘንድሮ ከአሜሪካው ስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ጋር የሶስተኛነቱን ደረጃ ተጋርቷል፡፡
8ኛ ደረጃን ከያዘው ኢምፔሪያል ኮሌጅ ኦፍ ለንደን እና 10ኛ ደረጃን ከያዘው የዙሪክ የፌዴራል የቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት በስተቀር፣ ከ3ኛ እስከ 15ኛ ያለውን ደረጃ የያዙት ሁሉም የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች መሆናቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ እነሱም ማሳቹሴትስ ኢንስቲቲዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ፣ ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ፣ ፕሪንሴተን ዩኒቨርሲቲ፣ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቺካጎ፣ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፔንሲልቫኒያ፣ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ እና ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ ናቸው ብሏል፡፡  
ከ30ዎቹ የአለማችን ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ሰባቱ የአውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎች ሲሆኑ ሶስቱ ደግሞ የእስያ አገራት ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው ያለው ዘገባው፤ እስከ 100 ባለው የአመቱ ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ዝርዝር ውስጥ አንድም አፍሪካዊ ዩኒቨርሲቲ አለመካተቱን አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1874 times