Monday, 11 September 2017 00:00

የለጋስነት ልማድ በአለማቀፍ ደረጃ ቀንሷል ተባለ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የተቸገሩትን የመርዳትና የመለገስ ልማድ በአለማቀፍ ደረጃ እየቀነሰ ቢመጣም አፍሪካን የመሳሰሉ ድሃ አህጉራት ግን ቸርነታቸውና ደግነታቸው እየጨመረ መምጣቱን ባለፈው ማክሰኞ ይፋ የተደረገ አንድ አለማቀፍ ጥናት አመልክቷል፡፡
በ139 የአለማችን አገራት ላይ የተሰራን ጥናት መሰረት ያደረገው አመታዊው አለማቀፍ የበጎ አድራጎት ልገሳ ሁኔታ አመላካች ሪፖርት እንዳለው፣ ባለፈው የፈረንጆች አመት የገንዘብ ልገሳ የማድረግ ወይም የማያውቁትን ሰው የመርዳት ልማድ በአለማቀፍ ደረጃ በ2 በመቶ የቀነሰ ሲሆን፣ የበጎ ፈቃደኝነት ተግባር ደግሞ በ1 በመቶ ቀንሷል፡፡
አሜሪካን ጨምሮ የአለማችን ቀዳሚዎቹ 10 ሃብታም አገራት፣ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ዘንድሮ በለጋስነት ማሽቆልቆል አሳይተዋል ያለው ሪፖርቱ፤ከአለማችን 20ዎቹ የበለጸጉ አገራት መካከል ከቀዳሚዎቹ 20 ለጋስ አገራት ተርታ መሰለፍ የቻሉት ስድስት ብቻ ናቸው ብሏል፡፡
ላለፉት ሶስት ተከታታይ አመታት የአለማችን እጅግ ቸር እና ለጋስ ህዝቦች መኖሪያ ናት ተብላ በሪፖርቱ በቀዳሚነት የተቀመጠቺው ማይናማር፣ ዘንድሮም የአንደኛነትን ደረጃ ይዛለች ያለው ዘገባው፤ ኢንዶኒዢያ የሁለተኛነት ደረጃን መያዟን አመልክቷል፡፡ በአመቱ በቸርነትና በልግስና ከፍተኛ መሻሻል ያሳየቺው ኬንያ መሆኗን በመጠቆም፣ አምና 12ኛ ደረጃ ላይ የነበረቺው ኬንያ፣ ዘንድሮ ሶስተኛ ደረጃን ላይ መቀመጧንም ገልጧል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ በቸርነት ከአለማችን አገራት የመጨረሻውን ደረጃ የያዘቺው በእርስ በእርስ ጦርነት የፈራረሰቺው የመን መሆኗን አመታዊው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
ቻሪቲስ ኤይድ ፋውንዴሽን በተባለው አለማቀፍ ተቋም የተሰራው ጥናቱ፤ የ139 የአለማችን አገራት ዜጎች የሆኑ ከ146 ሺህ በላይ ሰዎችን ቃለ መጠይቅ በማድረግ በተሰበሰበው መረጃ ላይ በመመስረት፣ የአገራቱን ዜጎች የበጎ ምግባር የገንዘብ ልገሳ ተሞክሮ፣ የበጎ ፈቃደኝነት ተሳትፎና የማያውቁትን ሰው የመርዳት ተነሳሽነት በመገምገም ደረጃ እንደሚሰጥም ተነግሯል፡፡

Read 2786 times