Print this page
Sunday, 10 September 2017 00:00

በዳይመንድ ሊግ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 • ዘንድሮ የኬንያ አትሌቶች ድርሻ ከ740.5 ሺ ዶላር በላይ ሲሆን የኢትዮጵያ አትሌቶች ድርሻ እስከ 198ሺ ዶላር ነው፡፡
                      • በ2017 ኬንያ 4 የዳይመንድ ሊግ ሻምፒዮኖች ኢትዮጵያ ምንም
                      • ባለፉት 8 የውድድር ዘመናት ኬንያ 37 ኢትዮጵያ 12 የዳይመንድ ሊግ ድሎች
                   
       ዳይመንድ ሊግ በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች የሚዘጋጅ ሲሆን ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት ከሚያቀርቡ የማራቶን ውድድሮች ቀጥሎ ለአትሌቶች ከፍተኛ የገቢ ምንጭ የሆነና በከፍተኛ እድገት ላይ የሚገኝ ዓመታዊ ውድድር ነው፡፡ ዳይመንድ ሊግ ዘንድሮ ለ8ኛ ጊዜ ሲካሄድ በአዲስ መዋቅር  ሲሆን በ32 የውድድር መደቦች በሁለቱም ፆታዎች 1200 አትሌቶች ተሳትፈውበታል፡፡ ትራክ ስታት www.track-stats.com የተባለ ድረገፅ በሰራው ስሌት  በ8ኛው የዳይመንድ ሊግ ላይ  ከቀረበው 8 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ሽልማት 607 አትሌቶች ከ1ሺ ዶላር ጀምሮ እስከ 134ሺ ዶላር ተሸልመዋል፡፡ ዘንድሮ በዳይመንድ ሊጉ ከፍተኛውን የገንዘብ ሽልማት በመውሰድ አንደኛ ደረጃ የተሰጣት 134ሺ ዶላር ማሸነፍ የቻለችው  ኤለና ቶምሰን ከጃማይካ ስትሆን፤ ሽዋኔ ሚለር ከባህማስ በ127ሺ ዶላር፤ ማርያ ላስቲስኤኔ ከራሽያ በ100ሺ ዶላር እንዲሁም ሙታዝ ኡሳ ከቦትስዋና በ100ሺ ዶላር እስከ አምስተኛ ደረጃ አከታትለው ወስደዋል፡፡ ከኬንያ ኤለን ኦቡሪ፤ ከደቡብ አፍሪካ ካስተር ሴማንያ፤ ከቦትስዋና ኒጄል አሞስ፤ ከአሜሪካ ሽዋን ሄንድሪክስ፤ ከግሪክ ካተሪን ሴፈንዲ በነፍስ ወከፍ 90ሺ ዶላር እንዲሁም ከክሮሽያ ሳንድራ ፔርኮቪች 86ሺ ዶላር ከሽልማት ገንዘቡ በመቋደስ እስከ 10ኛ ደረጃ ለማግኘት ችለዋል፡፡
በሌላ በኩል በ8ኛው ዳይመንድ ሊግ በቅርብ ተቀናቃኞቹ የኬንያ እና ኢትዮጵያ አትሌቶች መካከል ከሽልማት ገንዘቡ በተገኘ ድርሻ ከፍተኛ ልዩነት ተስተውሏል፡፡ የትራክ ስታት የሽልማት ገንዘብ ስሌት እንዳመለከተው ኬንያውያን ከ1 እስከ 10፤ ከዚያም እስከ 20 እንዲሁም እስከ ሃምሳኛ እና እስከ መጨረሻው ደረጃ በርካታ አትሌቶችን በማሳተፍ ከገንዘብ ሽልማቱ በ3 እጥፍ ከኢትዮጵያ የሚልቅ  ድርሻ በማግኘት ተሳክቶላቸዋል፡፡ በአጠቃላይ በዳይመንድ ሊጉ ላይ ዘንድሮ ኬንያ 49 አትሌቶችን በማሳተፍ ከ740.5ሺ ዶላር በላይ ስትሰበስብ አራት የዳይመንድ ሊግ ሻምፒዮኖች አግኝታለች፡፡ ከ7 የውድድር ዘመናት በኋላ የዳይመንድ ሊግ ሻምፒዮን ሳታስመዘግብ የቀረችው ኢትዮጵያ 19 አትሌቶችን በማሳተፍ ከሽልማት ገንዘቡ ያስመዘገበችው ድርሻ 148ሺ ዶላር ብቻ ሆኗል፡፡  የኢትዮጵያ አትሌቶች ከዳይመንድ ሊጉ የሽልማት ገንዘብ የሚኖራቸው ድርሻ የቀነሰው በዓለም ሻምፒዮና ተሳትፎ ሳቢያ አትሌቶች ከውድድር ተሳትፎ በመታገዳቸው፤ በምርጥ አሰልጣኞች እና በቂ የልምምድ ጊዜ ባለመስራታቸው፤ በውስን የውድድር መደቦች በሁለቱም ፆታዎች በመሳተፋቸው እና በተቃናቃኝ አትሌቶች የውድድር ታክቲክ እና ቴክኒክ በመበለጣቸው ነው፡፡ የኬንያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የአትሌቶችን የዳይመንድ ሊግ ተሳትፎ ባለማገዱ እንዲሁም ከኢትዮጵያ በተሻለ የውድድር መደቦች በብዛት መሳተፋቸው ከሽልማት ገንዘብ ያገኙትን ድርሻ የላቀ አድርጎታል፡፡
በትራክ ስታት www.track-stats.com ስሌት መሰረት ከኢትዮጵያ አትሌቶች ግንባር ቀደም ሆኖ የሚጠቀሰው በ5ሺ ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው ሙክታር ኢድሪስ በ42ሺ ዶላር የሽልማት ድርሻው ከዓለም 49ኛ ደረጃ በማግኘቱ ነው፡፡  ዮሚፍ ቀጀልቻ በ24ሺ ዶላር 93ኛ፤ ዳዊት ስዩም እና በሱ ሳዶ በ16ሺ ዶላር 136ኛ እና 137ኛ፤ ጉድፍ ፀጋይ በ15.5 ሺ ዶላር 142ኛ ላይ ናቸው፡፡ ሌሎች የኢትዮጵያ አትሌቶች ከ150ኛ በታች  እስከ 350ኛ ደረጃ ተዘበራርቀው ሊቀመጡ በቅተዋል፡፡ አማን ወጤ 13፤ ሶፍያ አሰፋ 13ሺ፤ ሃብታም አለሙ 12፤ ሰለሞን ባረጋ 12፤ ለተሰንበት ግደይ 11፤ የኔው አላምረው 8፤ በሱ ሳዶ 5.5፤ ገንዘቤ ዲባባ፤ 4.5፤ እቴነሽ ዲሮ 4.5፤ ጫላ ባዬ 3ሺ፤ ብርሃኑ ለገሰ 2.5፤ ስንታየሁ 1.5፤ ዳዊት ወልዱ 1.5 እንዲሁም ሰለሞን በልሁ 1ሺ ዶላር ከ8ኛው የዳይመንድ ሊግ የገንዘብ ሽልማት አግኝተዋል፡፡
ዳይመንድ ሊግ ከ1998 እኤአ እስከ 2010 እኤአ ለ11 የውድድር ዘመናት ይካሄድ የነበረውን የአይኤኤፍ ጎልደን ሊግ በተሻለ ደረጃ የተካ ነው፡፡ ለ12 የውድድር ዘመናት የተካሄደው ጎልደን ሊግ በ6 ከተሞች በሚደረጉ ውድድሮች የሚያሸንፉ አትሌቶችን 1 ሚሊዮን ዶላር ወይንም የወርቅ ጡቦች በማካፈል የሚሸለምበት ነበር። በጎልደን ሊግ በ1998 እኤአ ላይ ኃይሌ ገብረስላሴ 333,333 ዶላር፤ በ2006 እኤአ ላይ ቀነኒሳ በቀለ እና ጥሩነሽ ዲባባ በነፍስ ወከፍ 83,333 ዶላር እንዲሁም ቀነኒሳ በቀለ በ2009 እኤአ ላይ 333,333 ዶላር ተሸላሚዎች ነበሩ፡፡
የጎልደን ሊግ ውድድርን የተካው ዳይመንድ ሊግ  ባለፉት 8 የውድድር ዘመናት ከፍተኛ ለውጥ እና ድምቀት በማሳየት ከአይኤኤኤፍ ውድድሮች ስኬታማው ሆኖ እየተጠቀሰ ይገኛል፡፡ ዳይመንድ ሊጉ በየሚካሄድባቸው ከተማዎች ከፍተኛ የስታድዬም ተመልካች አለው። በተለይ በአሜሪካ ዩጂን፤ በስዊዘርላንድ ዙሪክ፤ በሞናኮ  እንዲሁም በእንግሊዝ በርሚንግሃም ከተሞች የሚካሄዱት የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ስታድዬም በሚገባ ተመልካች እየገዘፉ ናቸው፡፡ በቴሌቭዥ ስርጭት ከፍተኛውን ሽፋን በማግኘት ከአትሌቲክስ ውድድሮች ዋና ተጠቃሽ የሆነው ዳይመንድ ሊግ  የዓለም መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት በመሳብ ውጤታማም ነው፡፡ በዳይመንድ ሊጉ የየአገራቱ ምርጥ አትሌቶች፤ የዓለምና የኦሎምፒክ ሻምፒዮኖችን መሳተፋቸው ምርጥ ፉክክር የሚስተዋልበት መድረክ አድርጎታል፡፡ ካለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት ወዲህ በ4 አህጉራት ኤስያ፤ አውሮፓ፤ መካከለኛው ምስራቅ፤ አሜሪካን እንዲሁም አፍሪካን በማካለል የሚካሄደው ዳይመንድ ሊጉ በ4 ወራት  በ13 የተለያዩ አገራትና 15 ከተሞች ሲስተናገድ  በከፍተኛ የውድድር ደረጃው ሪከርዶች እና የውድድር ዘመኑ ፈጣን ሰዓቶች የሚመዘገቡበት ታላቅ መድረክ እየሆነ መጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ባለፉት ስምንት የውድድር ዘመናት በዳይመንድ ሊጉ ተግባራዊ የሆኑ አዳዲስ የአሰራር መዋቅሮች በሻምፒዮናው የእድገት ደረጃ ፈጣን ለውጥ እንዲመዘገብ ምክንያት ሆነዋል፡፡ በዳይመንድ ሊጉ የአሰራር መዋቅር ለውጦች የተደረጉት ለ3 ጊዜያት ነው፡፡ በመጀመርያዎቹ 6 የውድድር ዘመናት በ12 ከተሞች ውድድሮች እየተካሄዱ ከ1 እሰከ 3 ለሚወጡ አትሌቶች ብቻ   አሸናፊዎችን ለመለየት  ነጥብ በመስጠት በውድድር ዘመኑ መጨረሻ ከፍተኛውን ነጥብ ለሚያስመዘግቡት ሻምፒዮንነቱ ይፀድቅ ነበር።  በ2016 እኤአ በ7ኛው የውድድር ዘመን በተመሳሳይ ሻምፒዮኖችን በከፍተኛ ነጥብ የመለያ መንገድ ከ1 እሰከ 6ኛ ደረጃ ለሚያገኙ አትሌቶች ነጥብ በመስጠት ተሰርቶበታል፡፡ በ2017 እኤአ ላይ ግን የአሰራር መዋቅሩ በጣም ልዩ ለውጥ ተደርጎበታል፡፡ በመጀመርያ 12 የማጣርያ ውድድሮች የተካሄዱ ሲሆን ከ1 እስከ 8ኛ ደረጃ ለሚያገኙት ነጥብ  ተሰጥቶ የዳይመንድ ሊጉ አሸናፊዎች የሚለዩት በሁለት ከተሞች በሚከናወኑ የፍፃሜ ውድድሮች ሆኗል፡፡ 12ቱን የዳይመንድ ሊግ የማጣርያ ውድድሮች ዘንድሮ ያስተናግዱት የዶሃ ከተማ በኳታር፤ የሻንጋይ ከተማ በቻይና፤ የዩጂን ከተማ  በአሜሪካ፤ የሮም ከተማ  በጣሊያን፤ የኦስሎ ከተማ በኖርዌይ፤ የቶክሆልም ከተማ በስዊድን የፓሪስ ከተማ በፈረንሳይ፤ የዙሪክ ከተማ በስዊዘርላንድ፤ የበርሚንግሃም ከተማ በእንግሊዝ፤ የራባት ከተማ በሞሮኮ ፤ የሞናኮ ከተማ በሞናኮ እንዲሁም የለንደን ከተማ በእንግሊዝ  ናቸው። ከእነዚህ የ12 ከተሞች የማጣርያ ውድድሮች በኋላ በከፍተኛ ነጥብ በየውድድር መደቡ የጨረሱ አትሌቶች የዳይመንድ ሊጉ ሻምፒዮኖች በሚለዩት በስዊዘርላንድ ዙሪክ እና በቤልጅዬም ብራሰልስ የሚካሄዱ ውድድሮች ተለይተዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ዘንድሮ በዳይመንድ ሊግ ለማጣርያው እና ለፍፃሜ ውድድሮች ያቀረባቸው የተለያዩ የሽልማት ገንዘቦች ናቸው፡፡ በዳይመንድ ሊጉ በ12 ከተሞች በሚደረጉ የማጣርያ ውድድሮች  ከ1 እሰከ 8ኛ ደረጃ ላገኙ አትሌቶች በሚበረከተው የሽልማት ገንዘብ መሰረት ለ1ኛ 10ሺ ዶላር፤ ለ2ኛ 6ሺ ዶላር፤ ለ3ኛ 4ሺ ዶላር፤ ለ4ኛ 3ሺ ዶላር፤ ለአምስተኛ 2500 ዶላር፤ ለስድስተኛ 2ሺ ዶላር ፤ ለ7ኛ 1500 ዶላር እንዲሁም ለ8ኛ 1000 ዶላር የሚታሰብ ይሆናል፡፡ በሁለቱ የፍፃሜ ውድድሮች ደግሞ የሽልማት ገንዘቡ ለውጥ የተደረገለት ሲሆን ከ1 እሰከ 8ኛ ደረጃ ላገኙ አትሌቶች በሚበረከተው የሽልማት ገንዘብ መሰረት ለ1ኛ 50ሺ ዶላር፤ ለ2ኛ 20ሺ ዶላር፤ ለ3ኛ 10ሺ ዶላር፤ ለ4ኛ 6ሺ ዶላር፤ ለአምስተኛ 5ሺ ዶላር፤ ለስድስተኛ 4ሺ ዶላር ፤ ለ7ኛ 3ሺ ዶላር እንዲሁም ለ8ኛ 2ሺ ዶላር እንዲከፈል ተደርጓል። በፍፃሜዎቹ የዳይመንድ ሊግ ሻምፒዮኖች ለመሆን የሚበቁት 32 አትሌቶች በነፍስወከፍ ከሚያገኙት የ50ሺ ዶላር ሽልማት በተጨማሪ በአልማዝ ማእድን የተሰራ ልዩ የዳይመንድ ሊግ ዋንጫ  ይወስዳሉ። 4.9 ኪግ የሚመዝነው የዳይመንድ ሊግ ዋንጫው ተቀማጭነቱ በስዊዘርላንድ ዙሪክ የሆነው፤ ለ250 ዓመታት በዋንጫዎች፤ የክብር ሽልማቶች፤ ሰዓቶች እና ልዩ ልዩ ጌጣጌጦች ስራ የሚታወቀው ክሮኒዮ ሚቲዬሬ የሚሰራ እንደሆነ ታውቋል፡፡ የዳመንድ ሊግ ዋንጫው በ3 የአትሌቲክስ  ገፅታዎች በስታድዬም ፤ በተመልካች ድባብ እና በአትሌት ብቃት መገለጫነት የተቀረፀ ነው፡፡
12 የዳይመንድ ሊግ ሻምፒዮኖችና 6 የዳይመንድ ሊግ ክብረወሰኖች
የኢትዮጵያ 12 የዳይመንድ ሊግ ድሎች  በ10 አትሌቶች የተመዘገቡ ናቸው፡፡ በ800 ሜትር መሃመድ አማን በ2012 እና በ2013 እኤአ አሸንፏል። በ3ሺ እና 5ሺ ሜትር ወንዶች  በ2010 እና 2011 እኤአ ኢማና መርጋ እንዲሁም በ2013 እኤአ የኔው አላምረው ናቸው። አበባ አረጋዊ ዜግነቷን ሳትለውጥ በፊት በ1500 ሜትር በ2012 እኤአ ላይ አሸናፊ ነበረች፡፡ በሴቶች 5ሺ ሜትር መሰረት ደፋር በ2013 እኤአ ያሸነፈች ሲሆን በ3ሺ ሜትር መሰናክል ደግሞ 2014 እኤአ ላይ ህይወት አያሌው ድል አድርጋለች፡፡ በ2015 ደግሞ ዳይመንድ ሊጉን በ5ሺ ሜትር ለማሸነፍ የበቃችው ገንዘቤ ዲባባ ስትሆን በ2016 እኤአ ደግሞ በ3ሺ እና 5ሺ ሜትር መደብ አልማዝ አያና እና ሃጎስ ገብረህይወት አሸንፈዋል፡፡ በ2017 ኢትዮጵያ የዳመንድ ሊግ ሻምፒዮን አላስመዘገበችም፡፡
በ3ሺ ሜትር የኔው አላምረው በኳታር ዶሃ በ2011 እኤአ ላይ በ7፡27.26
በ5ሺ ሜትር ደጀን ገብረመስቀል በፈረንሳይ ፓሪስ በ2012 እኤአ 12፡46.81
በ10ሺ ሜትር ቀነኒሳ በቀለ በቤልጅዬም ብራሰልስ በ2011 እኤአ 26፡43.16
በሴቶች 1500 ገንዘቤ ዲባባ በፈረንሳይ ሞናኮ በ2015 እኤአ ላይ 3፡50.07 የዓለም ሪከርድ ነው፡፡
በሴቶች 5ሺ ሜትር አልማዝ አያና በሮም ጣሊያን በ2016 እኤአ 14፡14.32
በ10ሺ ሜትር ጥሩነሽ ዲባባ በአሜሪካ ዩጂን 2012 እኤአ ላይ በ30፡24.39
በ8  የዳይመንድ ሊግ የውድድር ዘመናት በሻምፒዮኖችና በክብረወሰኖች የአገራት  ደረጃ
ባለፉት 8 የዳይመንድ ሊግ የውድድር ዘመናት 59 የዳይመንድ ሊግ አሸናፊዎችና 9 የዳይመንድ ሊግ ክብረወሰኖች  ያስመዘገበችው አሜሪካ አንደኛ ደረጃ ይዛለች፡፡ ኬንያ በ37 የዳይመንድ ሊግ ሻምፒዮኖችና በ8 የዳይመንድ ሊግ ክብረወሰኖች ሁለተኛ ደረጃ ላይ ስትሆን፤ ጃማይካ በ18 የዳይመንድ ሊግ ሻምፒዮኖች እና 7 የዳይመንድ ሊግ ክብረወሰኖች ሶስተኛ ፤ ኢትዮጵያ በ2012 እኤአ ላይ አበባ አረጋዊ በ1500 ሜትር ዜግነቷን ወደ ስዊድን ሳትቀይር ያስመዘገበችውን ድል ጨምሮ በ12 የዳይመንድ ሊግ ሻምፒዮኖችና ስድስት የዳይመንድ ሊግ ክብረወሰኖች አራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡

Read 2662 times
Administrator

Latest from Administrator