Sunday, 17 September 2017 00:00

የአዋሽ ወንዝ መጥለቅለቅ ከ11 ዓመታት በኋላ የተፈጠረ ከባድ አደጋ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

· “አደጋው ከመድረሱ በፊት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶ ነበር”
· ከ2800 በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል

    የአዋሽ ወንዝ ሙላትን በተመለከተ የኦሮሚያና የአፋር ክልሎች ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቦ እንደነበር ያስታወቀው የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን፤የአዋሽ ወንዝ መጥለቅለቅ ከ11 ዓመታት በኋላ የተፈጠረ ከባድ የጎርፍ አደጋ ነው ብሏል፡፡
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ በጉዳዩ ላይ ለአዲስ አድማስ በሰጡት ዝርዝር ማብራሪያ፤ በዘንድሮ ክረምት በተለያዩ አካባቢዎች ጠንከር ያሉ የጎርፍ አደጋዎች መከሰታቸውንና አሁንም እየተከሰቱ መሆኑን ጠቁመው፣ ሰሞኑን በተፍኪ አካባቢ ከ2800 በላይ ሰዎች እንዲፈናቀሉ ምክንያት የሆነው አደጋ ግን የዓመቱ ከባድ አደጋ ሆኖ መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት በሚገኘው በሰበታ ሃዋስ ወረዳ በተለይ በተፍኪ ወረዳ የተከሰተው የአዋሽ ወንዝ መጥለቅለቅ አደጋ፣ 3 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የነበረ ሰብልና የግጦሽ መሬት ጎድቷል፤ በሰው ህይወት ላይ ግን ያደረሰው የሞት አደጋ የለም ብለዋል፤ አቶ ደበበ፡፡
በውሃው የተከበቡ ከ2800 በላይ ዜጎችን በሄሊኮፕተሮች፣ በጀልባዎችና ታንኳዎች በመጠቀም ወደ ሌላ ቦታ ለማጓጓዝ መቻሉን የጠቆሙት ሃላፊው የቀሩትንም በውሃ ከተከበበው አካባቢ ለማውጣት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
አደጋው ሊከሰት እንደሚችል ኮሚሽኑ አስቀድሞ በነሐሴ ወር ማስጠንቀቂያ ማስተላለፉን ጠቅሶ ሆኖም ግን ለማስጠንቀቂያው ተገቢው ትኩረት ባለመሰጠቱ የሰሞኑ ሰብአዊ ቀውስ መፈጠሩን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
የውሃ መጥለቅለቁ ያጋጠመው በሰበታ - ሃዋስ ወረዳ ስር በሚገኙ አዋሽ በሎ፣ ወሊካ፣ ቦንዴ፣ ተፍኪ፣ ቦሌ እና እስከ ሰበታ ጫፍ ድረስ መሆኑን አቶ ደበበ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ በየክረምቱ  1.5 ሚሊዮን ያህል  ዜጎች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ መሆናቸው ተገልጿል፡፡     

Read 3276 times