Sunday, 17 September 2017 00:00

የቅማንት ህዝበ ውሳኔ በነገው ዕለት ይካሄዳል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

ምርጫው፤“በነባሩ አስተዳደር” ወይስ “በቅማንት ራስ ገዝ” የሚል ነው

የፌዴሬሽን ም/ቤት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት፣ የቅማንት ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ህዝበ ውሳኔ በነገው ዕለት የሚካሄድ ሲሆን ከ23 ሺ በላይ ሰዎች ድምጽ ይሰጡበታል ተብሏል፡፡ ጊዜያዊ ውጤቱም ህዝበ ውሳኔው እንደተጠናቀቀ፣ በየቀበሌ ፅ/ቤቶችና ምርጫ ጣቢያዎች እንደሚለጠፍ ታውቋል፡፡  
በህዝበ ውሳኔው ላይ የሚቀርቡት አማራጮች፣ “በነባሩ አስተዳደር እንቀጥል” ወይስ “በቅማንት ራስ ገዝ እንተዳደር” የሚል መሆኑን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ ተስፋለም አባይ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡ በህዝበ ውሳኔው ላይ የበለጠ መተማመን እንዲፈጠር የህዝበ ውሳኔው አስፈፃሚዎች ሆነው የተመረጡት ከኦሮሚያ፣ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ከአዲስ አበባና ከደቡብ ክልል የተውጣጡ 175 ያህል ግለሰቦች መሆናቸውን አቶ ተስፋለም አስረድተዋል፡፡
ህዝበ ውሳኔው በጎንደር ስር በሚገኙ 4 ወረዳዎች ውስጥ ባሉ 12 ቀበሌዎች እንዲደረግ አስቀድሞ እቅድ ቢያዝም በ4ቱ ቀበሌዎች በጉዳዩ ላይ የሚደረገው ውይይት ባለመጠናቀቁ፣በነገው ዕለት በ8 ቀበሌዎች ብቻ  ህዝበ ውሳኔው ይካሄዳል ተብሏል፡፡
በእነዚህ 8 ቀበሌዎች በሚገኙ 24 የህዝበ ውሳኔ መስጫ ጣቢያዎች፣ከነሐሴ 29 ቀን 2009 እስከ ረቡዕ መስከረም 3 ቀን 2010 በተደረገው የመራጮች ምዝገባ፣12 ሺህ 832 ወንዶች እና 10 ሺህ 451 ሴቶች በድምሩ 23 ሺህ 283 ሰዎች መመዝገባቸውን አቶ ተስፋለም ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
የህዝበ ውሳኔው ድምፅ አሰጣጥ ስነ ስርአት ነገ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት የሚካሄድ ሲሆን ከህዝብ የተውጣጡ ታዛቢዎችም ሂደቱን ይታዘቡታል ተብሏል። ህዝበ ውሳኔው የሚከናወነው በአብላጫ ድምፅ (50+1) የምርጫ ሥርአት መሰረት መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የድምጽ ቆጠራ እንደተጠናቀቀ ጊዜያዊ ውጤቱ በየቀበሌው የሚለጠፍ ሲሆን የመጨረሻው የተጠቃለለ ውጤት ደግሞ ቦርዱ ለፌዴሬሽን ም/ቤት መስከረም 15 ቀን 2010 ዓ.ም ከላከ በኋላ በም/ቤቱ የፀደቀው ውጤት ይፋ ይደረጋል ተብሏል፡፡
በውጤቱ ላይ ቅሬታ ያለው አካል፣አቤቱታውን እስከ ፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ድረስ ማቅረብ እንደሚችልም አቶ ተስፋለም አስታውቀዋል፡፡   

Read 3657 times