Sunday, 17 September 2017 00:00

የአገራችን የፖለቲካ ቁማርና፣ 250ሺ ኢትዮጵያውያን ወደ የመን የሚሰደዱበት “ሚስጥር”

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(12 votes)

 • እነሱ ይሰደዱ። እኛስ ምን እየሰራን ነው? እኛማ... “የክልልና የዞን አዋሳኝ” የሚል የውዝግብና የጩኸት ሰበብ አለለን። እንጩህ። የትርምስ ዘር፣ በየአቅጣጫው
      እንዝራ።
     • እዚህና እዚያ፣ ክልልና ዞን በእሾህ ለማጠር ስንጮህ፣ በጅምላ የመጠፋፋት ድግስ ይሆንልናል። “የኦሮሚያና የሶማሌ ክልል ወሰን”፣ “ጠገዴ እና ፀገዴ” እያልን
       እንቆስቁስ!
     • ሩብ ሚሊዮን ስደተኞች፣ በአገራችን ተስፋ አጥተው፣ ርቀው ይሂዱ። ለኛ ግን፣ የፖለቲካ ቁማር ይበልጥብናል። ቋንቋ፣ ብሔር ብሔረሰብ፣ ሃይማኖት በሚሉ
       ካርዶች፣ ቁማር እናጧጡፍ!
     • ወጣቶቹ ይሰደዱ - ኑሮ ለማሻሻል ተመኝተው፣ ለመሞከር አስበው ይሂዱ። ለኛ ግን፣ “ራስ ወዳድነት” ነውር ነው። እንደማገዶ መንደድና ማንደድ ነው የኛ
        የበጎ ፈቃድ አድራጎት!

    
   ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ፣ ሩብ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ወጣቶች፣ በጂቡቲና በሶማሊያ በኩል፣ ወደ ጦርነት አገር፣ ወደ የመን ገብተዋል። ወደ የመን? ለዚያውም ወደ የመን! በርካታ ሺ የየመን ዜጎችኮ፣ አገራቸውን ጥለው እየሸሹ ነው - ከጦርነት ለማምለጥ፣ ከእልቂት ለመትረፍ።
በተቃራኒው፣ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች፣ ወደ የመን እየጎረፉ ነው - ከኢትዮጵያ እየሸሹ። እኛ ደግሞ፣ “ለምን? እኮ ለምን?” ብለን ራሳችንን ላለመጠየቅ እንሸሻለን። አይናችንን እንጨፍናለን። ነገር ግን፣ ከጦርነትና ከአገር መሸሽ ቢቻልም፣ ከጥያቄ ለማምለጥ መሞከር ግን፣ ቀሽም ፍርሃት ነው። እስቲ አንዳንዴ እንኳ፣ ራሳችንን ለመጠየቅና ለማሰብ እንሞክር።
ሩብ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን፣ በየመን በኩል ለመሰደድ የሚደፍሩትና የሚጨክኑት ለምን ይሆን? ሚስጥሩ ምንድነው?
መቼም፣ በእርግጠኝነት መናገር የምንችላቸው ነገሮች አሉ። አንደኛ... ብለን እንጀምር።
ሩብ ሚሊዮን ወጣቶች የሚሰደዱት፣ በብሔር ብሔረሰብ ለመቧደንና የተሿሚ ሚኒስትሮችን የትውልድ ሃረግ እየቆጠሩ ለመነታረክ ጓጉተው አይደለም። በተቃራኒው፣ የስደተኞቹ ጉዞ፣ “ከብሔር ብሔረሰብና ከትውልድ ሐረግ ጣጣ” ለመራቅ የሚጠቅም ጉዞ ነው። እንደመንጋ፣ በብሔረሰብና በጎሳ ከመቧደን እየራቁ፣ ወደ ኑሮና ወደ ሕይወት ለመቅረብ እየተመኙ ቢሰደዱ አይገርምም። ምኞታቸው መሳካት አለመሳካቱን፣ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም።
ሁለተኛ፤...
ሩብ ሚሊዮን ወጣቶች ከአገር የሚሰደዱት፣ የክልልና የዞን ወሰኖችን በእሾህ ለማጠር ጎምዥተው አይደለም። ለነገሩ፣ የወሰን ውዝግቦች፣ በአብዛኛው ለፖለቲካ ቁማር የሚያገለግሉና በጭፍን ለመቧደን የሚውሉ ሰበቦች ናቸው እንጂ፣ “ያችኛዋ መንደርና እነኛ ጎጆዎች”... በዚኛው ክልል፣ አልያም በዚያኛው ዞን መስተዳድር ውስጥ ቢሆኑ፣ ለማንም ሰው “የሞት ሽረት” ጉዳይ ሊሆን ባልተገባው ነበር። ሁሉም ኢትዮጵያዊ፣ በያለበት ቦታም ሆኖ በሌላ አካባቢ፣ ኑሮውን የመምራት ነፃነቱና መብቱ እንዲከበር የምንፈልግ ቢሆን ኖሮ፣ የቀበሌና የወረዳ፣ የክልልም ሆነ የዞን መስተዳድር መለያየት፣ የመተራመሻ ሰበብ አይሆንም ነበር።
በዚያ ላይ፣ በክልሎች ወይም በዞንና ወረዳ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖር ሰው ብዙ አይደለም። እንዲያውም፣ የድንበር አካባቢዎችን የሚያውቅ ሰው ጥቂት ነው። ስንቱ ነው፣ ስለ “ወልቃይት ጠገዴና ፀገዴ”  የሚያውቅ? የሶማሌ ክልልና የኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎችን፣ ወይም የጉጂ ዞንና የቦረና ዞን አዋሳኝ ቦታዎችን የሚያውቅም ሆነ ለማወቅ የሚፈልግ ሰው በጣም ጥቂት ቢሆንም፤... የፖለቲካ የቁማር ካርድ እየሆነ፣ በዚሁ ሰበብ ጩኸት ሲጋጋል እናያለን። አዋሳኝ አካባቢዎችን በእሾህ ለማጠር የሚካሄድ ቅስቀሳ፣ በመንጋና በጭፍን ስሜት ለማቧደን እየተመቻቸው፣ አገር ምድሩን የሚያተራምስ ጥፋት ለመደገስ ይጠቀሙበታል።
ሩብ ሚሊዮን ወጣቶች የተሰደዱት ግን፣ የወሰን አጥርና የፖለቲካ ቁማር ፍለጋ አይደለም። ይልቅስ፣ በክልልና በዞን ሳይታጠሩ፣ ከእሾህ አጥርና ከዚሁ የፖለቲካ ቁማር ርቀው ነው የሄዱት።
ሦስተኛ፤...
ሩብ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን፣ በጦርነት በምትተራመሰው በየመን በኩል የሚሰደዱት፣ በሃይማኖት ተከታይነት እንደመንጋ ለመቧደንና የአንድ ሃይማኖት ብቸኛ ስብከት ቀን ከሌት ለመስማት ቋምጠው አይደለም። ነገር ዓለሙን ሁሉ ለመርሳትና የሃይማኖት መሪዎችን ትዕዛዝ ብቻ ለመፈፀም፣ ኑሮንና ዓለማዊ ሕይወትን ለመናቅ ፈልገውም አይደለም።
የራሳቸውን ኑሮ ለማሻሻልና፣ እንደየአቅማቸው በራሳቸው ጥረት ስኬታማ ለመሆን መሻትን ጠልተውም አይደለም። በስራ አማካኝነት የራስን ኑሮ የማሻሻል ምኞት፣ “ራስ ወዳድነት” እንደሆነ ሳያውቁ ቀርተውም አይደለም።
በተለመደው የአገራችን ባህልተመርተው፣ “ራስ ወዳድነትን” እንደነውርና እንደወንጀል እየቆጠሩ፣ “ራሳቸውን ለሌሎች መስዋዕት ለማድረግ” በማሰብ አይደለም - የተሰደዱት።
እዚህ ላይ፣ ከምር እንነጋገር።
የሰረቀ ሰው እና ያመረተ ሰው፣... ያለ ልዩነት እንደ “ነውረኛ” የሚቆጠሩባት አገር ውስጥ እየኖርን መሆናችንን አትርሱ።
ሌቦችና አምራቾች እኩል ይወገዛሉ - በተመሳሳይ አባባል - (“ራስ ወዳድ”) ተብለው። ይሄ፣ አስገራሚ የውግዘት አባባል እንደሆነ አስታውሱ። በእርግጥ፣ አስገራሚነቱ ገና ድሮ ተረስቷል። “ራስ ወዳድ” ብሎ መተቸት፣ “ተመጋቢ” ወይም “ለባሽ” የሚል ስድብ እንደመፍጠር ማለት ነው። ምግብ መብላትና ልብስ መልበስ ነውር ሆኖ ያርፈዋል። ያው፣ “ኗሪ” የሚል ውግዘት ከመፍጠር አይተናነስም።
በዚህ ነባር የአገራችን የስነምግባር መርህ መነፅር የምናይ ከሆነ፣... ሰርቃ የበላችና የለበሰች ሴት፤ እንዲሁም አምርታ የበላችና በደሞዟ ልብስ የገዛች ሴት፣... ያው ናቸው፣  “ተመጋቢ” እና “ለባሽ” ናቸው። “ራስ ወዳድ” ናቸው - ማለትም “ነውረኛ”!
“ራስ ወዳድ” የሚል የውግዘት አባባል የተዘወተርባት አገር ውስጥ፤... የስነምግባር መርህ ምን ያህል “ባፍጢሙ” እንደሚፈጠፈጥ ተመልከቱ። መስረቅና ማረስ፣ ሙስናና ኢንቨስትመንት፣ ገንዘብ ማጭበርበርና በነፃ ገበያ ምርትን መገበያየት... ያው “ነውረኛ” ተብለው የሚወገዙበት ነው - የአገራችን የስነምግባር ቅኝት። ይሄ፤ “የተዛባ የስነምግባር ቅኝት” ተብሎ የሚታለፍ አይደለም። ከዚህም የባሰ ነው። “የኋሊት የዞረ፣ ቁልቁል የተደፋ ፀረ-ስነምግባር” ተብሎ ቢሰየም ይሻላል። የአገራችን ነባር የስነምግባር መርህ፣ እንዴት ነው ቁልቁል የተደፋው? እንዴት ነው የስነምግባር ፀር የሚሆነው?
በነባሩ የስነምግባር መርህ ላይ፣ “ዋናው ነገር፣ መስረቋ አልያም ልብስ መሸመኗ” አይደለም። ይልቅስ፣ ሰርቃም ሆነ ሸምና፣... የትም ፈጭታም ሆነ መንትፋ ታምጣው። ችግር የለውም። ዋናው ነገር፣ ሌሎችን ካለበሰችና እርቃኗን ከቀረች፤ ሌሎችን ካጎረሰችና በረሃብ ከጠወለገች... ያኔ፣ ትልቅ የበጎ አድራጎት ሞዴል ተብላ ትሸለማለች። ራሷን ከመገበችና ካለበሰች ግን፣... ያው ሃጥያተኛ ናት - “ራስ ወዳድ”።
እናም፣ ከዘራፊ ሰው ያላነሰ ውግዘት፣ ማን ላይ ይደርሳል? ሰርቶ ሃብት ያፈራ ሰው ላይ! ተምሮና ሰርቶ፣ የራሱን ኑሮ የሚያሻሽልና ሃብት የሚያፈራ ሰው፣ ልክ እንደ ቀማኛ፣ በንቀት የሚታይበት አገር ውስጥ መሆናችንን በየእለቱ ማረጋገጥ ትችላላችሁ። የአመቱ መጨረሻ ላይ ለተመራቂ ወጣቶች የሚቀርብላቸው የትልልቅ ባለስልጣናትና የታዋቂ ሰዎች ንግግር ምን ምን እንደሚል ለማስታወስ ሞክሩ። በአብዛኛው ተመሳሳይ ነው።
“የራሳችሁንና የቤተሰባችሁን ኑሮ ለማሻሻል፣ አላማችሁን ለማሳካት፣ በእውቀትና በብልሃት፣ በትጋትና በፅናት ስሩ!” የሚል ምክር፣... እንዲህ አይነት “ራስ ወዳድነትን” የሚያበረታታ ምክር፣.. ለአገራችን... ያልተለመደ እንግዳ ምክር ነው።
የተለመደው የዘወትር ምክር፣... “ከራሳችሁ በፊት የሌሎችን ጥቅም አስቀድሙ። መስዋዕት ሁኑ። እንደ ሻማ ቅለጡ”... የሚል ነው የአገራችን ድንቅ ምክር። እንደ ሻማ መቅለጥ፣ እንደ ማገዶ መንደድና መክሰል ነው - ከሰው የሚጠበቀው ተግባር።
ይሄው “ቁልቁል የተደፋ ስነምግባር” ነው፤ ነባርና አንጋፋ የአገራችን ባህል - ለዚያውም በጭፍን ለምዕተ ዓመታት የዘለቀ።
ሌላ “የስነ ምግባር አማራጭ”፣ ጨርሶ ቦታ የለውም። ትክክለኛ የስነ ምግባር መርህ ቢመጣ እንኳ፣ በቅጡ የመስማት ፈቃደኝነት፣... ያን ያህልም የለም። ይህንን ለማረጋገጥም፣ ለምሳሌ ያህል፣... አንድ የስነምግባር አማራጭ ብናይስ? ለምሳሌ...
“ራሱን በማገዶነት መጣልም ሆነ ሌሎችንም ሰዎች መማገድ... አፀያፊ ተግባር ነው” የሚል የስነምግባር መርህ የያዘ ሰው መጣ እንበል። ዘራፊ አልያም ተዘራፊ መሆንን የሚጠላ ነው። ሸክም አልያም ተሸካሚ መሆን ክብር አይደለም የሚል ነው። ይልቅስ፣ “ራስን ችሎ መኖር ነው፣ ወደር የለሽ ክብር” ይላል።
“በራሱ አእምሮ እየተመራ፣ በራሱ ብቃት እየተማመነ፣ በራሱ ጥረት ኑሮውን ማሻሻል ነው ክብር - የእኔነት ክብርን የተጎናፀፈ የእርካታና የፍቅር ሕይወት!... ይህንን የመሰለ ክቡር ሕይወት የለም” ይላል ይሄኛው የስነምግባር መርህ። ራስን በመቻል ላይ የተመሰረ የመገበያየት ተግባርም ትልቅ በጎ ተግባር እንደሆነ ይገልፃል። እነዚህን ዋና ዋና የሕልውና ዋስትናዎችን በማይነካ መንገድ (ማለትም፣ ራስን መቻልና መገበያየትን በማይሸረሽር መንገድ) ከቀጠልን ነው፣... ራስን ሳይጎዱ፣ እየማገዱ ወይም እየተማገዱ መንደድን እየተፀየፉ፣ በመስዋዕትነት መጠፋፋትን እያስወገዱ፣... በዚህ መንገድ ብቻ ነው፣... እርስበርስ በፍቅር መደጋገፍ፣ በአስቸጋሪ ጊዜያት ላይም በልግስና መረዳዳት የምንችለው... ይላል ይሄኛው መርህ። (የAyn Rand የስነምግባር መርህ በከፊል ይህንን ይመስላል። ጥሩ አማራጭ ነው። ግን... ያው፣ የአገራችን ጉዞ፣ ከነባሩ አቅጣጫ ውልፍት ሲል አይታይም - በነባሩ “የመስዋዕትነትና የማገዶ” አቅጣጫ፣ ቁልቁል የመጠፋፋት ጎዳና መጓዙን አላቋረጠም!)
በሌላ አነጋገር፣ በሦስት ዓመት ውስጥ፣ 250ሺ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በየመን በኩል ለስደት የተጓዙት፣ “ራስ ወዳድነትን” በመሸሽ፣ “መስዋዕትና ማገዶ” የመሆን ምኞት ገፋፍቷቸው፣ “ከራስ በፊት ሌሎችን ማስቀደም” አምሯቸው አይደለም። ገቢ በማያስገኝና ኑሮን ለማሻሻል በማይረዳ፣ “የበጎ ፈቃድ አገልግሎት” ላይ የመሰማራት ጥም ፀንቶባቸውም አይደለም። ከእነዚህ ሁሉ ጋር የሚያራርቅ ጉዞ ነው - የወጣቶቹ ስደት።
ምን ለማለት ፈልጌ ነው? መኖርን ከፈለግን፣... ማለትም፣ የራስ አእምሮን በመጠቀምና በመስራት የየራሳችንን ኑሮ ለማሻሻልና ስኬትን ለማጣጣም ከፈለግን፣ በራስ የመተማመን (ማለትም፣ በራስ ብቃትና የግል ማንነት የመተማመን) ሰብዕናን የተላበሰ፣ የደስታ፣ የእርካታና የፍቅር ሕይወትን ማጣጣም ከፈለግን፣... ይህንን የሚያፈርሱና ለስደት የሚዳርጉ አጥፊ የፖለቲካ ቁማሮችንንና ቁልቁል የተደፉ “የስነምግባር” ፀር የሆኑ መርሆችን እናስወግድ።     

Read 5215 times