Print this page
Monday, 18 September 2017 10:32

የአዲስ ዓመት ዕቅድ ...

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(13 votes)


     . ጳጉሜ ተጋመሰች…
ቀኑ ተጋመሰ…
“የይቅርታ እርዝመት” የሚል አዲስ አልበሙን ሊለቅ የተዘጋጀው ታዋቂው ድምጻዊ ኪሩቤል፣ ለጋዜጠኛው የገባውን ቃል ሳያፈርስ አልቀረም፡፡
ጋዜጠኛው በረጅሙ ተንፍሶ ሰዓቱን ተመለከተ - 5፡53 ይላል፡፡
“ሜሎዲ ካፌ በረንዳ ላይ እንገናኝ” ብሎ የቀጠረው፣ ታዋቂው ድምጻዊ ኪሩቤል ወርቁ ከግማሽ ሰዓት በላይ ዘግይቷል፡፡ከአሁን አሁን ይመጣል እያለ፣ አሻግሮ መንገዱን ሲያማትር ቆይቷል፡፡ አሁን ግን፣ ተስፋ ወደመቁረጡ ተቃርቧል፡፡
ትናንት ምሽት ደውሎለት ነበር፡፡ አዲሱን አመት በማስመልከት ለህትመት በሚበቃው የጋዜጣው ልዩ ዕትም ላይ፣ የመልካም ምኞት መግለጫ እና የአዲስ አመት ዕቅዳቸውን እንዲያስተላልፉ ከመረጣቸው ታዋቂ ኢትዮጵያውያን አንዱ እንደሆነ ነግሮት ነበር። ኪሩቤልም ግብዣውን በደስታ ተቀብሎ፣ ሜሎዲ ካፌ እንገናኝ ብሎ ቀጥሮት ነበር - አልመጣም እንጂ።
ጋዜጠኛው ሲያመነታ ቆይቶ፣ ምነው ዘገየህ ሊለው ወደ ኪሩቤል ደወለ፡፡
የፈራው አልቀረም… ኪሩቤል ቁርጡን ነገረው፡፡
“ሶሪ!... የአልበሜ ጉዳይ ቢዚ ስላደረገኝ መምጣት አልቻልኩም!... ሌላ ጊዜ ብናደርገውስ?...” አለው፡፡
“ጥ... ጥሩ!...” አለ ጋዜጠኛው ንዴቱን ለመሸሸግ እየሞከረ፡፡
ጋዜጠኛው ተናዷል፡፡
ጋዜጣው ማተሚያ ቤት ሊገባ ሁለት ቀናት ብቻ እንደቀሩትና፣ ጉዳዩ አስቸኳይ እንደሆነ ነግሮት ነበር። እሱ ግን፣ ቃለ-መጠይቁን ሌላ ጊዜ እናድርገው የሚል የጅል ጥያቄ ጠየቀው፡፡
የአዲስ አመት መልካም ምኞቱን እንዲያስተላልፍና የአዲስ አመት ዕቅዱን ለአንባብያን እንዲያጋራ ያቀረበለትን ግብዣ፣ ለሌላ ጊዜ ቢሆንስ ብሎ ማራዘም ምን ማለት ነው?...
ይህቺኛዋ ጳጉሜ ሄዳ፣ ሌላ ጳጉሜ ስትመጣ እንገናኝ ማለት አይደለምን?...
አንድ አመት ሙሉ ታገሰኝ ማለት አይደለምን?...
ጋዜጠኛው ስልኩን ዘግቶ በንዴት ተነፈሰ፡፡
ከቢሯቸው ክበብ የቡና ዋጋ ሶስት እጥፍ ዋጋ የተቆረጠለትን፣ በይሉኝታ ተጠፍንጎ ያለ ዕቅዱ አዝዞ ፈጥኖ የቀረበለትን፣ የቅንጡዎችን የሜሎዲ ካፌ ቡና በንዴት ጨለጠው፡፡
መረረው፡፡
ውሃ ሊጠይቅ ወደ አስተናጋጇ ዞር ሲል፣ አይኖቹ ጥግ ላይ የተቀመጠ ሰው ላይ አረፉ፡፡ ጥቁር ማኪያቶ በጉማማ ጭስ የሚያወራርደውን ሰው በጥርጣሬ አየው። የሆነ ቦታ እንደሚያውቀው እርግጠኛ ነው፡፡ የት እንደሚያውቀው ለማስታወስ ሞከረ፡፡
ሙከራው ተሳካለት፡፡
ሲጋራውን እየማገ አቀርቅሮ እያነበበ የሚያየው ሰው፣ ታዋቂው ሰዓሊ ጆኒ ነው፡፡
ጋዜጠኛው በአጋጣሚው አብዝቶ ተገረመ። ከጆኒ ጋር አምና በዚህ ወቅት ተገናኝተው ነበር። መገናኘታቸው ብቻም አይደለም ጋዜጠኛውን የገረመው፤ የተገናኙት ለተመሳሳይ ጉዳይ መሆኑ ጭምር እንጂ፡፡
ያለፈው አመት ጳጉሜ ላይ፣ የአዲስ አመት መልካም ምኞቱን እንዲያስተላልፍና የአዲስ አመት ዕቅዱን እንዲገልጽ ጠይቆት፣ በፈቃደኝነት አጭር ቃለ መጠይቅ አድርገው ነበር፡፡ ቃለመጠይቁም በጋዜጣው የአዲስ አመት ልዩ ዕትም ላይ ለንባብ በቅቶ ነበር፡፡
እየገረመው ጆኒን በርቀት ያየዋል… እያየው ያስባል… እያሰበ አዲስ ሃሳብ ብቅ አለለት…
“ኪሩቤል ከቀረ፣ ለምን ጆኒን ዘንድሮም አልጠይቀውም?...” ሲል አሰበ ጋዜጠኛው፡፡
ሃሳቡን መላልሶ አጤነው፡፡ ኪሩቤል ቀጠሮውን ስለሰረዘ፣ ሌላ ታዋቂ ሰው ከመጠየቅ ወደኋላ ሊል አይገባውም፡፡ ጆኒም ከኪሩቤል ያልተናነሰ ዝነኛ ሰው ነው፡፡ ኪሩቤል ያልመለሰውን ጥያቄ፣ ወደ ጆኒ ሊያዞረው ይችላል፡፡
እርግጥ አምና በዚህ ወቅት፣መልካም ምኞቱንና የአዲስ አመት እቅዱን ጠይቆት፣ ፈቅዶ በዝርዝር ነግሮት ነበር፡፡ ካልጠፋ ታዋቂ ሰው፣ ዘንድሮም እሱን መጠየቅ አግባብነት ላይኖረው ይችላል። ቢሆንም ከጊዜው መጣበብ አንጻር፣ ሌላ ታዋቂ ሰው ከሚፈልግ፣ ከፊቱ ያገኘውን ጆኒን ቢጠይቀው ምንም አይደለም፡፡
ጋዜጠኛው ፈራ ተባ እያለ ወደ ጆኒ አመራ፡፡
“አስታወስከኝ?...” እጁን ለሰላምታ እየዘረጋ ጠየቀው፡፡
“ኖ!... አ... አይ ሚን...” ጆኒ እላቂ ሲጋራውን መኮስተሪያው ላይ እየደፈጠጠ፣ ግራ በመጋባት አንጋጦ እያየ መለሰለት፡፡
“አክቹዋሊ ረጅም ጊዜ ሆኖናል!...” ፈገግ እንዳለ ጨበጠው፡፡
“ይ... ይሆናል...” አሁንም ግራ ተጋብቷል ጆኒ፡፡
“መቀመጥ ይቻላል?...” ወደ ባዶው ወንበር ጠቆመ፡፡
“ኦፍኮርስ!...” እንዲቀመጥ ጋበዘው፡፡
“የሚገርም አጋጣሚ ነው!... ምናልባት ካልረሳህ አምና በዚህ ወቅት...” ብሎ ጀመረና የእውቂያቸውን ሰበብ መተረክ ቀጠለ፡፡
“ኢትዝ አሜዚንግ!... በጣም ተለውጠሃል!... ጋዜጠኝነት ተስማምቶሃል ማለት ነው?...” ጆኒ ተገርሞ ጠየቀው፡፡
የሆነ ያልሆነውን ሲያወሩ ቆዩ፡፡ የሆነ ያልሆነው ሲያልቅ፣ ሃሳቡን አካፈለው፡፡
“በጣም ይቅርታ ግን!... አጋጣሚውን ለመጠቀም ብዬ ነው... አንድ ሁለት ሶስት አንቀጽ አጠር አድርገህ መልካም ምኞትህንና የአዲስ አመት ዕቅድክን ከነገርከኝ በቂ ነው!...” በስተመጨረሻ ጋዜጠኛው እያግባባ ጠየቀው፡፡
ጆኒ አመነታ፡፡ ባለፈው አመት መናገሩን በማስታወስ፣ የዘንድሮው መደጋገም ይሆናል ሲል አስተባበለ፡፡
ጋዜጠኛው አልተረታም፡፡ ያለፈው አመት አምና ማለፉን ጠቅሶ፣ ለዘንድሮው ደግሞ ቢሰጥ ችግር እንደሌለው ነገረው፡፡
ጆኒ አሳበበ፡፡ ስለአዲሱ አመት የሚያወራበት ጥሩ ሙድ ላይ አለመሆኑን አዲስ ሲጋራ እየለኮሰ ገለጸ፡፡
ጋዜጠኛው እንደዋዛ የጆኒን ሲጋራ አያት፡፡ ከሲጋራዋ ጭስ ውስጥ አዲስ መላ እየተጥመለመለ ሲወጣ ታየው። ደስ አለው፡፡
“አሪፍ አይዲያ መጣልኝ!... ስለአዲሱ አመት ለመናገር ጥሩ ሙድ ላይ ካልሆንክ፣ ለምን ስለአሮጌው አመት አናወራም?...” አለው በደስታ ተውጦ፡፡
“ማ... ማለት?...” ሰዓሊው ግራ ተጋብቶ መልሶ ጠየቀው፡፡
ጋዜጠኛው ፈጥኖ አልመለሰም፡፡
እንዴትስ ፈጥኖ ሊመልስ ይችላል?...
አሪፍ ያለው ድንገተኛ ሃሳቡ፣ ከለኮስከው ሲጋራ ላይ ብልጭ ያለ ነው ብሎ ይንገረው?...
“አምና በዚህ ሰዓት ስጠይቅህ እኮ፣ በአዲሱ አመት ሲጋራ የማቆም እቅድ እንዳለህ ነግረኸኝ ነበር!?... አልተውክም እንዴ?...” ብሎ አጉል ጥያቄ ሰንዝሮ ያስቀይመው?...
በፍጹም!...
ተለሳልሶ ጠየቀው፡፡
“ለምን ካለፈው አመት እቅድህ ምን ያህሉን እንዳሳካህ ጠይቄህ፣ ምላሽህን ጋዜጣችን ላይ አናወጣውም?...”
ጆኒ ከጭሱ ጋር እየተጫወተ ዝም አለ፡፡
“አይሻልም?...” በልመና ድምጽ ጠየቀው ጋዜጠኛው።
“አሪፍ ሃሳብ ነበር... ግን... ሰዓት የለኝም...” ታዋቂው ሰዓሊ ሰበብ ፈጠረ፡፡
“አታስብ!... እኔም ከኤዲተሬ ጋር ቀጠሮ ስላለብኝ፣ ብዙ ሰዓት አልፈጅም!...” አለና ምላሹን ሳይጠብቅ መቅረጸ-ድምጹን ከኪሱ አውጥቶ አፉ ስር ለገታት፡፡
ቃለ-መጠይቁ ተጀመረ፡፡
“ታዋቂው ሰዓሊ ዮሃንስ ታዬ... ያለፈው አመት ላንተ እንዴት ነበር?...”
“አ... አሪፍ ነበር!...”
“ለአመቱ ከያዝካቸው እቅዶችህ ምን ያህሉን አሳካህ?...”
“ብዙዎቹን ያሳካሁ ይመስለኛል!... ግን… ከታይም አንጻር ለመዘርዘር ትንሽ ያስቸግራል...”
“እውነት ነው!... ግ… ግን… ለምሳሌ አምና በዚህ ወቅት ባደረግኩልህ ተመሳሳይ ቃለመጠይቅ፣ በአዲሱ አመት አገር አቀፍ የስእል ኤግዚቢሽን የማዘጋጀት እቅድ እንደነበረህ ገልጸህልኝ ነበር፡፡ ተሳካልህ?...”
ሰዓሊው ላይተሩን ከደረት ኪሱ እየመዘዘ በንዴት መናገር ቀጠለ…
“ምን ይሳካል!?... በኤግዚቢሽኑ ላይ የማቀርባቸውን ስዕሎቼን አዘጋጅቼ ጨርሼ፣ አዳራሽ አልፈቅድልኝ ብለው ሳላቀርብ ቀረሁ!... ከእኔ የሚጠበቀውን ሁሉ በእቅዴ መሰረት አከናውኜ ብጨርስም፣ በቢሮክራሲ ሳቢያ እቅዴ ሳይሳካ ቀርቷል!...” አለና ላይተሩን ማፍተልተል ጀመረ፡፡
“ቢ… ቢሮክራሲ ስትል?...”ጋዜጠኛው ግራ ተጋብቷል፡፡
“እውነቴን ነው የምልህ!... በእዚህች አገር ላይ ተስፋ እየቆረጥኩ ነው!... ጥበብ በቢሮክራሲ ገመድ እየታነቀች ስትቃትት የምትኖርበት አገር ውስጥ ነው ያለነው!... ያሳዝናል!... እኛ አገር ጠቢብን እና ሚስጥር ኪስን ከጉዳይ የሚጥፋቸው ሰው የለም!...” አለና ከደረት ኪሱ የመዘዛትን ሌላ ሲጋራ ለኮሳት፡፡
ጋዜጠኛው ከሲጋራዋ ውስጥ ሌላ ጥያቄ መዘዘ፡፡
“ሌላው ዕቅድህ ደግሞ፣ በአዲሱ አመት ሲጋራ ማቆም ነበር... እሱስ?...”
ሰዓሊው በምጸት ፈገግ አለ፡፡
“በየት በኩል አቆማለሁ!?... እስኪ አንተን ልጠይቅህ?... ትልቅ ተስፋ ያደረግህበት፣ ሌት ከቀን የደከምክበት፣ ለወራት የለፋህበት ታላቅ የጥበብ ድግስህ፣ የስዕል ኤግዚቢሽንህ በቢሮክራሲ ሳቢያ ተሰናክሎ ሲቀር፣ ሲጋራ ይቅርና ሱረት አታጨስም?...” አለና አትኩሮ ተመለከተው፡፡
ጋዜጠኛው ሊያስቀይመው አልፈለገም፤ በአወንታ አናቱን ከፍ ዝቅ አደረገለት፡፡ አድርጎ ሲጨርስ ሌላ ጥያቄ ሰነዘረ፡፡
“ሌላው ደግሞ... ባለፈው አመት ስጠይቅህ... በአዲሱ አመት ከእጮኛህ ጋር ትዳር መስርተህ አዲስ ህይወት የመጀመር እቅድ እንዳለህ ነግረኸኝ ነበር...”
“ማን?... እኔ?...” ሰዓሊው ደንገጥ ብሎ አቋረጠው፡፡
“አ... አዎ!... ት... ትዝ ይልህ እንደሆን... በህዳር ወር መጀመሪያ ላይ፣ ወደ እጮኛህ ቤተሰቦች ሽማግሌ ለመላክና...”
ሰዓሊው ፈገግ አለ፡፡
“ኦ!... እሱን ነው እንዴ?... እሱማ ምን ሆነ መሰለህ... እጮኛዬ አንተ ያደረግክልኝን ቃለ-መጠይቅ ከጋዜጣችሁ ላይ አንብባ፣ በነጋታው እሳት ለብሳ እሳት ጎርሳ መጣችና፣ጥንብ እርኩሴን አውጥታ አትሰድበኝ መሰለህ?!...”
“ለ... ለምን?...”
“ካስታወስክ... ቃለ መጠይቁ መጨረሻ ላይ... ʻለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መልካም አዲስ አመት እመኛለሁʼ ብዬ አልነበር?... እሱን አንብባልህ... ʻእኔ ሜላት ከዘጠና ምናምን ሚሊዮን ህዝብ ጋር ተደባልቄ መላው የምባል ተራ ሰው አይደለሁም!... ስሜን ጠርተህ ሃፒ ኒው ይር ብትለኝ ምን ይጎድልብሃል!?...ʼ ብላ ሰድባኝ በቆምኩበት ጥላኝ ሄደች!... ከዚያች ቀን ጀምሮ አይቻት አላውቅም!...” አለና ሲጋራውን አጥብቆ መጠጣት፡፡
ጋዜጠኛው በሃዘኔታ አናቱን ወዘወዘና ወደ ሌላ ጥያቄ ተሻገረ፡፡
“እሺ ታዋቂው ሰዓሊ ዮሃንስ ታዬ... ሌላው ደግሞ... ʻአዲሱ አመት ያስቀየምኳቸውን ሰዎች ይቅርታ የምጠይቅበት የይቅርታ አመት ይሆናልʼ ብለኸኝ ነበር...”
ሰዓሊው ፈገግ ብሎ ጣልቃ ገባ፡፡
“አይደል?...” ሃፍረት ነገር ተሰምቶታል፡፡
“እንዴት ነው ታዲያ?... ምን ያህል ያስቀየምካቸውን ሰዎች ይቅርታ ጠየቅክ?...” ፈገግ ብሎ ጠየቀው፡፡
“በእውነቱ እንደዛ ያልኩት እንኳን፣ ሌሎች ሰዎች ሲሉ ስለሰማሁ ብቻ ነበር!... የምሬን ነው የምልህ!... እኔ በተፈጥሮዬ ሰው ማስቀየም አልወድም፡፡ ያስቀየምኩት ሰው የለም!... ምናልባት ቅድም ትታኝ ሄደች ያልኩህን እጮኛዬን ካገኘኋት፣ እግሯ ስር ወድቄ ይቅርታ እጠይቃታለሁ፡፡ ዛሬ እዚህ ካፌ የመጣሁት ራሱ፣ ምናልባት ባገኛት ብዬ ነው...” አቀርቅሮ የማኪያቶ ሲኒውን ማሽከርከር ቀጠለ፡፡
ጋዜጠኛው ያለፈውን አመት ቃለመጠይቅ እንደምንም እያስታወሰ፣ ሌላ ጥያቄ ሰነዘረ፡፡
“ሌላው ደግሞ... ʻበአዲሱ አመት የተቸገሩትን ለመርዳት ዕቅድ አለኝ ብለኸኝ ነበር፡፡ ይሄኛው ዕቅድህስ ተሳካ?...”
ሰዓሊው ረጅም የመደነቅ ሳቅ ሳቀ፡፡
“አቦ እናንተ ጋዜጠኞች ደግሞ!... ለጨዋታ ያህል ያልኩህን ሁሉ ጽፈኸዋል እንዴ?...”
ጋዜጠኛው ለሰዓሊው ጥያቄ የፈገግታ መልስ ሰጠና ወደ ሌላ ጥያቄ ተሸገረ፡፡
“እ... ሌላም ነገር አስታወስኩ... ትዝ ይለኛል... ʻበአዲሱ አመት ላሊበላ እና አክሱምን የመሳሰሉ የቱሪስት መስህቦችን የመጎብኘት እቅድ አለኝʼ ብለህ ነበር፡፡ የትኞቹን የቱሪስት መስህቦች ጎበኘህ?...”
“እውነቱን ለመናገር የተቻለኝን ጥረት ሳደርግ ብቆይም፣ እስካሁን ድረስ የትኛውንም አልጎበኘሁም...”
“ስለዚህ እሱም አልተሳካም ማለት ነው?...” ጋዜጠኛው ተገርሟል፡፡
“ለምን አይሳካም?... ይሳካል እንጂ!... ምን ማለትህ ነው?...” ሰዓሊው ተናዷል፡፡
“ማ... ማለቴ... ያው አመቱ አልቋል ብዬ ነው...”
“ምነካህ!?... ዛሬኮ ገና ጳጉሜ ሁለት ነው!... ዛሬ ማታ በአውሮፕላን ተሳፍሬ፣ ነገ ላሊበላን ጎብኝቼ፣ ከነገ ወዲያ ጧት አዲስ አበባ ከተፍ ማለት ያቅተኛል?...”
“ኧ... ኧረ አያቅትህም!... ምናልባት የአውሮፕላን ትኬት ካጣህ ብዬ ነው...” ለማስተባበል ሞከረ፡፡
ሰዓሊው በንዴት ጦፎ ሰዓቱን ተመለከተና አስተናጋጇን ፍለጋ በፍጥነት ዞር አለ፡፡
“ታዋቂው ሰዓሊ ዮሃንስ ታዬ... በስተመጨረሻም... አዲሱን አመት በማስመልከት ለጋዜጣችን አንባቢያንየምታስተላልፈው መልዕክት ይኖራል?...”
“አለኝ እንጂ!... በጣም አለኝ!... ʻአንዳንድ ግለሰቦች አመት ሊቀየር ሲል ጠብቀው፣ የአዲስ አመት ዕቅዳቸውን በተመለከተ የሚናገሩትን ነገር በሙሉ የምር አድርጋችሁ አትውሰዱትʼ ስል ለጋዜጣችሁ አንባቢያን መልዕክቴን አስተላልፋለሁ...” አለና ወደ አስተናጋጇ ዞረ፡፡
“እቸኩላለሁ አላልኩሽም!?... ቢል አምጪልኛ!?...” ጮ¤ባት፡፡
ከአዘጋጁ፡- (ከላይ የቀረበው አጭር ልብወለድ ከጥቂት ዓመታት በፊት “ሰው ሲያቅድ” በሚል ርዕስ ለአዲስ ዓመት ዋዜማ የወጣ ሲሆን ዘንድሮ ደራሲው አንዳንድ ማሻሻያዎች አድርጎበትና ርዕሱ ቀይሮ በድጋሚ የላከልን መሆኑን እንገልጻለን፡፡)

Read 3208 times