Monday, 18 September 2017 10:34

“የሠላም ፍኖት ለኢትዮጵያና ኤርትራ ሕዝቦች አንድነት” ምን ይላል? (ግምገማዊ አስተያየት)

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ደራሲ፡-ተሾመ ብርሃኑ ከማል
                                      የታተመው፡-2009
                                      አሳታሚው፡- በግል
                                      የገጹ ብዛት፡- 200     

       የኢትዮጵያና የኤርትራ ጉዳይ  እጅግ ወቅታዊ  አጀንዳ ነው፡፡ ሊተዉ ከማይችሉ  (unavoidable) ርዕሰ ጉዳዮች አንዱና ዋነኛውም ይመስለኛል፡፡ ይህ ጉዳይ የታሪክ፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ ---ወዘተ ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ ሂደት ማሳያም ጭምር ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ነው በቅርቡ የታተመውን፣ የተሾመ ብርሃኑ ከማል፣ “የሰላም ፍኖት ለኤርትራና ለኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነት” የተሰኘ መጽሐፍ፣  ልዳስሰው የተነሳሳሁት፡፡
የኢትዮጵያንና የኤርትራን ሕዝቦች ወቅታዊ ግንኙነት ከግምት በማስገባትም ይመስላል፣ የመንግሥትም ሆነ የሌሎች ፖለቲካ ድርጅቶች ወይም ግለሰቦች ተጽእኖ እንደሌለበት፣ ፕሮፓጋንዳም ሆነ ወገንተኛም አለመሆኑን ስጋት በተመላበት ሁኔታ ይገልጻል፡፡ ይህም ሆኖ፣  የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች በፖለቲካዊ ድንበር ቢለያዩም በማህበራዊ ኑሮ፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በስነ ልቦና፣ በታሪክ፣… ከጥንት እስከ ዛሬ አንድ መሆናቸውን በማውሳት፣ ወደ ቀዳማዊ አንድነታቸው ተመልሰው ጥንታዊ ታሪካቸውን እንዲያድሱ፣ የሕዳሴ እንቅስቃሴያቸውንም በሕዝቦች የታሪክ እርቅ ላይ እንዲመሠርቱ፣ የታሪክ እርቅን  መሥርተው የሚወስዱት መንገዶች ለሽምግልና የተሻሉ፣ ሰላማዊና ፍትሐዊ መሆናቸውን አውቀው በጋራ እንዲንቀሳቀሱ፣ ሰዎች “እኔ ማን ነኝ?” ብለው በመጠየቅ፣ ማንነታቸውን እራሳቸው እንዲመልሱ … ሐሳብ ለመሰንዘር ይሞክራል እንጂ በኃይል አንድ ይሁኑ ለማለት አይዳዳውም፡፡›› በማለት ከገጽ 7-8 ይገልጽና፣ ‹‹የተወሰኑ የገንጣይ ቡድኖችና ደጋፊዎቻቸው ሴራ ነው›› በሚል እምነት እንዳልተጻፈ፣ ሆኖም አንድ የነበሩ፣ በሥጋ ዝምድና፣ በጋብቻ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚ የተሳሰሩ ሕዝቦች፣ በታሪክ አጋጣሚ ተለያይተዋልና በሰላም ፍኖት እየተጓዙ፣ በመጀመሪያ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ወንድማማችነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንዲመሠርቱ፣ ደረጃ በደረጃ፣ ቀስ በቀስ፣ ስልትና ሐቅን በተከተለ መንገድ ከሁሉ አስቀድሞ የተለያዩ ግለሰቦች፣ ቤተሰቦች፣ ማህበረሰቦች፣ ህብረተሰቦች ብሎም ሕዝቦች በመንገድ፣ በስልክ፣ በደብዳቤና በመሳሰሉት እንዲገናኙ፣ ቀስ በቀስም በአንድ ላይ እንዲሆኑ፣ አንድ ሆነውም የተሻለ የጋራ ልማትና ብልጽግና በምሥራቅ አፍሪቃ እንዲያመጡ፣ ቢቻልም በረጅም ጊዜ ሂደት በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ ኑሮና በፖለቲካ እንዲዋሃዱ፣ ከተዋሃዱም በአፍሪቃ ቀንድ ስመ ገናና ሊሆኑ እንደሚችሉ ገለልተኛ በሆነ የሽምግልና ዓይን ለመጠቆም መሆኑን ያወሳል፡፡   
መጽሐፉ አዳዲስ መረጃዎችን አካትቷል። ከእነዚህም መካከል፡- የኢጣሊያውያን ወደ ኢትዮጵያ መምጣትና ኢጣሊያ በእንግሊዝ ድጋፍ ምጽዋን መያዝ፣ አሰብ በኢጣሊያ ቁጥጥር ስር ስለመሆን፣ የጁሰፔ ሳፔቶ፣ የኢጣሊያ ቅኝ ግዛት ፍለጋና የስለላ ሥራ፣ በሐሰን ቢን አሕመድ፣ በኢብራሂም ቢን አሕመድና በጁሰፔ ሳፔቶ መካከል የተፈረመ ስምምነት፣ በኢጣሊያ መንግሥትና በዓፋር ሱልጣኖች መካከል የተደረጉ ስምምነቶች፣ የኢጣሊያ መንግሥት ንጉሣዊ አዋጅ፣ በጣልያን ንጉሣዊ መንግሥትና በሮባቲኖ ድርጅት መካከል ስለ አሰብ ባለቤትነት ጉዳይ የተደረገ ስምምነት፣ በሱልጣን መሐመድ ሐምፈሬ፣ በንጉሥ ምኒልክና በኢጣሊያ ንጉስ እንደራሴ የተፈረመ ውልና ሌሎችም  ይገኙበታል፡፡
በመጽሐፉ ውስጥ በርካታ አስገራሚ ታሪኮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ጁሰፔ ሳፔቶ፣ ከ1811-1895 (እኤአ) የኖረ ኢጣሊያዊ የላዛሪት ሚሽን ተከታይ ሲሆን ይህም የላዛሪት ሚሽን የተባለ ድርጅት፣ ድሆችን በመርዳት ስም ፓሪስ  በ1625 (እኤአ) ውስጥ ሴንት ቪንቸንት ፖል በተባለ የሃይማኖት አባት የተቋቋመ ነበር፡፡ ጁሰፔ ሳፔቶ የላዛሪት ሚሽን ተከታይ የሆነው በ18 ዓመቱ ሲሆን ወደ ምጽዋ ከመምጣቱ በፊትም (በ1837) ወደ ሊባኖስና ግብጽ ሄዶ እንደነበር የሕይወት ታሪኩን የጻፉ ሰዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይሁንና ድርጅቱ ለድሆች እርዳታ ለመስጠት የተቋቋመ ይባል እንጅ ያቋቋመው የፖለቲካ ድርጅት እንደነበር ይነገራል፡፡ የታሪኩ ጸሐፊዎች እንደሚገልጹት፤ ወደዚህ ስፍራ የመጣው ከሁለት ፈረንሳውያን ወንድማማቾች ጋር ሲሆን ከእነርሱ ጋር ከ1837 እስከ 1847 ባለው ጊዜ ወደ መሃል ኢትዮጵያ በመግባት በአድዋና በጎንደር ጉብኝት አድርጓል፡፡   
ጁሰፔ ሳፔቶ፤ ፍራነቺሰ ጆቫኒ ከተባለ ሌላ ሚሽነሪ ጋር ኦገስት 23 ቀን 1851፣ በምጽዋ በኩል ወደ ከረን መጣ፡፡ በነዚህ ጸሐፊዎች መረጃ መሠረት፣ የላዛሪት ሚሽን ተልእኮውን ለመፈጸም የመጣው በመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጉዞው በጸና ታሞ ወዳገሩ ከተመለሰ በኋላ ነው፡፡ በሁለተኛ ጊዜ ጉብኝቱም እንደ ሚሽነሪ ሳይሆን እንደ ጎብኝ ወደ ምጽዋ በመምጣት፣ ደናኪል (የዓፋር) ጨዋማ ስፍራዎችን፣ ቦጎስንና ሓባብን በ1851 ጎበኘ፡፡ በዚህም ጊዜ ግዕዝ፣ ትግረና ቢለን ቋንቋዎችን በማጥናት መዝገበ ቃላት አዘጋጀ፡፡ ከዚያም ወደ አሰብ መጣ፡፡ በ1858 አጼ ቴዎድሮስ በመንግሥታቸው ላይ ያመጸው አገው ንጉሥን ድል አድርገው፣ በገደሉበት ጊዜ፣ ጁሰፔ ሳፔቶን እስረኛ አድርገው፣ እንደ አስተርጓሚ ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ሆኖም አጼ ቴዎድሮስ ከጊዜ በኋላ ነጻ አድርገው ስለለቀቁት ወደ ፓሪስ ተመለሰና በፓሪስ የቤተ መዘክር ሠራተኛ ሆነ፡፡ ስዊዝ ካናል በ1869 ሲከፈትም የኢጣሊያ መንግሥት በቀይ ባህር ዳርቻ እንደ ወደብ የሚጠቀሙበትን ቦታ እንዲያስገኝ አደራ ተሰጠው፡፡ ወደ አሰብ ከመጣ በኋላም የተሰጠውን አደራ ሳያሳውቅ፣ ከዓፋር ሱልጣኖች ጋር ወዳጅ መስሎ በመቅረብ፣ ከአሰብ የተወሰነውን መሬት፣ አፋር ግዛት በሚኖርበት ጊዜ ሊጠቀምበት በውል እንደገዛ፣ ከዚህ ቀደም ባልቀረበ መልኩ በመጽሐፉ ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
ሲኞር ጁሴፔ ሳፔቶ ኃላፊነቱን ከተወጣ በኋላ ወደ ኢጣሊያ ተመለሰ፡፡ በዚህም ጊዜ ከሚያውቁት ሰዎች ጋር እምብዛም አይገናኝም ነበር፡፡ ሲኞር ጁሴፔ ሳፔቶ ወደ ኢጣሊያ ከተመለሰ በኋላ በአራተኛው ዓለም አቀፍ ኦሪየንታሊስቶች ጉባኤ ላይ፣ በ1878 ተካፋይ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜም የተለያዩ ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ጥናታዊ ጽሑፎችን አቅርቧል፡፡
ከጁሴፔ ሳፔቶ በፊት የምናገኘው የሃይማኖት ሰው ጉልየሞ ማሳይ፣ በተለምዶ አባ ማስያስ (እ.ኤ.አ 1809-1889) የምንለው ቄስ ሲሆን ይህም ሰው ኢጣሊያ ቦቫ በምትባል ስፍራ የተወለደ ነው። በአገራዊ አባባል፣ አባ ማስያስ የተባለው የካቶሊክ እምነት ተከታይ በኢትዮጵያ በተለይም በደቡብና በደቡብ ምዕራብ ውስጥ ለ25 ዓመታት ኖሯል፡፡
አባ ማስያስ ወደ ኢትዮጵያ የተላከው በጉግሊየሞ ስም ሲሆን ጁሴፔ ከተባለ ሌላ ፈረንሳዊ ጋር በመሆን ወደ ሮም ሄዶ ስለ ኢትዮጵያ ሁኔታ ሪፖርት ካቀረበ በኋላ በ1846 ኦሮሞዎችን ክርስቲያን ለማድረግ በሚል ሰበብ ‹‹የኦሮሞ ቄስ›› ተብሎ እንደገና መጣ፡፡ ድሮውንም አባ ማስያስ እየተባለ የነበረው ኢጣሊያዊ አቡነ ባርቶኔሊ በሚል ስም ወደ ጎጃም ተልኮ እንደነበር እርሱን በሚመለከት የተጻፉ ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡ በ1849 ደግሞ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ሞንሲኞር ተባለ፡፡ ይህ ሰው  በ1879  ወደ ሀገሩ የተመለሰ ሲሆን በ1880 በፈረንሳይ በተካሄደው ጉባኤ ላይ በመገኘት ለኦሮሞዎች ተጨማሪ ሚሺነሪዎች እንደሚያስፈልጋቸው አበክሮ የገለጸ ሲሆን በ1884 የካርዲናንነት ሲመት በሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርእስ ሊቃነ ጳጳሳት በአቡነ ሊዮ 33ኛ (1878-1903). ተሰጠው፡፡ በሀገሩም ውስጥ ሕይወቱ አለፈ፡፡ ይሁንና እርሱ ከሞተ ከ75 ዓመታት በኋላ የኢጣሊያ ፋሽስት የአባ ማስያስ በኢትዮጵያ ውስጥ መኖር ለኢጣሊያ ቅኝ ግዛት መመቻቸት ቅድመ ሁኔታ እንደነበር አስታውቋል፡፡ ነገር ግን አባ ማስያስ ፖለቲካዊ ሚና ይኑረው አይኑረው ያሳየው ፍንጭ አልነበረም።  ዳግማዊ አጼ ምኒልክም የዚህ ሰው ጥሩ ወዳጅ እንደነበሩ የሚታወቅ ሲሆን በአማርኛና በኦሮምኛ ያዘጋጀውን የሰዋስው መጽሐፍ አሳትመውለታል፡፡ አባ ማስያስ ከዚህም በተጨማሪ “በኢትዮጵያ ደጋማ ስፍራዎች በሚሽን የቆየሁባቸው 35 ዓመታት” በሚል ርእስ መጽሐፍ ያዘጋጀ ሲሆን ይህም ስለ ኢትዮጵያውያን ማንነት የሚያወሳ መጽሐፍ በ1936 መታተሙ ይታወቃል፡፡ መጽሐፉ ጠቃሚ ሆኖ በመገኘቱም ወደ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛና ጀርመንኛ ተተርጉሟል፡፡
እነ አባ ጁሴፔ ሳፔቶና እነ አባ ማስያስ በአንድ በኩል ሃይማኖት በሌላ በኩል ደግሞ የፖለቲካ አማካሪ፣ በዋነኛነት ስለ ኢትዮጵያ ሁኔታ ለመንግሥታቸው መረጃ አስተላላፊ ሆነው ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ ተልእኳቸውን ሲፈጽሙም ወደ ሀገራቸው እየተጠሩ ሹመት የተቀበሉ ሲሆን  የኢጣሊያ መንግሥት ደግሞ ያገኘውን መረጃ በመጠቀም፣ ቅኝ ግዛት የማስፋፋት ዓላማውን ለማስፈጸም ተጠቅሞበታል፡፡
ስለ ዓድዋ ጦርነት በሚያወሳው ምዕራፍ እንደተጠቀሰው ሁሉ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን መውረር የጀመረችው በእነ ጋርባልዲና ማዚኒ ተበታትና የነበረችው ኢጣሊያ፣ በ1861 በተዋሃደች በ17 ዓመታት ውስጥ ነው፡፡ ያኔ ኢጣሊያ ከተዋሃደች በኋላ ብዙዎች ታላቋን ኢጣሊያ የመመስረት ሕልም ነበራቸው፡፡ በወቅቱ የኢጣሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረው ፍራንሲስኮ ክሪስፒ፤ ኢጣሊያን ትልቅ ማድረግ የሚቻለው በአፍሪካ ውስጥ ቅኝ ግዛት ለማስፋፋት የተቻለ እንደሆነ ነው ብሎ ያምን ነበር። ስለሆነም ቀደም ሲል በተጠቀሰው ውል መሠረት ጁሰፔ ሳፔቶ፣ የአሰብ የተወሰነ ክፍል በ1869 ሲገዛ፣ ዓላማው ለራፌኤሎ ሩባቲኖ ኩባንያ የመርከብ ከሰል መሙያ የነበረ ሲሆን የኢጣሊያ መንግሥት ግን በውሉ ውስጥ የነበሩትን ቀዳዳዎች ተጠቅሞ፣ የቅኝ ገዥነት እግሩን የሚተክልበት ቦታ አደረገው፡፡
ከውህደት ወዲህ የመጀመሪያ ንጉሥ የነበረው ዳግማዊ ቪቶሪዮ ኢማኑኤልም “ኢጣሊያ መከበር ብቻ ሳይሆን መፈራት አለባት” የሚል አቋም ነበረው፡፡ የስዊዝ ካናል በ1869 መከፈት ለኢጣሊያ የንግድ እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከቱ፣ መርከቦቿ የድንጋይ ከሰል ነዳጅ የሚሞሉበትና ዕቃዋን በቅብብሎሽ ወደ ሌሎች አገሮች የምታሻግርበትን ወደብ ትፈልግ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ‹‹ሊጉሬ›› የተባለው የንግድ መርከብ ማህበር (Associazione Marittima Mercantile Ligure) ‹‹ቀይ ባህርን በማቋረጥ እስከ እሩቅ ምሥራቅ አገሮች መጓዝ የሚቻለው በእንፋሎት በሚሄድ መርከብ መሆኑንና እንፋሎት ለመፍጠር የሚያስችለው ድንጋይ ከሰል የሚራገፍበት ወደብ በአፍሪካ ቀንድ ማግኘት እንደሚገባ  ለመንግሥት ሪፖርት ካቀረበ በኋላ፣ ሐሳቡ ተቀባይነትን በማግኘቱ፣ የመንግሥት ባለስልጣናት በጉዳዩ መምከር ጀመሩ፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ካሉት ስፍራዎች ያለ ችግር የሚያዙትና ለወደብነት የሚያመቸው የትኛው እንደሆነ ለማወቅ ከዚህ ቀደም ለመልክዓ ምድር ጥናት የላኳቸው ባለሙያዎች ያቀረቡትን መረጃ መመልከት ጀመሩ፡፡ ራፋኤሎ ሩባቲኖ፣ ያኔ ግንባር ቀደሙ የንግድ መርከቦች ኩባንያ ባለቤት ከመንግሥት ጋር መልካም ግንኙነት የነበረው ሲሆን መንግሥትም አዳዲስ የንግድ መስመሮችን በሜዲትራንያንና በቀይ ባህር አካባቢ ባሉ የአፍሪካ አገሮች የባህር ድንበር ላይ እንዲዘረጋ አደራ ጥሎበት ነበር፡፡  ‹‹ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል›› እንዲሉም ሲኞር ጁሰፔ ሳፔቶ ሆን ብሎ በውሉ ውስጥ እርሱ ለመኖሪያነት በገዛው መሬት ላይ ሌሎች የእርሱ ሰዎች መጥተው ቢኖሩ ምንም ዓይነት ተንኮል በአፋሮች ዘንድ እንደማይደርስባቸው ቅዱስ ቁርዓን አስይዞ አስምሏቸው ስለነበር በእርሱ እግር የሩባቲኖ ኩባንያ፣ በሩባቲኖ ኩባንያ እግር፣ የኢጣሊያ ቅኝ ገዥዎች እስከ መጨረሻው እያታለሉና እየሸፈጡ ቦታ ያዙ፡፡ ከፊል አሰብ ለሩባቲኖ ኩባንያ በ1870 ዓ.ም መሸጧን ተከትሎም ዘመናዊ ወደብ ተደርጋ ተሠራች፡፡ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላም ኩባንያው ከአሰብ እስከ መሃል ሐበሻ የነበረውን ንግድ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማካሄድ የጦር መርከቦች እንደሚያስፈልጉት ገለጸ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ካሮሊም የኢጣሊያ መንግሥት ምክር ቤት የተቀደሰ ሐሳቡን የደገፈው መሆኑን ገልጾ፤ ‹‹ቅኝ ግዛታችንን ለመጠበቅ ሁለት የጦር መርከቦች ልኬልሃለሁ›› የሚል መልእክት አስተላለፈለት፡፡  ክርሲፒ በሁለተኛው ደብዳቤው፣ በአሰብ የንግድ ማዕከል መቋቋሙ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በማሳደግ በኩል ጠቀሜታ እንደሚኖረው ጠቁሞ፣ በንግዱ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን የኢጣሊያን የባህር ኃይል ለማደራጀትም አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገለጸለት፡፡ ከዚህ ደብዳቤ በግልጽ እንደምንረዳውም፣ ምንም እንኳን ጁሰፔ ሳፔቶ ለመኖሪያነት ገዝቶ ለነዳጅ መሙሊያነት ለራፋኤሎ ሩባቲኒ ቢያስተላልፈውም አሰብ ወደ ኢጣሊያ ቅኝ ግዛትነት የመቀየር ፍላጎት የነበራት መሆኑን ነው፡፡
በዚህም መሰረት፣ በአዋጅ ቁጥር 857፣ በአሰብ የጣልያንን ቅኝ ግዛት በተመለከተ በ5/6/1882 ዓ.ም በወጣ አዋጅ ነጋሪት ጋዜጣ ቁጥር (160/10/7/1882 ዓ.ም) ‹‹ቀዳማዊ ኡምቤርቶ የጣልያን ንጉሥ፣ የሕዝብ እና የዘውድ ምክር ቤቶች የተስማሙበትን በማጽደቅ ከዚህ ቀጥሎ የቀረበውን አወጀች፡፡ በዚህም አዋጅ፣ ከቀይ ባሕር በስተደቡብ ምዕራብ ጠረፍ የምትገኘዋ የአሰብ ክልል፣ የጣልያን ቅኝ ግዛት ሆኖ በጣልያን መንግሥት ሥር እንድትተዳደር ተደርጓል፡፡ ክልሉም ከራስ ደርሚክ እስከ ራእስ ሎማ ድረስ ያለው ስፋቱ ስድስት ማይልስ፣ ከራስ ሎማ እስከ ራስ ደውራን ድረስ ያለው ስፋቱ ሁለት ማይልስ የሆነ፣ ከሼክ ደውራን አስኮ ራእስ ሣንቶራ ድረስ ያለው ስፋቱ አራት ማይልስ የሆነ፣ ከራስ ሎማ ፊት ለፊት የሚገኘው የሠንዓቡር ደሴት፣ ከጠረፍ ፊት ለፊት የሚገኙ ደሴቶች- ከራስ ሉማ እና ከራእስ ሣንቱር ፊት ለፊት ያሉትን ያጠቃልላል፡፡ በጣልያን መንግሥትና በሩባቲኖ ድርጅት መካከል በማርች 10/1882 ተደርጎ የነበረው ስምምነት ስለጸደቀ፣ በስምምነቱም መሠረት፣ የድርጅቱ ንብረት ወደ ጣልያን መንግሥት ተሸጋግሯል፡፡›› ንጉሥ ኡምፔርቶ፣ ጁላይ 5 ቀን 1882 ሮማ፡፡
ከዚህም አዋጅ በኋላ በምድረ ኤርትራ ስለተሾሙት የኢጣሊያ ባለስልጣኖች ስም ዝርዝር በመጽሐፉ ውስጥ እናገኛለን፡፡ ‹‹የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል›› እንዲሉ፣ የኢጣሊያ መንግሥት በ1882 ላይ አሰብ ቅኝ ግዛቱ መሆኗን አስታወቀ። ከሁለት ዓመታት በኋላም የውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ ሲኞር ማቺኒ፣ የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ፣ አሰብ ወደብን ከአውሮፓ ገበያ ጋር በቀጥታ የሚያገናኛቸው ማዕከል አድርገው ያለ አንዳች ችግር እንዲጠቀሙበት ጋበዘ፡፡ በእርግጥም አሰብ ለማደግ ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ የሚሄድና ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ ንግድ ያስፈልጋት ነበር፡፡
በመጽሐፉ ውስጥ መሠረታዊው ዓላማው የሽምግልና ጉዳይ በመሆኑ፣ ከሁሉ አስቀድሞ ኤርትራውያን ስለ ራሳቸው ምን እንደሚሉ ማወቅ እንደሚገባ ይገልጻል፡፡ በዚህም መሠረት ኤርትራውያን እንደሚሉት፤ ‹‹ኤርትራ ከሰሜን ሱማሊያ፣ ከጅቡቲና ከቀይ ባሕር ድንበር የሆነው የሱዳን ግዛት ጋር በመደመር የፑንት ግዛት ተብላ ጥንት በጥንት ግብጻውያን ዘንድ ትታወቅ ነበር። ትርጉሙም ምድረ እግዚአብሔር ማለት ነው። ስለዚችም አገር በታሪክ ምዕራፍ የሚጠራው ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ25ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ነው፡፡ ጥንታዊ የፑንት ግዛት ነዋሪዎች፣ ከጥንታዊዋ የፈርኦን ስርወ መንግሥት ጋር ግንኙነት የነበራት ሲሆን በተለይም በንጉሥ ሳሁርና በንግሥት ሐትኮፐስት ዘመን ግንኙነቷ ጠንካራ ነበር፡፡ ያኔም በተለይም ከስምንተኛውና ሰባተኛው ክፍለ ዘመን (ቅድመ ልደት) ደዓማት የሚባል መንግሥት በኤርትራና በኢትዮጵያ ነበር። ዋና ከተማውም ይሃ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ሲሆን በዚህም ጊዜ የነበረው መንግሥት በመሥኖ  እርሻ ያለማ፣ የብረታ ብረት ቁሳቁሶችንና የጦር መሣሪያዎችን ይሠራ ነበር፡፡ የደዓማት ሥርወ መንግሥት ከ5ኛው ክፍለ ዘመን (ቅድመ ልደት) ከወደቀ በኋላ የአክሱም ስርወ መንግሥት በ1ኛው ክፍለ ዘመን ተመሥርቶ እስኪያስተባብራቸው ድረስ አነስተኛ ነገሥታት በተበታተነ መልክ አካባቢያቸውን (የጥንቷን ኤርትራንና ኢትዮጵያን) ያስተዳድሩ ነበር፡፡ በኢጣሊያ ጊዜም ሆነ ከዚያ በፊትና በኋላ አፋሮች በኤርትራ መሬት ምንም አያገባቸውም፡፡ ባሕረ ነጋሽ፣ ትግራይ ትግረኝ የሚባለው ማዕረግና ብሔረሰብ ያልነበረ ዝም ብለው ሰዎች የፈጠሩት ነው፡፡ ስለዚህ ኤርትራን ባህረ ነጋሾች አላስተዳደሯትም፡፡››  
---በ1920ዎቹ መጀመሪያ ላይ ላይ የኢጣሊያውንና የሌሎችን ነጮች የበላይነት፣ የኤርትራውያንና የሌሎች ጥቁሮችን የበታችነት በግልጽ የሚደነግግ አዋጅ አወጀ፡፡ ይህም በአንድ አገር ውስጥ ሁለት ሕግ እንዲኖር አስቻለ፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረትም፣ ነጮችና ጥቁሮች በአንድ ሆቴል ውስጥ ተቀምጠው መመገብ አቆሙ፡፡ ጥቁሮችና ነጮች የተለየ የትራንስፖርት አገልግሎት መጠቀም ጀመሩ፡፡ ነጮች እንዲቀመጡባቸው በተከለሉት መንደሮች ጥቁር ኤርትራውያኖቹ እንዳይኖሩ ተከለከሉ፡፡ ጥቁሮቹ ኤርትራውያንና በኤርትራ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ጥቁሮች ከነጮች ጋር በሕግ ፊት እኩል የመሆናቸው ነገር አበቃ፡፡ ነጮችና ጥቁሮች ለየብቻ መዳኘት ጀመሩ፡፡ ጥቁሮች በነጮች በደል ቢደርስባቸው እንደ በደል መታየት አቆመ፡፡ በወቅቱ የነበሩ ብዙዎቹ ኤርትራውያን ትምህርቸው ከአንደኛ ደረጃ ከፍ እንዳይል ተደረገ፡፡ ይህም ትምህርት በአመዛኙ ከኢጣሊያውያን ገዥዎቻቸው ጋር በቋንቋ ለመግባባትና ለመታዘዝ እንዲችሉ እንጅ ዕውቀት እንዲያገኙ የሚያስችል አልነበረም፡፡ ይህም ኤርትራውያንና በኤርትራ የሚኖሩ ጥቁሮች የበለጠ በጭቆና እንዲገዙ አደረጋቸው፡፡ የፋሽስታዊ አገዛዙ ስልትም በጦር ቃል ኪዳን አገሮች ጫና በደረሰበት ቁጥር እየጨመረ ሄደ እንጅ አልቀነሰም፡፡
ይህም ሆኖ ደግሞ በኤርትራውያኑ መካከል የነበረው የመደብ፣ የዘር፣ የጎሳ፣ የቋንቋ፣ የጾታ፣ የዕድሜ፣ የእምነት ልዩነት እንዲሰፋና እርስ በእርሳቸው እንዲናናቁ የሚያስችል ስልት ቀየሰ። በተለይም ከአገዛዙ ጋር አንስማማም ብለው ወደ ኢትዮጵያ በመግባት የከዱት መሬት የደመኛ መሬት እየተባለ ይወሰድ ጀመር፡፡ ከበስተጀርባቸው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን እንዳሉ የሚያውቁት የነቁ ኤርትራውያን፣ ኢጣሊያን እየከዱ ወደ ኢትዮጵያ መምጣትና መውጋት ጀመሩ፡፡ ኢትዮጵያን ጠቅልላ ካልያዘች እረፍት እንደማይኖራት የተገነዘበችው ኢጣሊያም በ1928 ላይ ሠራዊቷን ወደ ኢትዮጵያ አዘመተች፡፡  በ1933 በእንግሊዝ እስክትሸነፍ ድረስም ቆየች፡፡ ከዚያም በመጽሐፉ ውስጥ በሚተነተነው ሰፊ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ተዋሃደች፡፡
በመሠረቱ፣ በኤርትራውያንና በኢትዮጵያውያኑ ትግሬዎች መካከል የብሔር፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት አንድነት ቢኖርም ኢጣሊያ በገነባችው የጥላቻና የንቀት አመለካከት ሳቢያ ትግሬዎችንና አማሮችን አጥብቀው ይንቁ፣ ያንቋሽሹ ነበር፡፡ በተለይም፣ በኤርትራውያንና በሰሜን ትግራይ ሕዝብ መካከል ጥላቻ እንዲዳብር ያደረጉባቸው መንገዶች በርካታ ናቸው፡፡ ቀንደኛ ባንዶቻቸው ከትግሬዎች በእጅጉ እንዲጠነቀቁ ማድረግ አንዱ ነበር፡፡ ይህም የሆነበት መሠረታዊ ምክንያት ኤርትራውያን ሰፍኖ በነበረው ዘረኛ አመራር እየተበሳጩ ከሰሜን ትግራይ ወገኖቻቸው ጋር እየተገናኙ አደጋ ያደርሱባቸው ስለነበር ነው፡፡ የኢጣሊያን ሀብትና ንብረት ጨለማ ለብሰውና ጫካ ጥሰው ወደ ወገኖቻቸው ያሻግሩ የነበረ ሲሆን ከጌቶቻቸው ጋር ተጣልተው ሲመጡ እጃቸውን ዘርግተው ይቀበሏቸው ነበር። ከዚህም በተጨማሪ  የሰሜን ትግራይ ሰዎች አመችም ሲሆን ድንበሩን ተሻግረው የጠላትን ሀብት ከመዝረፋቸውም በላይ የኢጣሊያ ቅኝ ገዥዎችን ሲቃወሙ ያለ አንዳች ማወላወል የሚመጡት ወደ ትግራይ ዘመዶቻቸው ዘንድ ስለነበር ከትግሬዎች እንዲጠነቀቁ ቢመክሩ የሚደንቅም፣ የሚገርምም ሊሆን አይችልም፡፡ ብዙዎቹ ኤርትራውያን፣ በተለይም ከሰሜን ትግራይ ሕዝብ ጋር የሥጋ ዝምድና፣ የጋብቻ ዝምድናና የእምነት ዝምድና ስላላቸው ባይቀበሉትም አንዳንዶቹ ግን እራሳቸውን ማራቃቸውና የትግራይ ሕዝብን ማጥላላታቸው አልቀረም፡፡ ኢጣልያውያን ቅኝ ገዥዎቹ ወጥተው እንግሊዝ በሞግዚትነት ታስተዳድር በነበረችበት ጊዜም የዘረኛነት አመለካከቱ እንዲቀጥል ተደርጎ የነበረ ሲሆን ለዚህም ጥሩ ማስረጃ የሚሆነው  የከተማው አስተዳደር፣ ሕግ አስከባሪዎች፣ ዳኞችና ባለኢንዱስትሪዎቹ ኢጣሊያውያን ሆነው እንዲቀጥሉ ማድረጋቸው ነው፡፡
መጽሐፉ ከዚህም ሌላ፣ በኤርትራ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ስለሆኑት  ወልደአብ ወልደማርያም፣ ራቢጣ አል-ኢስላሚያ፣ ዓብዱልቃድር ከቢረ፣ ኢብራሂም ሱልጣን ዓሊ፣ ኢድሪስ ሙሐመድ አደም፣ ሙሐመድ ሰዒድ ናዋድ፣ ሐሚድ ኢድሪስ ዓዋተ፣ ከአሚዶ ጉሌት ምን ያህል ያውቃሉ? አቶ ታምራት ላይኔን ጥርስ ውስጥ ያስገባቸው ጋዜጣዊ መግለጫ የቱ ነው? የኢትዮጵያ መንግሥትና የኤርትራ መንግሥት ወዳጅነት ለምን ምች እንደመታው ሰብል በአንድ ጊዜ ወየበ? የሚሉትን መሠረታዊ ጥያቄዎች በማንሳት ይተነትናል፡፡    
መጽሐፉ ከዚህ ቀደም ተነስቶ በማያውቅ ሁኔታ የኢሕአዴግ ትግልና የኤርትራ ነፃነት ትግልን፣ የኢህአዴግ አነሳስና እድገትን፣ በትግሬዎች ላይ ላለፉት መቶ ዓመታት የሚነዛው ቅኝ ገዥ ወለድ አስከፊ የንቀትና የጥላቻ አመለካከትን፣ የትግራይ ትግርኝ አጭር ታሪክን --- ከመተንተኑም በላይ ህወሓት፣ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ለምን እንድትነጠል ፈለገ? ምንስ ጥቅም አስገኘ? (በመላምት ላይ የተመሠረተ ሐሳብ)፣ የሕዝባዊ ወያኔ የፖለቲካ መሪዎች ለምን የውሕደቱን ፍላጎት ትኩረት የሚነፍጉበት ጊዜ ተከሰተ? ምንስ ጥቅም አስገኘ? ---- የሚሉትን ጥያቄዎች  ለመመለስ ይሞክራል፡፡   
ከዚህ ቀደም ታትመው ለንባብ ከበቁ መጻሕፍት የማናገኘው ሌላው ክፍል፣ የኢህአዴግ አሸናፊነትና የሽግግር መንግሥት መቋቋምን፣ በተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ የያዙ የፖለቲካ ድርጅቶችን፣ በተወካዮች ምክር ቤት ከተከናወኑት ሥራዎች በከፊል፣ ለኤርትራ ሬፈረንደም በኤርትራ ጊዜያዊ መንግሥት በኩል የተደረገ ዝግጅትን፣ በሬፈረንደሙ ዋዜማ የኤርትራ ሬፈረንደም ውጤት አቀባበል አጭር ታሪክን፣ የኤርትራን ሬፈረንደም እንዲታዘብ የተላከው የኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥት ልዑካን፤ በአስመራ ከተማና አካባቢው፣ በምጽዋና አካባቢው፣ በከረን፤ አቆርዳትና አካባቢው፣ በአካለ ጉዛይና ሠራዩ አውራጃዎች ያነጋገራቸው የተለያዩ የኀብረተሰብ ክፍሎች አስተያየት በዝርዝር ያቀርባል፡፡ የኤርትራን ሬፈረንደም እንዲታዘብ የተላከው የኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥት የልዑካን ቡድን አባላት እነማን እንደነበሩም ያመለክታል፡፡
መጽሐፉ ኢትዮጵያና ኤርትራ በሰበበ ባድመ፣ በግጭት ዋዜማ የነበራቸውን ግንኙነትን በሚመለከትም የኤርትራና የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የፖለቲካ ውህደት የምሥራች መግለጫ፣ ድንገተኛው የአቶ ታምራት ላይኔ ጋዜጣዊ መግለጫና ለእስር መዳረግ፣ የብር ኖት መቀየር፣ ኤርትራ የኢትዮጵያን ብር በናቅፋ የሚተካ አዋጅ ማውጣት፣ ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ፤ የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ድንበር የለሽ እየሆነ መምጣቱን መግለጣቸውና በኋላም ‹‹ለኢኮኖሚ ችግራችን ኢትዮጵያን አንወቅስም›› ማለታቸው፣ የባድመ ጦርነት የድንበር ጥያቄ ወይስ ኤርትራን በሚገባ የማስገንጠል ዘዴ? የሚሉትን በዝርዝር ይዳስሳል፡፡
በመጨረሻም መጽሐፉ፣ የሌሎች አገሮች የሰላም ፍኖትን እንደ አብነት በመውሰድ (የቬትናም፣ የጀርመንና የየመን ውህደት ታሪክ) የኢትዮጵያንና የኤርትራ ሕዝብን አንድነት ለማምጣት የሚያስችለውን ጥቅል-የማንነት ጥያቄን ይፈትሻል። የታሪክ እርቅን ለማምጣት ምን መደረግ አለበት? ጥላቻ ምንድን ነው? ጦርነት የሚያስከትለው ጥላቻ፣ መታረም ያለበት እጅግ አደገኛ አዝማሚያ፣ የሰዎች ጥላቻ የመጨረሻ ደረጃ፣---- የመሳሰሉትን መሠረታዊ ጉዳዮች ይተነትናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

Read 1468 times