Monday, 18 September 2017 10:35

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)

     “አምላኬ ከጓደኞቼ ጠብቀኝ፣ ጠላቶቼን ስለማውቃቸው እጠነቀቃለሁ”
             ከጥንቶቹ አማልክት አንዱ ኤሮስ ዐዋቂ፣ ደግ፣ ጎበዝና የሰው ልጆች ወዳጅ ነበር፡፡ በዚህ ባህርይውም ብዙ አማልክቶች ስለቀኑበት፣ ባንቀላፋበት ጊዜ በመብረቅ መቱት፡፡ በአደጋውም ግማሽ ኃይሉን አጣ፡፡
ኤሮስ የዐቅሙን መቀነስ እንዳወቀ፣ ለሚገዛው ህዝብ በነፍስ ወከፍ ‘ሚፈልገውን ለመስጠት ተነሳ፡፡ እያንዳንዱን ሰው በየተራ እየጠራ፣ በጣም ‘ሚያስፈልገውን አንድ ነገር መጠየቅ ጀመረ፡፡ ለመልሳቸውም አንድ አንድ ደቂቃ ሰጣቸው፡፡
“ጤና ስጠኝ” ይልና አንዱ፤ “ጤና ኖሮኝ ድሃ ብሆን እንዴት እኖራለሁ‘” ብሎ ሲያስብ ጊዜው ያልፍበታል፡፡ “ገንዘብ” ይልና ሌላው፤ “ገንዘብ ኖሮኝ ጤና ባጣስ ምን ‘ሆናለሁ?” እያለ ሲያመነታ፣ ሰዓቱ ዕልም ይላል፡፡ አንዱ ደግሞ “ትዳር ወይም ፍቅር” ልበለው? ይልና፤ “አይ … ትዳርም ሆነ ፍቅር በባዶ እጅ እንዴት ይዘለቃል?” እያለ ሲጨነቅ፣ ደቂቃዋ ብን ትልበታለች፡፡ “ጉልበት ወይም ስልጣን” ይሻለኛል ይልና ሌላው … “ጉልበትም ይዝላል፣ ስልጣንም አደጋ አለው” ብሎ ሲወላውል፣ ኪው ይላል-ደውሉ፡፡
አልፎ አልፎ ደግሞ “እውቀት ነው የሚያዋጣኝ” የሚል ብቅ ይልና “ኧረ ይቅርብኝ” ይላል መልሶ - “… ከአዳም ጀምሮ ጣጣ የመጣብን፣ ለምን አወቃችሁ ተብለን አይደለም እንዴ?” በማለት፡፡
ሰዎች እሚፈልጉትን ሳያውቁ፣ እሚያሻቸውን መምረጥ ሲሳናቸውና ሲወላውሉ ጊዜው ጅው ሲል በማየቱ ኤሮስ ተገረመ፡፡ “ለምንድነው ሰው የጎደለውን ከሌላው ወንድሙ እየሞላ፣ ኑሮውን ማቅለል የማይፈልገው? … እሱ ያጣውን ጓደኛው ወይ ጎረቤቱ ሲኖረው በማየቱ ለምን ቅር ይለዋል? … ያኛውስ ይህኛውን መደገፍ ፀጋ መሆኑን የማይረዳው ምን ሆኖ ነው?” እያለ አሰበ፡፡
… ዕፅዋት አይንቀሳቀሱም፤ ተፈጥሮ የምትለግሳቸውን በረከቶች ባሉበት ሆነው ይጠብቃሉ፡፡ … ይኸ ህግ ነው፡፡ እንስሳት ደግሞ ለፍላጎታቸው ይደክማሉ፡፡ ይኸም ህግ ነው፡፡ የሰው ልጅም ሊቀይራቸው የማይችላቸው ተፈጥሮአዊ ህጎች አሉ፡፡ … ቁመቱን፣ ቀለሙን የመሳሰሉት፡፡
በተለያዩ ማህበራዊ ሰበቦች አንድ ዓይነት ሆኖ፣ ባንድ ሚዛን ተሰፍሮ ለሁሉም ዕኩል ሊያዳርስ ያልቻለውን ‹ኑሮ› ወይም ፍላጎቱን ቢያንስ መሰረታዊ የሆኑትን ጉዳዮች ማሟላት አለመቻል ተፈጥሮአዊ ዕውነት አይደለም፡፡ ድህነትን ያለ ጥፋት መቀበል ባርነትን በፈቃደኝነት የመውረስ ያህል ያሳንሳል፡፡ ሰውን ‹ሰው› ከሚያሰኘው ሰብዓዊ ደረጃም ዝቅ ያረገዋል፡፡ ስለዚህ በመተጋገዝና በመረዳዳት፣ ፍትሃዊ የሀብት አስተዳደር መፍጠር አማራጭ የሌለው ማህበራዊ ጉዳይ ነው፡፡ ትንፋሽን ለማቆየት የሚደረገው ግብ-ግብ፣ ለነፃነትና ለመብት ከሚደረገው መዋደቅ ይከፋልና!! … ይሉናል ዐዋቂዎች፡፡
… እናም ወዳጄ፡- ኤሮስ ብዙ ነገሮችን እያሰላሰለ፣ ተሰልፈው ከነበሩት የመጨረሻውን ሰው፤ “አንተስ ምንድነው የምትፈልገው?” በማለት ጠየቀ፡፡
“እውነተኛ ጓደኛ” አለ ሰውየው … በፍጥነት፡፡
የሚፈልገውን የሚያውቅ አንድ ሰው በማግኘቱ እጅግ ደስ አለው - ኤሮስ፡፡ የተጠየቀውን መፈፀም ደግሞ ‹ስራው› ነው፡፡ የሚፈልገውን ከማያውቅ ‹ህዝብ› መካከል ቢጤውን እንዴት እንደሚያገኝለት ግን ቸገረው፡፡ … ማሰብ ጀመረ፡፡ ብዙም ሳይቆይ አዲስ ሀሳብ መጥቶለት ወይም የሰውየው መንፈስ (energy) ስሜቱን ኮርኩሮት ሳይታወቅ ብድግ አለና፤ … “ከአሁን ጀምሮ ጓደኛህ እኔ ነኝ” አለው፡፡ … ተቃቀፉ ፡፡ … በዚሁ ቅጽበት ኤሮስ ከበፊቱ የበለጠ ሙሉነት፣ ሃያልነትና አስተዋይነት ሲሰማው፣ ተመሳሳይ መንፈስ በሰውየውም ውስጥ ሰረፀ። “አንድ ነፍስ በሁለት አካል” (one soul in two bodies) እንደሚለው አርስቶትል፡፡
ከሚያስገርሙን ወይ ከምንደሰትባቸው ነገሮች፣ ከምናነባቸው መጽሃፍት፣ ከምናዘወትረው ስራና ከጓደኞቻችን ባህሪ ማንነታችን ይቀረፃል (… we mold our characters by our choice of friends, books, occupations and amusements) ያለውም እሱ ራሱ ነው - … አርስቶትል፡፡
ፍሬዴሪክ ኒች፣ ለዛራቱስትራ
“ብንን ስል ከሀሳቤ
ያወቅሁትን በውል አየሁ፣
መንፈሴ ውስጥ ውልብ ሲል
ከኔ ሌላ ‹እኔ” እንዳለሁ” … ብሎ ነበር፡፡      
ኒች የዚህ የ “የታላቁን ሰው” (Überman) ባህሪ ሲገልጽ፡- በራሱ ላይ መጨከንን ጨምሮ ማንኛውንም ነገር ለማድረግ የሚችል፣… ጓደኛን ከመክዳት በስተቀር (One will do almost anything except betray a friend… that is the last formula of the super man) ነበር ያለው፡፡
የሚካኤል አንጀሎና የካቫሌር፣ የሞንታኝና ላቤቴ፣ የሰር ፊሊፕ ሲድኒና ሁበርት ላንገት በምሳሌነት የሚጠቀሱ የቀድሞው ጓደኝነት ታሪክ ነው፡፡
አንዳንድ ፈላስፎች፤ “ሰዎች ሁሉ መልካምና ፍትሃዊ ቢሆኑ ኖሮ ጓደኝነት የተለየ ጥቅም የለውም” ብለው ያስባሉ፡፡ ይህ ባለመሆኑ ነው ደስታህንና ችግርህን የሚካፈሉህ ጥቂት ጓደኞች ሊኖሩህና እነሱንም በፍፁም ልብህ ልታፈቅራቸው የሚገባው” የሚሉት፡፡ … ሼክስፒርም እንደፃፈው፤ “keep your true friends close to your heart”
የዛኑ ያህል ከሃሰተኛና አስመሳይ ጓደኛም እንድንርቅ የሚመክሩን ሊቃውንት ብዙ ናቸው።  “…watch out for false friends…” የሚለንም እሱው ራሱ ነው፡፡… ሼክስፒር!!
ታላቁ ቮልቴር፤ “አምላኬ ከጓደኞቼ ጠብቀኝ፣ ጠላቶቼን ስለማውቃቸው እጠነቀቃለሁ” (God preserve me from my friends, I will take care of my enemies) ሲል የነበረውም ያለነገር አልነበረም፡፡
ወዳጄ፡- አጭር የጓደኝነት ታሪክ ልጨምርልህ። አንድ ነፍስ በሁለት አካል እንዳልነው  አይነት። ሁለት በጣም የሚዋደዱ ባልንጀራዎች፣ በአንድ ትልቅ ሃይቅ ላይ ሲንሸራሸሩ፣ ጀልባቸው ተቀደደና አደጋ ላይ ወደቁ፡፡ የነበረው መንሳፈፊያ ጎማ ደግሞ አንድ ብቻ ነበር፡፡ ፍቅራቸው ጥልቅ ነበርና አንዱ ሌላኛው እንዲተርፍለት ቢሞክርም አልተቻለም። ቁርጥ ሲሆን አንደኛው ወደ ባህሩ ዘለለ፡፡… ጓደኛው እንዲተርፍለት፡፡.. ብዙም ሳይቆይ ሌላኛው ተከተለው፡፡ አስክሬናቸው ሲወጣ በየግል ፅፈውት የነበረው ማስታወሻ ተነበበ፡፡
ያንደኛው፡-… “ወንድሜ ሆይ፤ እኔ አግብቼ ወልጃለሁ፤ አንተም ይህን አለም ማየት አለብህ፤ የጀመርከውን መፅሃፍ ለኔም ለሃገርህም ስትል መጨረስ ይኖርብሃል፣ ቤተሰቦቼ ቤተሰቦችህ ናቸውና አደራ አልልህም በርታ” የሚል ሲሆን የጓደኛው ደግሞ፤ “ውድ ጓዴ፤ እስከ ዛሬ ሚስጢር አድርጌ በማቆየቴ ይቅርታ፤ ከአሁን በኋላ በህይወት መቆየት የምችለው ቢበዛ አስር ወራት ያህል ነው፣ የካንሰር ህመም አለብኝ፣ አለመዳኔ በሃኪም ተረጋግጧል፤ መፅሃፉን ከኔ በተሻለ እንደምትጨርሰው አምናለሁ፤ አይዞህ..” ይላል፡፡
ይኸውልህ ወዳጄ፤ “የማይተማመን ባልንጀራ በየወንዙ ይማማላል፤ ዕውነተኛ ወንድምህ ግን ሞት አፋፍ ላይ ተንጠልጥሎ፣ “ጓደኛዬ ይዳን ይላል” የሚባለው እንደዚህ ነው፡፡
ወዳጄ ልቤ፤ ወደ ተረታችን ልመልስህና … ኤሮስ ታላቅነቱን ያረጋገጠው፤ ዳግም ወደ ክብሩ የተመለሰው እንዴት ሆኖ ይመስልሃል? “ሲያንቀላፋ የሚቀሰቅሰው፤ ሲተኛ የሚጠብቀው ጓደኛ በማግኘቱ ነው” ካልከኝ… ልክ ነህ!! ሠላም

Read 1110 times