Monday, 18 September 2017 10:37

ቼ በለው የዘመኑን መንፈስ የሣለው መጽሐፍ

Written by  ዳዊት
Rate this item
(9 votes)

 በእዮብ ምሕረተአብ ስለተጻፈው “ቼ በለው” የተሰኘ መጽሐፍ በሰፊው ከማተቴ በፊት በመጀመሪያ ጠቅለል ያለ ዳሰሳ፣ በወፍ በረር ልሂድበትና ከዚያ ሁለት ዋና ዋና ነጥቦችን አነሳለሁ። በኋላ ላይ የማነሳቸው ሁለት ሀሳቦች ዛይትጋይስት እና ቢጫ ናቸው፡፡ (ቀብድ ያዙልኝ)፡፡
ቼ በለው የሚጀምረው በምክር ነው፡፡ እንደ ደራሲው በጉራማይሌ ላውራና That is so unlike the him፡፡ “እሺ አይለውም”፤ ያ ትውልድን ያንቆለጳጵሳል፡፡ “The ጥበብ ጠራችኝ” የኢትዮጵያን የሥነ-ጥበብ በተለይም የድርሰት ሁኔታን ይተቻል፡፡ “ጎኔ ስትወሸቅ ጡቷ ነካኝ። ወይንም በድሮ ደራሲ አገላለጽ ጡቷ እንደ ጦር ወጋኝ” ይላል ለምሳሌ። “አስባለሁ” በሚለው ትረካ ውስጥ ተራኪው የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ከዓለም አቀፍ ሁኔታ ጋር እያነጻጸረ፣ ለአገሩና ለአገሩ ሰዎች ከንፈሩን ይመጣል፡፡ May Day የሚለው ታሪክ ደግሞ የዚህ ዘመን ቱሉ ፎርሳ ነው፡፡ የተዘነጋውን መደብ ዳይናሚክስ ያሳያል፡፡ ሠራተኛው መደብ ከየት ወደ የት የሚለውን ያስቃኛል፡፡
የመጽሐፉን ርዕስ የያዘው እና መጨረሻ ላይ የሚመጣው ትረካ ደግሞ “ቼ በለው” በፖስት ሞደርን የአጻጻፍ ስልት የተዘጋጀ ነው፡፡ ድርሰቱ የተዋቀረው በPastiche ነው፡፡ ከዚሀ በፊት የነበሩ ድርሰቶችን እየቆራረጡ በመቀጣጠል ስልት የተሠራ ነው፡፡ ሆኖም በየመካከሉ በገቡ አያያዦች እርዳታ ያልተቆራረጠ ፍሰት አለው፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ አንድም የደራሲው ድምፅ አይሰማም፡፡ የጸሐፊው የንባብ አድማስ ግን ምን ያክል ሰፊ እንደሆነ እናስተውላለን፡፡ ደራሲው ሰፊ የንባብ ልምድ ከማካበቱም በላይ መረጃን ሰብስቦ በመተንተን፣ ለነባራዊው ሁኔታ ጥቅም ላይ እንዲውል አድርጎ  የማስቀመጥ አመዛዛኝ፣ የአንባቢነት ችሎታ እንዳለው ያሳየበትም ነው፡፡
በግል ከማውቀውም ውጪ ጽሑፉ ላይ በግልጽ እንደሚታየው፣ እዮብ ምሕረተአብ አራዳ ደራሲ ነው፡፡ ደራሲ ማለት ከፊደል ጋር ብቻ የተጣበቀ ደብተራ ሳይሆን ሕይወትንም እያጣጣመ የሚኖር ሙሉ ሰው መሆን እንዳለበት ማሳያም ነው። ኬኦስ ቲዮሪ (Chaos Theory) እና Butterfly Effect ገብቶታል፡፡ ሕይወት ማለትም የነገሮች ሁሉ ትሥሥር ውጤት እንጂ አንድ ነጠላ ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ ተረድቷል፡፡ በኑሮ የተረዳውንና ያጋጠመውን ሁሉ በልዩ የአተራረክ ችሎታና በአዝናኝ አቀራረብ፣ “ቼ በለው” በተሰኘው መጽሐፉ አንድም ሳያስቀር  ሰጥቶናል፡፡
“ቼ በለው” ቋንቋው ቀላል፣ ግልፅና ሂዩመረስ ነው፡፡ በቀላል ቋንቋውና በዚቀኝነቱ ተከልሎ ቁምነገሩን መሳት ግን ትልቅ ስህተት ነው፡፡ የቋንቋው ጉዳይ ከተነሳ አይቀር ጉራማይሌ መሆኑን መጥቀስ ያስፈልጋል፤ ይሄ በእኔ አመለካከት እጅግ ተገቢ ነው፡፡ ስለ አማርኛ ሥነ ጽሑፍ እያተትኩ፣ ጉራማይሌ ቋንቋን እንዲህ ማዋደዴ ለምን እንደሆነ ወደ በኋላ እመለስበታለሁ፡፡
ቢጫው መጽሐፍ
ከላይ እንደ ቀብድ ካስያዝኳቸው ርዕሶች አንዱ “ቢጫ” ነው፡፡ እሱን እናውራ፡፡ ቢጫ የአገራችን ቀለም ነው፡፡ ባንዲራችን ውስጥ መሀል ላይ አለ። ኢትዮጵያ የሚለው ቃል መካከል “ዮጵ” የሚል ቃል አለ፡፡ ያልተነጠረ ወርቅ ማለት ነው፡፡ ቀለሙም ቢጫ ነው፡፡ የዘመናችን መጀመሪያ የሆነው መስከረም ወር በቢጫ አደይ አበባ የተሸፈነ ነው፡፡ ቢጫ ቀለም የአገሪቱ ማዕከል እንደሆነ ሁሉ የ”ቼ በለው” መጽሐፍ ማዕከልም ቢጫ ነው፡፡ “ቼ በለው” ቢጫ መጽሐፍ ነው፡፡ ስለ ምን እንደዚህ አልኩ? አብረን እንቀጥል…
“ቢጫ” የሚል ርዕስ በተሰጠው ትረካ ውስጥ “ትዝታ ዘ ቢጫ ቀለም” የሚል ምዕራፍ አለ፡፡ ትውስታና ቀለም እንዴት ተሰናስለው እንደሚፈስሱ ያሳያል… ተራኪያችን ወዳጆቹ ቤት ሄዶ፣ ባልና ሚስት ቢጫ ጄሪካንን መነሾ ያደረገ ጭቅጭቅ ሲጀምሩ ሲያይ፤ ስለ ቢጫ ቀለም ያለውን ትውስታ ሁሉ የሚበረብርበት ምዕራፍ ነው….
የሚያስታውሰውም ይሄን ነው… “ቢጫ ቀለም ሲባል የሼል ማደያ ምስል - Western Union - የሀምሳ ብር ኖት - የፀሐይ ብርሃን ያጣ ሣር - የመነኩሴ ቆብ - እርድ የበዛበት መኮሮኒ - National Geography - ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ - የበላይ ተክሉ ኬክ ቤት ተቆራጭ - ደምበል ሕንጻ - DHL - የሸገርን ባቡር የሚነዳ ቻይናዊ ፊት - የስዕል መምህራችን ʻከሰንደቅ አላማችን ቀለማት መካከል መሥራች ቀለም ያልሆነው የቱ ነው?ʼ ብሎ ጠይቆኝ ʻቢጫʼ ብዬ በመመለሴ እንደ ሀገር ክህደት ቆጥሮት የኮረኮመኝ ኩርኩም - ለሊያ ልጅ ለናፒ ልደት የገዛሁላት ሸራ ጫማና - የአብዛኛው ኮንዶሚኒየም ሳሎን ቤት ቀለም ይታወሰኛል፡፡”
ይሄን ሁሉ የትውስታ ሰልፍ ደርድሮ፣ በመጨረሻም ገጠር ለስራ ሲወጣ ቧንቧ ስር ተኮልኩሎ የሚያየውን ቢጫ ጄሪካን ያሳየናል፡፡ አደይ አበባንም ያስታውሳል፡፡ አበባውን አስታክኮ አንደኛ ደረጃ አብራው የተማረችው አደይ የተባለች ልጅ ትዝ ትለዋለች፡፡
ተራኪውም ሆነ እኔ፣ ይሄን ሁሉ የትውስታ ጋጋታ የምናቀርብላችሁ ያለ ነገር አይደለም፡፡ ተራኪው ቀስ ብሎ ወደ ቀለም ሥነ ልቦና (psychology of color) ሊገባ ነው፡፡ እኔ ደሞ ተያያዥ ስለሆኑ ነገሮች ላነሳሳ ነው፡፡ ተራኪው የቢጫ ቀለምን ሥነ ልቦናዊ ትዕምርት ለመረዳት፣ የቀለም ሥነልቦናን ተጠቅሞ ትርጓሜውን እንዲህ ያስነብበናል……
“Yellow is truly joyous and radiant color. It exudes warmth, inspiration and vitality. It is the happiest of colors. Yellow signifies communication, enlightenment, sunlight and spirituality. If your treasured color is yellow, you look forward to the future. Intellectual, highly imaginative and idealistic, you have a cheerful spirit and expectations of greater happiness”
ቢጫ ቀለምን ለመግለጽ የተጠቀሟቸውን ዋና ዋና ገላጭ ቃላት ጎን ለጎን ብንደረድራቸው የምናገኘው፤ “ቼ በለው” የተባለው የእዮብ ምሕረተአብ መጽሐፍ ትክክለኛ መገለጫዎችን ነው፡፡ ልክ እንደዚህ…. Joyous, radiant, warm, communication, enlightenment, looking forward to the future, intellectual, highly imaginative, idealistic, cheerful spirit and expectations of greater happiness. የቼ በለው መጽሐፍ ምንነት ይሄው ነው፤ ቼ በለው Joyous ነው። ቼ በለው radiant ነው፡፡ ቼ በለው intellectual እና imaginativeም ነው፡፡ ለዚህም ነው “ቼ በለው ቢጫ መጽሐፍ ነው” ብዬ የጀመርኩት፡፡
ደራሲው እዚህ እና እዚያ ዐሥር ጊዜ “ቢጫ ጄሪካን” ቢላችሁ አንድምታ አለው፤ አንድም የኢትዮጵያ ምድር ከዚህ በኋላ በቢጫ ጄሪካን እንጂ በአደይ አበባ አለመሸፈኑን በማስተዋሉ፤ አንድም ደሞ የልቦለዱን አውድ ለመገንባት እንደ ሞቲፍ ሊጠቀምበት፤ አንድም አጨራረሱን ሊያሳምር ነው። ቢጫ ጄሪካን ቀላል አይደለችም፡፡ አገሪቱ ላይ ያላት ተጽዕኖ በዝርዝር ቀርቦልናል - “የቢጫ ዘይት ጄሪካን እና የአገሪቱ እርምጃ” በሚል ፌዘኛ መሳይ ርዕስ፡፡
“…ሸኖ ላይ የሰላሌ ኦሮሞ ወተቱን በአባ ዱላ ወደ አዲስ አበባ የሚልከው በነዚህ ቢጫ ጄሪካኖች ነው፡፡ የደንበጫ ጎጃሞች የግብጦ አረቄን ጠምቀው የሚያስቀምጡት በእንስራ አይደለም፤ በዚህ ቢጫ ጄሪካን ነው፡፡ ከጅቡቲ ወደብ እስከ ገዳማይቱ ይሄንን ቢጫ ጄሪካን በኮንቲነርና በግመል ተጭኖ በገፍ ሲገባ ታየዋለህ፡፡ አዲስ አበባ የሚገኙ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ላይ አራተኛ ፎቅ ተከራይቶ ቢጫ ጄሪካን የሌለው ሰው የለም፡፡ በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ የቦኖ ውሃዎች ላይ ረጅም ወረፋ ካየህ፣ የተደረደረ እንስራ ወይም ሌላ አይነት ከለር ያለው ጄሪካን በብዛት አይገጥምህም - ይሄው ቢጫ ጄሪካን እንጂ!”
አሁንም ልብ በሉ፤ ደራሲው ይሄን ሁሉ የሚለው በወለፈንድ ሲዘባርቅ አይደለም፡፡ ነገር የሚፈተፍተው ወደ ዛሬ መልሶን፤ ሁኔታውን ካለንበት ነባራዊ እውነታ ጋር ጠቅልሎ ሊያጎርሰን ነው፡፡
እዮብ ቢጫ ጄሪካን ተሸክሞ እንደ ጦስ ዶሮ ስንትና ስንት ቦታ ከተሽከረከረ በኋላ ማረፊያውን የሚያደርገው ጌቱ ገለቴ ላይ ነው፡፡ ጌቱ ገለቴ የቢጫ ጄሪካን አባት፤ ኦሎምፒያ አካባቢ ያለው የጌቱ ኮሜርሻል ሴንተር ባለቤት ነው፡፡ በዚያን ዘመንም ጌቱ የተቀሸበ ባለ ሀያ አምስት ሊትር ዘይት ከታይላንድ አገር አስመጥቶ ያከፋፍል ነበር፡፡ ዛሬ ግን “የሆነች ማኖ ነክቶ” ከአገር የወጣ በኢንተርፖል የሚፈለግ ባለሃብት ነው፡፡ ደራሲው የጌቱን ጉዳይ በአጭሩ አውስቶ፣ መንግሥትን ጎሸም ያደርጋል፡ “መንግሥት የዘይትንና የስኳርን ዋጋ ልተምን ብሎ ቡራ ከረዩ ሲል የዚህን ባለ ቢጫ ጄሪካን የታይላንድ ዘይት መቆጣጠር ግን ተስኖታል”፡፡
የቼ በለው ደራሲ ሕይወትን ለመዘገብ ቢጫ ቀለምን ሞቲፍ (motif) አድርጎ መምጣቱ ከተራ አጋጣሚነት ያለፈ ነገር እንዳለ ያስታውቃል። ምክንያቱም እንደ ቢጫ ቀለም ግራ የሚያጋባ ትእምርት ያለው ሌላ ቀለም የለም፡፡ ዓለም ብሩህ እና ጸሊም እንደሆነችው ሁሉ ቢጫ ቅዱስም እርኩስም ነው፡፡ እናም ክፉና ደግ ተዋህደው፣ አንድ አካል ሆነው የሚኖሩባትን ዓለም ለመሣል፣ ቢጫ ቀለምን መጠቀም የመሰለ ተገቢ ምርጫ ሊኖር አይችልም፡፡ ስለ ቀለማት ትእምርትና አመጣጥ በሰፊው የመረመረችው Victoria Finlay ስለ ቢጫ ቀለም እንዲህ ትላለች፡ “No color has a neat unambiguous symbolism, but yellow gives the most mixed messages of all. It is the color of pulsating life—of corn and gold and angelic haloes—and it is also at the same time a color of bile, and its sulphurous incarnation it is the color of the Devil” (Color: A Natural History of the Palette, pp 202) በግርድፉ ስንተረጉመው፤ “እንደ ቢጫ ቀለም ያለ የተደበላለቀ ስሜት የሚፈጥር ቀለም የለም፡፡ ቢጫ የሕይወት ቀለም ነው - የበቆሎ፣ የወርቅ እና የቅዱሳን አክሊል፤ ቢጫ በሌላ መልኩ የክፋት ቀለም ነው፤ ቢጫ ቀለም ያለው ሰልፈር ለምሳሌ የሰይጣን ቀለም ነው”፡፡ ታዲያ የእግዜርም የሰይጣንም የሆነችው አለም፣ ከዚህ ባለ ብዙ ገጽ ቀለም ሌላ በምን ትሳላለች? ቼ በለው የተሰኘው መጽሐፍስ ቅድስና እና እርኩሰት በደቦ የነገሡበትን ዘመናችንን ለመግለጽ፣ ማዕከሉን ቢጫ ከማድረጉ በላይ ተገቢ ነገር አለን?
“ቢጫ” የሚል ርዕስ ባለው ትረካ ውስጥ ጉልህ ቦታ የተሰጣትን ቢጫ ጄሪካን ደራሲው አናሎጂ ለመፍጠርም ተጠቅሞባታል፡፡ የዚህን ታሪክ የመጨረሻዎቹን ሁለት አንቀጾች እንመልከት። የመጀመሪያው እንዲህ ይላል… “ጋን፣ እንስራና ማሰሮም ወደ ቀድሞው ስፍራቸው አይመለሱም። ወደ ሰባ ሚሊዮን ከሚሆነው የገጠሩ ህዝብና በርኸኛው እንስራንና ማሰሮን በዚህ ክብደት በሌለው ግን ጠንካራ በሆነ ውሃ መቅጃ እየተኩት ነው፡፡ የሴት ልጅ ወገብም ከከባዱና ከተሰባሪው ገል ተገላግሏል፡፡ ዕድሜ ለጌቱ ገለቴ - ዕድሜ ለቢጫ ጄሪካኑ”፡፡
በዚህ ታሪክ ውስጥ የሚገኘው ተራኪ የሆነ መስሪያ ቤት ጉዳይ ሊያስፈጽም ሲሄድ ያገኛት አንደኛ ደረጃ አብራው ስለተማረችው አደይ ስለተባለች ልጅ ሲነግረን ነበር፡፡ ሁለተኛው አንቀጽ የሚያሳየን የእሷን መጨረሻ ነው፡፡ እንዲህ ይላል… “ያ! የሙዝ ቅርጽ የነበረው፤ ያ! የብርጭቆ ቂጥ መነጽር ዓይኗን ምስር ያስመሰለው፤ ያ! ቡጉንጅ የሞላው ድንጉጥ የአደይ ፊትም፤ መቼም መቼም አይመለስም”፡፡ የጄሪካኑ እና የአደይ ሕይወት ተነጻጻሪ ሆነው ቀርበዋል፡፡ ሁለቱ የሚገናኙበት ነጥብ ደግሞ ቢጫ የተሰኘው ቀለም ነው፡፡ ቢጫ ቀለም እንደዚህ ታሪኩንና አጨራረሱን ለማሳመር ተጠቅሞበታል፡፡ በእርግጥ ደራሲው በአጨራረስ የሚታማ አይደለም፡፡ እንዲያውም የሚደነቅ የአጨራረስ ችሎታ አለው፡፡ ለዚህም አብነት የሚሆነን “መርዓ” የሰኘው ታሪክ ነው፡፡
መርዓ የሚጀምረው በሆነ የትግርኛ ዘፈን ነው። ባለ አራት መስመር የዘፈኑ ግጥም እንጂ ትርጉሙ አልተሰጠንም፡፡ “ከም ኤርትራ አዴታት መንም አይወለዳ” ይላል የመጨረሻው ስንኝ፡፡ ባይገባንም ይሁን ብለን እናልፈዋለን፡፡ አስገራሚው ነገር ትርጉሙን የምናገኘው የታሪኩ መቋጫ ላይ መሆኑ አይደለም፡፡ አስገራሚው ነገር ትርጉሙ ከኋላ መምጣቱ፣ ለአጨራረሱ የሰጠው ክብደት ነው፡፡
መርዓ በትግርኛ ሰርግ ማለት ቢሆንም፤ ተራኪው የሚያሳየን ያለውን የብሔር ብሔረሰብ ውጥረት ነው፡፡ የአንዱን የተጨቆንኩ ለቅሶ፣ የአንዱን የተበደልኩ ዋይታ፣ የሌላውን የበላይነት ትምክህት። ይሄን ሁሉ አስተውሎ ተራኪያችን በሰርግ ቤት መሀል እንዲህ ይተክዛል… “ይሄ እርጉም አህጉር - ይሄ ከይሲ ጥቁር ሕዝብ - ይሄ ችጋር የሚጠበጥበው የአፍሪቃ ቀንድ - ይሄ ጦርነት የማያጣው ቀንዳም ክፍለ አህጉር - ይሄ ደዌና ቸነፈር ያቀረጨጨው ጊንጥ ሕዝብ - በዘር፣ በክልል፣ በድንበር የተከፋፈለ - ሊባላ ከጫፍ የደረሰ - ድሮም፣ አሁንም፣ ወደፊትም ራሱን ችሎ በልቶ ማደር የማይችል አፍሪቃዊ!... እውነትም The Hopleless Continent!”፡፡
እዮብ በጉራማይሌ ቋንቋው ታሪኩን እንደዚህ ይፈጽመዋል… “(Afterall) ʻዘርህ ከአሜሪካዊያን፣ ከአውሮፓውያንና ከእስያውያን ይበልጣልʼ የሚል ዘፈን፣ (አፍሪካም የለበትም) ከውስኪና ከፊያሜታ ጋር ተጨምሮ ሌላም ያስረሳል፡፡ Self Denial… Identity Crisis…. Narrow Identity… Grey Nationalism… Greed… Pessimism.” እንደዚህ አይነት ውብና ጠንካራ አጨራረስ የሚታየው ጥቂት የፈጠራ ስራዎች ብቻ ላይ ነው፡፡
ዛይትጋይስት (Zeitgeist)
ቃል ወደ ገባሁላችሁ ወደ ሁለተኛው ሀሳብ ልቀጥል፡፡ ዛይትጋይስት፡፡ ዛይትጋይስት ከሁለት ቃላት የተሰራ የጀርመንኛ ቃል ነው፡፡ “ዛይት” ማለት ጊዜ ሲሆን “ጋይስት” ደሞ መንፈስ ነው፡፡ የዘመኑ መንፈስ እንበለው፡፡  
የዘመኑን መንፈስ ለመዘገብ የዘመኑን ቋንቋ መጠቀም ግድ ይላል፡፡ ለዚያም ነው ከላይ “ቼ በለው” ላይ ያለው የቋንቋ አጠቃቀም ጉራማይሌ መሆኑ ተገቢ ነው ያልኩት፡፡  
ከቋንቋ አጠቃቀም ውጪ የዘመን መንፈስ እንዴት ይዘገባል? እንደዚህ ነው፡፡ ቼ በለው ውስጥ ሁሉም ታሪኮች ውስጥ ማለት ይቻላል እየተደጋገመ የሚመጣ ጭብጥ አለ፤ ይሄውም ገንዘብ ነው፡፡ ይሄም የዘመኑ መንፈስ ዋና መለያ ነው፡፡ ለምሳሌ I wanna be a Billionaire በሚል ግልፅ ርዕስ የተቀመጠው ታሪክ አንድ ማሳያ ነው። በአብዛኞቹ ታሪኮች (ሁሉም ማለት ይቻላል) እየተመላለሰ የሚመጣ ጭብጥ ነው፡፡ መቼም ውሻ ውሻን የሚበላበት የካፒታሊዝም ሥርዓት ውስጥ እየኖርን፣ ካሽ የሁሉም ነገር ቁልፍ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ደራሲው በእርግጥ የብዙ ነገር ቅይጥ የሆነውን “የኛን ካፒታሊዝም” የሚጠራበት አባባል አለው - “ሚስቶ ካፒታሊዝም”፡፡  በአማርኛ ልቦለድ ትልቅ ድርሳን የሆነው “ፍቅር እስከ መቃብር” ዘመኑን በማሳየቱ፣ ዘመን ተሻጋሪ ሆኖ እስከ ዛሬ ድረስ ይወደሳል፡፡ የእዮብ ምሕረተአብ “ቼ በለው”ም የዘመኑን መንፈስ በቃላት ሥሎ በማቅረቡ የዘመናችን ፍቅር እስከ መቃብር ነው ብል አላጋነንኩም፡፡ ልዩነቱ ቼ በለው ውስጥ ያለው ጉዱ ካሳ ደራሲው ራሱ መሆኑ ነው። አዎ፤ እዮብ ምሕረተአብ የዘመኑ ጉዱ ካሳ ነው፡፡ እዮብ ኑሯችንን ያለ ፍርሃትና ያለ ሃፍረት ያወራዋል፤ የሚያወራውን ይጽፈዋል፡፡ አይፈራም፤ አያፍርም፡፡ የማይደፈር የተባለውን ደፍሮ ይነግረናል (ወይም በራሱ አባባል ይቀድልናል)፡፡ ድርሰቱ (በእሱ አባባል ቀደዳዎቹ) ዛሬን ያሳያሉ፡፡ ደራሲ እዮብ ቀጥተኛ ነው፡፡ ሆኖም ይሄ ቀጥተኛነቱ የአንዳችን ሕይወት ከሌላኛችን የተሳሰረበትን ቀጭን መስመር ከማስተዋል፤ ትስስራችን የቆመበትን ተዋረድም ከመመርመር አያግደውም፡፡ አብዛኛውን ጊዜም ቀላል በመሰለ ንጽጽሮሽ እልፍ ነገር ይነግረናል፡፡ መርዓ የተሰኘው ታሪክ ላይ ለምሳሌ ጋሽ ካህሳይ የተባሉ የአንደኛ ደረጃ ሒሳብ አስተማሪ አሉ፡፡ “አብዮት ቅርስ ትምህርት ቤት ኤለመንተሪ ተማሪ ሆነን ሒሳብ ያስተማሩን፣ በግማሽ ትግርኛና በግማሽ አለንጋ ነበር” ይላቸዋል ተራኪው፡፡ በስንት ችግር ውስጥ አልፈው ዛሬም በድህነት ይኖራሉ፡፡ “ሰርክ እንደተጫወቱ፤ ሁሌ እንደቀለዱ ነው፡፡ ምንም አልተቀየሩም”፡፡ ታዲያ እዚያው ታሪክ ላይ እንደ ማነጻጸሪያ ሆኖ የቀረበ ታናሽ ወንድም አላቸው፡፡
 “ታናሽ ወንድማቸው ደሞ ሌላ ታሪክ ያለው ሰው ነው” ብሎ ይጀምራል ትረካው፡፡ ታናሽዬው ታጋይ ነበር፡፡ አዲሳባ ገብቶ ኑሮና ብልሃቱን መታገል ቀጠለ፡፡ ድህነትን “አቸንፎ” ኢንቬስተር ሆነ፡፡ “ምሥራቅ በር ዱከም ቁርጥ ቤት፣ ቶቶት ክትፎ፣ ጽጌ ሽሮ እና ቃተኛ ሰርክ የማይጠፋባቸው ሥፍራዎች ሆኑ፡፡ ሞሮኮ ባዝ እና ኤሮቲክ ማሳጅ ሆቢው ሆኑ። በየቀኑ ውስኪ ያወርዳል፡፡ በግልፅ ከብዙ ሴቶች ጋር ይማግጣል”፡፡ ይሄ በቀላሉ የተቀመጠ የዘመኑ ቀለም ነው፡፡  ዘመንን መሣል ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ደራሲ እዮብ የከፈለው ዋጋ ደግሞ ከሁሉም መጣላትን ነው፡፡ ምርጥ ደራሲ ከገዛ ፈሱ ጭምር መጣላት አለበት፤ የቼ በለው መጽሐፍ ደራሲ ያደረገውም ይሄንኑ ነው፡፡ ከማንም ጋር ስምሙ አይደለም፡፡ ሁሉንም ይነቁራል፡፡ ሁሉንም ይተቻል፡፡ ሁሉም ላይ “ሙድ ይይዛል”፡፡ ፖለቲከኞች፣ መንግስት፣ ተቃዋሚ፣ ባለሃብት፣ ደሃ፣ ጸሐፊዎች፣ ጋዜጠኞች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ብሔር ብሔረሰብ፤ ሐይማኖት፣ ፌሚኒዝም፣ አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ወዘተ…
“የዘፈን ምርጫ” ላይ አላሙዲ እና ኢንጂነር ይልቃል ተፎግረዋል፡፡ “The ጥበብ ጠራችኝ” ደራሲዎችን ይነቁራል፡፡ “ስብሰባው” እና መርዓ ብሔር ብሔረሶቦች ላይ ይቀልዳል፡፡ የመንግስት ጋዜጠኞች እና ተመራጭ ገጸ ባሕሪዎቻቸው - ማለትም አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፤ ሁለቱም ድህነት የሚሉት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ሆነው ተስለዋል፡፡ በዚህ ዘመን አለ የተባለ የማሕበረሰብ ክፍል፤ ዛሬ ላይ የሚገኝ የአኗኗር ዘይቤ ሁሉም ተዳርሰዋል፤ ሁሉም ተጎሽመዋል፡፡
ለምሳሌ ደራሲው የብሔር ብሔረሶችን ጉዳይ skillfully mock ከሚያደርግበት ክፍል አንዱ “ስብሰባው” በተሰኘው ታሪክ ውስጥ ይገኛል፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ መስሪያ ቤታችን ውስጥ የጀበና ቡና መጀመር አለበት የሚለውን ሀሳብ ተመካክሮ ለመወሰን ሰራተኛው በሙሉ ይሰበሰባል፡፡ የመስሪያ ቤቱ ስራ አስኪያጅ ጉዳዩን ጠላቶቹን ለመምታትና ወዳጆቹን ለማበልፀግ ይጠቀምበታል፡፡ ዋና ዋና ከሚባሉ ብሔሮች ወካይ እንደሆኑ በግልጽ የሚያስታውቁ ገጸ ባሕሪዎች እየተነሱ ይናገራሉ፡፡ ጉዳዩ ከቡና ወደ ፖለቲካ ይቀየራል፡፡ ከጀበና ወደ ማንነት ጥያቄ፡፡ ቆይቶ ሌላ አጀንዳ ይጨመራል - ፌሚኒዝም፡፡ ይሄንን ክፍተት ተጥቅሞ፣ ስራ አስኪያጁ፣ ያንንም ያንንም ጃስ ካለ በኋላ “ችግሩ የጀበና ቡና አለመኖሩ ሳይሆን የመስሪያ ቤቱ ካፌ ጥሩ አገልግሎት በማይሰጥ ድርጅት እጅ ውስጥ በመሆኑ ነው” በሚል ሰበብ ጉዳዩን ለግል ጥቅሙ ሲያውለው ይታያል፡፡ “ሴቶችን ለማበረታታት” በሚል “ጆካ”፣ ካፌውን ለአንዲት ዘመዱ ይሰጣታል።  
“የመስሪያ ቤታችን ስራ አስኪያጅ እጅግ ዴሞክራት ነው” ብሎ የጀመረው ታሪክ መጨረሻም ላይ በአጽንዖት ጭምር ይደግመዋል፡፡ እንደዚህ…
“እውነቴን ነው - የመስሪያ ቤታችን ስራ አስኪያጅ ዘመኑ የገባው ʻዴሞክራትʼ ነው”፡፡
ይሄ ዘመናችን ነው፡፡ ይሄ አሁን ነው፡፡ ይሄ ሕይወታችን፤ ኑሯችን ነው፡፡ “ቼ በለው”ን ጠቅለል ባለ መልኩ ስገልጸው፣ የሸገር ከተማ አንትሮፖሎጂና ኮስሞፖሊታን ተረክ ነው፡፡ ከላይ ከላይ የሚታየውን ሳይሆን፤ ውስጥ ለውስጥ ይህቺን ከተማ (by extension ይቺን አገር) ማን እንዴት ባለ ብልሃት እንደሚመራት እያሳሳቀ የሚያሳይ የዘመናዊ አዲስ አበባ መምሪያ መጽሐፍ (guidebook) ሆኖ ሊያገለግልም ይችላል፡፡ ነገሮች ከላይ እንደሚታዩት እንዳልሆኑ የሚያስረዳ ውስጠ-አዋቂ መረጃ ያቀብላል፡፡    
 “ቼ በለው” ውስጥ በግልፅ እና በደማቁ የተሣለው የዘመኑ መንፈስ ነው፡፡

Read 5345 times