Monday, 18 September 2017 10:40

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በነሐሴ ወር 1.7 ቢሊዬን ብር ዋጋ ያለው 33,528 ቶን ምርት አገበያየ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

      የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፈው ነሐሴ ወር 2009 ዓ.ም፣ በ23 የግብይት ቀናት፣ የ1.7 ቢሊየን ብር ዋጋ ያለው የሰሊጥ፣ ቦሎቄና ቡና ምርት ማገበያየቱን አስታውቋል፡፡ ምርት ገበያው በአዲስ መልክ በጀመረው የቡና ግብይት ሞዴል እንዲሁም ሰሊጥና ቦሎቄን በሚያገበያይባቸው የኤሌክትሪክ ግብይት ዘዴ፣ በዚህ ወር ብቻ 33,528 ቶን ምርት ማገበያየት መቻሉን ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫው አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በዚህ ወር ካገበያያቸው ምርቶች መካከል ቡና 1.40 ቢሊየን ብር ዋጋ ያለው 21,159 ቶን የምርት ግብይት አፈፃፀም በማሳየት፣ በዋጋ 82 በመቶ፣ በመጠን 63 በመቶ የቅድሚያ ደረጃውን ይዟል ብሏል ምርት ገበያው፡፡ ከዚህ ግብይት ውስጥ ለውጪ ገበያ የተዘጋጀ ቡና 15,817 ቶን፣ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ 4,152 ቶን፣ ስፔሻሊቲ ቡና 1,190 ቶን ድርሻ አላቸው፡፡ እያንዳንዱ የቡና ዘርፍ በፈረሱላ የተሸጠበት ከፍተኛ ዋጋ ስፔሻሊቲ 2,807፣ የታጠበ ቡና 1550፣ ያልታጠበ ቡና 2,753 ሲሆን ዝቅተኛ ዋጋ ደግሞ ስፔሻሊቲ 950 ብር፣ የታጠበ ቡና 810 ብር፣ ያልታጠበ ቡና 800 ብር መሆኑንም ምርት ገበያው ጠቁሟል፡፡
የነሐሴ ወር የቡና ግብይት ከሐምሌ 2009 አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የምርት መጠኑ በ52 በመቶ፣ አጠቃላይ የምርት ዋጋው ደግሞ በ66 በመቶ አድጓል ያለው ምርት ገበያው በተለይ ወደ ውጪ የሚላክ ቡና ግብይት መጠን በ66 በመቶ፣ በዋጋ 80 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ ይህም እድገት ከተገኘባቸው ምክንያቶች አንዱ፣ የቡና መገኛን ባለቤትነት የተመረኮዘ የመኪና ላይ ግብይት ሥርዓት፣ በምርት ገበያው መካሄዱ መሆኑን ገልጿል፡
እንዲሁም ከቡና ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ የያዘው ሰሊጥ ሲሆን 303 ሚሊየን ብር ዋጋ ያለው 11,479 ቆን ግብይት መከናወኑም ተጠቅሷል፡፡ ከአጠቃላይ ገብይቱ በመጠን 34 በመቶ፣ በዋጋ 18 በመቶ ድርሻ አለው፡፡ በኩንታል የነበረው ዋጋም ከፍተኛው 2,906 እንዲሁም ዝቅተኛው 2,200 ብር አውጥቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 205 ሚሊየን ብር ዋጋ ያለው 7,455 ቶን ነጭ የሁመራ ጎንደር ሰሊጥ ግብይት በመፈጸሙ ግንባር ቀደም ቦታ ይዟል ብሏል ምርት ገበያው፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ - የሁሉም ገበያ

Read 3164 times