Monday, 18 September 2017 10:39

የሻንዶንግ ዶንግ የአህያ ቄራ ፋብሪካ ባለቤቶች ቅሬታ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

 ሻንዶንግ ዶንግ ኤኖአኮ ሊሚትድ በቻይና የሚገኝ መድሃኒት አምራች ድርጅት ነው፡፡ ኩባንያው በተለይ ኢጂዎ (Ejiao) የተባለውን ባህላዊ መድሀኒት ከአህያ ቆዳ የሚያመርት መድሃኒቱም የሰዎችን ደም በማዳበር ለብዙ ህመምተኞች ፈውስ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ሻንዶንግ ዶንግ ኩባንያም በ2011 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት፣ የአህያ ቆዳ ለመግዛት ጥያቄ ባቀረቡበት ወቅት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አህያ አርዶ ቆዳ የሚሸጥ ምንም አይነት ኩባንያ ስለሌለ እዚህ መጥታችሁ የራሳችሁን ማረጃና ማቀነባበሪያ ገንብታችሁ ስራ ጀምሩ የሚል ግብዣ እንደቀረበላቸው የሻንዶንግ ዶንግ ኩባንያ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ዳይሬክተርና ባለሀብት ሚስተር ዠያንግ ሊዩ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ ይሁን እንጂ 50 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት ተደርጎ ከቀረጥ ነፃ ማሽነሪዎች ገብተውና አህያ አቅራቢዎች ተደራጅተው ፋብሪካው የአህያ ቆዳና ስጋ ወደ ቻይና መላክ ከጀመረ አንድ ወር ሳይሞላው ከቢሾፍቱ ከተማ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት በወጣ ደብዳቤ ስራው እንዲቆም በመደረጉ ሚስተር ሊዮ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡ ህጋዊ ፈቃድ አውጥተው ለኩባንያው አህያ የማቅረብ ስራ የሚሰሩ ከሶስት በላይ ድርጅቶች
ከሚስተር ሊዩ ጋር ሰራተን በመምጣት የደረሰባቸውን ኪሳራና አሁንም ገዝተው ያስቀመጧቸው አህዮች ጉዳይ እንዳስጨነቃቸው ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በፋብሪካው አከፋፈት በተዘጋበት ሂደት፣ ቻይናዊያኑ ባለሀብት ከተዘጋ በኋላ ስላደረጉት እንቅስቃሴና ከመንግስት በሚጠብቁት ፍትህ ዙሪያ ሚስተር ዥያንግ ሊዮ ጋር በሸራተን አዲስ ሆቴል ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡

      በመጀመሪያ ቻይና ስለሚገኘው ዋናው ሻንዶንግ ዶንግ ኩባንያ ይንገሩኝ …
ዋናው ኩባንያችን በቻይና ትልቅ የመድኃኒት አምራች ድርጅት ነው፡፡ ከተመሰረተም በርካታ አመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ከ50 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሀብት ያለው ኩባንያ ነው፡፡ “Ejlao” የተሰኘውንና ደምን የሚያበለፅገውን ባህላዊ መድኃኒት፣ ከአህያ ቆዳ በማምረት የህመምተኞችን ህይወት በመታደግ ሥራ ላይ ነው የተሰማራነው፡፡  
ወደ ኢትዮጵያ መጥታችሁ ኢንቨስት ለማድረግ እንዴት ፍላጎት አደረባችሁ?
እኛ መጀመሪያ ወደ ኢትዮጵያ የመጣነው ለመድኃኒት አምራች ድርጅታችን የሚውል የአህያ ቆዳ ለመግዛት ነው፡፡ ይህንን ጥያቄ ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ስናቀርብ፣ “ኢትዮጵያ ውስጥ አንድም አህያ አርዶ ቆዳም ሆነ የአህያ ስጋ የሚሸጥ ኩባንያ ስለሌለ እዚህ መጥታችሁ የራሳችሁን ፋብሪካ ከፍታችሁ ስሩ” ተባልን። ይህን ጥያቄ ያቀረብነው በ2011 ነበር፡፡ ከዚያ በ2014 ቢሾፍቱ ከተማ ላይ መሬት ወስደን፣ ከውጭ ከቀረጥ ነፃ መሳሪያዎችን አስገብተን፣ በ50 ሚ. ብር ኢንቨስትመንት ፋብሪካውን በ2016 መጨረሻ ላይ ገንብተን ጨረስን፡፡ በ2017 ማርች ወር ላይ አህያ ማረድና ቆዳና ስጋውን ወደ ቬትናም ልከን፣ ከቬትናም ወደ ቻይና ማስገባት ጀመርን፡፡ ስራውን ጀምረን ብዙ ሳንጓዝ፣ ከቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት በወጣ አንድ ደብዳቤ፣ ስራውን አቁሙ ተባልን። ወዲያውኑ ፖሊሶች መጥተው፣ በአንዴ ስራው ቆመ፡፡
ከከንቲባው ጽ/ቤት የተፃፈው የስራ ማስቆሚያ ደብዳቤ ምን ይላል?
ይሄው ደብዳቤውን መመልከት ትችያለሽ (ደብዳቤውን እያቀበሉኝ) ደብዳቤው የሚለው በፍፁም ትክክል አይደለም፡፡
(ደብዳቤው የሚለው ድርጅታችሁ የተሰማራበት የአህያ ቄራ ሲሆን ስለ ኢንቨስትመንቱ ከመነሻው ከህብረተሰቡ ጋር ተወያይተን ስምምነት ላይ ሳንደርስ ግንባታ የጀመራችሁ በመሆኑ ከአካባቢው ማህበረሰብ በተነሳ ተቃውሞ፣ ንብረታችሁ ላይ ከፍተኛ ውድመት ደርሶ ነበር ከከተማው ነዋሪውና ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በመተባበር፣ ድርጅታችሁ ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ የመከላከል ሰራ ተሰርቷል፣ ይሁን እንጂ አሁንም አካባቢው የማህበረሰብ ታቃውሞ ስለቀጠለና ተቃውሞውንም የከተማ አስተዳደሩ ስላመነበት፣ የጀመራችሁትን ስራ እንድታቆሙ አጥብቀን እንጠይቃለን ይላል፡፡ መጀመሪያ ስምምነት ላይ ሳትደርሱ እንዴት ግንባታ አጠናቅቃችሁ ወደ አህያ ማረድ ገባችሁ?
ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ያወጣነውን የስራ ፈቃድ ተመልከቺ፡፡ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና ከሚመለከታቸው አካላት የኢንቨስትመንት ፈቃድ አውጥተናል፡፡ የንግድ ሰራ ፈቃዱ በኢንቨስትመንት አዋጅ ቁጥር 280/1984 ዓ.ም የተሰጠን ነው፡፡ የኦሮሚያ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ቦታ ሰጥቶናል፡፡ ተመልከቺ የቦታውን ካርታ፡፡ ይሄ ሁሉ ሲደረግ ሁሉም ያውቃል፣ ስራችን ግልፅ ነው። የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ የግብር ከፋይ ምዝገባ ሰርተፍኬታችንን ተመልከቺ ይህ ሁሉ ባለበት “ከህዝቡ ጋር ስምምነት ላይ ሳንደርስ ግንባታ ጀመራችሁ” የሚለው አያሳምንም፡፡ በጣም ቅር ብሎናል፡፡ ሌላው ቀርቶ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ሀምሌ 15 ቀን 2005 ዓ.ም በዚሁ ጉዳይ በቢሾፍቱ ከተማ ኢንቨስትመንት ጽ/ቤት ከጠዋቱ 3፡00 እስከ 6፡00 ድረስ ከቢሾፍቱ ከተማና አካባቢው አባ ገዳዎች፣ ከተለያዩ የሀይማኖት አባቶች፣ ከመንግስት ኃላፊዎችና በከተማዋ ዙሪያ ከሚገኙ የቀበሌ ሊቀመንበሮች ጋር ውይይት ተደርጓል። ህዝቡ “የአህያ ስጋ” በባህላችንም በሀይማኖታችንም ስለማይፈቀድ፣ ከስጋ ጋር ተቀላቅሎ ወደ ገበያ ቢገባስ፣ ቢሾፍቱ የቱሪስት መዳረሻ ከተማ ሆና ሳለ እንዴት የአህያ ቄራ ይከፈትባታል” የሚልና መሰል በርካታ ስጋት አዘል ጥያቄዎች አንስቶ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡
በውይይቱ ምን ስምምነት ላይ ደረሳችሁ?
የእኛ ኩባንያ የአህያ ቆዳን ለመድኃኒትነት እንደሚጠቀም፣ ስጋውም ሆነ ሌሎች ተረፈ ምርቶች ፕሮሰስ ተደርገው ወደ ውጭ ኤክስፖርት ብቻ እንደሚደረጉ፣ የአህያ ዋጋ ውድ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ተጠቃሚ ስለሌለም ለአገሬው የውስጥ ፍጆታ ለማዋል ምንም እቅድ እንደሌለ… በደንብ አስረዳን፡፡ ህዝቡም ለመንግስት ኃላፊዎች የአህያ ስጋ በምንም መልኩ ወደ ገበያ እንዳይቀርብ፣ አስጠንቅቆና ባህላችንንና ሀይማኖታችንን የሚጋፋ ነገር እስካልተሰራ ድረስ ፋብሪካው ስራውን ቢቀጥል ምንም ችግር እንደሌለ ስምምነት ላይ ተደርሶ፣ ውይይቱ ስድስት ሰዓት ላይ ተበተነ፡፡ ይሄው ተመልከቺ የተሳታፊዎቹን ስም ዝርዝር፣ ፊርማ፣ ከየት ከየት ተወክለው እንደመጡ፤ ምን ምን ስጋቶችን እንዳነሱ… (ከኩባንያው የተሰጠውን ምላሽና የማጠቃለያ ሀሳብን የያዘውን ባለሶስት ገፅ ወረቀት በዋቢነት እየሰጡኝ፡፡) እኛ መጀመሪያ ብንከለከል አንገባበትም ነበር፡፡ ሁለተኛ የአህያ ቆዳ ስንልክ፣ ገበሬው ደክመው ጅብ ሊበላቸው የሚችሉ አህዮችን ሳይቀር ለአቅራቢዎች በመሸጥ ተጠቃሚ እየሆነ ነው፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያም የውጭ ምንዛሬ እያገኘች ነው፡፡ በፋብሪካውም ከመቶ በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች በጥሩ ደሞዝ ሥራ አግኝተው ራሳቸውን መምራት ችለዋል፡፡ ይህ ሁሉ ጥቅም አለ፡፡  
የህብረተሰቡም ስጋት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በሃይማኖትም ሆነ በባህል በኢትዮጵያ የአህያ ስጋም ቆዳም ጥቅም ላይ አይውልም፡፡ ይሄንን እንዴት ያዩታል?
ይሄ ትክክል ሊሆን ይችላል፤ እኛ ምንም አይነት የአህያ ስጋም ሆነ ቆዳ ለአገር ውስጥ ፍጆታ አናውልም። በዚህ ላይ ያለንን አቋም የኢትዮጵያ መንግስት ያውቃል። ሁለተኛው ነገር አንድ አህያ ታርዶ ቆዳውም ሆነ ስጋው ኤክስፖርት እስኪደረግ ያለውን ሂደት የሚከታተሉ ከግብርና ቢሮ ከስጋና ወተት ድርጅት፣ ከከስተምና ጉምሩክና ሌሎች መስሪያ ቤቶች የተወከሉ ሂደቱን የሚከታተሉ ሰዎች ተመድበዋል፡፡ በሌላ በኩል ሀይማኖትም ባህልም አይፈቅድም ከተባለ፣ ጭራሽ ኢንቨስትመንቱ መፈቀድ አልነበረበትም፡፡ አሁን የእኛ ፋብሪካ ለሌላ ስራ አይሆንም፤ ስራ ካቆምን አምስት ወራት አልፈዋል፡፡ እቃዎች ያለ ስራ እየተበላሹ ነው፣ ለጥበቃ ሰራተኞች ለመብራትና ለመሰል በርካታ ወጭዎች ተዳርገናል፡፡ አቅራቢዎቻችንም ለእኛ ለማስረከብ ገዝተው ያስቀመጧቸውን አህዮች የት ያድርሷቸው፡፡ ለምሳሌ መቂ ከተማ የሚገኙ “ሰናይትና ጓደኞቿ ፍሩትና ቬጂቴብል” የተባሉ አቅራቢዎች ከመቶ በላይ አህዮችን እስከ 150 ሺ ብር አውጥተው ገዝተው፣ ይሄው ለቀለብና ለጠባቂ ወጪ እያወጡ ቁጭ ብለዋል፡፡ ይሄ በጣም የሚያሳዝንና ቅር የሚያሰኝ ነው፡፡ እነዚህ አቅራቢዎች አህዮቹን መልሰው ወደ ገበያ ማውጣት አይችሉም፤ አገልግሎታቸውን የጨረሱ ናቸው፡፡
ስራ እንድታቆሙ ከተደረጋችሁ በኋላ ምን አይነት እንቅስቃሴዎችን አደረጋችሁ? ቅሬታዎችሁንስ ለማን አቀረባችሁ?
ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ቅሬታ አቅርበናል፡፡ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት ከአቶ ለማ መገርሳ ጋርም ለመነጋገር ቀጠሮ ጠይቀን ነበር፡፡ በጣም ስራ ስለበዛባቸው አልተገናኘንም። ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ደግሞ የኦሮሚያን ክልላዊ መንግስት አነጋግሮ፣ መፍትሄ ሊሰጠን አልቻለም፡፡ ብቻ እናየዋለን ብለው ይነገሩናል፤ ወሬ ያወሩልናል ግን እስካሁን መፍትሄ አልገኘም፡፡ የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት ምንም ፕሮሲጀር ሳይከተል ደብዳቤ በመላክና ፖሊሶችን ልኮ የአቅራቢዎችን ቦታ በማፈራረስ ስራ እንድናቆም ማድረጉ ተገቢ አይደለም፡፡ እኛ ከፌደራል ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ፣ ከዚያም ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ከዚያም ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት፡፡ ከቢሾፍቱ ከተማ ፈቃድ አውጥተን ህጋዊ ሆነን ነው ስራ የጀመርነው፡፡ ስንዘጋም ፕሮሲጀር መኖር አለበት፡፡ እርግጥ ነው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኩባንያው ስራ እንዲያቆም የሚጠይቅ ደብዳቤ ለኢንቨስትመንት ኮሚሽን ልኳል፡፡ ኮሚሽኑ ግን ምንም ውሳኔ ሳይሰጥ እስካሁን ዝም ብሏል፡፡ መፍትሄ አላገኘንም፡፡
እና ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤትስ የመውሰድ ሀሳብ አላችሁ?
እኛ ጉዳዩ በሰላም ያልቃል…፡፡ የሚል ተስፋ ነው ያለን፡፡
በሰላም ለመጨረስ ተስፋ የሚሰጡ ነገሮች አሉ?
በኩባንያው መከፈት የምንጠቀመው እኛ ብቻ አይደለንም፡፡ የአገሪቱ ገበሬዎችም ናቸው፡፡ እኛ አገልግሎቱን የጨረሰ ወንድ አህያ ነው በውድ ዋጋ የምንገዛው፡፡ የውጭ ምንዛሬ እናመጣለን፡፡ ይሄ ሁሉ ግምት ውስጥ ይገባል የሚል ተስፋ አለን፡፡ በሌላ በኩል፣ እኛ ኢትዮጵያን አምነን፣ ገንዘብ አውጥተን፣ ፋብሪካ ከፍተናል፡፡ እቃዎችም ከቀረጥ ነፃ ነው የገቡት፡፡ ህጋዊ ሆነን ነው ስራ የጀመርነው፡፡ ይሄ ሁሉ ነገር ሲታሰብ፣ ችግሩ በሰላም ያልቃል የሚል ተስፋ አለን፡፡
እንደ ሴራሊዮን ያሉ አገራት ውስጥ እንደ እናንተ ያሉ ኩባንያዎች በህዝብ ቅሬታ መዘጋታቸውን ሰምቻለሁ፡፡ በአህያ እርድ ላይ ያለው የተቃውሞ አቋም በኢትዮጵያ የሚብስ ይመስለኛል፡፡ እንዴት ወደ ስራው ገባችሁበት?
በሌላው የአፍሪካ አገር እንዲህ አይነት ስራዎች በደንብ ይሰራሉ፡፡ ለምሳሌ እዚህ ጎረቤት ኬንያ ብትሄጂ፣ ይህን ስራ የሚሰሩ አራት ትልልቅ ኩባንያዎች አሉ፡፡ አህዮችን ከኢትዮጵያ ጭምር ይገዛሉ፡፡ ተዘጉ የሚባሉት ህጋዊ ፍቃድ ሳያወጡ ስራ የሚጀምሩ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ስራው ኤክስፖርት ማድረግ ብቻ ነው፡፡ አገር ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውል አይደለም፡፡ እዚህ አገር ጥቅም ላይ እንደማይውል፣ ባህልና ሀይማኖት እንደማይፈቅድ አውቀናል፡፡ እኛ መጥታችሁ፣ “ራሳችሁ አህያውን አርዳችሁ፣ ፕሮሰስ አድርጋችሁ ወደ ውጭ መላክ ትችላላችሁ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይህን የሚሰራ ግለሰብም ሆነ ድርጅት የለም፤ ባህሉ አይፈቅድም” ተብሎ ተነግሮናል፡፡ አሁንም ችግራችሁን ተነጋግረን እንፈታለን ይለናል፡፡ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ግን ይሄው ከኤፕሪል 15 ጀምሮ ስራ አቁመን፣ ለተለያዩ ወጪዎችና ኪሳራ እየተዳረግን ነው፡፡ አቅራቢዎቹም ከእኛ ጋር ተዋውለው ተደራጅተው አህያ ገዝተው አስቀምጠዋል፡፡ እኛ ስራውን ስላቆምን ልንረከባቸው አልቻልንም፡፡ በዚህ ችግር ውስጥ ነን፡፡
ለትንሽ ጊዜም ቢሆን ስራ ጀምራችሁ ነበር… ምን ያህል የአህያ ቆዳና ስጋ ኤክስፖርት አደረጋችሁ?
1800 ያህል ቆዳና 75 ቶን ስጋ ኤክስፖርት አድርገናል። ይሄ የውጭ ምንዛሬን አምጥቷል፡፡ በነገራችን ላይ ደጋግሜ እንደተናገርኩት፤ አገልግሎታቸውን የጨረሱ ወንድ አህዮችን እስከ 3 ሺህ ብር እንገዛለን። እኛ ባንገዛቸው ገበሬው ለጅብ ነበር የሚሰጣቸው፡፡ እየገዛን ተጠቃሚ ያደረግናቸው፡፡ ሰናይትና ጓደኞቿ ከተሰኙት የተደራጁ አቅራቢዎች እንኳን ወደ 400 አህዮች ተረክበን ነበር ገዝተው ያስቀመጧቸው ከመቶ በላይ አህዮች ሳይቆጠሩ፡፡ ለአቅራቢዎችም ጥሩ የስራ እድል ፈጥረን ነበር፡፡
በመጨረሻ ምን መልዕክት ማስተላለፍ ይፈልጋሉ?
እኔ በበኩሌ፤ የፌደራል መንግስትም ሆነ በርካታ ሰው ይደግፈናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ህጋዊ ፍቃድ ተሰጥቶን፣ እንድንሰራ ተጋብዘን፣ ብዙ ወጪ አውጥተን ነው ስራ የጀመርነው፡፡ የመጣነው የህዝቡን ባህልና ሀይማኖትም ልንጋፋ አይደለም፡፡ ስራችን ግልፅና ግልፅ ነው፡፡ ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል አንዳችም የአህያ ስጋም ቆዳም የለም፡፡ የአህያ ቆዳ በጣም ስስና በቀላሉ የሚቀደድ በመሆኑ ለልብስ ለጫማም ሆነ ለቦርሳ አያገለግልም፤ ግን ቻይና ውስጥ ኢጂዎ ለሚባለው መድሀኒት ከፍተኛ ጥቅም ስላለው የሰዎችን ህይወት ያተርፋል፡፡ የእኛም አላማ ከአህያ ቆዳ መድሀኒቱን መስራት ስለሆነ ህዝቡም መንግስትም ይሄን ተረድቶ እንደሚደግፈን፣ መጉላላታችንም በቅርቡ እልባት እንደሚያገኝ ተስፋ አለኝ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትና ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ችግራችንን ግምት ውስጥ በማስገባት ከውጭ ምንዛሬ ማስገኘት፣ ከፋብሪካው ሰራተኞችና ከአህያ አቅራቢዎች እንዲሁም ከገበሬዎች ጥቅም አንፃር ጉዳዩ ተቃኝቶ፣ ስራችንን መቀጠል እንድንችል አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጠን እጠይቃለሁ፡፡

Read 2619 times