Monday, 18 September 2017 10:41

እንኩዋን ለ2010/ዓ/ም በሰላም አደረሳችሁ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ
Rate this item
(0 votes)

  ዘመኑ የጤና የሰላም እና የብልጽግና እንዲሆንላችሁ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ይመኛል፡፡

     ያለፈውን  አመት ስራ ባለፈው ሳምንት አጠናቀን ወደ አዲሱ አመት በዚህኛው ህትመት ስንሸጋገር የስራችን መጀመሪያ ያደረግነው የመልካም ምኞት መግለጫ ነው። ለዚህም የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደረጀ ንጉሴ እና የመስሪያ ቤቱ ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሰላማዊት ክፍሌ ስለመስሪያ ቤቱ ያለፈ የአሁንና የወደፊት አቅጣጫ እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም ለእናቶችና ሕጻናት የመልካም ምኞት መግለጫቸውን አስተላልፈዋል፡፡    
ዶ/ር ደረጀ ንጉሴ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ፕሬዝዳንት እንደገለጹት የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ESOG ከተመሰረተ አሁን 26ኛ አመቱን እያስቆጠረ ነው፡፡ አመሰራረቱም በወቅቱ የነበረውን ከፍተኛ የእናቶች ሞት ምክንያት በማድረግ የሙያ ማህበራት የተሻለ ሚና መጫወት እንደሚችሉ ታምኖበት የተመሰረተ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ነው፡፡ ከምስረታውም በሁዋላ በተለያዩ የእናቶችና የጨቅላ ሕጻናት ጤና በተለይም በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን አከናውኖአል፡፡ ለአብነት ያህልም ከ21/ በላይ ፕሮጀክቶችን ከአለም አቀፍ፣ ከአገር በቀል እና ከሌሎች በጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በመተባበር አከናውኖአል፡፡ እነዚህ ከሀያ በላይ የሚሆኑ ፕሮጀክቶች በእናቶች እና ጽንስ ጤንነት እንዲሁም ጨቅላ ሕጻናት ጤና ላይ ያተኮሩ ስለነበሩ በአገር ደረጃ ወጤት ለማስመዝገብ የረዱ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ይህ የሙያ ማህበር ከፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር በመተባበር የጤና አገልግሎቱን በተሻለ መንገድ ለሕብረተሰቡ ለማዳረስ የሚያስችሉ ሙያዊ መመሪያዎችን፣ አቋሞችን በማዘጋጀት በኩል ተሳትፎ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጎአል፡፡ ከዚህም በላይ ESOG የተለያዩ ጥናቶችን በማዘጋጀት ለፖሊስ አቅጣጫ ግብአት እንዲሆኑ አቅርቦ ሁነኛ ለውጦች እንዲመጡ አስችሎአል፡፡ ESOG በአሁኑ     ወቅት ቁጥራቸው ከ318/በላይ የሚሆኑ የሙሉ ጊዜ አባላትና ወደ 76/ የሚደርሱ ተባባሪ አባላት አሉት፡፡
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎች ማህበር ESOG ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሰላማዊት ክፍሌ ስለማህበሩ ያለፈው አመት እንቅስቃሴ የሚከተለውን ነበር ያሉት፡፡
2009/ አመተ ምህረት ብዙ ስኬት የታየበት አመተ ምህረት ነበር፡፡ አንዱን እንኩዋን ብንጠቅስ ማህበሩ  የምስረታውን 25ኛ/ አመት ያከበረበት ነበር፡፡ የማህበሩን አመሰራረት መለስ ብለን ስንቃኝ ኬንያ ላይ ከእናቶች ጤንነት ጋር በተያያዘ በተደረገ ስብሰባ  መነሻነት በአዲስ አበባ ከአንድ አመት በሁዋላ ተመሳሳይ ስብሰባ ተደርጎ ነበር፡፡
በጊዜው ባለሙያውን የሚወክል ማህበር ባለመኖሩ እና በእናቶችና ጨቅላዎች ጤንነት ላይ በተቀናጀ መልኩ የሚሰራ የባለሙያ ስብስባ በማስፈለጉ የተቋቋመ ማህበር ነው፡፡ ESOG ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የእናቶችን እንዲሁም የጨቅላዎቻቸውን የስነተዋልዶ ጤንነት እንዲሻሻል እና በአገር አቀፍ ደረጃም የነበረውን ሞት ለመቀነስ የሚረዳ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርግ የቆየ ማህበር ነው፡፡ በፖሊሲ፣ በስትራቴጂ ረገድ ያሉ ስራዎችን ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እንዲሁም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማምጣት ጭምር አባላቶችን አስተባብሮ ሲሰራ የቆየ አሁንም በመስራት ላይ ያለ ማህበር ነው፡፡ በአጠቃላይም ለስነተዋልዶ ጤና መሻሻል በአገር ደረጃ ለተመዘገበው ውጤት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደረገ ሲሆን ማህበሩ ወደፊትም እስከአሁን ከነበረው በተሻለ አገልግሎቱ ለተጠቃሚው እንዲደርስ ለማድረግ ለመስራት ዝግጁ ነው፡፡ ብለዋል፡፡
ዶር ደረጀ በስተመጨረሻውም ህብረተሰቡ የእናቶችን እና የጽንስን እንዲሁም ጨቅላዎችን ጤንነት ከማስጠበቅ አኩዋያ ኃላፊነት ስላለበት በባለሙያዎች ከሚሰጠው እገዛ በተጉዋዳኝ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ማለትም ቅድመ ወሊድ ክትትል በማድረግ በጤና ተቋም እና በሰለጠነ ባለሙያ ልጅን በመውለድ እንዲሁም የቤተሰብ እቅድን ተግበራዊ በማድረግ ለቤተሰብ እንዲሁም ለአገር ጠቃሚ ነገር እንዲያደርጉ ያስፈልጋል፡፡ የተወለዱ ልጆችንም በሚመለከት ተገቢውን እድገት እንዲያገኙ በተገቢው በመመገብ እንዲሁም የክትባት ፕሮግ ራሞችን ተግባራዊ በማድረግ ባጠቃላይም የጤናሕይወታቸውን መቆጣጠር እንዲቻል ወደጤና ተቋም ልጆችን በመውሰድ የባለሙያ ምክር ማግኘት እንዳለባቸውም በዚሁ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ ብለዋል፡፡
ዶ/ር ደረጀ  በመጪው አመት ሙያተኞች በተለይም የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህር አባላት ከዚህ ቀደም ከነበረው በላይ ለህብረተሰቡ ሙያዊ እገዛ እንደሚያደርጉ እምነት እንዳላቸውና በጽህፈት ቤቱም ያሉ ሰራተኞች በየተሰለፉበት መስክ ተግባራዊ እንቅስቃሴያቸውን ለህብረተሰቡ በሚጠቅም መልኩ እንዲያከናውኑ የተጣለባቸውን አደራ እንደሚወጡ ተስፋ አለኝ ብለዋል፡፡
ወ/ሮ ሰላማዊት በበኩላቸው የተለያዩ ፕሮጀክቶች በጅምር ላይ ያሉ በመሆናቸው በመጪው አመት የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ ለመስራት እቅድ መኖሩንና ተደራሽነትን፣ ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎችን በስፋት እና በብቃት ለመወጣት በአመራሩና በሰራተኞች የተቻለውን ያህል ጥረት ለማደረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመቀጠልም ማህበረሰቡን ጤናውን እንዲንከባከብ ለማድረግ ማስተማር ትልቁ ስራ እንደሆነ ገልጸው እስከአሁን ከሚደረገው በላይ በተለያዩ መንገዶች በመጪው ዘመን ትኩረት የሚደረግባቸው ተግባራት መሆናቸውን ጠቁመው መጪው አመት የሰላም፣ የጤና፣ የእድገትና የብልጽግና እንዲሆን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ተመኝተዋል፡፡
        መልካም አዲስ አመት፡፡

Read 1757 times