Print this page
Monday, 18 September 2017 10:48

የኡጋንዳ ገዢ ፓርቲ፣ የፕሬዚዳንቱን የዕድሜ ገደብ ለማስቀረት ወሰነ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ከዚህ በፊትም ፕሬዚዳንቱን በስልጣን ለማቆየት ህገ መንግስቱ ተሻሽሏል

        በኡጋንዳ የገዢው ፓርቲን የሚወክሉ የፓርላማ አባላት፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የዕድሜ ጣራ 75 አመት እንዲሆን የሚገድበውን የህገ መንግስት አንቀጽ እንዲሰረዝ የሚጠይቀውን የውሳኔ ሃሳብ ባለፈው ማክሰኞ በሙሉ ድምጽ መደገፋቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የፕሬዚዳንቱን የእድሜ ገደብ ለማስቀረት ያለመው የውሳኔ ሃሳቡ፣ የአገሪቱን ህገ መንግስት በማሻሻል፣ የ72 አመቱን ፕሬዚዳንት ዮሪ ሙሴቬኒ፣ በ2021 በሚካሄደው ቀጣዩ የአገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዲወዳደሩ ለማስቻል የተደረገ ሙከራ ነው ሲሉ ተቃዋሚዎች ትችት መሰንዘራቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡
ፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ በቀጣዩ ምርጫ ዕድሜያቸው ከ75 አመት በላይ ስለሚሆን፣ በህገ መንግስቱ መሰረት፣ ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር እንደማይችሉ የጠቆመው ዘገባው፤ ፓርቲያቸው ናሽናል ሬዚዝታንስ ሙቭመንት ግን፣ ያለ አግባብ ህግ በማሻሻል በስልጣን እንዲቆዩ ለማድረግ ዘመቻ መጀመሩን አመልክቷል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከሁለት ወራት በፊት በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት፣ አሁን የዕድሜ ገደብን በተመለከተ የምንወያይበት ጊዜ ላይ አይደለሁም፣ አገር በመምራቱ ላይ ነው ትኩረት የማደርገው ሲሉ መናገራቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
የዕድሜ ገደቡን የሚያነሳው የውሳኔ ሃሳብ በፓርላማው የሚጸድቅ ከሆነ፣ የፕሬዚዳንት ሙሴቬኒን ስልጣን ለማራዘም ሲባል 20 አመታትን ባስቆጠረው የአገሪቱ ህገ መንግስት ላይ የተደረገ ሁለተኛው ማሻሻያ እንደሚሆን የጠቆመው ዘገባው፤ በ2005 ላይም ሙሴቬኒን በስልጣን ላይ ለማቆየት ሲባል ከሁለት የስልጣን ዘመን በላይ መግዛትን የሚከለክለው የህገ መንግስቱ አንቀጽ መሻሻሉን አስታውሷል፡፡

Read 1425 times
Administrator

Latest from Administrator