Print this page
Monday, 18 September 2017 10:50

ሁዋዌ በአለማችን የስማርት ፎን ሽያጭ 2ኛ ደረጃን ያዘ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ሳምሰንግ በመሪነቱ ሲቀጥል፣ አፕል ወደ 3ኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል

     የቻይናው የቴሌኮም ኩባንያ ሁዋዌ፣ አይፎንን በሚያመርተው የአሜሪካው አፕል ለዓመታት ተይዞ የነበረውን የአለማችን የስማርት ፎን ሽያጭ የሁለተኛነት ደረጃ መረከቡን የእንግሊዙ ቴሌግራፍ ዘግቧል፡፡
ሁዋዌ ባለፉት ሰኔ እና ሐምሌ ወራት ያስመዘገበው የስማርት ፎን ሽያጭ ከአፕል ብልጫ በማሳየት ወደ ሁለተኛነት ደረጃ ከፍ ማለቱን ከሰሞኑ ይፋ የተደረገን የገበያ ጥናት ጠቅሶ ያመለከተው ዘገባው፤ ይህም ሆኖ ግን አፕል በጉጉት ሲጠበቁ የነበሩ አዳዲስ የአይፎን ሞዴሎችን በዚህ ሳምንት ለገበያ ከማቅረቡ ጋር በተያያዘ፣ ሽያጩን ከፍ አድርጎ ወደ ቀድሞ ደረጃው ሊመለስ እንደሚችል ይጠበቃል ብሏል፡፡
ሁዋዌ ለዚህ ስኬት የበቃው በስማርት ፎን ምርት ኢንዱስትሪው፣ በሰፋፊ የገበያና የማስታወቂያ ስራዎችና በሽያጭ መስመሮች ማስፋፊያ ዘርፎች ላይ በቋሚነት ትልቅ ኢንቨስትመንት በማድረጉ ነው መባሉንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ኩባንያው ከቅርብ አመታት ወዲህ በአለማችን የስማርት ፎን ገበያ ሽያጭ መሪነቱን ከያዘው የደቡብ ኮርያው ሳምሰንግ ጋር ለመፎካከር ብርቱ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ያስታወሰው ዘገባው፤ በኔትወርክ ዝርጋታና በሌሎች ተያያዥ መስኮች ላይ ከነበረው እንቅስቃሴ ወደ ስማርት ፎን ምርት በመዞር ወደ ገበያው ከገባ አጭር ጊዜው ቢሆንም፣ በፍጥነት በማደግ ከታላላቆቹ ሳምሰንግ እና አፕል ጋር ለመፎካከር መብቃቱን ገልጧል፡፡
አፕል ኩባንያ እ.ኤ.አ ከ2010 አንስቶ በአለማችን የስማርት ፎን ሽያጭ ገበያ፣ ከአንደኛ ወይም ከሁለተኛ ደረጃ ዝቅ ብሎ እንደማያውቅም ዘገባው አክሎ አስታውሷል፡፡

Read 2054 times
Administrator

Latest from Administrator