Monday, 18 September 2017 10:53

“በኒውክሌር ቦምብ ጃፓንን ውሃ አስበላታለሁ፤ አሜሪካን ዶግ አመድ አደርጋታለሁ” - ሰሜን ኮርያ

Written by 
Rate this item
(11 votes)

ባለፈው ሰኞ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አዲስ ማዕቀብ የተጣለባት ሰሜን ኮርያ፣ ይህ ማዕቀብ እንዲጣልብኝ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋልና እቀጣቸዋለሁ በሚል፣ “ጃፓንን በውሃ ማዕበል አሰምጣለሁ፣ አሜሪካን ደግሞ ዶግ አመድ አደርጋለሁ” ስትል መዛቷን ዘ ጋርዲያን ከትናንት በስቲያ ዘግቧል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት፣ በቅርቡ ካደረገቺው የኒውክሌር ሙከራ ጋር በተያያዘ በሰሜን ኮርያ ላይ ባለፈው ሰኞ አዲስ ማዕቀብ መጣሉን ያስታወሰው ዘገባው፤ የአገሪቱ መንግስት የውጭ ግንኙነት ኮሚሽንም ይህን አድርጋለች በሚል በአሜሪካ ላይ ከተለመደው በተለየ መልኩ ጠንከር ያለና ብዙዎችን ያነጋገረ ዛቻ መሰንዘሩን ገልጧል፡፡
የሰሜን ኮርያ መንግስት የዜና ወኪል ሃሙስ ዕለት ባሰራጨው ዘገባ፤ የሰሜን ኮርያ መንግስት አራት የጃፓን ደሴቶችን በኒውክሌር ቦንብ ጥቃት ውሃ ውስጥ እንደሚያሰምጥና አሜሪካንም በከፍተኛ ጥቃት ዶግ አመድ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
ይህን ተከትሎ የጃፓን መንግስት ቃል አቀባይ፣ የሰሜን ኮርያን ዛቻ “ጸብ አጫሪና እጅግ አደገኛ” በሚል ማውገዛቸውንና ዛቻው በአካባቢው ያለውን ውጥረት የሚያባብስና ተቀባይነት የሌለው ነው በሚል ማጣጣላቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
ዘ ኢንዲፔንደንት በበኩሉ፣ 15 አባላት ያሉት የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት፣ ሰሜን ኮርያ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶችን ወደ ውጭ አገራት እንዳትልክ የሚከለክለውንና በአሜሪካ የረቀቀውን የማዕቀብ ሃሳብ ባለፈው ሰኞ ማጽደቁ በአካባቢው ያለውን ውጥረት የበለጠ እንዳባባሰው ዘግቧል፡

Read 5938 times