Monday, 25 September 2017 11:43

በኦሮሚያ የሰሞኑ ግጭት የተፈናቃዮች ቁጥር 140 ሺህ ደርሷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

ከመንግሥት ሰራተኞች ከ45 ሚ. ብር በላይ ተሰባሰበ

   በኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ የተፈናቃዮች ቁጥር 140 ሺህ መድረሱ የተገለፀ ሲሆን ተፈናቃዮችን ለመደገፍ ከኦሮሚያ የመንግስት ሰራተኞች ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ መሰባሰቡ ታውቋል፡፡
የክልሉ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በም/ኮሚሽነር ማዕረግ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ግርማ ዋተሬ፣ ለተፈናቃዮች እየተደረገ ያለውን ድጋፍ አስመልክቶ ለአዲስ አድማስ በሰጡት መረጃ፣ መንግስትና የበጎ አድራጎት ተቋማት ከሚያደርጉት አስተዋፅኦ ባሻገር ህብረተሰቡ ለድጋፍ ማሰባሰቢያ በተከፈቱ የባንክ ሂሳቦች እጁን እየዘረጋ መሆኑ ታውቋል፡፡  በተለይ አብዛኞቹ የመንግስት ሰራተኞች የአንድ ወር ደመወዛቸውን በመለገስ ለተፈናቃዮች አለኝታነታቸውን እየገለፁ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ግርማ፤ ሌሎችም ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን ተናግረዋል፡፡
መንግስት በበኩሉ፤ ተፈናቃዮችን የማረጋጋት ስራ እያከናወነ መሆኑንና በዘላቂነትም ወደ ቀድሞ ቀዬአቸውና ሀብት ንብረታቸው የሚመለሱበት ሁኔታ ላይ በአትኩሮት እየሰራ መሆኑን አቶ ግርማ አስታውቀዋል፡፡
“በአሁን ወቅት መፈናቀሉ ሙሉ በሙሉ ቆሟል ባይባልም የመከላከያ ሰራዊት መሃል ገብቶ ሁኔታዎችን እያረጋጋ እንደሚገኝ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
“በአሁን ሰዓት ትልቁ ስራችን የማረጋጋት ስራ ነው” ያሉት አቶ ግርማ፤ “ተፈናቃዮችን በዘላቂነት በማቋቋም ጉዳይ ላይም ጥናቶች ይደረጋሉ” ብለዋል፡፡
ተፈናቃዮቹ በባሌ ዞን፣ ቦረና፣ በጉጂ፣ ሐረርን ጨምሮ በሶማሌን በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች ተጠልለው እንደሚገኙም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ለተፈናቃዮች በገንዘብ ከሚደረገው አስተዋፅኦ በተጨማሪ በየአካባቢው ያለው ማህበረሰብ እህልና የተለያዩ የአይነት ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን አቶ ግርማ አስረድተዋል፡፡

Read 3346 times