Sunday, 24 September 2017 00:00

የሕንዱ ፓትርያርክ የመስቀል ደመራን በአዲስ አበባ ያከብራሉ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

* የቅዱስ ላሊበላ ደብርንና የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ይጐበኛሉ
* ከፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ጋር እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል

     የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ቅዱስ ባስልዮስ ማር ቶማ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ የፊታችን ማክሰኞ በሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ላይ ለመገኘት ከነገ በስቲያ ቀትር ላይ አዲስ አበባ የሚገቡ ሲሆን ከርእሰ ብሔሩ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ጋራ ተገናኝተው እንደሚነጋገሩ ተጠቁሟል፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን አምስት ልኡካን በመምራትም፣ በኢትዮጵያ የአራት ቀናት ጉብኝት እንደሚያደርጉ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ምንጮች ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡
ለጉብኝቱ በወጣው መርሐ ግብር መሠረት፥ ሰኞ፣ ከቀትር በኋላ፣ የህንዱ ፓትርያርክ፣ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ኦፌሴላዊ አቀባበል ይደረግላቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱና የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንት፣ የሰንበት ት/ቤት አባላትና ምእመናን በተገኙበት በሚደረገው አቀባበል፣ ፓትርያርኩ፣ ትምህርተ ወንጌል ይሰጣሉ፤ ተብሏል፡፡
በማግሥቱ ማክሰኞ፣ ከርእሰ ብሔሩ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ጋራ ተገናኝተው እንደሚነጋገሩ የተጠቀሰ ሲሆን፤ ከቀትር በኋላም፣ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጋራ ወደ መስቀል ዐደባባይ በማምራት፣ የደመራን በዓል ያከብራሉ፡፡ ብዙ ሺሕ የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች የሚያቀርቡትንና የሥነ በዓሉ ድምቀት የሆነውን ዐውደ ትርኢት የሚመለከቱት የህንዱ ፓትርያርክ፤ የሁለቱን አገሮችና አብያተ ክርስቲያናት ጥንታዊ ወዳጅነትና ቀጣይ ግንኙነት የተመለከተ ንግግር የሚያደርጉ ሲሆን ደመራውን፣ ከፓትርያርክ አቡነ ማትያስና ከአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ጋራ በአንድነት እንደሚለኩሱ ተጠቁሟል፡፡
በዕለተ ረቡዕ የመስቀል በዓልን፣ በላሊበላ ደብር ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በመገኘት እንደሚያከብሩም የተገለጸ ሲሆን ከዚያም መልስ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ቤተ መጻሕፍት ወመዘክርን፣ የሰበታ ጌቴሰማኔ ቤተ ደናግል ሴቶች ገዳምንና የደብረ ሊባኖስ ገዳምን እንደሚጎበኙ መርሐ ግብሩ ያስረዳል። ከጉብኝታቸው ፍጻሜ በኋላ፣ በሁለቱ እኅትማማች አብያተ ክርስቲያናት አንድነትና ዓለም አቀፍ አገልግሎት ዙሪያ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ የጋራ ምክክር እንደሚያካሒዱና መግለጫም እንደሚሰጡ ምንጮች ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ባለፈው ዓመት ኅዳር ሕንድን በጎበኙበት ወቅት ባቀረቡላቸው ግብዣ መሠረት፣ መስቀል ደመራን በኢትዮጵያ የሚያከብሩት ቅዱስ ባስልዮስ ማር ቶማ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተገኙበት የካቲት ወር 2005 ዓ.ም. በዓለ ሢመት ወዲህ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ የሚያደርጉት ጉብኝት እንደሆነና የሁለቱን አብያተ ክርስቲያናት የተጠናከረ ግንኙነት እንደሚያሳይ ተጠቅሷል፡፡
ከቀድሞም ጀምሮ በአገራችን ዘመናዊ ትምህርት ቤቶች ጎልቶ የሚታየው የሕንዳውያን መምህራን አገልግሎት፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሥነ መለኰት ኮሌጆችም መኖሩን ምንጮቹ አስገንዝበዋል፡፡ በአንጋፋው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በማስተማር የሚታወቁ ዕውቅ የሥነ መለኰት ሊቃውንትን ያወሱት ምንጮቹ፤ ኮሌጁ በቀድሞው መንግሥት ተዘግቶ ዳግም ከተከፈተበት ከ1987 ዓ.ም. ወዲህም አገልግሎታቸው መቀጠሉንና ከመምህራኑም  መካከል ለማዕርገ ጵጵስና የበቁ እንዳሉ ጠቅሰዋል። ይህም፣ የቆየውን ግንኙነትና ትብብር ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና መጫወቱን አስረድተዋል፡፡
ቅዱስ ባስልዮስ ማር ቶማ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ እ.ኤ.አ ከኖቨምበር 2010 ጀምሮ፣ በሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ቶማስ የተሠየሙ 91ኛው የምሥራቅ ካቶሊኮስና የማላንካራ መጥሮጶሊጣን ናቸው፡፡ በኦፊሴላዊ ስያሜዋ፣ የማላንካራ ኦርቶዶክስ ሶርያ ቤተ ክርስቲያን ወይም የኦርቶዶክስ ሶርያዊ ምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ተብላ የምትጠራው የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ በሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ በ52 ዓ.ም. የተመሠረተች ጥንታዊት ናት፡፡ በደቡብ ሕንድ የምትገኘው ኬሬላ ወይም ማላንካራ፣ የክርስትናው መሠረት የተጣለባት የመንበሩ መቀመጫ ስትሆን፤ ካቶሊኮስ የሚለው የርእሰ መንበሩ ሥያሜም የፓትርያርክ አቻ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በአሁኑ ወቅት ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ በሊቃነ ጳጳሳት የሚመሩ 25 የሀገር ውስጥና የውጭ አህጉረ ስብከትን እንዳቋቋመችና ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች እንዳሏት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በሌላ በኩል፣ ትውልደ ሕንዳውያንና የኦርቶዶክስ ክርስትና ተከታይ የሆኑ በርካታ ተሳላሚዎች፣ የሕንዱን ፓትርያርክ በመከተል በአዲስ አበባ የመስቀል ዐደባባይ ተገኝተው የደመራን በዓል እንደሚያከብሩ ታውቋል። ነዋሪነታቸውን በሕንድ፣ በአሜሪካና በእስራኤል ያደረጉ መነኰሳትን፣ ካህናትንና ምእመናንን ያካተተውና በአርባ አምስት ቡድን የተደራጀው ይኸው የተሳላሚዎቹ መንፈሳዊ ጉዞ፣ በአንጋፋው የሙምባዩ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ የሚመራ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ምንጮች እንደገለጹት፣ ተሳላሚዎቹ፣ “በኢትዮጵያ ገዳማት ሥርዓትና አኗኗር ዝና ተስበው የመጡ መንፈሳውያን ተጓዦች ናቸው፡፡” በኒውዴልሂ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢሮ አስተባባሪነት በተዘጋጀው ጉብኝት ፓኬጅ መሠረትም፣ የደመራን በዓል በመስቀል ዐደባባይ ተገኝተው ያከብራሉ፤ የላሊበላ ደብር ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን፣ የጣና ገዳማትንና የጠቅላይ ጽ/ቤቱን ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ይጎበኛሉ፤ ብለዋል - ምንጮቹ፡፡

Read 2230 times Last modified on Monday, 25 September 2017 11:56