Monday, 25 September 2017 11:44

ሰማያዊና መኢአድ ለግጭት ተፈናቃዮች ዕርዳታ ሊያሰባስቡ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

በግጭቱ ለሞቱ ዜጎች የሃዘን ቀን እንዲታወጅ ጠይቀዋል

ሰማያዊ ፓርቲ እና መኢአድ፤ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል ሰሞነኛ ግጭት፣ ለተፈናቀሉ ዜጎች  ድጋፍና እርዳታ ለማሰባሰብ፣ ግብረ ኃይል ማቋቋማቸውን የገለፁ ሲሆን፤ በግጭቱ ለሞቱ ኢትዮጵያውያን በሙሉ መንግስት የሃዘን ቀን እንዲያውጅ ጠይቀዋል፡፡
ፓርቲዎቹ ትናንት አርብ መስከረም 12 ቀን 2010 ዓ.ም. በጽ/ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር በሚገኙ አባሎቻቸው አማካይነት ለተጎጂዎች ድጋፍ የሚያሰባስብ ግብረ ኃይል ማቋቋማቸውን አስታውቀዋል፡፡
“በጥቃቱ ህይወታቸው ላለፉ ዜጎች ሀዘናችን ጥልቅ ነው፤” ያሉት ፓርቲዎቹ፤ መንግስት አጥፊዎችን በአስቸኳይ ለህግ እንዲያቀርብና ለሞቱት የሀዘን ቀን እንዲያውጅ እንዲሁም ግጭቱን ምክንያት በማድረግ “በጅምላ” የታሰሩ ዜጎች ጉዳይ በአፋጣኝ ተጣርቶ ውሳኔ እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡
የውጭ ሀገር ዲፕሎማቶች፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ለተፈጠረው ችግር ርዳታ እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀረቡት ሰማያዊና መኢአድ፤ ከሃይማኖት መሪዎች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች የጎሳ መሪዎች የተውጣጣ፣ በገለልተኛ ወገን የሚመራ አጣሪ ቡድን ተቋቁሞ፣ ሁኔታውን በጥልቀት እንዲመረምር ጠይቀዋል፡፡ ችግሩም በሀገር ሽማግሌዎች እንዲፈታ ፓርቲዎቹ አሳስበዋል፡፡

Read 4009 times