Monday, 25 September 2017 11:46

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል ግጭቶች ከ400 በላይ ሰዎች ሞተዋል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(27 votes)

· “የእርስ በርስ ግጭቶች የአገሪቱን እጣ ፈንታ አሳሳቢ አድርገውታል”
· “አንድ ሚሊዮን ያህል ዜጎች ተፈናቅለዋል”
· “በኦሮሚያ ክልል ዙሪያ የተስፋፋ አዳዲስ ግጭቶች የሠው ህይወት እየቀጠፉ ነው”  

በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ሊቀመንበርነት የሚመራው “የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ”፤ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል አዋሳኞች በተቀሰቀሰውና ለወራት በዘለቀው ግጭት እስካሁን ከ400 በላይ ዜጎች ህይወት መቀጠፉንና ከ1 ሚሊዮን በላይ መፈናቀላቸውን አስታወቀ፡፡
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ የእርስ በእርስ ግጭቶች የሀገሪቱን ቀጣይ እጣ ፈንታ አሳሳቢና አስጊ አድርጎታል ብሏል ፓርቲው፡፡
የኦሮሚያ - ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት ወደሌሎች አካባቢዎች መስፋፋቱን፣ በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ጉጂ ዞን እና በደቡብ ክልል ኮሬ ብሄረሰብ አካባቢ በተፈጠረ ግጭት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ፓርቲው አስታውቋል፡፡
ከመስከረም 1 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በደቡብ ክልል አማሮ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ የኮሬ ብሄረሰብ እና በኦሮሚያ ክልል በገላና አባያና በቡሌ ሆራ ወረዳ በሚኖሩ የጉጂ ኦሮሞ ህዝብ አዋሳኝ አካባቢ በተቀሰቀሰ ግጭት፤ የ7 ዜጎች ህይወት አልፎ፣ 14 ሰዎች መቁሰላቸውን የጠቆመው ፓርቲው፤ በሺዎች የሚቆጠሩ የ12 ቀበሌዎች ነዋሪ ህዝብ የእህል ክምር በእሳት መቃጠሉን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡ በዚህ ግጭት ቤተ እምነቶችም ለዘረፋና ጉዳት መጋለጣቸውን ፓርቲው አክሎ ገልጿል፡፡
ከመስከረም 3 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በጉጂ እና በቡርጂ ብሔረሰቦች አዋሳኝ በተፈጠረ ግጭት የ11 ሰዎች ህይወት መጥፋቱን አስታውቋል - ፓርቲው፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጤፍና የበቆሎ ክምሮችም መቃጠላቸውን ጨምሮ ገልጿል፡፡ በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በባሌ ዞን እና በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን አዋሳኝ በተፈጠረ ግጭት 6 ሰዎች መሞታቸውንና 5 ሺህ ያህል ሰዎች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸውን ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ የሚመሩት ፓርቲ አስታውቋል፡፡
የእነዚህን መሰል ግጭቶች መበራከት በእጅጉ አሳስቦኛል ያለው ፓርቲው፣ በመንግስት በኩል አስቸኳይና የማያዳግም እርምጃ የማይወሰድ ከሆነ ግን ለሀገሪቱ አንድትና ለህዝብ ሰላምና ደህንነት የከፋ አደጋ መሆኑን አስገንዝቧል፡፡
በተመሳሳይ ጉዳዩን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጠው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት መድረክ ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲቆምና የግጭት ተጎጂዎችም ካሳ ተከፍሏቸው በድጋሚ መንግስት እንዲያቋቁማቸው፣ አጥፊዎችም በህግ እንዲጠየቁ አሣስቧል፡፡ የኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ኢዴፓ በበኩሉ መንግስት ለግጭቶች መነሻ እየሆነ ያለው የፌደራሊዝም ስርአት እንዲፈትሽ ጠይቋል፡፡ አጥፊዎችም ለህግ እንዲቀርቡና ተጎጂዎች ካሣና ድጋፍ እንዲደረግላቸው ኢዲፓ ተማፅኗል፡፡
 ሰሞኑን የኦሮሚያና የሶማሌ ክልል አመራሮችንና የሀገር ሽማግሌዎችን በጽ/ቤታቸው ያነጋገሩት ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ የግጭቱ መነሻና ጉዳት እየተጣራ መሆኑን ጠቁመው በዚህ ግጭት ውስጥ እጃቸውን ያስገቡ ማናቸውም አካላት ምህረት እንደማይደረግላቸው አስታውቀዋል፡፡
በግጭቱ ሳቢያ የተፈናቀሉና የሞቱ ሰዎች ጉዳይም በሰብአዊ መብት ኮሚሽን በኩል ተጣርቶ እንደሚቀርብ ጠ/ሚኒስትሩ አስታውቀው የነበረ ሲሆን ሁለቱ ክልሎች የሞቱ ዜጎችን ቁጥር በተመለከተ የማይጣጣም መረጃ ማውጣታቸው ይታወሳል፡፡


Read 5048 times