Monday, 25 September 2017 11:50

“አንድ የጋራ አገር የመገንባት ጉዳይ ተረስቷል”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

     መስከረም ከጠባ ወዲህ የኢትዮጵያ ሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ ድንበር ላይ በተፈጠረ ግጭት፣ በርካቶች ለሞት ሲዳረጉ፣ ከ22 ሺ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸው ባለፈው ሳምንት መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ለመሆኑ የድንበር ግጭቱ እንዴት ነው የተፈጠረው? የፌደራል ሥርአቱ የግጭት አፈታት ዘዴ ለምን አልተተገበረም? እንዴትስ ግጭቱን መቆጣጠር አልተቻለም? “ከድንበር ግጭቱ ውጭ ነው” የተባለው የዜጎች
ሞትና መፈናቀል ሰበቡ ምንድን ነው? ቀጣዩ ዕጣ ፈንታችን -- እንደ ዜጎች፣ እንደ ህዝብ፣ እንደ ክልል፣ እንደ አገር ---- ምን ይሆን? ፍርሃትና ስጋታችን? ተስፋና ተግዳሮታችንስ? በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ነን፡፡ መወያየት አፋጣኝ መፍትሄ ማፍለቅም ከሁሉም ወገን ይጠበቃል፡፡ለፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄው ፖለቲካዊ ውይይት ብቻ ነው፡፡የቀድሞው የህውሓት ታጋይና አባል፣ በኋላም የአረና ፓርቲ አመራር እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገራዊ የፖለቲካ ትንታኔ በመስጠት የሚታወቁት አቶ ገብሩ አሥራትን፣ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ በፌደራሊዝም ሥርዓቱና ባረበበው አደጋ ዙሪያ አነጋግሯቸዋል፡፡

         የፌደራል ሥርአቱ የሀገር አንድነትን በማጠናከር በኩል ምን ያህል ርቀት ተጉዟል ይላሉ?
በመጀመሪያ ደረጃ በኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ ፌደራሊዝም የለም፡፡ ፌደራሊዝም ሲባል የክልል አስተዳደርና የጋራ አስተዳደር የሚጣመሩበት ስርአት ነው፡፡ የእነዚህን ሚዛን ጠብቆ መሄድ መቻል ነው ፌደራሊዝምን ስኬታማ የሚያስብለው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ማዘንበል ያለበት ሀገራዊ አንድነቱን እያጠናከረ መሄድ በሚችልበት አቅጣጫ ላይ ነው፡፡ በኛ ሁኔታ ስናየው ግን ይሄን አላማ ትቶ፣ ዋና ትኩረቱ የብሔሮችን መብት ማስጠበቅ ጉዳይ ላይ ነው፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የሆነውን እሴትና መርህ ያገናዘበ፣ አገራዊ ግንባታ አልተደረገም የሚል እምነት አለኝ፡፡
ክልሎች ሄደው ሄደው ለአካባቢያቸው እንደ ብቸኛ መንግስት የሚቆጠሩበትና የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ጉዳይ የተረሳበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ከሰሞኑ ለተፈጠሩ ግጭቶች መሰረቱም ይሄው ነው፡፡ ሁለተኛው ነገር ብሔርን መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝም ሲኖር፣ ከዲሞክራሲ ውጪ ሊታሰብ ያለመቻሉን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ፡- ህንድ በተመሳሳይ ፌደራሊዝም አለ፡፡ ሀገሪቱ ከምትከተለው የዲሞክራሲ ስርአት አንፃር ግን ዋና ዋና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገር አቀፍነትን ያማከሉ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ ሀገር እየመራ ያለውም ኢህአዴግ፣ ግንባር ነው እንጂ አንድ ውህድ ፓርቲ አይደለም፡፡ ሌሎች ሀገራዊ ፓርቲዎችም እንዳያቆጠቁጡ ጨምድዶ ይዟቸዋል፡፡
የአንድ ኃይል ፈላጭ ቆራጭነት ተባብሷል፡፡ ችግሮቹ እነዚህ ናቸው፡፡ በዚህ መሃል አንድ የጋራ አገር  የመገንባት  ጉዳይ ተረስቷል፡፡ ሁሉም ስለሚኖርበት ክልሉ ብቻ እንዲያስብ ተደርጓል፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት፣አገር የሚባል ነገር ተረስቶ፣ እያንዳንዱ ተከልላ በተሰጠችው ክልል፣ ያለውን ስልጣን የሚያጠናክርበት አካሄድ ነው የተፈጠረው፡፡ ፌደራሊዝሙን እንዳይሰራና ወደ አደገኛ ሁኔታ እንዲያመራ ያደረጉትም እነዚህ ጉዳዮች ይመስሉኛል፡፡
የክልሎች ጥንካሬ ከፌደራል መንግስቱ በልጧል ማለት እንችላለን?
በሚገባ በልጧል፡፡ እኔ ሳየው፣ የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም በአንድ ኃይል፣ ፈላጭ ቆራጭነት የሚመራ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ዘላቂነት አይኖረውም፡፡ በተለይ ማዕከሉ በሳሳ ቁጥር ክልሎቹ እየጠነከሩ መሄዳቸው የማይቀር ነው፡፡ እነዚህ የክልል መስተዳድሮች ስለ ሀገር እምብዛም አይጨነቁም፡፡ ዋነኛ ስራቸው በክልላቸው የፖለቲካ ምቾት ማደላደል ነው የሚሆነው፡፡ ለምሳሌ የሱማሌ ክልል፣ የሱማሌ ህዝብ ብቸኛ ጠበቃ በመምሰል በስልጣን ላይ ለመቆየት ይሞክራል፡፡ የኦሮሚያ ህዝብን ኦህአዴድ “ጠበቃህ እኔ ነኝ” ይላል፡፡ ህውኃት በበኩሉ፤ “ከኔ ውጪ ለትግራይ ህዝብ ጠበቃ የለም፤ ለመሬትህ ጠበቃ ነኝ” ይላል፡፡ ሁሉም “ላንተ ከኔ ውጪ ጠበቃ የለም” በሚል ስሜት፣ ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት፣ እነሱ በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚያደርጉት ጥረት ነው፡፡ አሁን ለግጭት መነሻ እየሆነ ያለው የድንበር ውዝግብም የዚሁ ነፀብራቅ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ክልል፣ እንዴት ድንበር አስምሮ ይጋጫል? ይሄ የሚያሳየው ክልሎች የራሳቸው ግዛት እየፈጠሩ መሄዳቸውን ነው። ዜጎች ሲፈናቀሉም የሌላ ክልል ተወላጅ በሀገሪቱ ተንቀሳቅሶ የመስራት እድሉን በዘላቂነት እያጠበበ ነው የሚሄደው፡፡ ይሄ አደገኛው አካሄድ ነው፡፡
በሌላ በኩል፣ እንዲህ ያሉ የውዝግብ መንገዶች፣ ሌሎች የፖለቲካ ጥያቄዎችን ማስቀየሻ ስልቶችም ናቸው፡፡ ችግሩን ፈጥረው የችግሩ ፈቺም ሆነው በመቅረብ አደገኛ ጨዋታ ውስጥ እየገቡ ነው ያሉት፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የክልሎች አካሄድ ከቀጠለ፣ ማዕከላዊ መንግስቱ መቀመጫ ላይኖረው ይችላል፡፡ ሀገር ሊፈርስ የሚችለውም በሌላ አይደለም፤ በእንዲህ ያለው አደገኛ አካሄድ ነው፡፡ በአጠቃላይ ባለፉት 25 ዓመታት፣ አገራዊ  አንድነትና ማንነት ቦታ አልተሰጠውም፤ ትኩረቱ ለአካባቢና ክልል ነው የሆነው፡፡
በፌደራል ሥርአቱ ላይ ተጋርጠዋል የሚሏቸው ዋና ዋና አደጋዎች ምንድን ናቸው?
የፌደራል ግቡ አንድ ኢትዮጵያ የሚባል ሀገር መፍጠር ከሆነ፣ የሚያስተሳስሩን እሴቶች አለመፈተሻቸውና በእነዚህ ላይ አለመሰራቱ ነው አንዱ፡፡ በሌላ በኩል፣ እነዚህን ግጭቶች፣ ህዝብ በባህላዊ ስርአቶች መፍታት እየቻለ እንዳይፈታ መደረጉ ሌላው አደጋ ነው፡፡ ልዩነቶች እየሰፉ እንዲሄዱ እየተደረገ መሆኑንም ያሳያል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አለመጠናከራቸው፣ የሲቪል ማህበረሰቡ፣ ሚዲያው ---ነፃነት አልባ መሆናቸው በጉልህ ካልታየ አደጋ ነው፡፡ በየጊዜው ጊዜያዊ አዋጅ ማስቀመጥም ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም፤ ቆም ብሎ ማሠብ፣ ነገሮችን ማጥናትና የህዝብን ፍላጎት ማድመጥ ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ ግን መንገዳችን አደገኛ ነው የሚሆነው፡፡
የድንበር ግጭቶች ዘላቂ መፍትሄ ካልተሰጣቸው፣ ለአገሪቱ ህልውና ምን ያህል አስጊ ናቸው ይላሉ?
አሁን ግጭቶቹ፣ ከድሮው መልካቸው እየተለወጠ ነው፡፡ ድሮ የግጦሽ፣ የውሃ ወዘተ-- ጉዳይ ሊሆን ይችላል። አሁን ግን የግጭቱ መንስኤ፣ በታጣቂዎች የተደገፈ፣ የክልል መንግስታት የተሳተፉበት መሆኑን እየሰማን ነው፡፡ ይሄ ወደ እርስበርስ ጦርነት እንዳይወስደን ነው መስጋት ያለብን፡፡ በእርግጥ ህዝቡ ይሄን የሚያከሽፍባቸው ይመስለኛል፡፡ ባጠመዱት ወጥመድ ውስጥ ይገባል የሚል እምነት የለኝም፡፡ በሌላ በኩል የሃገር ተቆርቋሪዎች ነን የምንል ሁሉ፣ የእርስ በእርስ መካረሩን አስወግደን፣ ከዚህ ወጥመዳቸው ማምለጥ አለብን፡፡ የዚህችን ሃገር ህልውና የማስጠበቅ ጉዳይ የህዝቡም ሃላፊነት ይመስለኛል፡፡ ህዝቡም ያደርገዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
እኔ እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ የሚታዩ ግጭቶች፣ ኢትዮጵያን ሊበታትኑ ይችላሉ የሚል ስጋት አልነበረኝም፡፡ አሁን ግን ነገሮች እየተቀየሩ ነው፡፡ ስጋት አለኝ፡፡ ምክንያቱም ፅንፍና ፅንፍ ከረገጡ አስተሳሰቦች መሃል ያለው መካከለኛ ሃሳብ ቦታ እያጣ መጥቷል፡፡ መካከለኛ ሃሳብ ሲታፈን ደግሞ ነጥሮ የሚወጣው ፅንፉ ነው፡፡ ይህን ነው ከፍተኛ ስጋት እየፈጠረብኝ ያለው፡፡ እውነተኛ ሚዲያዎችም ፈተና ላይ ናቸው፡፡ በዚህ መሃል በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉት ቦታ እያገኙ በመሆኑ አደገኛ ስጋት ደቅነዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን አሁንም ተስፋ አልቆርጥም፡፡
በአሁኑ አካሄድ ከቀጠልን የወደፊት ዕጣ ፈንታችን ምን ሊሆን ይችላል ብለው ይገምታሉ?
በ2008 ዓ.ም በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በትግራይ --- የህዝብ እንቅስቃሴ በርትቶ ነበር፡፡ ያኔ ኢህአዴግ እነዚህን ችግሮች ከተለያዩ አካላት ጋር መክሮበት፣ መፍትሄ ያበጃል የሚል ተስፋ ነበረኝ። ነገር ግን ይሄን አላደረገም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ፣ ከ40 አመት በፊት ወደነበርንበት ቦታ ነው የመለሰን። ይህ ሁኔታ በወቅቱ ተስፋ አስቆርጦኛል፡፡ አዋጁ በራሱም መፍትሄ አልሆነም፡፡ ለወደፊትም ቢሆን በኢህአዴግ በኩል የለውጥ ትንፋሾች አይሰሙም። የለውጥ ትንፋሽ ከሌለ ደግሞ ተስፋ አስቆራጭ ነው። ነገር ግን የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ሁሉ፣ በቅጡ አስቦበት ይሄን አደገኛ ሁኔታ ማስቆም አለበት፡፡ በሌላ በኩል፣ እንዲህ ያለው አጋጣሚ ለወታደራዊ መንግስት ወደ ሥልጣን መምጣት ምቹ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የባሰ ነው፡፡ በእርግጠኝነት ለወደፊት ምን ይሆናል የሚለውን ለመገመት ግን ይከብዳል፡፡
የፌደራል ሥርአቱ ዘመኑን ከግንዛቤ ውስጥ ባስገባ መልኩ ተጠንቶ፣ እንደገና መዋቀር አለበት፤ ብለው የሚሞግቱ ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በዋናነት መምጣት ያለበት የዲሞክራሲ ስርአት ነው፡፡ ይሄ እስከሌለ ድረስ ፌደራሊዝም እንደገና ቢዋቀር ባይዋቀር ለውጥ የለውም። ዋናው ህዝብ በነፃነት የሚወስንበት ስርአት አለመፈጠሩ ነው፤ የፌደራል አደረጃጀቱ ብቻ የችግሩ መንስኤ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ዋናው ችግር በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ መታፈኑ ነው፡፡
እንዲህ ያሉ ደም አፋሳሽ የድንበር ግጭቶችን  በዘላቂነት ለማስቆም ከመንግስት ምን ይጠበቃል?
እኔ አሁንም ጥሪ የማቀርበው ለህዝቡ ነው እንጂ ለመንግስት አይደለም፡፡ ህዝቡ፤ የክልል አመራሮች፣ ታጣቂዎችና ካድሬዎች የሚሰጡትን የግጭት አቅጣጫ ፈጽሞ መቀበል የለበትም፡፡ የቆየ የእርስ በእርስ ግንኙነቱን አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ችግሮች ቢፈጠሩ እንኳ ህዝቡ በገለልተኛ ሽማግሌዎች መፍትሄ ማምጣት ነው ያለበት፡፡ ፈፅሞ የፖለቲካ መጠቀሚያ መሆን የለበትም። ለተከሰቱት ግጭቶች ተጠያቂ መሆን ያለበት ደግሞ የወረዳ አመራሩ ሳይሆን አናቱ ላይ ያለው አመራር ነው። ከላይ ያለው አመራር ነው ለጥፋቱ ይቅርታ መጠየቅ ያለበት፡፡
 በሌላ አገር እኮ እንዲህ አይነት ችግር ሲያጋጥም ጠ/ሚኒስትሩ፤ “ከአቅሜ በላይ ነው” ብሎ ስልጣን ይለቃል። ፓርቲም ስልጣን የሚለቅበት ሁኔታ አለ፡፡ ለነገሩ በኛ ሀገር ለስልጣን ብቁ የሆነ ተተኪ ፓርቲም የለም፡፡ ነገር ግን ህዝቡ በተጠመደው ወጥመድ ውስጥ መግባት  የለበትም፡፡ ጥሪዬም ይኸው ነው፡፡  Read 3466 times