Monday, 25 September 2017 11:48

“ዲሞክራሲው ችግር ሲኖርበት ፌደራሊዝሙ ችግር ይኖርበታል”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

• ህገ መንግስቱ መብት ያረጋግጣል፤ በሌላ በኩል ፖለቲካው መብት ይነጥቃል
• ባህላዊ የግጭት አፈታት መንገዶችን ማሳደግና ማስፋፋት ያስፈልጋል
• የቴዲ አፍሮ “ኢንተርቪው” እንዳይተላለፍ መታገዱ ተገቢ አይደለም
• የማታ ማታ አገሪቱን ሊታደጋት የሚችለው ወጣቱ ትውልድ ነው


በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝም መምህር የነበሩት እና በሰላም ደህንነት የዶክትሬት ተማሪ የሆኑት የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ሃይል ዋና አዛዥ፣ ሜ/ጀነራል አበበ ተ/ሃይማኖት፤ በሰሞኑ የኢትዮጵያ ሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎች የድንበር ግጭት፣በፌደራሊዝም ሥርአቱና አተገባበሩ እንዲሁም በኢትዮጵያዊነትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡
ፖለቲካዊ ችግሮች የሚፈቱት በፖለቲካዊ ውይይቶች ብቻ ነው፡፡

   የፌደራል ስርአቱ ባለፉት 25 ዓመታት የሀገሪቱን አንድነት በማስጠበቅም ሆነ አንድነቱን በማጠናከር በኩል አስተዋጽኦው ምን ያህል ነበር?
ይሄን ጉዳይ በሁለት መልኩ ማየቱ ጠቃሚ ነው። አንደኛው ህገ መንግስቱ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ፖለቲካው ነው፡፡ በኔ አመለካከት፣ ህገ መንግስቱ የኢትዮጵያን አንድነት ከማናቸውም ጊዜ የበለጠ ያጠናክራል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እስካሁን ድረስ የተገኘው አንፃራዊ ሰላምም የመጣው በተወሰነ ደረጃ ህገ መንግስቱን ተግባራዊ ማድረግ ስለተቻለ ነው፡፡ የኛ ህገ መንግስት ዘመናዊ ሊባል የሚችል፣ አለማቀፋዊ መብቶችን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ነገር ግን ፖለቲካው የፌደራሊዝም ፅንሰ ሀሳቡን መሰረት አድርጎ እየሰራ አይደለም፡፡ ህገ መንግስቱን በሚፃረር መልኩ እየሄደ ነው፡፡ ስለዚህ ችግሩ ፌደራላዊ ስርአቱ ላይ ሳይሆን ስርአቱን ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ላይ ነው፡፡ በአንድ በኩል፣ ህገ መንግስቱ መብት ይሰጣል፤ በሌላ በኩል ፖለቲካው መብቱን ይነጥቃል፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ይህ ነው፡፡
መሰረታዊ ችግሮችም የሚመነጩት ከዚሁ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያዊ ነን የማይሉ ብሄር ብሄረሰቦች ኢትዮጵያውያን ነን ማለት የጀመሩበትን ሁኔታ የፈጠረው የፌደራል ስርአቱ ነው፡፡ የፌደራል ስርአት ካለ ዲሞክራሲ የሚመራ አይደለም፡፡ ማዕከሉ ዲሞክራሲ ነው፡፡ ዲሞክራሲ ደግሞ የግለሰብ መብትና የቡድን መብት ነው። የፌደራል ስርአት ሲሆን ደግሞ መሰረቱ፣ራስን በራስ የማስተዳደርና የጋራ አስተዳደር ነው፡፡ ይህን ሁለቱን የሚያያይዘው ደግሞ ዲሞክራሲ ነው፡፡ ዲሞክራሲው ችግር ሲኖርበት፣ ፌደራሊዝሙ ችግር ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ የፌደራል ስርአቱ አወቃቀር ሳይሆን ዋናው ችግሩ የዲሞክራሲ እጥረት ነው፡፡ በእርግጥ ሙሉ ለሙሉ የተሟላ የፌደራል ስርአት በዓለም ላይ የለም፡፡ ህገ መንግስቱ ወይም ፌደራል ስርአቱና ፖለቲካው ተጣጥመው አብረው መሄድ ከጀመሩ በኔ አመለካከት፣ የኢትዮጵያ አንድነት የበለጠ እየተጠናከረ ይሄዳል፡፡ ምክንያቱም ማናቸውም ብሔርና ብሔረሰብ ሊጠቀሙ የሚችሉት እኩልነትን ማዕከል ካደረገው የኢትዮጵያ አንድነት ነው፡፡ አንድነቱ ልዩነቱንም ማስተናገድ ሲችል፣ ኢትዮጵያዊ አንድነቱ የበለጠ ሊጠነክር ይችላል፡፡ ግን ፖለቲካው ላይ በዋናነት የዲሞክራሲ እጥረት ስላለ ስርአቱ በከፍተኛ ውጥረት ላይ ይገኛል ማለት ይቻላል፡፡
የዲሞክራሲ እጥረት ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ እርስዎ የዲሞክራሲ እጥረት ሲሉ ምን ማለትዎ ነው? መገለጫዎቹ  ምንድን ናቸው?
ይሄን ህገ መንግስት ከቀደሙት የኢትዮጵያ ህገ መንግስቶች ለየት የሚያደርገው ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ምንድን ናቸው? ብሎ በግልፅ ማስቀመጡ ነው፡፡ በዋናነት ደግሞ አለማቀፍ ስምምነቶችን፣ ተቀባይነት ያላቸው የመብት ጉዳዮችንም አስቀምጧል፡፡ ዲሞክራሲ ሲባል የመላ ኢትዮጵያ ህዝብ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብትን ማስጠበቅ ማለት ነው፡፡ አዲስ አበባ ወይም ዋና ዋና ከተሞች የሚደረግ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን በወረዳና በቀበሌ ያለውም ህዝብ የፈለገውን አስተሳሰብ እንዲይዝ፣ እንዲያራምድ፣ በፈለገው መንገድ እንዲተዳደር፣ የፈለገውን ፖለቲካ እንዲያካሂድ እንዲሁም ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳይን በተመለከተም ማህበረሰቡ በፈለገው መንገድ እንዲያራምድ ነፃነት መስጠት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ገበሬው ማዳበሪያ በግድ ውሰድ ይባላል፤ “አልወስድም፣ ሌላ አይነት ማዳበሪያ እጠቀማለሁ” ካለ፣ ቅጣት ይጣልበታል ወይም ጥቅሞች እንዳያገኝ ይደረጋል፡፡ ዲሞክራሲ እነዚህን መብቶች ከማረጋገጥ ይመነጫል፡፡
 ህገ መንግስቱ መጀመሪያ መብቶችን ነው የሚያስቀምጠው፡፡ መንግስት የሚቋቋመውም እነዚህን መብቶች ለማስጠበቅ ነው መሆን ያለበት። መንግስት ሌላ አላማ አይኖረውም፡፡ በህገ መንግስቱ ያሉ መብቶች፣ በሁለት መንገድ ነው የሚታዩት። በመጀመሪያው መንግስት በህብረተሰቡ ላይ ጫና እንዳያደርግ የሚከለክሉት ድንጋጌዎች አሉ። ሁለተኛው ደግሞ መንግስት ጣልቃ ገብቶ የህብረተሰቡን መብት እንዲያስከብር የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡- ንፁህ ውሃ የማግኘት፣ ንፁህ አካባቢ የመኖር፣ የመልማት መብት--- የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ህገ መንግስቱ፣ እነዚህን መብቶች ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው፡፡ ጥያቄው ግን እነዚህ መብቶች በተግባር እየተረጋገጡ ነው ወይ? የሚለው ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው በነፃነት መናገር፣ መፃፍ ይችላል ወይ የሚለው ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አሁን ያለንበት ሁኔታ አፋኝ ተብሎ የሚገለፅ ነው፡፡
የፌደራል ስርአቱ ዋነኛ መሰረቱን ብሄር ላይ ማድረጉ ለሩብ ክፍለ ዘመን በበርካቶች ዘንድ ጥያቄ ሲቀርብበት የዘለቀ ነው፡፡ እርስዎ በዚህ አወቃቀር ላይ ያለዎት  አቋም ምንድን ነው? የግጭቶች መነሻ ነው ብለው ያስባሉ?
በመሰረቱ አንድን ስርአት ሙሉ ለሙሉ እንከን አልባ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች፣ ጂኦግራፊያዊም ሆነ ብሄር ተኮር ፌደራሊዝም፣ በሁለቱም ግጭቶች መኖራቸው አይቀርም፡፡ የግጭቶቹ መልክ ነው የሚቀየረው እንጂ ይኖራሉ፡፡ ምናልባት አንደኛው ግጭቶችን በቀላሉ ለመፍታት አመቺ ሊሆን ይችላል፤ ሌላኛው ደግሞ ግጭቶችን ሊያጠናክር ይችል ይሆናል፡፡ ግን ግጭት በሁለቱም ይኖራል፡፡ መታየት ያለበት ግጭቱ ምን ድረስ ነው የሚሰፋው የሚለው ነው። አሁን ያሉትን ግጭቶች ማየታችን ግን ያሳዝናል፡፡
ይሄን ከቅድመ 1983 ዓ.ም በፊት ካለው የሀገሪቱ ሁኔታ አንፃርም መመልከት አለብን፡፡ ከግንቦት 83 በፊት በርካታ የታጠቁ ቡድኖች ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ሶማሊያ ትሆናለች የሚል ስጋት ነበር፡፡ “ይህቺ ሀገር የነፃ አውጪ ድርጅቶች ሀገር ሆናለች” እስከመባል ደርሳ ነበር በወቅቱ፡፡ አሁን ፌደራል ስርአቱ ከተዋቀረ በኋላ ግን ሀገሪቷን ሊበታትናትና ሊያተራምስ የሚችል የትጥቅ ግጭት ሁኔታ ተቀይሯል፡፡ አሁን ያለው መከላከያ ሃይል ጠንካራ በመሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ሜዳ ላይ ታጣቂዎች እንደፈለጉ የማይሆኑት ህብረተሰቡ የተቀበለው ስርአት ስለሆነ ነው፡፡ አሁን ችግሩ ያለው ስርአቱ በሚፈለገው መንገድ አለመሄዱ ላይ ነው፡፡ ግጭቶቹንም የሚፈጥረው ይሄው ነው። ፖለቲካዊ ስርአቱ ሲበላሽና ፖለቲካዊ ሙስና ሲስፋፋ፣ ሙሰኞች በብሔራቸው ላይ ተሸፍነው ለማለፍ ሲሉ፣ የብሔር ግጭቶች ይፈጥራሉ፡፡ አሁን ያለው ግጭት የተከሰተው ፖለቲካዊ ስርአቱ በመበላሸቱ ነው እንጂ ብሔር ተኮር ፌደራሊዝም በመሆኑ አይደለም፡፡ መጀመርያ ላይ የህገ መንግስቱ አቀንቃኝ ኢህአዴግ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ግን “ህገ መንግስቱ ይከበር” እያለ የሚጮኸው ተቃዋሚው ሆኗል፡፡ ሰው ለመብቱ በሚታገልበት ጊዜ ደግሞ ወደ ግጭት ሊሄድ ይችላል፡፡ ይሄ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡
በተለይ ከ5 ዓመት ወዲህ በድንበር ውዝግቦች፣ በማንነት ጥያቄዎች ወዘተ --- ሰበብ በሚፈጠሩ ግጭቶች፣ ዜጎች ለሞትና ለአካል ጉዳት እየተዳረጉ ሲሆን የማህበራዊ ኑሮ መናጋትም እየተፈጠረ ነው።
በመጀመሪያ ላይ ህብረተሰቡ ብሄር ተኮር በነበረው ስርአት የመርካት ሁኔታ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ጊዜው እየተለወጠ ሲሄድ ብዙ ነገር እየፈለገ ይመጣል፡፡ የህብረተሰቡ ፍላጎት መልኩን እየቀየረ ሲያድግ ፖለቲካው ደግሞ ይሄን ፍላጎት የሚያስተናግድበትን አቅም ማዳበር አልቻም፡፡ ህብረተሰቡ አደገ፣ ብዙ መብቶችን ያውቃል፡፡ አሁን አዲስ ያወቃቸው መብቶቹም እንዲረጋገጡለት ጥያቄ እያቀረበ ነው፡፡ ይሄን የህዝቡን ፍላጎትና ጥያቄ ደግሞ ለጊዜ መግዣ ይጠቀሙበታል፡፡ ለምሳሌ፡- የወልቃይትን ጉዳይ ስንመለከት፣ መፍትሄው አጭርና ግልፅ ነው፡፡ “ወልቃይት የትግራይ ነው ወይስ የአማራ ክልል ነው?” የሚለውን የሚወስነው የወልቃይት ህዝብ ራሱ ነው፡፡ ህዝበ ውሳኔ እንደማካሄድ ይሄን ጥያቄ ማንከባለል ነው የተፈለገው፡፡ የአማራ ክልል፤ “ድሮ በጎንደር አስተዳደር ስር ስለነበረ የሚወሰነው በአማራ ክልል ነው” ሲል የትግራይ ደግሞ፤ “አሁን በትግራይ ስር ስላለ የሚወሰነው በትግራይ ክልል ነው” ይላል። እነዚህ ሁለቱም ከህገ መንግስቱ ውጪ ናቸው። ወሳኙ የወልቃይት ህዝብ ነው፡፡ የፌዴሬሽን ም/ቤት እንኳ በወልቃይት ጉዳይ የመወሰን ስልጣን የለውም፡፡ ፌዴሬሽን ም/ቤት፣ የህዝበ ውሳኔውን ሂደት ማመቻቸት ነው የሚጠበቅበት፡፡ ልክ የስልጤ ህዝብ ፍላጎት በህዝበ ውሳኔ እንደተረጋገጠው፣ የወልቃይት ህዝብ ፍላጎትም በህዝበ ውሳኔው ነው መመለስ ያለበት፡፡ በአጠቃላይ ህብረተሰቡ ፍላጎቱ ሲያድግ ስርአቱ ለፍላጎቱ መጣኝ እድገት አለማምጣቱ ነው ተቃርኖ የፈጠረው፡፡ የፌደራል ስርአት ከግጭት ነፃ ነው ማለት ግን አይቻልም። በአሜሪካም ቢሆን የነጮች የበላይነት ለመያዝ በሚደረግ ትግል ዛሬም ችግሩ ቀጥሏል፡፡ የኛ ደግሞ ገና ጅምር  እንደመሆኑ፣ ብዙ ውጣ ውረዶች ማለፍ ይጠበቅብናል፡፡
የፌደራል ስርአቱ ቀጣይ ተግዳሮቶች  ምንድን ናቸው ይላሉ?
አንደኛው “ቆሞ ቀር” ኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ነው፡፡ ከ3 ሺህ ዓመት በፊት ወይም ከ100 እና 200 ዓመት በፊት የነበረ ኢትዮጵያዊነት፤ በአፄ ቴዎድሮስ፣ በአፄ ዮሐንስ ወይም በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የነበረ ኢትዮጵያዊነት እና አሁን ያለውን ኢትዮጵያዊነት ተመሳሳይ አድርጎ የማሰብ ጉዳይ  አንዱ ተግዳሮት ነው፡፡ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የኢትዮጵያዊነት ዋና መለኪያ፣ ከቅኝ አገዛዝ ነፃነትን ጠብቆ መኖር መቻል ነው፡፡ ምክንያቱም ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች በቅኝ አገዛዝ ስር ነበሩ፡፡ አሁን ሁሉም ነፃ በሆኑበት፣ ህብረተሰቡ ልማትና ዲሞክራሲ ሲጠይቅ፣ ኢትዮጵያዊነት በልማትና ዲሞክራሲ ይተረጎማል። መሰረቱ የድሮ ኢትዮጵያዊነት ሆኖ፣ አሁን የሚፈለገው ኢትዮጵያዊነት፣ ልማትና ዲሞክራሲን ያረጋገጠ መሆን አለበት፡፡
በዘመነ መሳፍንት ወይም በአፄ ኃይለሥላሴ የነበረው ኢትዮጵያዊነት፣ አሁን ካለው ጋር አንድ ይሁን ከተባለ “ቆሞ ቀር” መሆን ነው፡፡ ኢትዮጵያውነት እያደገ፣ እያበበ፣ እያሸበረቀ የሚሄድ ነገር ነው፡፡ በምስራቅና በምዕራብ፣ በደቡብ ወይም በሰሜን አሊያም በመሃል ያለው ኢትዮጵያዊነት ትርጉም ሊለያይ ይችላል፡፡ ይሄ ተፈጥሮአዊ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊነት የምንለው ስም ብዙ ድሎች ያገኘንበት እንደመሆኑ ሁሉ ብዙ ግፍም የተፈፀመበት ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊነትን ስናስብ በተለያየ አመለካከት ነው፡፡ ነገር ግን ፈፅሞ “ቆሞ ቀር” መሆን የለበትም፡፡ ኢትዮጵያዊነት በሙዚየም የሚቀመጥ ነገር አይደለም፤ ከህብረተሰቡ ጋር ተሳስሮ የሚቀጥል ነው፡፡ ስለዚህ ዋነኞቹ ተግዳሮቶች፣ ጠቅላይና ቆሞ ቀር ኢትዮጵያዊነት አመለካከትና “ለብሔሬ ቆሜያለሁ” የሚለው አመለካከት ነው፡፡
እነዚህ አመለካከቶች በነፃነት ለውይይት ቀርበው፣ የሚጠቅመን ነጥሮ መውጣት አለበት። ለምሳሌ የቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) “ኢትዮጵያዊነት” አለ፡፡ በመሰረቱ እኔ ቴዲ አፍሮን አደንቀዋለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ ሙዚቃውን እሰማለሁ፡፡ በእሱ “ኢትዮጵያዊነት” አገላለፅ ላይ የምስማማበትም የማልስማማበትም ጉዳይ አለ። አንድ አርቲስት 600 ሺህ አልበም ሲሸጥ ሃሳቡን የሚከተል ህዝብ አለ ማለት ነው፡፡ ሰው አማራጭ ሃሳቦችን የመስማት፣ የማራመድ መብት አለው። ይሄ አማራጭ መታፈን የለበትም፡፡ ሆኖም የቴዲ አፍሮ ኢንተርቪው፣ በኢቢሲ እንዳይተላለፍ ተደርጓል፡፡ ይሄ ለኔ ሞኝነትም ድንቁርናም ነው። ልጁ ኢንተርቪው በሚደረግበት ጊዜ ለእነሱም ይጠቅማቸው ነበር፡፡  እስኪ ምን ይላል ብሎ ሰው ያያል፡፡ ከዚያ በኋላ በሀሳቡ ላይ ሰፊ ውይይት ሊደረግ ይችል ነበር፡፡ ይሄን ጥቅም አለማወቅና ማፈን ተገቢ አይደለም፡፡ ፖለቲካው የአግላዮች (ብሔርተኞች) እና ጠቅላይ ፅንፍ ብቻ የሆነው እንዲህ ያሉ የሀሳብ መንሸራሸሮች ስላልተፈጠሩና እንዲፈጠሩ ስላልተፈለገ ነው፡፡
ለሰፊ ውይይት ሊቀርቡ ከሚችሉ ሌሎች ጉዳዮች መካከል፣ “የኦሮሞ በፌደራል ያለው የውክልና መጠን”፣ “የትግራይ የበላይነት አለ” የመባሉ ጉዳይ የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ለህዝብ ውይይት መቅረብ አለባቸው። ውስጥ ለውስጥ የሚሄድ ጉዳይ መዘዙ ጥሩ አይሆንም፡፡ ህብረተሰቡ የሚበጀውንም መወሰን የሚችለው አማራጮቹን በግልፅ ሲረዳ ነው። ይሄ እንዳይሆን ያገደው ደግሞ የዲሞክራሲ እጥረቱ ነው። በሌላ በኩል ህዝቡ የፈለገውን አደረጃጀት መምረጥ እንዲችል አለመደረጉ ነው። እነዚህ ተግዳሮቶች ምናልባት የፌደራል ስርአት ሽግግሩ አንድ አካል መሆን ይችላል፡፡ ለወደፊትም የግለሰቦች፣ የህዝቦች፣ የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ እያደገ ይሄዳል፡፡ ከዚህ ጋር የተመጣጠነ እድገት ሊኖረው የሚችል ፖለቲካዊ ስርአት ያስፈልጋል፡፡ አሁን ግን ተቃዋሚዎችም ገዥው ፓርቲም ከዚህ ጋር የሚመጣጠን ፖለቲካ የላቸውም፡፡
አሁን የሚታዩት ግጭቶች ዘላቂ መፍትሄ ካልተገኘላቸው ወደመበታተን እንዳናመራ የሚሰጉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎስ ይሄን ስጋት  ይጋሩታል?
እነዚህ ግጭቶች በራሳቸው የትም አይደርሱም። በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ ነገሮች ናቸው፡፡ የዚህችን ሀገር ህልውና አደጋ ውስጥ ሊጥል የሚችለው በአጠቃላይ በፖለቲካዊ ስርአቱ ላይ ያለው ችግር ነው፡፡ ፖለቲካዊ ስርአቱ ሙሰኛ ሆኗል። ስርአቱ ካልተስተካከለ፣ ይህቺ ሀገር ስጋት ላይ ናት፤ ከተስተካከለ ግን የሚያሳዝን ጥፋት የደረሰ ቢሆንም ስጋት አይኖርም፡፡ እንደ‘ኔ አመለካከት፤ “የዲሞክራሲው ትውልድ” የምለው፣ ስልጣን ከ”ነፃ አውጪው” ላይ እስካልተረከበ ድረስ አደጋው አለ። ዲሞክራሲው እየሰፋ በሄደ ቁጥር ግን የመበታተን ስጋቱ እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ አሁን በዋናነት ቅራኔው ያለው ዲሞክራቲክ በሆነው ህገ መንግስትና ሙሰኛ በሆነው የፖለቲካ ስርአት መካከል ነው፡፡ በዚህ መሃል ደግሞ ህዝቦች መብታችን ይረጋገጥልን ይላሉ፡፡ ስለዚህ ህገ መንግስቱ፣ ፖለቲካዊ ስርአቱና የህዝቡ ፍላጎት የሚጣጣምበት ሁኔታ ካልተፈጠረ አደጋው አለ፡፡ ዋናው አደጋ፣ ህገ መንግስቱ የሚፈቅደውን መብት የሚጠይቅ ማህበረሰብና መብቱን የሚከለክለው ፖለቲካዊ ስርአት መካከል ያለው ተቃርኖ ነው፡፡ ፌደራሊዝም ከግጭት ነፃ አይደለም፡፡ ስለዚህ ዋናው መዳበር ያለበት፣ግጭት የሚፈታበትና በህዝብ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥበት መንገድ ነው፡፡
በሰሞነኛው የድንበር ግጭት የክልል መንግስታት ቃል አቀባዮች፣ እርስ በእርስ መወነጃጀል ደረጃ መድረሳቸው ምን ያመለክታል? ኢህአዴግ በግንባር ደረጃ ላይ መቀጠሉስ ጥንካሬውን አሳጥቶ ለመበታተን አደጋ አይጋለጥም?
የአደረጃጀትን ጉዳይ ስናነሳ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የአንድነት ሃይሉ (ህብረብሄራዊ) በአንድ ጎን፣ ቅንጅትና ግንባር በአንድ ጎን ያለ ነው፡፡ ይሄ ለብዙ ጊዜም ይቀጥላል። ዋናው መነሳት ያለበት ጉዳይ ህብረተሰቡን የበለጠ የትኛው አደረጃጀት ነው የሚያስተሳስረው የሚለው ነው፡፡ አሁን ባለው የሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ብዙ ማንነሮች አሉ። ከነዚህ ውስጥ የብሔር እና ኢትዮጵያዊነት ማንነት ወሳኝ ናቸው።  አብረው የሚጓዙ ነገር ግን የየራሳቸው ተነፃፃሪ ነጻነት ያላቸው ናቸው ።  ዋናው ጉዳይ ህዝቡን የበለጠ የሚያንቀሳቅሰው የትኛው ነው የሚለው ነው፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ የብሄር ማንነት ነው፡፡ ይሄ እኛ ጋ ብቻ አይደለም። ስፔን- ከታሎኒያ የተነሣው ጉዳይ የዚህ ነፀብራቅ ነው። በኛ ሃገር ሁኔታ እንደምናየው፣ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲዎች እየከሰሙ ነው የሄዱት፡፡ ይሄ የተአምር ጉዳይ ወይም እንደሚባለው የህውሃት ተፅዕኖ ብቻ አይደለም፡፡ ትልቁ ችግር የበለጠ ህዝብን ማንቀሳቀስ የሚያስችለው የትኛው ማንነት ነው የሚለውን አለመረዳት ነው፡፡ የኢህአዴግ ድርጅቶች የእርስ በእርስ መወነጃጀል ደግሞ የተጋረጡ ችግሮችን ለማስቀየሻነት ከሚደረግ ጥረት የሚመነጭ ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን የብሄር ማንነቱን ከኢትዮጵያዊ ማንነት ጋር አጣምሮ የመሄድ ጉዳይ መታሠብ አለበት። አንድነት የመጣው ልዩነት ስላለ ነው፡፡ ልዩነት ሲኖር ነው ስለ አንድነት መነጋገር የምንችለው፡፡ ትልቁ ብልሃት እነዚህን አጣምሮ የመሄዱ ጉዳይ ነው፡፡ በአንድ ጎን በህዝብ ቅቡልነት የሌለው ገዥ ፓርቲ ሲኖር፣በሌላ ጎን በህብረተሰቡ ውስጥ ቅቡልነት አግኝተው መዋኘት ያልቻሉ ተቃዋሚዎች አሉ፡፡ አሁን ያለነው በዚህ የፖለቲካ ድባብ ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ ክፍተት አለ ማለት ነው፡፡ ይሄ ክፍተት እንዴት ነው የሚሞላው የሚለው በኋላ ነው የሚታየው፡፡
ግጭቶች በሚከሰቱ ወቅት ምን አይነት የችግር አፈታት ዘይቤ መጠቀም ነው የሚገባው?
በፖለቲካዊ መሠረቱ ጠንካራ የሆነ ሥርዓት እስከሌለ ድረስ ስልታዊ የሆኑ ችግሮች አይፈቱም፤ ስለዚህ ስርአቱ መቀየር አለበት፡፡ ዲሞክራሲያዊ መሆን አለበት፡፡ በሌላ በኩል የግጭት አፈታት ስልት መንደፍ ያስፈልጋል፡፡ አስቀድሞ ግጭቶችን መተንበይና ማጥናት፣ መፍትሄውንም ማስቀመጥ ይገባል፡፡ ከዚያ በመለስ ችግሮችን በፍጥነት አይቶ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል። ይሄ እንዲሆን ግን ፖለቲካዊ ስርአቱ ዲሞክራሲያዊ መሆን አለበት፡፡ በሌላ በኩል ባህላዊ የግጭት አፈታት መንገዶችን፤ ለምሳሌ፡- የሶማሌ እና የኦሮሞ ህዝብ የራሱ የግጭት አፈታት ባህል አለው፡፡ ይሄን ማስፋፋትና ማሳደግ አንዱ አማራጭ ነው፡፡ ሌላው ግጭቶች ሲያጋጥሙ መጥፎውን ብቻ ሳይሆን በጎ ገፅታችንንም ማሳያት ተገቢ ነው፡፡ ለምሳሌ በጎንደር፡- የትግራይ ተወላጆች ሲፈናቀሉ፣”ወንድሞቼ ናችሁ” ብሎ ከጥቃት የተከላከላቸው የጎንደር ሰው አለ፡፡ ይሄ አዎንታዊ እሴት ነው፡፡ እነዚህ እሴቶች ተጠንተው፣ መጎልበት አለባቸው፡፡
የማታ ማታ ከዚህ ሁሉ ምስቅልቅል አገሪቱን የሚታደጋት ማነው ?
በአንድ በኩል ወጣቱ ትውልድ፣ በተለይ ምሁሩ፣ ያሉትን የፖለቲካ ድርጅቶች ቀይሮ ወይም ሌላ ድርጅት ፈጥሮ ይህቺን አገር ሊታደግ ይችላል። እኔ በጎ የምለው ይሄኛውን ነው፡፡ ይሄ ህዝብ ብዙ የመንግስት ለውጦችን አስተናግዶ፣ የሀገር አንድነትን አስጠብቆ ኖሯል፡፡ ይሄ ለወደፊትም ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ችግሮች በተገቢው መንገድ ካልተፈቱና ምላሽ ማግኘት ካልቻሉ፣ የ2008 አይነቱ ግርግር፣በድጋሚ ከፍቶ ሊመጣ ይችላል፡፡ ስለዚህ መጠንቀቅ የግድ ይላል፡፡     

Read 3013 times