Monday, 25 September 2017 11:57

አዲሱ የባህል ፖሊሲ ምን ይላል?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

የባህል ኢንዱስትሪ መንደሮች ይቋቋማሉ ተብሏል
ደ.ኮሪያና ቻይና የባህል ማዕከላቸውን ሊከፍቱ አቅደዋል


    በዓለም ላይ ከባንክና ኢንሹራንስ፣ ከመድኃኒትና የህክምና ቁሳቁሶች እንዲሁም ከቱሪዝም በመቀጠል አምስተኛው ግዙፍ የኢንቨስትመንት ዘርፍ፣ የባህል ኢንዱስትሪ መሆኑን የዓለም ባንክ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ የማህበረሰቡን ባህላዊ እሴቶች ወደ ኢንዱስትሪ ለውጦ የገቢ ምንጭ በማድረግ ረገድ አሜሪካ፣ ቻይና፣ አውስትራሊያ፣ ሜክሲኮ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡  ከአፍሪካ ደግሞ ሞሮኮና ጋና ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡
አሜሪካ የባህል መገልገያ ቁሳቁሶችን ወደ ኢንዱስትሪ ቀይራ ለዓለም ገበያ በማቅረብ፣ 55 በመቶ የዓለም ገበያ ድርሻ አላት፡፡ ቻይና በበኩሏ፤ ማህበረሰቡ ከቀርከሃ ተክል ጋር ያለውን የፋብሪካውን የኑሮ መስተጋብር ባህል ወደተለያዩ የኢንዱስትሪ አይነቶች በመቀየር፣54 በመቶ የዓለምን የቀርከሃ ውጤቶች ግብይት ተቆጣጥራለች፡፡ ቀርከሃ ለቻይናውያን ለአልባሳት፣ ለቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች፣ ለጌጣጌጥ፣ … ወዘተ መሥሪያነት እንደ ዋነኛ ግብአት የሚያገለግል ነው፡፡ ቻይና በሌላ በኩል፤የወለል ምንጣፍ ስራ ባህልን ወደ ንግድ ኢንዱስትሪ በመቀየርም፣73 በመቶ የዓለም የምንጣፍ ገበያን ልትቆጣጠር ችላለች፡፡
ሜክሲኮ የባህል እሴቶቿን ወደ ኢንዱስትሪነት ቀይራ፣ ወደ ዓለም ገበያ በመላክ፣ ከአማካይ አመታዊ ገቢዋ 6 በመቶ ድርሻ እንዲኖረው አድርጋለች፡፡ ጀርመንና እንግሊዝ ከኢንዱስትሪው በየዓመቱ በአማካይ ከ7 እስከ 20 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከአፍሪካ ሀገራት በዚህ ረገድ ተጠቃሽ የምትሆነው ሞሮኮ፤ የተለያዩ የማህበረሰቡን ባህላዊ መገልገያ ቁሳቁሶች፣ ወደ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ምርት በመለወጥ፣ ከዓመታዊ ገቢዋ 15 በመቶ ያህሉን ማግኘት ችላለች። ጋናም እንዲሁ በተለይ ባህላዊ አልባሳትን ወደ ዘመናዊ  ኢንዱስትሪ በመቀየር ዋነኛ ተጠቃሚ አፍሪካዊ ሀገር ነች፡፡
በአንፃሩ በርካታ ባህላዊ አልባሳት፣ ምግቦች፣ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች ያላትና “የባህል ሀብታም” እንደሆነች የሚነገርላት ሀገራችን፤ባህላዊ እሴቶቿን ወደ ኢንዱስትሪ ለውጦ ተጠቃሚ በመሆን ረገድ በእጅጉ ወደ ኋላ የቀረች ናት ተብሏል - ሰሞኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ባዘጋጀው አዲሱ የባህል ፖሊሲ ላይ በተደረገ ውይይት። የአገራችን ማህበረሰብ የባህላዊ እሴቶች ባለፀጋ መሆኑ በስፋት ይታወቃል፡፡ በጥቂቱም ቢሆን በተበታተነ ሁኔታ፣ በባህላዊ ቁሳቁስነት ለቱሪስቶች በስጦታ እቃነት የምትሸጠው፣ከአጠቃላይ ዓመታዊ ገቢዋ አንድ በመቶ እንደሟይሞላ በውይይቱ ላይ ተገልጿል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተዘጋጀው አዲሱ የባህል ፖሊሲ፣ በዋናነት የባህል ኢንዱስትሪዎች ማስፋፋት ላይ የሚያተኩር  ሲሆን  በባህል ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚካተቱትን ባህላዊ ሀብቶች ስርጭት የመለየትና የማጥናት ስትራቴጂ ተቀምጧል፡፡  የባህል ኢንዱስትሪዎችን ለሚያቋቁሙ ባለሀብቶችም የኢንቨስትመንት ማበረታቻ እንደሚደረግና የገበያ ትስስር እንደሚፈጠርላቸውም የፖሊሲው ሰነድ  ይጠቅሳል። ሀገሪቱ ከዘርፉ ሰፊ ገቢ ለማግኘት እንድትችልም የባህል ኢንዱስትሪ መንደሮች ይመሰረታሉ፤ የባህል ምርቶችና አገልግሎቶች ሀገራዊ ባለቤትነትን ማስጠበቅና ማረጋገጥ የሚያስችል መለያ እንዲኖራቸውም ይደረጋል - ይላል ፖሊሲው፡፡
በተለያዩ ታሪካዊ አጋጣሚዎችና መንገዶች ከሀገር የወጡ ቅርሶች እንዲመለሱ ጥረት እንደሚደረግ የሚጠቁመው የባህል ፖሊሲው፤ የከተማ ልማትና የስነ ህንፃ ስራዎች የሀገሪቱን ባህላዊ ቅርሶችና ትውፊቶች የሚያንጸባርቁ ይሆናሉ ይላል፡፡ ባህላዊ እሴቶቻችንንና አገር በቀል እውቀቶችን በተመለከተም፣ በተለይ የሃገሪቱ መልአከ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የህብረተሰቡ የአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ባህሎች (ለምሳሌ፡- ገዳማትና ቤተክርስቲያናት አካባቢ ያለው የደን ሃብት ጥበቃ) ተጠንተው፣ የሃገሪቱ ይፋዊ ባህላዊ መገለጫ እንደሆኑ ይደረጋል ይላል- ፖሊሲው፡፡
አርሶ እና አርብቶ አደሩ፤ ስለ አዝርዕትና ምርት እንዲሁም ስለ እንስሳት እርባታ ያለው ባህላዊ ልምድ እንደሚጠና የሚጠቁመው ፖሊሲው፤ ባህላዊ የመድሃኒት ቅመማና አገልግሎትም ተጠንቶ እውቅና እንደሚሰጣቸው ይገልጻል፡፡ አዲሱ የባህል ፖሊሲ በተጨማሪም፣ በተለያዩ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ያሉ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችና ዕውቀቶች፣ የእርቅና የሸምግልና ሥርአቶች በጥናት እንደሚለዩና ከዘመናዊ የግጭት አፈታት ስልት ጋር ተቀናጅተው አገልግሎት ላይ እንዲውሉም  አቅጣጫ ያስቀምጣል፡፡
እንደ “እቁብ” የመሣሠሉ የቁጠባ ባህልን የሚያዳብሩ ባህላዊ እሴቶች ይበረታታሉ ድጋፍም ይደረግላቸዋል የሚለው ፖሊሲው፤ ሌሎች ትውፊታዊ የባህል ተቋማትም እንዲጠናከሩ ይደረጋል ብሏል፡፡ የምሽት የመዝናኛ ቦታዎችና የባህል ተቋማት፣ የሃገሪቱን ባህላዊ እሴቶችና መልካም ገፅታዎች የጠበቁ እንዲሆኑ እንደሚደረግ፤ የንባብ ባህልን ለማሳደግም የንባብ ቤቶች፣ ቤተመፃህፍት በግለሰብ ደረጃም ጭምር እንዲከፈቱ ማበረታቻ ይሰጣል ተብሏል፡፡ ኤምባሲዎች በባህል ዲፕሎማሲ አዳዲስ አሠራሮችን እንዲዘረጉ አቅጣጫ የሚያስቀምጠው ፖሊሲው፤ የኢትዮጵያ የባህል ማዕከላትንም በተመረጡ ሃገራት ለማቋቋም እቅድ መኖሩን ይጠቁማል፡፡ በባህል ልውውጥ ረገድ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ የባህል ማዕከላቸውን የከፈቱት ሩሲያ፣ ጀርመን፣ እንግሊዝ፣ ጣሊያንና ፈረንሳይ ሲሆኑ የደቡብ ኮርያና የቻይና መንግስትም የባህል ማዕከሎቻቸውን የመክፈት ጥያቄ ማቅረባቸው ተመልክቷል፡፡  
በተመሳሳይ የፊልም፣ የሙዚቃ፣ የመፅሐፍ ፖሊሲዎችም እየተዘጋጁ መሆኑን ሰሞኑን በተደረገው የባህል ፖሊሲ ውይይት  ላይ የተገለጸ  ሲሆን የሃገሪቱን የኪነ ጥበብ እድገት ለማፋጠንም የኪነ- ጥበባት ምክር ቤት ይቋቋማል ተብሏል። በሌላ በኩል፤ከዚህ በኋላ ባህላዊ ቱሪዝምን ለማስተዋወቅ የሃመር፣ የመርሲና የሌሎች ልጃገረጆችን ራቁት ፎቶግራፍ መጠቀም በጥብቅ የተከለከለ መሆኑ በሰሞኑ የውይይት መድረክ ላይ ተጠቁሟል፡፡


Read 2681 times