Print this page
Monday, 25 September 2017 12:01

“አበባየ’ሽ ወይ”…የልጃገረዶች ጨዋታ

Written by  በሠርጸ ፍሬ ስብሐት
Rate this item
(8 votes)

“አበባየ’ሽ ወይ”…የልጃገረዶች ጨዋታ
(ምጥን መጣጥፍ፤ ስለ ትውፊቱና ባህላዊ አጨዋወቱ)

  1  ዐውደ ዓመት፡-
በጊዜ ወሰን ውስጥ ያልተሠፈረ የሕይወት ልክና ወግ የለንም፡፡ በጊዜ ቀመር ውስጥ ያልተጓዘ ቀን ልናሳልፍ አንችልም፡፡ በጊዜ ሀሳብ ውስጥ ያልተፈተነ ፍልስፍናም የለንም፡፡ ከሁሉም ከሁሉም፤ ጊዜያችንን ያልተረከ፣ ጊዜያችንን ያልመሰለ ጥበባዊ ሥራ ሊኖረን አይችልም፡፡ የጥበብ መሥፈሪያው  ‘ዘመን’ ነው። ‘ዘመን’ ፍልስፍናው ነው፡፡ ‘ዘመን’ መታያ ጌጡ ነው፡፡ ‘ዘመን’ አንድምታው ነው፡፡ ዘመን የሰጠው ወይም ጊዜ የማይሽረው ጥበብ፤ “እንደ ወይን እየጣፈጠ የሚሄድ” የሚባል ዓይነቱ ነው፡፡ የጠንካራ ጥበባዊ ሥራ ቀዳሚ መለኪያው የተፈጠረበትን ዘመን ተሻግሮ፤ ከነተጽዕኖው እመክረሙ ወይም እመሸጋገሩ ላይ ነው፡፡ የጥበብ ሥራ እና ባለ ጊዜዎቹ ጠቢባን በዘመን ሥፍር ውስጥ የሄዱበት መንገድ አጎዳኝቷቸው፤ የተጠቀሙት ዘይቤ አመሳስሏቸው፣ በጊዜያቸው “ፋሽን” ተለይተው፤ በጊዜ ሥፍር ውስጥ ሥም አግኝተው “የእከሌ ዘመን ሥራዎች” ተብለው በዘመን ተለይተው ይጠራሉ፡፡
ጊዜ ተለክቶ ወይም ተሠፍሮ እንዲታወቅ፤ ‘አንድ’ ተብሎ የሚቆጠር የዙር መጀመሪያ ያስፈልግ ነበርና፤ የሰው ልጅ ቀናትን ሊቆጥር፣ ዘመንን ሊሠፍር ሞከረ፡፡ የሚያመርተውን፣ የሚሸጠውን ሌላ ሌላውን በተለያዩ መለኪያዎችና ሚዛኖች እንደለካው ሁሉ፤ ጊዜንም ሊለካ የተለያዩ ዐዕዋድን ለመፍጠር ዘመናት የፈጀ ጥረት አደረገ፡፡ ሌትና ቀን በብርሃንና በጨለማ መለያየታቸው ብቻ በቂ መሠፈሪያ ሆኖ አላገኘውም፡፡ የክረምትና በጋ መፈራረቅ እንደ አንድ የዘመን መሥፈሪያ ብቻውን ምሉዕ ሊሆንለት አልቻለም፡፡ እነዚህን የተፈጥሮ ክስተቶችና ዑደቶች እንደ ጊዜ መሥፈሪያ አምኖ አልተቀመጠም፡፡ የጊዜን አዕዋድ በረጅም ምርምር፣ እስከ ሥነ-ከዋክብት በደረሰ ጥበብ ፈተሸ መረመረ። ከዚህ ሁሉ በኋላ፤ የዘመን ውል የታሰረበትን “የዑደት አንደኛ ቀን” ወሰነ። ቁጥር “አንድ” ብሎ የሚነሳበት አንዳች መነሻ አሐዝ እንደሚያስፈልገው ሁሉ፤ ዘመንም “አንደኛ ቀን” ብሎ የሚቆጥረው መነሻ የግድ ያስፈልገው ነበር፡፡    
ለኢትዮጵያውያን የዘመንን መቀየር አብሳሪው ዐውደ-ዓመት ዕንቁጣጣሽ፤ የቀኖች ሁሉ ደማቁ፣ የደስታ ቀኖች ሁሉ ታላቁ ሆኖ፤ የዘመን ሽግግር “አንደኛ ቀን” ሆነ፡፡ የሰው ልጅ የዘመን ሽግግር ፍላጎት፣ የሰለቸን የማደስ ሰበብ፣ እና ተፈጥሯዊ ሂደት፤ “ዐውደ-ዓመት” ነው፡፡ ይሁን እንጂ፤ ‘ዘመን’ ዕለቱ ስለተቆጠረ ብቻ አይሻገርም፡፡ 365 ቀናት በውስጡ ስላለፉ ብቻ ‘ዘመን’ አይቀየርም፡፡ ዘመኑ ዕለቱን ጠብቆ ሲቀየር “የዙር ዑደቱን መሠረት አድርጎ በቀመር ተቀየረ” ይባል ይሆናል እንጂ፤ በሰው ሀሳብ ውስጥ ያለው የዘመን ዑደት ሽግግር አደረገ ለማለት ግን ሌላ አጽዳቂ ይፈልጋል፡፡ ዘመን መቀየሩን ለሰው አእምሮ የሚያበስረው የተፈጥሮና የባሕል አጀብ በሌለበት፤ “አዲስ” የተባለው ቀን ብቻውን “አንደኛ ቀን” ሆኖ አይደምቅም፡፡ ይህንን ዕለት የሚያስናፍቅ ሽር-ጉድ፣ ይህንን ቀን “ደረሰ”… “ደረሰ”… የሚያሰኝ የሚያውድ መዓዛ፣ የሚደልቅ ከበሮ፣ “ቀን ተቆጠረ 365 ዕለት ሞላ” ከሚለው ስሌት ጋር፤ ስሌቱን “እውነት ነው” ብሎ የሚያረጋግጥ የተፈጥሮ አጽድቆት ይፈልጋል፡፡ ዐደይ ብቅ የምትለው እዚህ ጋር ነው፡፡ የመስከረም ፀሐይ መውጣት የሰበሰበው የሰው ትርምስ፣ ለበዓል ዝግጅት፣ የሚትጎለጎለው ጭስ፤ የተፈጥሮንና የሰውን የሀሳብ ስሌት ስምምነት ያመለክታል፡፡
እንደ “ዕንቁጣጣሽ” በተፈጥሮ ምስክርነት ዐውደ ዓመት መሆኑን ያስመሰከረ የዘመን መለወጫ ዕለት በዓለም የተለያዩ አቆጣጠሮች ውስጥ መኖሩ ያጠራጥራል፡፡ ‘ዐደይ’ በበጋም በክረምትም ያልታየ የጠፋ ሥሯ ብቅ የሚለው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ ‘የመስቀል ወፍ’ የላባውን ጌጥ አድምቆ ለመውጣት ከዚህ ጊዜ ውጪ የሚጠብቀው ሌላ ጊዜ ያለው አይመስልም፡፡
“ዘመን አለፈና ዘመን ተለወጠ፣
ደመናው ተሸኘ ሰማዩ ገለጠ፣
ምድራችን ባበባ በልምላሜ አጌጠ፤
እንዲህ ተንቆጥቁጦ የሚታየው መሬት፣
ራቁቱን ነበር በጋ ልብሱን ገፎት፤
አምላክ ግምጃ ቤቱን ከፈተለትና፣
አማርጦ ለበሰ አገኘ ቁንጅና፤”
                                           (በጸሐፌ ትእዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ እና በሊቁ ያሬድ ገብረ ሚካኤል፤ ለንጉሠ ነገሥቱ ከተበረከተ ግጥም የተወሰደ የዘመን መወድስ፡፡)
ተፈጥሮ በውበት ራሷን አሽሞንሙና ይህንን ሁሉ ትንገረን እንጂ፤ የዚህን ዕለት ብስራት ለመንገር ግን ከልጃገረዶቹ ፈጥኖ ማልዶ የሚነሳ ማንም የለም፡፡ “ተፈጥሮም ተናገረች”… “ይኸው ውጡና ተመልከቱ”… ብለው ከግጫው፣ ከዐደዩ በእቅፋቸው ይዘው፤ “ከዚህ ጊዜ በላይ የዜማ ጊዜ የለም” ያሉ ይመስል፤ “አበባ አላያችሁም ወይ?”፣ “ውጡ… ዐይናችሁን ግለጡ፣ ዘመን ተለውጧል..” የሚለውን ብስራት በውብ ዜማ ይነግሩናል፡፡ ምናልባት፤ በዘመን ለውጥ አዲስ ተስፋ እንዲታየን ማድረግ የሚችለው፣ የልጃገረዶቹ ዜማ ባይኖር ኖሮ፤ ዓመት በተቀየረ ቁጥር የዕድሜያችን መክነፍ፣ ከተሠፈረልን የዕድሜ መቅኑን፣ የቀረን ጥቂት መሆኑ እየታየን፤ የዐውደ ዓመት እንጉርጉሯችን፤
“እኛ‘ኮ ለዘመን ክንፎቹ አይደለንም… ሰንኮፍ ነን ለገላው፣
በታደሰ ቁጥር የምንቀር ከኋላው፡፡” የሚለው የበዕውቀቱ ሥዩም ግጥም ሊሆን ይችል ነበር፤ ቢባል የተጋነነ መደምደሚያ ይሆን ይሆን?    
አበባ’የሽ ወይ?
የባሕላችንን ወግ ጥቂት ከመረመርነው፤ ወላጆች፣ ልጃገረዶች ልጆቻቸውን ካለምንም ምክንያት በየሰዉ ደጃፍ እየቆሙ እንዲታዩ፣ በዚህ ዕለት የፈቀዱበት ምክንያት ምን ይሆን? ብለን እንድንጠይቅ የሚያስገድድ ትልቅ ሀሳብ ወደ አእምሯችን ይመጣል፡፡ አንዳች መንፈሳዊ ወይም ባሕላዊ ስምምነት ይህንን ፈቃድ እንዲሰጡ ካላስገደዳቸው በስተቀር፤ ልጆቻቸውን በየመንደሩ እንዲዞሩ ሊፈቅዱ አይችሉም፡፡ አለቃ ነቢየ ልዑል ዮሐንስ፤ “የታሪከ-ነገሥትን” እና “የክብረ ነገሥትን” የታሪክ ጭብጥ ይዘው ስለ ልጃገረዶቹ ጨዋታ ምክንያት ሲያብራሩ፤
“ንግሥቲቱ ሳባ ወደ ንጉስ ሰሎሞን ዘንድ ስትሄድ፤ አምስት መቶ ደናግል ተከትለዋት ነበር።” ይላሉ። “የእልፍኝ አሽከሮቹም እነርሱው (ልጃገረዶቹ) ሲሆኑ፤ የአበባው (የዕንቁጣጣሽ) አሰጣጡም በእነዚሁ ልጃገረዶች ለንግስቲቱ ክብር የተደረገ ነው፡፡” ሲሉ ያመሰጥሩታል፡፡
በመሆኑም ዛሬ ልጃገረዶቹ፣ በየሀገሩ በተለይም በሰሜናዊው የኢትዮጵያ ባሕል ውስጥ ዐደይ አበባ ቀጥፈው እንግጫ ነቅለው፣ በተለያዩ ጌጣጌጦች ተሸልመው፣ በየዓመቱ የሚቀርቡት፤ ይህንን የሳባ ዘመን ‘ሥርዓተ-ደናግል’ ወግ አድርገው ነው ማለት ነው፤ እንደ ሊቁ አተራረክ፡፡
ዕንቁጣጣሽ የሚለው የበዓሉ ሥያሜም፣ ልጆቹ ከሚይዙት “ዕንቁጣጣሽ” ወይም “ግጫ” ከተሰኘው ሣር የወጣ ሥያሜ ነው፡፡ አለቃ ነቢየ ልዑል ዮሐንስ፤ በብርሃንና ሰላም ጋዜጣ ላይ በወጣው ቀደም ሲል በተጠቀሰው ጽሑፋቸው፤ ስለ ልጃገረዶቹ ጨዋታ ሰበብና ስለ ዕንቁጣጣሽ ትርጉም በሰጡት ትንታኔ ላይ እስከ ዛሬ የሚታመንበትን “ዕንቁጣጣሽ” የሚለውን ቃል ተለምዷዊ ትርጓሜ ጠንከር አድርገው ይሞግታሉ፡፡
“አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት፤ ‘ዕንቁጣጣሽ’ ማለት፤ ንግሥተ-ሳባ ወደ ኢየሩሳሌም በሄደች ጊዜ ሰሎሞን ‘ለችግርሽ’ ወይም ‘ለጣጣሽ ይሁንሽ’ ብሎ ዕንቁ ስለሰጣት በጊዜ ብዛት ‘ዕንቁ-ጣጣሽ’ ወደሚል ሥያሜ እንዲመጣ ሆኗል ወይም ‘ዕንቁጣጣሽ’ ተብሏል፤ ይላሉ፡፡ ይህም ግን አከራካሪ ሆኗል፡፡ ምክንያቱም፤ ሰሎሞን የሚናገረው በዕብራይስጥ፣ ሳባ ወይም ንግሥተ-አዜብ የምትናገረው ደግሞ በሳባ ቋንቋ በመሆኑ፤ ‘ዕንቁ’ የሚባለው ቃል በዕብራይስጥ ቢኖርም፤ ‘ጣጣሽ’ የሚለው ቃል ግን በአማርኛ እንጂ በሌላ ስለሌለ ነገሩን ልክ ሊያደርገው የሚችል አይመስልም፤” ይላሉ፡፡
የምክንያታቸው ሚዛን የሚያጋድለው “ዕንቁጣጣሽ” የሚለው ሥያሜ፣ ልጃገረዶቹ ከሚይዙት “ዕንቁጣጣሽ” ከተሰኘው ቄጠማ መሰል ሣር መገኘቱን ወደ ማጽናቱ ይመስላል፡፡ ይህንን ቄጠማ በየሰዉ ደጃፍ እየቆሙ መስጠታቸውና ዕንቁጣጣሽ ማለታቸው፤ ትልቅ ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው ሲሆን፤ በኖኅ ርግብ አምሳያ እንዲታሰቡ አድርጓቸዋል፡፡ የያዙት መልዕክት “የደስታ ብስራት” መሆኑ፣ ለኖኅ የጥፋትን ውሃ መጉደል ካበሰረችው ርግብ ጋር ተምሳሌታዊ ትስስር እንዳለው የሚተርኩ የሊቃውንት ትርጓሜዎችም አሉ፡፡ ልጃገረዶቹ ይህንን የመሰለ ታላቅ ሃይማኖታዊ ተምሳሌት ወክለው መቆማቸውን አወቁትም አላወቁትም፤ የሥርዓተ ባሕሉን ተምሳሌታዊ ወግ የሚተነትነው የሊቃውንቱ ተዋስዖ ግን፤ ይህንን እና ሌሎች ብዙ ሃይማኖታዊነታቸው የሚያመዝኑ አንድምታዎችን ያስቀምጡላቸዋል፡፡
በዓለም በሰው ልጅ የሕይወት ትርጉም ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚይዝ ተናፋቂ የስምምነት ሥርዓት ነው። አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ በመጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ላይ ስለ በዓል ምንነት ሲተረጉሙት፤ በዓል ማለት፡-
“የደስታ ቀን፣የእረፍት ቀን፣ ባመት፣ በወር፣ በሳምንት፣ የሚከበር፤ ያለፈን ነገር የሚያስቡበት ተዝካር፣ሕዝብ የበዓሉን ምሥጢር እያሰበ ደስ ብሎት እና ለብሶ የሚዘፍንበት፣ የሚዘምርበት፣ ዕልል የሚልበት፣ ሽብሸባ፣ ጭብጨባ፣ ቀኒጽ ነፈርግጽ የሚያደርግበት ሲያረግድ እስክስታ ሲያወርድ በአንገቱ የሚቀጭበት እንደ ጥጃ የሚፈነጭበት ነው፡፡”
ሲሉ ገልጸውታል፡፡ በትርጓሜው ውስጥ ያሉት የደስታ ስሜት ገላጭ ድርጊቶች፤ በዓል ለልጆች ብቻ ሳይሆን በዕድሜ ለገፉትም ቢሆን ትልቅ የስሜት መነቃቃት የሚፈጥር መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡
ሪቻርድ ኤም. ዶርሰን የተባለው ሊቅ “Folk lore and Folklife: An Introduction”  በሚለው መጽሐፉ ላይ እንደሚገልፀው፤ “የበዓላት የመጀመሪያ ሚና ለቡድኖች ህልውና ወሳኝ የሆነ አጋጣሚ ማመቻቸት እና የቡድኖችን መልካም ግንኙነት መፍጠር ነው፡፡” ይላል፡፡ በከረምንበት የገጠሩ ኢትዮጵያ ባሕል ውስጥ፤ በግል ሥራ ምክንያት እርሻው፣ ጉልጓሎው፣ አረሙ… አራርቋቸው የከረሙትን የገበሬ ቤተሰቦች የሚያገናኛቸው የበዓላት ቀናት ጨዋታዎች ናቸው፡፡ የበዓላት ቀናት በየቤቱ የሚመጡት ልጃገረዶችም ለየገበሬው ቤተሰብ የሚሰጡት ትርጉም፤ የማደግ፣ የመድረስ፣ በትዳር ለመተሳሰር የሚሆን የቤተሰብ ዐይንንና ቀልብን የማግኘት፣ በቆየው ባሕል የመጣውን “የ ልጅህን ለልጄ” የዕይታ እርግጠኝነት የሚገኝበት፣ መልካም የግንኙነት አጋጣሚን ሁሉ በአንድነት የያዘ ነው፡፡ ልጃገረዶቹ በየቤቱ መዞራቸው ይሄንንና ይሄንን የመሳሰሉ ሌሎች በማኅበረሰብ ሳይንስ ሊቃውንት ሊተነተኑ የሚችሉ ብዙ ትርጓሜዎችን የያዙ ሲሆኑ፤ የጨዋታዎቻቸው ግጥማዊ ይዘት ደግሞ ይበልጥ ብዙ ሊባልበት የሚገባ ነገር ነው፡፡
ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል፣ “ባለን እንወቅበት” በሚለው ጽሑፋዊ ሥራቸው፤ “በየአደባባዩና በየመስኩ ለበዓላቱ የሆኑት ዘፈኖች የግጥም ምሥጢር ጊዜውን የሚከተል ነው” ይሉና፤ “ለምሳሌ፤ ‘መስከረም’ ምድር በልምላሜ የምትታይበትና በአበባ የምትሸፈንበት ወቅት በመሆኑ ለዕንቁጣጣሽ የሚደረገው ዘፈን፤ ልምላሜን በሚያደንቁ ቃላት የተመሠረተ ነው፡፡” ይላሉ።
በ1986 ዓ.ም  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በኢትዮጵያ  ቋንቋዎችና ሥነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል በለምለም በቀለ የተሠራ የመጀመሪያ ዲግሪ ማሟያ ጽሑፍ እንደሚያመለክተው፤ ይህ የልጃገረዶች ጨዋታ በቀላሉ የማይታዩ ታላላቅ የዘመን ሀሳቦችን፣ የተፈጥሮ ለውጥ ብሥራትን የያዘ ዜማ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ሆነን ስንሰማው፣ በአሁኑ ሥርዓተ ማኅበራችን ወግ ውስጥ የቀሩ ወይም የማናውቃቸውን፤ ነገር ግን የቀደመውን ሥሪት የሚያሳዩ ትረካዎችን ሁሉ የያዙ ቃላትም አሉት፡፡
    “እውዬ…ተዋውዬ፣
     ካሽከር ተዋውዬ፣
     ጌቶች አሉ ብዬ፣
     መጣሁ ሰተት ብዬ፣”
የባሪያና የጌታ ሥርዓቱ የቆየ ልማድ በነበረበት ጊዜ ይባል የነበረና ዛሬም ከዜማው ተቆርጦ ያልወጣ የጨዋታው ግጥም አንድ ክፍል ነው፡፡ በቀደመው ጊዜ ልጃገረዶቹ በሚጨፍሩባቸው ቤቶች ውስጥ ያሉት ሰዎች፤ ‘የጌታ ዘር’ ሆኑም አልሆኑም ልጆቹ ግን በትህትና “ዝም ብዬ አልመጣሁም፣ ለአሽከር ነግሬ፣ እርስዎ (ክቡርነትዎ) እንዳሉም ጠይቄ ነው” ይላሉ፡፡ ለምለም በቀለ ስለዚህ ወግ ሲያብራሩ፤ “በዛሬው ጊዜ ይህ ዓይነቱ ሥርዓት (የባሪያ እና የጌታ ወግ ማለታቸው ነው፤) ስለሌለ ዜማው አይሰራም ወይም ዋጋ የለውም ማለት አይደለም፡፡ ትልቅ የፈቃድ ሥርዓት የሚያስተምር፣ የወላጆችን ከብር የሚገልጽ ትሁት፣ ግብረ-ገባዊ ዋጋው ከፍ ያለ ግጥም ነው፤” በማለት በጊዜና በሥርዓት ለውጥ ምክንያት ሊለወጥ እንደማይገባ፤ ሮበርት ጆርጅ `Reactions and Games` በተሰኘው ታዋቂ ድርሳኑ ያሠፈረውን አስተምህሮ መሠረት አድርገው ያስረዳሉ፡፡
ይሁን እንጂ፤ በሁሉም ትውፊታዊ ጨዋታዎችና የሀገረ-ሰብዕ ጨዋታዎች ላይ የሚታየው፤ ከአንድ ሀሳብ ወደ ሌላው ሀሳብ የሚደረገው የግጥም ሽግግር ያልተያያዘ ወይም ወጥነት የሌለው የመምሰል ባህርይ በዚህ በአበባየሽ ወይ ጨዋታዎችም ውስጥ ሊታይ ይችላል፡፡ ሆኖም ግን የሀሳብ መሠረቱን ይዘን ከሄድን አንድ የዐውድ ትርጓሜ ላይ ማረፋችን አይቀርም፡፡                                   
        “አበባየሽ ወይ፣
        ባልንጀሮቼ ቁሙ በተራ፣
        እንጨት ሰብሬ ቤት እስክሠራ፣”
ልጃገረዲቱ ለጓደኞቿ ይህን ስትል፤ “ጎጆ አልወጣሁም፣ ባል አላገባሁም፤” ማለቷ ነው፡፡ የታጨች እንደሆነ ጨዋታው ስለማይኖር፣ ልጅቱ ገና ልጃገረድ ሆና ያልታጨች ናት ማለት ነው፡፡ የልጃገረዶቹ አጨዋወትና  አሰላለፍ እንደሚያስረዳን፤ ከ12 ዓመት በላይ (በአብዛኛው ከ12-18 ዓመት) በሆኑት ልጃገረዶችና ከ12 ዓመት በታች በሆኑት (ከ8-12 ዓመት) ልጃገረዶች መካከል ለሁለት ተከፍለው የሚያደርጉት ‘ድራማዊ’ ሕብረ-ዝማሬ ነው። ከ12 ዓመት በላይ ያሉት (ለመታጨት የደረሱት) “ባልንጀሮቼ ቁሙ በተራ” ብለው በማዘዝ፤ ከ8-12 ላሉት፣ ላልታጩትና የሴት ወግ ላላደረሱት ልጃገረዶች ጥሪ ያደርጋሉ፡፡ “ለምለም” እያሉ የሚቀበሉት እነዚህ ከ8-12 ዓመት ዕድሜ ላይ ያሉት ያልታጩት (የወር አበባ ያላዩት) ልጃገረዶች ናቸው ማለት ነው፡፡
“አበባየሽ ወይ ለምለም”
የሚለውን ያወረደችው ወይም ያወረዱት ልጃገረዶች ቀጥለው፤
“እንኳን ቤትና፣
የለኝም አጥር፣
እደጅ አድራለሁ፣
ኮከብ ስቆጥር፤” ትላለች ወይም ይላሉ፡፡
አጥኚዋ ለምለም በቀለ እዚህ ግጥም ላይ ሲደርሱ፤ እንድናስተውላቸው የሚፈልጓቸውን መጠይቆች ያነሳሉ፡፡ ከላይ “ቁሙ በተራ…ቤት እስክሠራ” ያለችው ልጃገረድ፤ ቀጥሎም ጓደኞቿ ምንም ሲጠይቋት ሳንሰማ፤ “ቤት ቀርቶ አጥር እንኳን እንደሌላት” ትናገራለች፡፡ አጥኚዋ በጥናታቸው፣ እዚህ አካባቢ አንድ የቀረ ግጥም እንዳለ ይጠረጥራሉ፡፡ ወይም “አንድ የጎደለ ግጥም እንዳለ ጠርጥሩ፤” ይሉናል፡፡ ምናልባትም በዘመናት ብዛት በዝንጋዔ የጠፋ፣አንድ ስንኝ ወይም ሙሉ ቤት ሊኖር ይችላል፡፡ ባልንጀሮች፤ “ቤት የለሽም ወይ” ሳይሏት በምን ምክንያት “እንኳን ቤት እና የለኝም አጥር ልትል ትችላለች?” የሚለውን ምክንያት በማስገባት ይሞግታሉ።
በ“ፎክ” ልማዳዊ ጨዋታዎች ውስጥ የዚህ አጥኚዋ የፈለጉት ዓይነት ወጥነት ብዙም ሊጠበቅ አይችል ይሆናል፡፡ አጥኚዋ እንዳሉት፣ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ፣ የመረሳት አጋጣሚ እንዳለው የሚታመን ቢሆንም፤ እንደ አበባየሽ ወይ ባሉ ትውፊታዊ ጨዋታዎች ውስጥ ወጥነት የማይጠየቅበት የግጥም አካሄድ ሊኖር እንደሚችል መረዳት መልካም ነው፡፡ አለዚያም፤ አጥኚዋ በዕማሬያዊ ፍቺ ሀሳቡን ለማስታረቅ፣ ቀጥለን በምንገልፀው መልኩ እንዳደረጉት ያለ የትርጉም ሀሰሳ በማደረግ፤ ሀሳቡን የተሟላ ማድረግ ይቻል ይሆናል፡፡
“እንኳን ቤት እና የለኝም አጥር” ስትል፤ “እንኳን ባል እና እጮኛም የለኝ” ማለቷ ነው፡፡ ቀጠል አድርጋ ደግሞ “እደጅ አድራለሁ ኮከብ ስቆጥር” ትላለች። እማሬያዊ ፍቺው፤ “ማደሪያ ቤት ስለሌለኝ እደጅ ቁጭ ብዬ ሰማይ ላይ ፈሰው የሚታዩትን ቁጥር ስፍር የሌላቸው ከዋክብት ስቆጥር ሌሊቱን እገፋዋለሁ ማለቷ ነው፡፡” ልንል እንችላለን፡፡ አቀራረቧ ግን ምፀታዊ ገለፃ የተላበሰ ነው፡፡ “ኮከቦችን ቆጥሮ ለመጨረስ መሞከር እንደ ሞኝ የሚያስቆጥር ነው፡፡ እኔም ማደሪያ የሌለኝ ሥራ ፈት በመሆኔ፣ እንደ ሞኝ ደጅ ተቀምጬ ኮከብ ላይ አፍጥጬ አድራለሁ ማለቷ ይሆን?” ያሰኛል፡፡ በሌላ ጠንካራ አንድምታ ካየነው ግን “ኮከብ” ከዕጣ ፈንታ ጋር ይተረጎማል፡፡ “ይህችም ልጅ ኮከብ ቆጣሪ እንደሚባሉት አዋቂዎች የወደፊት ዕጣዋን ለመተንበይ እየጣረች ይሆን?…ብንልም ያስኬዳል፡፡
“ኮከብ ቆጥሬ ስገባ ቤቴ፣
ትቆጣኛለች የእንጀራ እናቴ፤
እንዴ?...ቀደም ሲል “እንኳን ቤት እና አጥርም የለኝ” ስትል ቆይታ፤ “ኮከብ ቆጥሬ ስገባ ቤቴ” እያለች ግጥሙን ስትቀጥል ምን ማለቷ ነው ማለታችን አይቀርም፡፡ “ይቺ ልጅ ያጣችው በርግጥ ማደሪያ ቤት አይደለም፡፡ ምክንያቱም የእንጀራ እናቷ ቤት አለ፡፡ ግን በተለመደው ብሂል፣ የእናት ያልሆነ ቤት እንደ ራስ ቤት ስለማይታይ፤ የእንጀራ እናቷን ቤት “ቤቴ” ባትለው ነው፡፡ “እንዲያውም ውጪ በማደሯ ትቆጣታለች፤” ብለን ከላይ የሰጠነውን ፍቺ፣ ልክ ነው እንድንል ያደርገናል፡፡
“አበባም አለ በየውድሩ፣
ባልንጀሮቼ ወልደው ሲድሩ፣
እኔ በሰው ልጅ ማሞ እሽሩሩ፤”
“አበባም አለ”፣ “አበባየሽ ወይ”፣ “ለምለም” የሚሉትን ቃላት በተደጋጋሚ ስንሰማ፤ ወቅቱ ምድር የምታጌጥበት ልምላሜና የአበባ ምንጣፍ መሆኑን እንድናስብ ያደርገናል፡፡ “ውድር” ማለት ጢሻ ማለት ነው፡፡
“ከባልንጀር ጋር ስጫወት ውዬ፣
ራታችንን ንፍሮ ቀቅዬ፣
ላ‘ቶ(ለአቶ) ባለቤት ብላ ብለው፣
ጉልቻ አንስቶ ጎኔን አለው፣
ከጎኔም ጎኔ ኩላሊቴን፣
 እናቴን ጥሯት መድኃኒቴን፣
በቀደመው ጊዜ “ከገዳይ ጋራ ስጫወት ውዬ፣ ይባል የነበረው፤
“የመስቀል ለታ የደመራው፣
 ንፍሮ ቀቅዬ ብላ ብለው…” ተብሎ ተቀይሯል፡፡
“ኮከብ ቆጥሬ ስገባ ቤቴ፣
ትቆጣኛለች የእንጀራ እናቴ፣” የሚለው ደግሞ፤
“ኮከብ ቆጥሬ ስገባ ቤቴ፣
ይነሳብኛል የጎን ውጋቴ” ብለው ሲዘፍኑት ይሰማል።
እንዲህ እንዲህ እያለ “አበባየሽ ወይ” የተባለው ጨዋታ በርካታ እማሬያዊና ፍካሬያዊ ትርጓሜዎች ይወጡታል፡፡ የአበባየሽ ወይ የልጃገረዶች ጨዋታ፣ትልቅ ድራማዊ አቀራረብ ያለው ሙዚቃ ነው፡፡ በዘመናት ለውጥ ዛሬ ላይ ደርሶ እንኳን፤ ካለ እርሱ አዲስ ዓመት አይደምቅም፡፡ ለታደሉት ሀገራት የሀገረ-ሰብዕ የባሕል ጨዋታዎች ራሳቸውን ችለው፣ ያለምንም መሸራረፍ እንዲሸጋገሩ፣ጥበባዊ ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ ተሠርተው፣ በወግ ጠባቂ ተቋሞቻቸው በኩል በክብር ይቀመጣሉ፡፡ የዘመኑ የቀረጻ ቴክኒዮሎጂ ምስጋና ይድረሰውና፤ የምሥራቅ አውሮፓ “ማዙርካ” ባህላዊ ጨዋታዎችና “ፖሎኔዞች” እንዲሁም የአውሮፓና አሜሪካ “ክሪስማስ ካሮሎች” ልክና ሥርዓቱን በሚያውቁ ባለሙዎችና ኦርኬስትራዎች ዋጋ እንዲኖራቸው ተደርገው ዳግም ይሠራሉ፣ በጥራትም ይቀረጻሉ፡፡
ጠንካራ ተከታይ አላገኙም እንጂ፤ ጋሽ አውላቸው ደጀኔ፣ በ1960ዎቹ መጀመሪያ እነ ጠለላ ከበደን፣ ፍቅርተ ደሳለኝን፣ አልማዝ ኃይሌንና ሌሎቹን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ቤት ድምፃውያንንና ተዋንያንን ይዘው አበባየሽ ወይን ድንቅ አድርገው ከውነው፣ በኢትዮጵያ ሬዲዮ አስቀርጸውት ነበር፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም ይኸንኑ ጨዋታ፣ በየዓመቱ በቴአትር ቤቱ ተዋንያትና ድምጻውያት ሲቀርብ፤ በአድናቆት ያዩ እንደነበር የእነ ሰሎሞን ተሰማንና የጳውሎስ ኞኞን የጊዜውን የጋዜጣ ጽሑፎች ዋቤ ማድረግ ይቻላል። በዚህ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ቤት የአበባየሽ ወይ ጨዋታ ውስጥ ዛሬ ዛሬ እየታወቀ ያለውን የላስታ አካባቢውንና የትግራዩን ‘የአሸንድያ’ እና ‘የአሸንዳዬ’ ጨዋታ እንደ ማሳረጊያ “ቲም” መርጠው “አይ ወለቤ” በሚለው የጨዋታው መደምደሚያ ላይ ውብ ቦታ ሰጥተው ከውነውታል፡፡ ኋላ ላይ ደግሞ የኦርኬስትራ ኢትዮጵያ የሀገረሰብ ጨዋታ ሙዚቀኞችም ይህንኑ የአበባየሽ ወይ ጨዋታ ወጉን ጠንቅቀው በእነ ፀሐይ እንዳለ ድምጻዊትነት ያቀርቡት ነበር፡፡ በ1970ዎቹ እና 80ዎቹም አንዳንድ ድምጻውያን ጥቂት የፈጠራ ሥራዎችንና ድራማዊ አቀራረቦችን አክለው፤ አበባየሽ ወይን ለትውልድ ለማስተላለፍ ሞክረው ነበር፡፡ በዚህ ጥረታቸው አስቴር አወቀን (“ካቡ” በተሰኘው አልበሟ ውስጥ በተካተተው የአበባየሽ ወይ ጨዋታዋ፤) እና ሰሎሞን ደነቀን (“ስርቅታዬ” በተሰኘው ዜማው “ሆያሆዬን” በወንዶች ድምጽ እና ‘አበባየሽ ወይን’ ደግሞ በብርቱካን ዱባለ ድምጽ እንዲቀነቀን በማድረግ፤) አለማንሳት ውለታቸውን እንደ መዘንጋት ይቆጠራል፡፡ አለመታደል ሆኖ ብዙኃን መገናኛው በእጁ የሚገኘውን ይህንን የቴአትር ቤቶቹን ተዋንያንንና ድምፃውያን ያቀረቡትን ሥራ አያስደምጡንም እንጂ ለዛና አቀራረቡን የዘመናችን ልጃገረዶች ደህና አድርገው ሊያጠኑት ይችሉ ነበር፡፡
የዛሬ ልጃገረዶች ያበላሽዋቸው ወይም አለወጋቸው ያቀረቧቸው የአበባየሽ ወይ ጨዋታዎች ላይ በየጊዜው ትችቶች ይቀርባሉ፡፡ “ቃላት ተገደፉ”፣ “የአቀራረብ ወጎቹ ተቆነጻጸሉ” ወ.ዘ.ተ. የሚሉት ትችቶች በዘመናችን ልጃገረዶች ላይ ብቻ መቅረባቸው፤ የትችቶቹን ቀስቶች ከእውነተኛው ኢላማ ውጪ ያደርጋቸዋል፡፡ እውነት ለመናገር የትውፊት ግድፈቶቹ፣ የልጃገረዶቹ የብቻ ጥፋቶች አይደሉም፡፡ በአብዛኛው እናቶች፣ ለልጆቻቸው ትክክለኛውን ክዋኔ የሚያስተምሩበት አጋጣሚ ባለማግኘታቸው፣ ወይም የአነዋወር ወጋችን ፍፁም እየተቀየረ በመምጣቱ፣ እንዲህ ያሉ ትውፊታዊ ሥርዓቶች የሚሸጋገሩባቸው የትውልድ ወግ፣ የቅብብል ድልድዮች በመፍረሳቸው የተከሰተ በመሆኑ፤ ልጃገረዶቹ ባላዩትና ባልሰሙት ነገር ሊወቀሱ፣ “ወግ አልጠነቀቃችሁም” ሊባሉ ሁኔታው አይፈቅድም። ይህንን ወግ፣ ይህንን ሥርዓትና ትውፊት ለማሳየት ትልቁ ኃላፊነት የብዙኃን መገናኛዎቹና የወግ ጠባቂ የባሕል ተቋማቱ (የቴአትር ቤቶቹ)፣ በተለይም የሬዲዮና የቴሌቪዥኑ ነው፡፡ ብዙኃን መገናኛው፣ የሥነ-ጥበብ ተቋማቱ፣ የባሕል ተቆርቋሪዎች፣ ድምፃውያንና ወላጆች እንደ ኃላፊነት ደረጃቸው ሊንከባከቡት፣ ልክ እና መልኩ ሲሸራረፍም ቆጣ በማለት ሊጠብቁት የሚገባ ትልቅ ማኅበረሰብዓዊ ወግ ነው፡፡   

Read 8783 times Last modified on Monday, 25 September 2017 12:37