Monday, 25 September 2017 12:00

በሀሳብ ጎዳና ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

“የዕድሜ ቃጭል በሁላችንም ጆሮ ላይ ያንቃጭላል”

ጊዜ እንዲሁ ቦታ የለው
          ሲደክመው ‹ሚያርፍበት፤
ቀን፤ቀን በብርሃን አልጋ
          ወይ በጨረቃዋ ሌት፣
መሄድ፤ መሄድ ብቻ
        መጓዝ፣ መጓዝ መሮጥ፤
ጭፍልቅልቅ አድርጎ
           ክፉ በጎ ሳይመርጥ፡፡
ሥነ ፍጥረታዊ ቀመር (Biorigonal calculus ) እና ሃይማኖታዊ ብፅዐት (Religions beliefs) እንዳሉ ይሁን። እነሱ ላይ ጊዜን እንጨምርበት፡፡…. ዋናው የህይወት ቅመም.. (substance) በመሆኑ፡፡
ፍጥረት በጊዜ ይሰራል፡፡… በመጀመሪያ ቀን… ሰማይና ምድር ተፈጠሩ፤ በሁለተኛው ቀን እንዲህ ሆነ፣ በሶስተኛው ቀን ደግሞ… እየተባለ ይቀጥላል፡፡
ነጥብ የማታክል፣ ትንሽ ፍሬ አድጋ፣ ዋርካ ትሆናለች። የዛኑ ያህል ትልቅ ተራራ በጊዜ ቡጢ ይዘረራል፡፡…. እንደ ዳዊትና ጎልያድ፡፡ ‹ሁሉም በጊዜው ሆነ› የሚሉን ያለ ነገር አይደለም፡፡ “Time is the best arbiter” (የጊዜ ዳኝነት ፍትሃዊ ነው ለማለት ይመስላል፡፡)
ያለ ጊዜ ፍጥረት አይታሰብም፡፡ ጊዜ ደግሞ ብቻውን ሃሳብ ብቻ ነው፡፡ ሃሳብ ደግሞ እንደ ሃሳብ “ምንም” ነው። የሚያስብና የሚታሰብ ነገር ከሌለ፣ ሃሳብ እራሱን አያስብም፡፡ ሰውና ማህበራዊ  ኑሮም እንዲሁ!!
ሕይወትና ጊዜ በጥብቅ የተቆራኙ ናቸው፡፡… አንዱን ከአንዱ መነጠል አይቻልም፡፡፡ ሕይወት ማለት ጊዜ፤ ጊዜ ደግሞ ህይወት!! ወዳጅህን፤ “ህይወት እንዴት ናት?” ብለህ ስትጠይቀው፣ ጊዜ እንዴት እያደረገህ ነው? ለማለት ይመስለኛል፡፡ “መልካም ጊዜ ይሁንልህ” ስትልም “ኑሮ ይመችህ፣ ቀን ይሳቅልህ” ለማለት ነው፡፡
በእስር ቤት፣ በሆስፒታል አልጋ ላይ ወይም በሌላ መከራ ቦታ የሚገኝ ሰው፤ አንዳንዴ ሊስቅና ሊጫወት ይችላል፡፡ በሰርግ፣ በጭፈራና የደስ ደስ ባለው ስፍራ ሆኖ ደግሞ የሚያዝን፣ የሚከፋና የሚበሳጭ ሞልቷል፡፡ ዐዋቂዎች “The words happiness and sadness are derived from the word this moment…” ይላሉ፡፡
አስር ሳንቲም አለኝ፣ አንድ ብር አለኝ፣ አምስት ብር ወይ ሃምሳ ብር አለኝ ስንል… የቢሉ ቁጥር የሚናገረው የትንንሽ ገንዘቦች ወይም የሽርፍራፊ ሳንቲሞች ድምር መሆኑን ነው፡፡ ሰውም ዕድሜዬ ሃያ ነው፤ ሰላሳ ነው፤ ሃምሳ ወይም ሰባ ነው ሲል፣ ቁጥሩ የሚያሳየው ሰውየው ያለፈባቸው ወይም የተሰራባቸው ጥቃቅን ጊዜዎች (moments) ድምር መሆኑን ነው፡፡ ለምሳሌ ይህንን ማስታወሻ ለመፃፍ፣ የመጀመሪያዋን ፊደል ወደ አረፍተ ነገር ስከትብና አሁን እዚህ መስመር ላይ ስደርስ፣ ወደድኩም ጠላሁም ዕድሜዬ ጨምሯል፣ እኔነቴ ተቀይሯል፡፡… ያንተ ያንባቢው ወዳጄም እንደዚሁ፡፡
አዝርዕትና እንስሳት፣ ጨረቃና ከዋክብት፣ አለቶችና ውቅያኖሶች፣ በረዶና እሳተ ጎሞራም… “ደስታና ሃዘናቸው” በጊዜ ድንኳን ውስጥ ነው፡፡ ያለ፣ የቆመ፣ የማይንቀሳቀስ የሚመስለን ወይም እንደ ወራጅ ውሃ እንድ ዓይነት መስሎ እምናየው ሁሉ በጊዜ ዓይን ተለውጧል፡፡… ሌላ ሆኗል፣… ሌላውም ሌላ፡፡ አንድን ወንዝ ሁለቴ አይሻገሩትም እንደሚባለው፡፡
ጊዜ ስንል የምንኖርበት ወይም የምንገኝበት ሁኔታ ማለት ነው፡፡ እዚህ ውስጥ መውደቅ፣ መነሳት፣ መሮጥ፣ መቀመጥ፣ መተኛት… ሃዘንና ደስታ፣ ክፋትና ደግነትም አለበት፡፡
የሰው ልጅ ከእናቱ ሆድ ሊገላገል ሲቃረብ፤ የጊዜ ቁጥር እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ ሶስት ሳምንት ቀረው፣ ሁለት ሳምንት ቀረው፣ አስር ቀን ቀረው… እየተባለ ሄዶ… ዜሮ ይሆናል፡፡ ራሱን ችሎ በነፃነት ሲተነፍስ፣ ኑሮን ማሽተት ሲጀምር ግን አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት እየተባለ… ሽቅብ ይቆጠራል፡፡ እዚህ ጋ ወዳጄ፤ አንድ ነገር ልብ በል። የሰው ልጆች ስንባል…ሁላችንም ተመሳሳይ መልክና ቁመና ይዘን፣ ከአንድ ማህፀን በአንድ ጊዜ የተፈለፈልን፣ በተመሳሳይ ትምህርትና ችሎታ የታነፅን ብንሆን እንኳ እኩል ሮጠን እኩል አንደርስም፡፡ አንዳንዶች ይቀድማሉ፣ አንዳንዶች ኋላ ይቀራሉ፣ የመሃለኞቹም እንዳቅማቸው ያስመዘግባሉ፡፡
በሌሎችም ጉዳዮች አቅማችን ይበላለጣል። ለምሳሌ ማሰብና መረዳት ላይ፡፡ አንዳንዶቻችን… አርቀን ማሰብ እንችላለን፡፡ አንዳንዶቻችን መካከለኛ አእምሮ ሲኖረን፣ ሌሎቻችን ደግሞ ኋላ ቀሮች ነን። ይህ ማለት ወዳጄ፤ ተሰራንበት ያልነው ጉዳይ ወይም ጊዜ ሁላችንም ወይም ሁሉም ነገር ላይ እኩል ተፅዕኖ የለውም ማለት ነው፡፡… ቢኖረው ኖሮ… ረሃብና ጥጋባችን፤ ሳቅና ለቅሷችን… አንድ ሆኖ ለመብትና ለነፃነት፤ ለፍቅር፤ ለሰላምና ለወንድማማችነት… በግልም ሆነ በቡድን ያለን አስተሳሰብና ትርጓሜ፣ በጊዜ መስታወት ውስጥ መልኩ አይለዋወጥም ነበር፡፡
አንዳንድ ሰው ሰዓቱ አይሄድም፤ ጊዜው አይንቀሳቀስም ሲል፣ አንዳንዱ ደግሞ ሰዓቱ ከነፈ፤ ጊዜ አጠረኝ በማለት ይቆጫል፡፡ ሁለቱም ልክ ናቸው፡፡…ስንፍናና ጥረት እንዳሉ ሆነው፡፡ ለተራበና ለተቸገረ፣ ለታመመና መድሃኒ ላጣ፣ ጊዜ ከሱ ጋር ይራባል፣ ጊዜ ከሱ ጋር ይታመማል፡፡ ለደላውና ለተመቸው ደግሞ ጊዜ ከሱ ጋር ይደላዋል፣ ይመቸዋል፡፡
የትምህርትም ሆነ የስራ ዕድል እኩልነት በተነፈገበት በኛ አገር አውድ ስናየው ደግሞ ጊዜ Merit መፍጠር አልቻለም፡፡ አልፎ፣ አልፎ የነበረውም ሞቶ፣ ተቀብሮ፤ ተዝካሩ ወጥቷል፡፡… ምክንያቱም `Merit comes after equal opportunity is given for all` ተብሎ፣ ተብሎ ያለቀለት ዕውነት ስለሞተ!!
እንግዲህ ወዳጄ፤ ሰው በጊዜ ይሰራል፤ ያልኩህ ጉዳይ ከፍ ስናደርገው፣ ሃገርም በጊዜ ይሰራል ማለት ይሆናል፡፡ አንድ ችግር በሚያድግበት ወቅት ነፋስ ወይም ሌላ ነገር እንዳያወላግደው በለጋነቱ ካልተስተካከለና ካልታረቀ ይጎብጣል፡፡ … እየጠነከረ ሲሄድ ደግሞ ለማቃናት ያስቸግራል፡፡
ለማንኛውም ግን ወዳጄ፤ የዕድሜ ቃጭል በሁላችንም ጆሮ ላይ ያንቃጭላል፡፡ በብርቱና በሰነፉ፣ በጨዋና በዋልጌው፣ በብልጥና በብልሁ… በሁሉም!!... ያለ አድልዎ!!... “ጊዜ ወርቅ ነው፡፡…- ሳይረፍድብህ ድመቅበት” እያለ!!
ለሚሰማ የውስጥ ጩኸት ብቻ ይመስለዋል፡፡ ለሚያደምጠው ግን ከጩኸቱ ውስጥ ቁጥር አለ፡፡ ቁጥር ደግሞ ቢያንስ መጀመሪያ አለው፡፡ እየጨመረ ሊሄድ ወይ እየቀነሰ ሊመጣ ይችላል፡፡ ወሳኙ የጀመርክበትን ቦታ ወይም bench mark…አለመርሳት ነው!!
ሠላም!!Read 535 times