Print this page
Monday, 25 September 2017 12:06

ለመሆኑ ቅኔ ፍልስፍና መሆን ይችላል?

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ፣ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(17 votes)

    “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” የሚለው አዲሱ መፅሐፌ፣ የቤተ ክርስትያን ምሁራን አካባቢ ቅሬታን መፍጠሩን ተረድቻለሁ፡፡ የቅሬታቸው መነሻም፡-
የኢትዮጵያውያን ፍልስፍና የሚገኘው በዋናነት በቅኔ ውስጥ ነው፡፡ ስለሆነም፣ የኢትዮጵያ ፍልስፍና በዘርዓያዕቆብ አስተሳሰብ ልክ መለካት የለበትም። ምክንያቱም፣ ዘርዓያዕቆብ ካነሳቸው ሐሳባቸው በላይ ከፍታ ያላቸው ሐሳቦች በቅኔያቸው ያነሱ ሊቃውንት ነበሩንና፡፡ በመሆኑም፣ ትክክለኛውን የኢትዮጵያውያን ፍልስፍና ለማግኘት ቅኔያችንን ፍልስፍና ማዋለድ አለብን፡፡
 የሚል ነው፡፡
አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄም፤ “አልቦ ዘመድ” በተባለው ተወዳጅ መፅሐፋቸው ውስጥ የተለያዩ ቅኔዎችን እየጠቀሱ፣ ቅኔዎቹ እንዴት ከጥንት ግሪካውያን ፈላስፎች ፍልስፍና ጋር እንደሚመሳሰል በማስረዳት፣ የኢትዮጵያውያን ፍልስፍና በቅኔ ውስጥ እንደሚገኝ አጠንክረው ተከራክረዋል፡፡
እውነት ለመናገር እኔ በቅኔና በፍልስፍና መካከል ስላለው ዝምድና አስቤበት አላውቅም ነበር፡፡ የእነዚህን ምሁራን ቅሬታ ከሰማሁ በኋላ ግን ስለ ቅኔ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ በቅኔ ላይ የተፃፉ መፃህፍትንም አነበብኩ፡፡ እናም ከዚህ ንባቤ በመነሳት፣ “እውን ከሊቃውንቶቻችን ቅኔያት ውስጥ የኢትዮጵያን ፍልስፍና ማውጣት እንችላለን?” ለሚለው ጥያቄ፣ የግሌን ምልከታ ላቀርብ ወደድኩ፡፡
የቅኔን ትርጉምና ምንነት በተመለከተ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬን በመጥቀስ፣ አቶ ማርዬ ይግዛው፣ “ቅኔያዊ የእውቀት ፈጠራ” በሚል ርዕስ በ2006 ዓ.ም ባሳተመው መፅሐፍ ውስጥ እንዲህ ይላል፡-
ቅኔ አንድ ሰው ስለ አንድ ነገር ወይም ድርጊት ያገኘውን እውቀት ወይም ምሥጢር ምሳሌ መስሎ፣ ምሥጢር ወስኖ፣ ቃላት መጥኖ፣ በአዲስ ግጥም የሚያቀርብበት ድንገተኛ ድርሰት ነው፡፡
ከዚህ የመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ፣ የቅኔ ትርጉም ተነስተን፣ የቅኔን ባህሪያት መዘርዘር እንችላለን፤ ይሄውም ቅኔ - የሚሥጥራዊነት፣ የግጥምነት እና የድንገተኛነት ባህሪዎች አሉት፡፡ ቅኔ፣ ሚሥጥራዊነትን ከቃላት (የሰምና ወርቅ ፍቺ ካላቸው ቃላት)፣ ግጥምን ከሥነ ፅሁፋዊ አቀራረብ እንዲሁም የድንገተኛነት ባህሪን ደግሞ ከባለቅኔው ንቁና ፈጣን አእምሮ ያገኛል፡፡
እንግዲህ ክርክሩ “ከባለቅኔው ንቁና ፈጣን አእምሮ የሚመነጨው ይህ ቅኔያዊ ሐሳብ፣ ዘርዓያዕቆብ ካነሳቸው ሐሳቦች በላይ ከፍታ ያላቸው ናቸው” የሚል ነው፡፡ ይህ መከራከሪያ ስለ ሊቃውንቶቻችን ምጡቅነት በመከራከር ብቻ አያቆምም፤ ይልቅስ ከዚያ አልፎ ዘርዓያዕቆብ ኢትዮጵያዊ ላለመሆኑ የቅኔን ከፍታ እንደ ማስረጃ ያቀርባል እንጂ፡፡
በዚህ መስመር ከሚከራከሩ ምሁራን መካከል የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መምህር የነበሩት አቶ ፍስሐ ታደሰ አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ፍሰሐ በአንድ ወቅት ፈላስፋው ዘርዓያዕቆብ፣ ኢትዮጵያዊ አለመሆኑን ሲከራከሩ እንዲህ ብለው ነበር፡-
በኢትዮጵያ ውስጥ ነገረ ሃይማኖትንና ነገረ መለኮትን የሚፈታተኑ አስተሳሰቦች በየዘመኑ በቅኔያችን ውስጥ ሲነገሩ የነበረ ነው፡፡ እንዲያውም የዘርዓያዕቆብ ሐሳቦች ከእነዚህ ምጡቅ ቅኔያት አንፃር በጣም ደካማና የወረደ ነው፡፡
በመሰረቱ አንድ ሐሳብ ፍልስፍና የሚሆነው ነገረ ሃይማኖትን ስለሚፈታተን ሳይሆን ፍልስፍናዊ ለሆነው ጥያቄ ከእምነት ይልቅ አመክንዮ ላይ የተመሰረተ መልስ ሲቀምር ነው፡፡ ቅዱስ አኳይነስንና ቅዱስ ኦገስቲንን ፈላስፋ ያደረጋቸው በአመክኖያዊ የሐሳብ አደረጃጀታቸው እንጂ፣ ነገረ ሃይማኖትን የሚፈታተን ሐሳብ ስለቀመሩ አይደለም፡፡ በመሆኑም፣ ቅኔ ፍልስፍና የሚሆነው ነገረ ሃይማኖትን የሚፈታተን ሆኖ ሲቀርብ ነው የሚለው ድምዳሜ ትክከል አይደለም፡፡ ቅኔ ፍልስፍና ሊሆን የሚችለው ፍልስፍናዊ በሆኑ ሐሳቦች ላይ በአመክንዮ የተያያዘ የአስተሳሰብ ህንፃ መገንባት የሚችል ከሆነ ብቻ ነው፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ቅኔያችን ፍልስፍናን ሊያዋልድ ያልቻለበት አንድ መሰረታዊ ምክንያት አለ — ይሄውም ቅኔያችን የተለያዩና የተበታተኑ ሐሳቦችን መያዙ ነው፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ፣ ቀደም ብለን እንደጠቀስነው፣ ቅኔ ግጥም ነው — ሰምና ወርቅ ያለው ቃላትን የያዘ ግጥም። በዚህም ምክንያት ቅኔ የግጥምን ባህሪ የያዘ ነው። ምንድን ነው የግጥም ባህሪ? ቅኔ ከፍ ያሉ ፍልስፍናዊ ሐሳቦች ጭምር የሚንፀባረቁበት ቢሆንም ግጥም መሆኑ ግን ይጎትተዋል፡፡ ምክንያቱም፣ ቅኔ እንደ ግጥምነቱ የሚያነሳቸው ሐሳቦች የተበታተኑ በመሆናቸው የተነሳ ሐሳቦቹ ተያይዘው የባለ ቅኔውን ፍልስፍናዊ የአስተሳሰብ ሥርዓት (philosophical thought system) መፍጠር አይችሉም፡፡
ለምሳሌ ኤፍሬም ሥዩም ካዘጋጀው የሊቁ የተዋነይ፣ ቅኔዎች ውስጥ ነገረ መለኮትን የሚፈታተነውን አንድ ቅኔ እንመልከት፡-
 የአምን ወይገኒ፣
ኵሉ ዓለም በዘፈጠረ ለሊሁ፣
ብዙኃን እንዘ ይገንዩ ይሰግዱ ቅድሜሁ፣
ለነጽሮ ዝኒ ከመ እሥራኤል ይፍርሁ፣
ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ፣
ወ ፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ።
ኤፍሬም የዚህን ቅኔ የመጨረሻ ሁለት ስንኞች ሲተረጉም፣ “ሙሴ ፈጣሪን ወደደ፣ ፈጣሪም ሙሴን ፈጠረ” ይለዋል፡፡ በግሌ ያናገርኳቸው የቅኔ መምህራንም እንዲሁ ነው የሚተረጎመው እንጂ “ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ” የሚለው ስንኝ፣ “ሙሴ ፈጣሪን ፈጠረ” ተብሎ አይተረጎምም ብለውኛል፡፡ እዩት እንግዲህ ፍርደ ገምድልነታቸውን!! - ‘ፈጠረ’ የሚለውን ቃል ለሙሴ ሲሆን ‘ወደደ’፣ ለፈጣሪ ሲሆን ደግሞ ‘ፈጠረ’ እያሉ ይተረጉሙታል። ይህ ትርጓሜ፣ “ሙሴ ፈጣሪውን ፈጠረ ብሎ አንድ ክርስቲያን ሊጽፍ አይችልም” ከሚል ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ የፈለቀ እንጂ ትርጓሜው ከላይ ያሉት ስንኞች ከሚነግሩን አውድ ውጭ ነው።
ይሄ ነው እንግዲህ የእኛነታችን ተቃርኖ!! በአንድ በኩል በቅኔያችን ውስጥ ፍልስፍና አለ እያልን እየተከራከርን፣ በሌላ በኩል ግን ክርስትያን እንዲህ ሊያስብ አይችልም በማለት ከዐውዱ አውጥተን ትርጉም እናዛባለን፡፡ ቅኔውን ሃይማኖታዊ በሆነው የትርጉም አጥር ውስጥ ብቻ አምቀን፣ነፃነቱን ስንነፍገው ደግሞ ቅኔው ወደ ፍልስፍና የሚያድግበትን እድል እንዘጋዋለን።
የመጨረሻዎቹ ሁለት ስንኞች፣ ከላይ ያሉት ስንኞች ከሚነግሩን አውድ ጋር ሊጣጣሙ የሚችሉት “ሙሴ ፈጣሪን ፈጠረ” ተብሎ ሲተረጎም ብቻ ነው። ሕይወት ተፈራም፣ “ኀሠሣ” በሚለው መፅሐፏ፣ ይሄንኑ ነው በድፍረት የፃፈችው፤ እንዲህ በማለት (የቅኔው ሙሉ ትርጉም)፣
የሰው ልጅ በገዛ’ጁ፣ ላስቀመጠው ፈጥሮ፣
ይገ’ዛል ባንክሮ፣
ሰው ፈርቶ እንዲገዛ፣ እንዲሰላ ኑሮ፣
ለዚኽም ማስረጃው የሙሴ ነገር ነው አምላኩን መፍጠሩ፣
 አምላኩም ፈጠረው በአምሳሉ በግብሩ።
ይህ “ሙሴ ፈጣሪን ፈጠረው” የሚለው የተዋነይ ቅኔ፣ ትልቅ የፍልስፍና መነሻ መሆን ይችላል። የሰውን ልጅ በመልኩ እንደ ምሳሌው የፈጠረው እግዚአብሔር ሳይሆን፣ ሰው ነው በመልኩ እንደ ምሳሌው እግዚአብሔርን የፈጠረው የሚለው ሐሳብ በዴቪድ ሂዩም (D. Hume 1711-1776)፣ በፎየርባህ (L. Feuerbach 1804-1872) እና በካርል ማርክስ ፍልስፍና ውስጥም አለ፡፡
ሆኖም ግን እነዚህ ምዕራባውያን ፈላስፎች እንዳደረጉት፣ ራሱ ተዋነይ ወይም የሱ ተማሪ ይሄንን ሐሳብ ለብቻው አዳብሮት፣ ራሱን የቻለ ሥነ ዓለማዊ (Metaphysical) የሐሳብ ሥርዓትና ከዚህ የሐሳብ ሥርዓትም የሚመነጭ የግብረገብነት ህልዮት (Ethics) አላፈለቀለትም፡፡ ይሄ የተዋነይ ሐሳብ ግን በእነዚያ የምዕራባውያን የሐሳብ ሥርዓት ውስጥ በአመክንዮ የተሳሰረ፣ ራሱን የቻለ ትልቅ ስፍራ አለው፡፡
ተዋነይ “ሙሴ ፈጣሪን ፈጠረ” ከሚለው ፍልስፍናዊ ሐሳብ ተነስቶ፣ ራሱን የቻለ ሥነ ዓለማዊ የሐሳብ ሥርዓት ከማዋቀር ይልቅ፣ ይሄንን ሐሳቡን በሌላ ወቅት ላይ ይተወውና፣ የበፊት ሐሳቡን የሚቃረን ሌላ የመወድስ ቅኔ ያመጣል፤ እንዲህ የሚል፡-
ሰው - ባዶ ሰው፣ ራቁት ሰው፣
በረዶ ለበረዶ፣ መብረቅም ለመብረቅ ተገዥ እንዳለው፣
በኃጢአተኛው የሚፈርድበት፣
አምላክ በኢዮር (ሰማይ) ላይ መኖሩን ልቦናህ ሲያውቀው፣
የህይወቱ ዓመት በፍጥነት ለሚያልቅ ለዚህ ለባዶ ሰው፣
አጥንቱ መቃብር ለሚወርድ ለዚህ ለራቁት ሰው፣
በወርቅ ለመገዛት ልብህ እንዴት ከጀለ፣ ነገ አፈር ለባሹ አምላክ እንዲሆነው፡፡
በእነዚህ ሁለት የተዋነይ ቅኔዎች መካከል አመክንዮአዊ ትስስሩን (Logical Coherence) ጠብቆ የተገነባ የሐሳብ ሥርዓት (thought system) የለም። ከዚህ ይልቅስ ሁለቱ ቅኔዎች እርስበርስ የሚጣረሱ ሆነው ይታያሉ፡፡ የሀገራችን ቅኔና ባለ ቅኔዎች ይሄ ነው አጠቃላይ መገለጫ ባህሪያቸው - የተለያዩ ቅኔዎች ውስጥ የሚነሱ ሐሳቦች የተበታተኑና አልፎ አልፎም እርስበርስ የሚጋጩ ናቸው፡፡
ሐሳቦቹ የተበታተኑ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው ደግሞ አንድም የድንገቴነት ባህርያቸው ሲሆን፣ ሌላም በአብዛኛው ከተለያዩ ወቅታዊ ነገሮች (ወቅታዊ ስሜቶችን፣ ክስተቶችን፣ በዓላትን …ተንተርሰው) የሚመነጩ  መሆናቸው ነው፡፡ ሐሳቦቹ ከወቅታዊ ነገሮች መመንጨታቸው ደግሞ ከወቅታዊ ነገሮች ባሻገር ካሉት ዘላለማዊ የፍልስፍና ጥያቄዎች የራቁ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡
ቅኔያት ይሄንን ውስንነታቸውን ተሻግረው ፍልስፍናዊ ሐሳቦችን ቢያንፀባርቁ እንኳ ሐሳቦቻቸው ግን አሁንም የተበታተኑ ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ቅኔያቱ በተለያየ ወቅት ላይ በሚያነሷቸው ሐሳቦች መካከል በአመክኖያዊ ትስስር የሚገነባ ፍልስፍናዊ የሐሳብ ሥርዓት አይፈጥሩም፡፡
ሌላ ተጠራጣሪ ባለ ቅኔ የተቀኘውን ቅኔ ደግሞ እንመልከት፡፡ ይህ ባለ ቅኔ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ “በመጀመሪያ ቃል ነበር፤ …ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ፀጋንና እውነትንም ተሞልቶ በእኛ አደረ፡፡” የሚለውን የሐዋርያው የዮሐንስ መልዕክት ላይ ያለውን ጥርጣሬ በቅኔ ሲገልፅ እንዲህ ይላል፡-
ቃልን ሥጋ ማድረግ፣
ቃልን ማበላሸት ነው፤
ሥጋ ደካማ ነውና፡፡
ይህ ተጠራጣሪ ቅኔ የፍልስፍና መነሻ መሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ጠርጣሪነት (Skepticism) አንዱ የፍልስፍና ዘውግ ነውና፡፡ ሆኖም ግን ይህ ጠርጣሪነት በኢትዮጵያ ፍልስፍና ውስጥ ራሱን የቻለ ዘውግ ሆኖ መውጣት የሚችለው ባለ ቅኔው በዚህ ተጠራጣሪነቱ ፀንቶ፣ ቅኔዎቹ በሙሉ ይሄንን ተጠራጣሪነቱን ይበልጥ እያጠናከሩ የሚሄዱ ከሆነና በቅኔዎቹ መካከልም በአመክንዮ የተሳሰረ የሐሳብ ዝምድ ሲፈጠር ብቻ ነው። ሆኖም ግን እንዳለመታደል ሆኖ፣ የኛ ሀገር ባለቅኔዎች፣ እንደዚህ ዓይነት ወጥ የሆነና እየተገነባ የሚሄድ የሐሳብ ሥርዓት (thought system) የላቸውም። ቅኔ የሚቆጥሩት ወቅታዊ ክሰተቶችን ተከትለው ስለሆነ በቅኔያቸው ውስጥ ያሉት ሐሳቦች የተበታተኑና እርስበርስም የማይደጋገፉ ናቸው፡፡
በመሆኑም፣ በተለያዩ ቅኔዎች መካከል በየጊዜው የሚገነባ አንድ ወጥነት ያለው ፍልስፍናዊ የሐሳብ ሥርዓት መዘርጋት ስለማይቻል፣ የኢትዮጵያን ፍልስፍና ከቅኔያት ውስጥ ማውጣት አይቻልም። ስለዚህ፣ የሚሻለው ነገር የቅኔን ውበት በዚያው በቅኔነቱ መያዝ ነው እንጂ፣ ቅኔን ፍልስፍና ነው እያሉ መከራከር፣ አንድም በፍልስፍና መቅናት ነው፤ ሌላም የቅኔን ውበት ማሳነስ ነው፡፡
በአንፃሩ ዘርዓያዕቆብ ራሱን የቻለ ፍልስፍናዊ የሐሳብ ሥርዓት እንዴት እንደዘረጋ እንመልከት። በመጀመሪያ ዲበአካላዊ ፍልስፍናውን ከስር አነጠፈ፤ እንዲህ በማለት፡-
ፍጡር ያለፈጣሪ ሊኖር አይችልም፡፡ ስለዚህ ፈጣሪ አለ፡፡ ፍጡር አዋቂ ከሆነና ጥበብንም የሚያንፀባርቅ ከሆነ፣ የእነሱ ፈጣሪ ይበልጥ አዋቂና ጥበበኛ የመሆኑ ነገር የግድ ነው፡፡ ፈጣሪ ከነፍስና ከስጋ ሰውን ፈጠረ። በፈጣሪ የተፈጠረ ነገር ሁሉ መልካም ነው፡፡ ስለዚህ ነፍስና ስጋ በፈጣሪ የተፈጠሩ ስለሆነ እርስበርስ የሚቃረኑ አይደሉም፤ ነፍሳችን እንድትፀድቅ ስጋችንን እንጣላት የሚባል ነገር የለም፡፡
ይሄ ነው የዘርዓያዕቆብ ሜታፊዚክስ፤ በመጀመሪያ ከሃይማኖታዊው አስተሳሰብ ይነሳና በስተመጨረሻ ግን ስለ ሰው ልጅ እሳቤ (የነፍስና የስጋን ግንኙነት) በተመለከተ ከሃይማኖታዊው አስተሳሰብ ይገነጠላል። ዘርዓያዕቆብ በዚህ መልኩ ሜታፊዚክሱን ካነጠፈ በኋላ፣ በሜታፊዚክሱ ላይ የሥነምግባር እሳቤውን (ስለ ምንኩስና፣ ስለ ፆም፣ ስለ ባርነት፣ ስለ ሴቶች፣ ስለ ብልፅግና) በአመክንዮ እየገነባ ይሰራል፡፡ በዘርዓያዕቆብ ሜታፊዚክስና በሞራል ፍልስፍናው መካከል ምንም ዓይነት ቅራኔ የለም፡፡ ይሄ ነው ፍልስፍናዊ የአስተሳሰብ ሥርዓት ማለት፡፡ አንድ ሰው ሃይማኖታዊው አስተሳሰብ አይመቸኝም ቢል፤ ዘርዓያዕቆብ በዘረጋው ፍልስፍናዊ የአስተሳሰብ ሥርዓት ውስጥ መኖር ይችላል፡፡ ደግሞም ራሱ ዘርዓያዕቆብ ኖሮበት አሳይቶናል፡፡ በቅኔ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት አማራጭ የሆነ ፍልስፍናዊ የአስተሳሰብ ሥርዓት ማግኘት አንችልም፡፡
የአዘጋጁ ማስታወሻ፡ (ጸሐፊው፤ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ሲሆን “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” መጽሐፍ ደራሲም ነው፡፡ በኢ-ሜይል አድራሻው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡)





Read 16567 times