Print this page
Monday, 25 September 2017 12:09

“ቋንቋ እና ብሔረተኝነት”

Written by  ሒስ፡- በዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ
Rate this item
(5 votes)

ጸሐፊ ፡- ሑሴን አዳል መሐመድ (ዶ/ር)
የገጽ ብዛት:- 293
የኅትመት ዘ መን:- 2 009 ዓ .ም.
ሒስ፡- በዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ

     የአንድ መጽሐፍ የሐሳብ ከፍታና ጥልቀት በብዙ መንገድ ሊፈተሽ ይችላል፡፡ ማንኛውም ጽሑፍ የራሱ የብቻ አቀራረብ ይኑረው እንጂ፣ ንባብና የአረዳድ ዓይነት መልከ ብዙ በመኾኑ፣ በተለያየ አንድምታ እየተተነተነ መቅረቡ፣ ባሕርያዊ የንባብ ወግ ነው፡፡ እኔም፣ “ቋንቋ እና ብሔርተኝነት” ብለው፣ ዶ/ር ሑሴን አዳል የሰየሙትን መጽሐፍ፣ መጀመሪያ፤ የአቀራረብ መንፈሱን፣ በመቀጠልም፤ ጽሑፋቸው ያቀረበውን ፅንሰ ሐሳብና የተመረኮዘበትን የአመለካከት ጥንካሬ ልመለከተው ወደድኹ፡፡
ከመጽሐፉ የአቀራረብ መንፈስ ጋራ፣ ጽሑፉ የያዛቸውና በተለየ ዐውድ የሚያስተዋውቃቸው፣ በፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ያሉትን ተግዳሮቶችና ቅራኔዎች የሚገልጹ ቃላትን ብንጠቅስ፡- “አብሮነትን” የሚገዳደር “የቋንቋ አጥር”፣ “የአማራ ብሔርተኝነትን” የሚገዳደር “የአማራ ዴሞክራሲዊ ብሔርተኝነት”፣ አንድ ላይ የቆመ“ የዘር መለያየት” እና “የዘር ማነባበር”፣ “በቋንቋ ፖሊሲ አልባነት” የተፈጠረ “የቋንቋ ጉራማይሌ”፣ “ከአንድ ገዢ መደብ” የሚነሣ “የተዋሐደ ገዢ መደብ” ተቃርኖ፣ የሚሉት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡
መጽሐፉ ስለ ሀገራችን ታሪክና የፖለቲካ ሥርዓት የተለያዩ ርእሶችን ያነሣል፡፡ በሚያነሣቸው ርእሰ ጉዳዮች ላይ፣ “ትችት ከመሠረቱ ውስጣዊ መኾን ይኖርበታል፤” ብሎ፣ አሪስቶትል እንዳስተማረው፤ ዶ/ር ሑሴን የሚሰነዝሯቸው ትችቶች፣ ሀገራዊ የመንግሥት ፖሊሲዎችን፣ የፓርቲ (የብአዴን/ኢሕአዴግ) ፖለቲካዊ ፕሮግራሞችን በሚገባ በመፈተሽ፣ ፕሮግራሞቹን፥ አዘጋጆቻቸው ባስቀመጡላቸው መርሖዎችና አፈጻጸሞች ላይ ተመርኩዞ ውስጣዊ ትችት ያቀርባል፡፡
ይኸውም፣ ብዙ ጊዜ እንደተለመደው፣ ከውጭ ወደ ውስጥ የሚደረገውን የትችት ልማድ ውስንነት የተሻገረ የሒስ ዘይቤ ነው፡፡ ዋናተኛ ሲዋኝ፣ የነፋሱንና የማዕበሉን አቅጣጫ ተከትሎ እንደሚዋኘው፣ አስተሳሰብም፣ ብዙ ጊዜ የተለመደውን ወይም ብዙዎች የተስማሙበትን የስምምነት ምኅዋር ተከትሎ መጓዝ ነው፡፡ በተለየ አቅጣጫ የሚያስቡ ሰዎችን ወይም የማዕበሉን ተቃራኒ የሚከተሉቱን፣ ትልቁ የ20ኛው ክፍለ ዘመን የአስተሳሰብ ታሪክ ሊቅ ሰር አይዛያ በርሊን፤ “Against The Current” በሚለው አስደማሚ መጽሐፋቸው፣ “ሰዎች ከተስማሙበት የወል ሐሳብ ጎዳና ውጪ የሚቆሙ፣” ካሏቸው ዓይነት ሰዎች ጋራ ጸሐፊውን ልንመድባቸው እንችላለን፡፡
ደራሲው ወደ ዋናው የመጽሐፉ ይዘት ከመግባታቸው በፊት፣ ስለ ሀገር ፍቅርና ስለ የኢትዮጵያዊነት ስሜት፣ ሦስት ነጥቦች ላይ በማተኮር አጠር ያለ ትንተና ያቀርባሉ። እነኚህም፣ ሀ/የሀገር መውደድ ጸጋ፤ ለ/ የሀገር የበላይነት፣ ሐ/ ማንነት በሀገራዊነት ውስጥ፣ ያሏቸው ነጥቦች፣ እንደ መሸጋገሪያ መደላድሎች ኾነው ወደ መጽሐፉ ዐቢይ ጉዳይ ይወስዱናል፡፡
ሀ) የሀገር መውደድ ጸጋ፤
ዶ/ር ሑሴን፣ “ሀገርን መውደድ ትልቅ ጸጋ ነው፤” ይሉናል፡፡ ኢትዮጵያ፤ በእጅጉ የሚያኮራ ታሪክ፣ የሚከበሩ የሞራል ዕሴቶች፣ ጥንታዊ ታላላቅ (የአይሁድ፣ የክርስትና እና የእስልምና) ሃይማኖቶች፣ ከሺሕ ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ ታላላቅ የዕውቀት የልሕቀት ማዕከላት፣ ከጥቁር ሕዝብ ብቸኛ ሥነ ጽሑፍ፣ ያሬዳዊ ዜማ፣ መንዙማና ነሺዳ፣ በሕክምናውም በኩል “የሥር መማስና ቅጠል መበጠስ” (ሐርባሊዝም)፣ ጠቅለል ሲል፥ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት በመኾኗ፣ በዜጎቿ በእጅጉ መከበርና መወደስ እንዳለባት አበክረው ገልጸዋል፡፡
ለ) የሀገር የበላይነት፣
ከቅርቡ የሀገራችን ታሪክ በመነሣት፣ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን፣ ዘለቄታዊ የሀገር ጥቅምን ወደ ጎን በማድረግ፣ “እንደምን ለውጪ ጠላት ድብቅ ፍላጎት አገልጋይ እንደሚኾኑ፤” ለመግለጽ ሞክረዋል፡፡ “ከሩቅ ጠላቴ ጋራ ኾኜ፣ የቅርብ ጠላት ላጥቃ፤” የሚለው አመለካከት በእጅጉ ሀገር እንደሚጎዳ፤ ኹለት የቀድሞ የህወሓት መሪዎች፥ ለሻዕቢያ የተሰጠው ገደብ የለሽ ዕውቂያ ታሪካዊ ስሕተት እንደኾነ በጸጸትና በቁጭት፣ ለአሜሪካ ድምፅ ራድዮ የሰጡትን ቃለ ምልልስ እንደ ምሳሌ ጠቅሰው ያስረዱናል፡፡
እዚህ ላይ፣ ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ፣ ከዐፄ ኃይለ ሥላሴ ጋራ የተጣሉ፣ አንዳንድ ባላባቶች፣ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋራ በነበራቸው የግል ፀብና ቁርሾ፣ ለጣሊያን በማደር፣ ታሪካዊ ስሕተት ስለ መሥራታቸው የሚታወቀውን ያህል፤ በአንጻሩ፤ ከንጉሡ ጋራ ጠበኞችና ከሹመታቸው የተሻሩ ኾነው ሳለ፣ “የሀገር ጉዳይ ከግል ጠብ በላይ ነው፤” በማለት፣ በአርበኝነት ተሠማርተውና ተዋግተው፣ ለሀገር መሥዋዕትነት ከከፈሉት ውስጥ፣ እነ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎን (አባነፍሶ) እና ደጃዝማች በየነ ወንድማገኘሁን (ሊጋባ) መጥቀስ ይቻላል፡፡
ሐ) ማንነት በሀገራዊነት ውስጥ፣
አሁን ያለው መንግሥት፤ “ከቀድሞዎቹ ሥርዓቶች በተሻለ፣ ዴሞክራሲያዊ በኾነ መንገድ የሕዝቦችን የማንነት ጥያቄ ተቀብዬ የመጨረሻ ዕልባት ሰጥቻለሁ፤” የሚለው አቋሙን፣ ዶ/ር ሑሴን አዳል፣ ጥያቄ ውስጥ ያስገቡታል፡፡ እንደገናም “የማንነት ጥያቄ ለመጨረሻ ጊዜ ተፈቷል፣ ተደምድሟል፤” እያሉ ኦፊሴላዊ መግለጫዎች ከመስጠት ባሻገር፣ በሀገሪቱ የተለያዩ ግዛቶች ላይ እየተነሡ ያሉትን የማንነት ጥያቄዎች እንደገና ለመመልከትና አግባብ ያለው መፍትሔ ለመስጠት ጥረት እንደሚያስፈልግ ደራሲው ይጠቁማሉ፡፡
በቅርቡ ግን፣ መንግሥት በፊት ከነበረው ቀኖናዊ ግትርነት ሻገር በማለት፣ የማንነትን ጥያቄ ለመመልከት ሙከራ እያደረገ ቢኾንም፣ በአካሔዱ ላይ ግን ኹለት መሠረታዊ ችግሮች እየታዩ እንደኾነ ደራሲው ያሳዩናል፤
1ኛ) በመሠረታዊነት፣ ላቀረበው የማንነት ጥያቄ መልስ በሚጠብቀው የኅብረተሰብ ክፍልና ጉዳዩ በሚመለከተው አካል መካከል የጥቅም ግጭት እንዳለ እንረዳለን፡፡ ዶ/ር ሑሴን፣ ይህን ኹኔታ ለማስረዳት በሰጡን ትንታኔ ላይ፣ በስም ጠቅሰው “ወልቃይት” አላሉትም እንጂ፣ የሐሳቡ አንድምታ የት እንዳረፈ ግን በግልጽ ተቀምጧል፤ የሚል እምነት አለኝ፡፡ አቤቱታ አቅራቢ፥ ወልቃይት፣ ዳኛ፥ የትግራይ ክልል መንግሥት መኾኑ፤ መሠረታዊ የኾነን የሕግ የበላይነት መርሕ የሚጥስ ጉዳይ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት እንደሚያስረዳን፤ “አንድ ሰው በራሱ ጉዳይ ላይ፣ ራሱ መልሶ ዳኛ ሊኾን አይችልም፤” የሚለውን ቀዳሚ መርሕ የጣሰ በመኾኑ ነው፡፡ አካሔዱ የጥቅም ግጭት ስለሚያመጣ፣ ውጤቱ አስቀድሞ ፍትሐዊ እንደማይሆን መተንበይ አያስቸግርም፡፡
በተጨማሪም፣ የእርሳቸውን ትንታኔ ተመርኩዘን፣ ከላይ የጠቀስነውን የወልቃይትን ጉዳይ እንደ ምሳሌ ብንወስድ፣ ስለ አካባቢው ኹኔታ የመንግሥት ወኪሎች፤ “ጥያቄው መፈታት ያለበት፣ በትግራይ ክልላዊ መንግሥት ነው፤” ይሉና፣ “ክልሉ መፍታት ካቃተው ግን፣ ጉዳዩ ወደ ፌደራል መንግሥቱ ይመጣል፤” ይላሉ፡፡ ይህንንም ለማለታቸው ሕገ መንግሥቱን እንደ ዋቤ ይጠቅሳሉ። እዚህ ላይ በወሳኝነት ሊነሡ የሚገባውቸውን ሦስት ጥያቄዎች እናቅርብ፣
ይህ ለዓመታት የከረመ ደም ያፋሰሰ ኹኔታ፣ ምን ያህል የጥፋት ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው፤ ክልሉ መፍትሔ ማቅረብ አልቻለም የሚባለው?
ጉዳዩ ከክልሉ አቅም በላይ ነው ተብሎ የሚበየነው፣ ያለዕልባት ካኹን በኋላ ስንት ዓመታት ሲያስቆጥር ነው?
ክልሉ የወልቃይትን ጥያቄ አልፈታም ወይም ፈቷል ብሎ የሚወስነውስ ማን ነው? ማለትም፣ ይህን ውሳኔ እንዲሰጥ የተፈቀደው ለክልሉ ወይስ ለወልቃይቴው?  
2ኛ) እንደ ዶ/ር ሑሴን አቀራረብ፣ የማንነነትን ጥያቄ በሚገባ ለማስተናገድ፣ አስቸጋሪ የኾነው ሌላው ጉዳይ፣ ለኹሉ የሚኾን ሁነኛ የአሠራር ስልትና መመሪያ አለመኖር እንደኾነ እንረዳለን፡፡ ይህን ለማየት የሚከተለውን አገላለጽ ከመጽሐፉ እንውሰድ፤
“ አንዳንዴ የተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል፣ የማንነነት ጥያቄ ይከበርልን ብሎ፣ እንዲነሣሣ ለመቀስቀስም ኾነ፣ ለቀረበ የማንነት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት፣ ቋንቋ ወሳኝ መሥፈርት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በሌላ ወቅት፣ ቋንቋው ጭራሽ በመጥፋቱ የተነሳ፣ በሚናገሩት ቋንቋ ብቻ ማንነታቸውን ለመለየት የሚያስቸግር የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የመንግሥት ድጋፍ አግኝተው መጠሪያ ስም ያወጣሉ፡፡” (ገጽ.16)
ከዚህ የምንረዳው የማንነት ጥያቄን፣ ከማኅበረሰባዊ ተፈጥሯዊ እውነታው በመነሣት ከማስተናገድ ይልቅ፣ በፖለቲካ ኃይሎች ፍላጎትና ውሳኔ፣ በስያሜ የማንነት መልክ እንዲይዝ ያደረገ ውሳኔ መሰጠቱ፣ ወደ ኋላ ላይ፣ ችግር እንደሚያስከትል መዘንጋት የለበትም፡፡
ነገረ ቋንቋ፣
ደራሲው በትንታኔያቸው ውስጥ ቋንቋን ከባህላዊ ህላዌው ጀምረው፣ የማኅበረሰብ አንዱ መገለጫነቱን በአጽንዖት ካስረዱ በኋላ፣ በአንጻሩ፣ የአንድ ሕዝብ ብቸኛ መለያና ማካለያ ማድረግ ግን ተገቢ እንዳልኾነ በሰፊው ሞግተዋል፡፡ ቋንቋን በተመለከተ ዶ/ር ሑሴን ያቀረቡት ሐሳብ፣ በኹለት መደብ የተከፈለ ነው፡፡ በመጀመሪያ፥ ቋንቋ እና ማኅበረሰብ በሚል ክፍል፤ ኹለተኛው፥ አማርኛ ቋንቋ የገጠመው ችግር፤ የሚሉ ናቸው፡፡
ቋንቋ እና ማኅበረሰብ፣
ቋንቋ ወሳኝ የሰው ልጅ የማንነነት መገለጫ ቢኾንም፣ የአስተዳደር ክልል በሚቋቋምበት ወቅት፣ ቋንቋን እንደ ብቸኛ መሥፈርት መውሰዱ ተገቢ አይኾንም፡፡ እንደ እርሳቸው አባባል፡-
“በአዲስ የአስተዳደር ክልል ውስጥ የሚከለሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የማንነት ጥያቄ በአግባቡ ለማስተናገድ ቋንቋን ጨምሮ፣ የሕዝቡን ባህል፣ የጋራ ታሪክን፣ ሥነ ልቡናን፣ መልክአ ምድርን፣ የተፈጥሮ ሀብትን፣ የጋራ ተጠቃሚነትን፣ ከሕዝቡ የሚመነጭ ፍላጎትንና ተጨማሪ ሌሎች የሕዝብ ማንነት ገላጭ መሥፈርቶችን ከግምት ውስጥ ማስገባት ይጠይቃል፡፡” (ገጽ፣ 39-40)
ቋንቋን በብቸኝነት እንደ አንድ ወሳኝ መሥፈርት ወስደን፣ ለሕዝቦች ማንነትና መለያ በምናደርግበት ወቅት፣ ትልቅ ስሕተት ውስጥ እንወድቃለን፡፡ በርካታ መሥፈርቶችን መጠቀም፣ አስፈላጊ የሚኾንበት ምክንያት፣ በአስተዳደር ክልሉ ውስጥ የሚከለሉ ሕዝቦችን “የአብሮነት እና የእኛነት” ስሜት ጠብቆ በፍትሐዊነት ለማስተናገድ እንዲቻል ነው፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ፣ የወሎን ሕዝብ ኅብራዊነት እንደ ምሳሌ በመውሰድ ለገለጻቸው ተገቢና ገሐዳዊ ማስረጃ ያቀርባሉ፡፡
እንደ ደራሲው አመለካከት፤ “በወሎ የሚታየው ከዘር ልዩነትና ጥላቻ የጸዳ አስተሳሰብ፣ ለሀገራችን አንድነትና ዕድገት ትልቅ ማሳያ ነው፡፡” ኾኖም ግን፤ ከአሁን ቀደም ስድስት ብሔረሰቦች አብሮ በመኖር ያዳበሩትን ጠንካራ የወሎዬነት ስሜት፣ “በቋንቋ መክፈል” በሚል ሰበብ፣ ሕዝቦቹ ወደተለያዩ ክልሎች እንዲካተቱ መደረጋቸውን ጸሐፊው ይተቻሉ፡፡ እንደ እርሳቸው አተያይ፣ ይህ ዓይነቱ ቋንቋን ብቻ መሠረት ያደረገ የመበታተን ሒደት፣ ለኅብረ ብሔራዊ ሀገራዊ አንድነት ፍጹም የማይበጅ መኾኑንም አትተዋል፡፡
የአማርኛ ቋንቋ የገጠመው ችግር፣
ጸሐፊው ስለ አማርኛ ቋንቋ አመጣጥ በጣም ጠቃሚና አጠር ያለ መረጃ ከሰጡን በኋላ፣ በቀጥታ ወደ አማርኛ ቋንቋ ሥርዓተ ትምህርት፣ ቋንቋው በየዘመኑ የገጠመውን ችግር፣ ከዚህም ጋራ በማያያዝ አማርኛ ቋንቋን ለማዳከም የተወጠኑ ስልቶችን፣ በመጨረሻም የቋንቋው ዕጣ ፈንታ፣ በአማራ ሕዝብ ብሔርተኝነት ላይ ያመጣውን ጫና ተንትነውታል፡፡
እንደሚታወቀው፣ ሀገሪቱ ቋሚ የኾነ የቋንቋ ፖሊሲ የላትም፡፡ በመኾኑም፣ “በኢፌዴሪ፣ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 5 በተደነገገው መሠረት፣ አማርኛ የፌደራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ መኾኑን ተከትሎ፣ ብሔራዊ ክልሎች የአማርኛን ሥርዓተ ትምህርት፣ በትምህርት ሥርዓታቸው ውስጥ ያካተቱ ቢኾንም፣ የትምህርት አሰጣጡ በተገቢው መጠን አይካሔድም፤” ሲሉ ዶ/ር ሑሴን ይተቻሉ፡፡ ይህም ማለት ብሔራዊ ክልሎቹ፣ ፖሊሲውን አንድ ወጥ በኾነ አተገባበር አያከናውኑትም፤ ማለት ነው፡፡
በተጨማሪም፣ አማርኛ ቋንቋ እንዲበለጽግ፣ የግእዝ ቋንቋ ረዳትነት በእጅጉ እንደሚያስፈልገው በሊቃውንቱ ይታመናል፡፡ ከእነርሱም አንዱ፣ ሊቀ ጠበብት አክሊለ ብርሃን ወልደ ቂርቆስ ቀደም ሲል፣ “ግእዝ ለአማርኛ ዕድገት አስፈላጊ ነው፤” ሲሉ፣ ሰጥተውት የነበረውን ምክር ወደ ጎን በመተው፣ የግእዝ ድጋፍ ለአማርኛ ይጨምርለት የነበረው ትልቅ ጸጋ እንዲቀርበት ማድረግ፣ ቋንቋውን እንደ መበደል ነው፤ ይላሉ፡፡  
ይባስ ብሎም፣ በግል ትምህርት ቤቶች፣ አስተማሪዎችና ተማሪዎች፣ አማርኛን ዝቅ አድርገው እንዲመለከቱ ስለሚደረግ፣ ቋንቋው በኅቡእና በገሐድ ተጽዕኖ እየደረሰበት ነው፡፡ ይህንንም ለማድረግ ተቀዳሚ መሣሪያ አድርገው የሚጠቀሙት፣ “ዕውቀትና የእንግሊዝኛ ቋንቋ የማይነጣጠሉ መኾናቸውን”፣ በአንጻሩ፣ “አማርኛ ቋንቋን ማወቅ፣ ምንም ዓይነት የዕውቀት ትሩፋት እንደሌለው፣” አድርገው ያቀርባሉ፡፡ በመኾኑም፣ ተማሪዎች እንግሊዝኛ በተናገሩ ቁጥር እንደ አዋቂ፣ አማርኛ በተናገሩ ቁጥር እንደ አላዋቂ ይቆጠራሉ። ይህም በመኾኑ፣ በየትምህርት ቤቱ የተመደቡ የአማርኛ ቋንቋ መምህራን፣ የሚገባቸውን አክብሮት እንዳያገኙ አድርጓል፡፡  
ከአማርኛ ቋንቋ ክሂል እጥረት ጋራ ተያይዞ የሚመጣው ክፍተት ግን፣ በከፍተኛ ትምህርት ገበታ ላይ በገሐድ እየታየ መጥቷል፡፡ ይኸውም፣ በአብዛኛው ከተለያየ ክልል የሚመጡ ተማሪዎች፣ አማርኛ መናገር ስለማይችሉ፣ ቀደም ሲል፣ በእንግሊዝኛ ሲማሩ የከበዳቸውን ፅንሰ ሐሳብ፣ በአማርኛ እየተተረጎመ ሲቀርብበት የነበረውን አቀራረብ፣ አሁን ማድረግ ስላልተቻለ፣ አስተማሪዎቹም ኾኑ ተማሪዎቹ ችግር ላይ ወድቀዋል፡፡
በዚህ በኩል፣ ብ.አ.ዴ.ን.ም፣ ምናልባት በሌላ ነገር ስለተወጠረ፣ ለቋንቋ ጥያቄ እስከ አሁን ትኩረት አልሰጠውም፡፡ እንደ ድርጅት፣ በቋንቋ ላይ የሚደርሰውን በደል ተቋቁሞ፣ ቋንቋው እንዲዳብርና እንዲበለጽግ ማድረግ ሲገባው፣ በባይተዋርነት መቆሙን ደራሲው በአጽንዖት ይተቻሉ፡፡
ጠቅለል አድርገን ስናየው፣ “የአማርኛ ቋንቋ የነፍጠኛ ቋንቋ” ተብሎ መፈረጁ፣ ከቋንቋው ቤተሰብ ያልኾኑ ልጆች እንዲያውቁት ወይም እንዲናገሩት የማያስችል የፖለቲካ ጫና አድርሶባቸዋል፡፡   
ብሔርተኝነት፣
ዋለልኝ መኮንን፡-
የዋለልኝ መኮንን ስም፣ ከብሔር ጥያቄ ጋራ በእጅጉ የተሳሰረ እንደኾነ ይታወቃል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የአማራን ብሔር በተመለከተ፣ ዋለልኝ ከነበረው አመለካከት ጋራ በተያያዘ የሚነሣው ግን፣ በአሉታዊነት እንጂ፣ አዎንታዊ በኾነ መልኩ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ዶ/ር ሑሴን በብዕራቸው ደፈር በማለት፣ ዋለልኝ፥ መወቀስ ሳይኾን መወደስ ያለበት፣ ከአማራ አብራክ የወጣ፣ ለብሔር ብቻ ሳይኾን፣ ለዴሞክራሲና መሬት ለአራሹ ብሎ በሰፊው የታገለ ሰው እንደነበር፣ ይገልጻሉ፡፡ በዚሁ አጋጣሚም ጸሐፊው፣ ዋለልኝን በሚመለከት፣ የአተያይና የአመለካከት እርማት እንዲደረግ ያሳስባሉ፡፡ እንደ እርሳቸው አመለካከትም፡-
የኢትዮጵያ ታሪክ እንደሚያስተምረን፣ በማንኛውም ሥርዓት ቁንጮ ላይ የሚቀመጡት ኃይሎች፣ ከአንድ ብሔር አብራክ የወጡ ሳይኾን፣ የአማርኛ ቋንቋን የሚጠቀሙ ሕብረ ብሔራዊ ምንጭ የነበራቸው የተዋሐዱ ገዥ መደቦች ናቸው፡፡ ይህ በሚኾንበት ገዜ፣ የገዢ መደቡ አባላት፣ ከራሳቸው ቋንቋም በተጨማሪ አማርኛም ስለሚናገሩ፣ ኹሉም ከአማራ ብሔር የወጡ ተደርገው መወሰዳቸው ትክክል አይደለም፡፡ ስለ ዋለልኝም ቢኾን፣ “…በኢትዮጵያ የነበረው ገዢ መደብ የወጣው፣ ምጣኔው ይለያይ እንጂ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አብራክ ነው፤”(ገጽ 96) የሚል የታሪክ አረዳድ እንደነበረው ደራሲው ይገልጻሉ፡፡  
ዋለልኝ “አነሣው” የሚባለው ነጥብ፣ “ከኹለት ብሔር ብሔረሰብ ሕዝቦች አብራክ ማለትም፣ ከአማራና ትግሬ ስለወጣ ነፍጠኛ ሥርዓት የነበረ ቢኾንም፣” ዛሬ ላይ የሚስተጋባው ግን፣ ስለ ነፍጠኛ አማራ ብቻ ነው፡፡ ይህን፣ “አማራ ነፍጠኛ” የሚለውን የአስተሳሰብ መስመር ገፍቶ እንዲወጣ ያደረገው የኢሕአዴግ የፖለቲካ መድረክ እንደኾነው ኹሉ፣ “የብ.አ.ዴ.ን. አባላትም ቢኾኑ፣ ከራሳቸው ብሔር ወጥቷል ስለሚባለው ነፍጠኛ ብቻ ከመናገር ውጪ፣ ስለ ሌላ ነፍጠኛ ተናግረው አያውቁም፤” (ገጽ 100)
ብሔርተኝነት እና ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት፤
በዚህ ንዑስ ርዕስ ዙሪያ፣ አማራውን እወክላለሁ፤ የሚለው ብአዴን፤ ስለ አማራው ብሔር ያለውን አቋም በመመርመር ጸሐፊው ሰፋ ያለ ትችት ያቀርባሉ። የትችቱ ሁነኛ ማጠንጠኛ፣ “የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን” በሚመለከት በቀረበው ፅንሰ ሐሳብ ላይ ነው፡፡ እንደ ጸሐፊው፤ ከአማራው ብሔር ውጪ ያሉትን ብሔሮች፣ ብሔርተኝነታቸውን እንዲያስፋፉ፤ ማለትም፣ በራስ መተማመንን፣ ባህልንና ቋንቋን ማሳደግን፣ ታሪካቸውንና ቅርሳቸውን መከባከብን፣ ወዘተ. እንዲያደርጉ ኹኔታዎች ሲመቻቹ፤ ወደ አማራው ብሔር ስንመጣ ግን፣ ብሔርተኝነቱን በማበልጸግ ፈንታ፣ በቅድሚያ ወደ “ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ግባ” መባሉን ነው፡፡ ይህም ከፈረሱ ጋሪውን እንደ ማስቀደም እንደሚቆጠር ደራሲው በስፋት አትተዋል፡፡ እንደ እርሳቸው አገላለጽ፤ “እንዴት ነው ብሔርተኛ ሳይኮን፣ ስለ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ማሰብ የሚቻለው? ይህ፤ ‘በቅድሚያ ማን ተፈጠረ? ዕንቁላል ወይስ ዶሮ?’ የሚለውን የተለመደ “ዕንቆቅልህ ምን አውቅልህ” ጨዋታ ይመስላል፤” (ገጽ 171) በማለት ጉዳዩን ገልጸውታል፡፡
ማጠቃለያ
ይህ መጽሐፍ በቋንቋና ብሔርተኝነት ዙሪያ መሠረታዊ ጥያቄ በማንሣት፣ ከዚህ ቀደም በርእሰ ጉዳዩ ላይ የነበረንን እይታ ደግመን መፈተሽ እንዳለብን በአንክሮ ያስገነዝበናል፡፡ ጸሐፊው ሐሳብን እንደወረደ የማይቀበሉና አቋማቸውን በሚገባ በምክንያታዊነት ሚዛን በመፈተሽ ወይም በማጠየቅ ያምናሉ፡፡ ይህን እምነታቸውንም በተዋበ አማርኛ እንደሚከተለው ይገልጹታል፡- “እንደ ወረደ መጠጣት የሚያረካው የሀገራችንን ቡና ብቻ ነው፤” በማለት፡፡
ለእርሳቸው፣ ማንኛውንም መርሕም ኾነ ትግበራ እንደወረደ መቀበልን ትቶ፣ የፍተሻና የጥያቄ መርሕን መሠረት አድርጎ፣ በትንተና የሚቀርብ መኾን አለበት፡፡ በሚያነሧቸው ጥያቄዎች ላይ፣ ያለፍርሃት ያመኑበትን አቋም፣ ግልጽ በኾነ አማርኛ የማስቀመጥ አቅማቸው አስደናቂ ነው፡፡ በመኾኑም፣ የመጽሐፉ አንባቢዎች፣ ዶ/ር ሑሴን፣ የሞራል ድፍረት እንዳላቸው በቀላሉ ሊገነዘቡ ይችላሉ፡፡  ደራሲው ያነሧቸው ጥያቄዎች፣ እንደ አንድ በሓላፊነት ላይ እንደተቀመጠ ምሁር፣ የሞራል ልዕልና ያላቸውና በሀገራችን የአካዳሚው ምሁራን ዘንድ ሊኖር የሚገባውን ሀገራዊ ሓላፊነትን የመወጣት ድርሻ ለማሳየት አርኣያ ኾነዋል፡፡
ጽሑፉን ያቀረቡበት ሥነ ጽሑፋዊ ለዛም፣ እጅግ ውብ የኾነ ብዕራዊ ትረካ እንዳላቸው የሚያሳይ ኾኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ የወሎን ተምሳሌታዊ ለዛን ተጠቅመው የሚያቀርቡት ትረካ፣ ለመጽሐፉ ትልቅ ሥነ ጽሑፋዊ ላህይ ጨምሮለታል፡፡ የዚህ መጽሐፍ አንባቢ፣ ጸሐፊው ለወሎ ልዩ ፍቅርና ቦታ እንዳላቸው በቀላሉ ማየት እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ ይኹን እንጂ፣ የደራሲው የወሎ “ናሽናሊዝም”፥ ኢትዮጵያዊነትን አቃፊ እንጂ ኢትዮጵያዊነትን ተጋፊ እንዳልኾነ በተዋበ ስንኝ ጭምር አስረድተዋል፡፡ በመኾኑም፣ ይህ መጽሐፍ መነበብ ያለበትና በሰፊው ለውይይት ሑዳድ መቅረብ እንዳለበት በትሕትና አሳስባለሁ፡፡  

Read 5483 times