Saturday, 23 September 2017 00:00

14ኛው “ኢትዮ ኮን” የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን ነገ ይጠናቀቃል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“የተሻለ ኮንስትራክሽን፣ ለተሻለች ኢትዮጵያ”


የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር በየዓመቱ የሚያዘጋጀው “ኢትዮ ኮን” ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን ባለፈው ረቡዕ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የተከፈተ ሲሆን ነገ አመሻሽ ላይ ይጠናቀቃል ተብሏል። “የተሻለ ኮንስትራክሽን፣ ለተሻለች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል በተከፈተው በዚህ ኤግዚቢሽን ላይ ከ100 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች የተሳተፉ ሲሆን ከውጭዎቹ ሀገራት፡- ቻይና ቱርክ፣ ህንድ፣ ደቡብ ኮሪያና ሌሎችም ተሳታፊ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በኤግዚቢሽኑ ላይ የኮንስትራክሽን እቃ አምራቾች፣ አቅራቢዎች፣ ዲዛይንና ስፔስፊኬሽን አዘጋጆች፣ ስራ ተቋራጮች፣ የሪል እስቴት አልሚዎች፣ ኤጀንቶች፣ የኮንስትራክሽን ማሽነሪ የአገር ውስጥ አምራቾች፣ አስመጭና አከፋፋዮች እንዲሁም ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዚዳንት ኢ/ር አበራ በቀለ በመክፈቻው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው የኮንስትራክሽን ዘርፍ፣ እድገቱ ጤናማና ትክክለኛ እንዲሆን ለማድረግ፣ ሀላፊነቱ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ቢሆንም በዋናነት ከዘርፉ ባለቤት ከኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ብዙ እንደሚጠበቅ ጠቁመው፣ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኤግዚቢሽኑ ምርትና አገልግሎትን ለጎብኚ በማቅረብ ብቻ ሳይወሰን የውይይት መድረክም አዘጋጅቷል፡፡ በዛሬው ዕለት ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ በኢሲኤ አዳራሽ፤ “ወቅታዊ የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ተግዳሮቶችና የእድገት ማነቆዎች”፣ “የቴክኖሎጂ ሽግግር በካፒታል ኢንተንሲቭ፣ በኮንስትራክሽን ዘዴ”፣ “የኮንስትራክሽን ግዢና የኮንስትራክሽን አስተዳደር”፣ “ብክነትና ሊን ኮንስትራክሽን” በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው  ውይይት እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 988 times