Monday, 25 September 2017 12:53

በህፃናት አመጋገብ ላይ አዲስ የስልጠና ማኑዋሎች ተዘጋጁ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

   በህፃናት አመጋገብ ዙሪያ በጥናት ላይ ተመስርቶ ያዘጋጃቸውን ማኑዋሎች ሰሞኑን ለባለድርሻ አካላት ይፋ ያደረገው  ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ፤ በስልጠና ማኑዋሎቹ አማካኝነት ሰፊ ለውጥ ይመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቋል። በተለይ ህፃናት ተወልደው 1 ሺህ ቀናት ድረስ ባሉት ጊዜያት ያለው አመጋገባቸው ለእድገታቸው ወሳኝ መሆኑን በተመለከተ በኦሮሚያ ክልል ሁለት ወረዳዎች በወላጆችና ህፃናት ላይ ውጤታማነቱን ማረጋገጥ እንደተቻለ የጠቆመው ወርልድ ቪዥን፤ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተወካዮችና በህፃናት ላይ ለሚሰሩ መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች፣ከትላንት በስቲያ በሳርማሪያ ሆቴል  ስልጠና ሰጥቷል፡፡
በስልጠናው ላይ በቀረበው ጥናታዊ ፅሁፍ፤ በሁለቱ ወረዳዎች በተለይ የህፃናት አመጋገብን አስመልክቶ በቤተሰብ ግንዛቤ ላይ በተሰራ ስራ፣ አመርቂ ውጤቶች መምጣታቸው የተገለጸ ሲሆን ይህንን የግንዛቤ ስራ ወደ አገር አቀፍ ደረጃ በማሳደግ፣ ህፃናትን ከመቀንጨር በመከላከል፣ በቂ ክብደት ኖሯቸው እንዲያድጉ በማድረግ፣ ምርታማ ዜጋን ለማፍራት አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው ብለዋል - በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ፣ የፕሮግራም ውጤታማነትና የማስተማር ስትራቴጂ ዳይሬክተር አቶ በየነ ገለታ፡፡ አዲሱ የስልጠና ማንዋል በተለይ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ግብአት በመሆን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ አገልግሎት ላይ እንደሚውልም ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል፡፡
ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ወደ 55 በሚጠጉ ወረዳዎች በአገር አቀፍ ደረጃ እንደሚሰራ የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ ትኩረቱንም በጤና፤ በትምህርት፣ በማህበረሰብ ልማትና በምግብ ዋስትና ላይ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የኒዩትሪሽን ዲፓርትመንት ቴክኒካል ሀላፊ አቶ በኩረፅዮን አሳሳኸኝ በበኩላቸው፤ ይህንን የህፃናት አመጋገብ በማስተካክል በኩል ዋናው ተዋናይ መንግስት ቢሆንም ወርልድ ቪዥን የጥናት ውጤቶችን ለመንግስት በማቅረብ የበኩሉን እንደሚወጣ ገልፀዋል፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች በምግብ እጥረት፣በሌላ አካባቢ በግንዛቤ እጥረት፣ ልጆች ከህፃንነታቸው ጀምሮ ሁለት ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ባለው ጊዜ የተመጣጠነ ምግብ እንደማያገኙ ጥናቱ በተደረገባቸው ሁለት ወረዳዎች መረጋገጡን የጠቆሙት አቶ በኩረፅዮን፤ በጥናቱ ወቅት ግንዛቤ ያገኙ ወላጆች፣ አመጋገብ ላይ በሠሩት ስራ አመርቂ ውጤት መምጣቱንና በስልጠና ማኑዋሎቹ በስፋት ለውጥ ይመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

Read 4498 times