Saturday, 30 September 2017 14:05

አንጎላ ከ38 አመታት በኋላ ፕሬዚዳንቷን ቀየረች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    ላለፉት 38 አመታት በጆሴ ኤድዋርዶ ዶስ ሳንቶስ ስትመራ የቆየቺውና ዜጎቿ የነዳጅ ሃብቷ ተጠቃሚ ሳይሆኑ የከፋ ኑሮን እንደሚገፉ የሚነገርላት አንጎላ፤ የቀድሞውን የመከላከያ ሚኒስትሯን ጃኦ ሎሬንኮን በሳምንቱ መጀመሪያ ቃለ መሃላ አስፈጽማ በፕሬዝዳንትነት ሾማለች፡፡አንጎላ ከአራት አስርት ዓመታት ገደማ በኋላ መሪዋን ብትቀይርም ይህ ነው የሚባል ለውጥ እንደማይጠበቅ የዘገበው ቢቢሲ፤ ለዚህ በምክንያትነት
ያስቀመጠውም፣አዲሱ ፕሬዚዳንት በእነዚህ አመታት በብቸኝነት ስልጣኑን ተቆናጥጦ የዘለቀው የገዢው ፓርቲ ኤምፒኤልኤ ቁልፍ ሰው መሆናቸውን ነው፡፡ፕሬዚዳንት ዶስ ሳንቶስ፣ የፕሬዚዳንትነቱን ቦታ ቢያስረክቡም፣ በፓርቲው ውስጥ ያላቸውን የአገሪቱን የፖሊስ አዛዥና የጦር ሃይል አዛዥ የመሾም ስልጣን ይዘው እንደሚቆዩ የጠቆመው ዘገባው፤ ይህም ሰውዬው ከወንበራቸው ቢነሱም አሁንም ቁልፍ ሚና እንዲጫወቱ እድሉን እንደሚሰጣቸው አመልክቷል፡፡በነዳጅ ሃብት በበለጸገቺው አንጎላ፣ የሃብት ክፍፍል ልዩነቱ እጅግ ከፍተኛ ሆኖ መዝለቁን የጠቆመው ዘገባው፤ አዲሱ ፕሬዚዳንት በነባሩ የፖለቲካ ስርዓት ላይ ለውጥ ለማምጣት ቢያቅዱም ብዙ ፈተና ይገጥማቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጧል፡፡ አንጎላ ከፖርቹጋል ቅኝ አገዛዝ ነጻ ከወጣችበት ከ1975 አንስቶ በገዢ ፓርቲነት የዘለቀው የኤምፒኤልኤ ፓርቲ ሊቀመንበር በመሆን ለረጅም አመታት ስልጣንን የሙጥኝ ብለው የዘለቁት የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት፣ ከፍተኛ ነቀፋ ሲሰነዘርባቸው እንደቆዩ ያስታወሰው ዘገባው፤
የአፍሪካ ቁጥር አንድ ሴት ቢሊየነር የሆነቺው ልጃቸው ኤልሳቤጥ ዶስ ሳንቶስም አባቷን መከታ በማድረግ፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ተቆጣጥራዋለች በሚል እንደምትተች አስረድቷል፡፡

Read 651 times