Saturday, 30 September 2017 14:31

የኤርትራ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ስላለው ግንኙነት ለተመድ አቤቱታ አቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(19 votes)

የኤርትራ መንግስት፤ በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ አካባቢ ላለው አለመረጋጋትና የሰላም እጦት የኢትዮጵያ መንግስት ተጠያቂ ነው ሲል ሰሞኑን በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት 72ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ መውቀሱ ታውቋል፡፡
የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ኡስማን ሳሌህ መሃመድ በኩል ለተሰብሳቢዎች ባደረሱት መልዕክት “ኢትዮጵያ ግዛቴን በኃይል ወርራ እስከዛሬ ይዛለች፤ ለአካባቢው ሰላምም እንቅፋት እየሆነች ነው” ሲሉ ወንጅለዋል፡፡
ለ15 አመታት ግዛቷ በኃይል እንደተያዘባት ያስታወቀችው ኤርትራ፤ ይህም ለአካባቢው የደህንነትና ሰላም መጓደል ዋናው መንስኤ ነው ብላለች፡፡
ኢትዮጵያ አባል የሆነችበት የፀጥታው ም/ቤት ይህ አቤቱታዋን ተቀብሎ፣ ጉዳዩ አለማቀፍ ህግና ስምምነት መጣስ መሆኑን በመገንዘብ፣ እልባት እንዲሰጠው ጠይቃለች - ኤርትራ፡፡ በተጨማሪም እ.ኤ.አ በ2009 በተባበሩት መንግስታት የተጣለባት ማዕቀብ እንዲነሳላት በዚሁ ጉባኤ ላይ በአፅንኦት ተማፅናለች፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ “በኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራው የኤርትራ መንግስት በአካባቢው ያሉ አሸባሪዎችንና ፀረ - ሰላም ኃይሎችን ይደግፋል፣ ኢትዮጵያንም ሆነ የአፍሪካ ቀንድ አከባቢን ለማተራመስ ቀን ተሌት ይተጋል” በሚል በተደጋጋሚ ኤርትራን ወንጅሏል፡፡  





Read 8179 times