Print this page
Saturday, 30 September 2017 14:33

ወጋገን ባንክ በአገሪቱ ረዥሙን ህንፃ ዛሬ ያስመርቃል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(8 votes)

ለህንፃ ኪራይ በየዓመቱ 20 ሚ. ብር ሲያወጣ ቆይቷል

   ወጋገን ባንክ ስቴዲየም ፊት ለፊት ያስገነባውን ባለ 29 ፎቅ ዘመናዊ ህንፃ፤ በዛሬው ዕለት የሚያስመርቅ ሲሆን በአገሪቱ ረዥሙ ህንጻ ነው ተብሏል፡፡
የህንጻ ግንባታው ከ805 ሚሊዮን ብር በላይ እንደፈጀ የተገለጸ ሲሆን ህንጻውን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ከአምስት ዓመት በላይ እንደወሰደ ታውቋል፡፡  
ባንኩ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ዋና መሥሪያ ቤቱን ወደ አዲሱ ህንፃ እንደሚያዘዋውር የተገለፀ ሲሆን  ለዋና መሥሪያ ቤት የህንፃ ኪራይ፣ በየዓመቱ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ሲያወጣ መቆየቱ ተጠቁሟል። አዲሱ ህንጻ ባንኩን ከዚህ የኪራይ ወጪ የሚያድነው ሲሆን የህንጻውን የተወሰኑ ወለሎች በማከራየትም ተጨማሪ ትርፍ እንደሚያገኝበት አስታውቋል፡፡    
ህንፃው 550 የባንኩን የዋና መሥሪያ ቤት ሠራተኞች እንደሚይዝና ከ2ኛ እስከ 8ኛ ያሉ የህንጻው ወለሎች ለንግድ አገልግሎት እንደሚከራዩ ታውቋል፡፡ የተለያዩ መጠን ያላቸው የመሰብሰቢያ አዳራሾች እንዲሁም የሠራተኞች ካፊቴሪያ ያለው ህንጻው፤ 8 አሣንሠሮች (ሊፍቶች) ተገጥመውለታል፡፡ የህንጻው 3 የምድር ቤት ወለሎች የመኪና ማቆሚያ ሲሆኑ በአንድ ጊዜ አንድ መቶ ተሽከርካሪዎችን የመያዝ አቅም እንዳላቸው ተነግሯል፡፡
የህንጻ ግንባታውን ያከናወነው ጃንግዙ ኮርፖሬሽን ፎር ኢንተርናሽናል ኢኮኖሚስ ኤንድ ቴክኒካል ኮርፖሬሽን የተባለ የቻይና ህንፃ ተቋራጭ ሲሆን አማካሪው ኢቲጂ ኮንሰልታንሲ እንደሆነ ታውቋል፡፡  
ወጋገን ባንክ እ.ኤ.አ በ2025፣ በአፍሪካ ከሚገኙ አስር ስመ-ጥር ተፎካካሪ ባንኮች አንዱ ለመሆን ያስቀመጠውን ራዕይ ለማሳካት አዲሱ ህንጻ  ዋነኛ አጋዥ ይሆናል ተብሏል፡፡


Read 9106 times