Saturday, 30 September 2017 14:34

በደብረ ታቦር በርካቶች መታሰራቸውን መኢአድ አስታወቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

   በደብረ ታቦር ከቤተ ክርስቲያን የይዞታ መሬት ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ውዝግብ፣ በከተማዋ የተቃውሞ ሰልፍ  መደረጉን ተከትሎ፣ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ በርካታ ነዋሪዎች መታሰራቸውን መኢአድ አስታወቀ፡፡
ከጥንታዊው የደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ይዞታ፣ አንድ ሺህ አምስት መቶ ካሬ ሜትር መሬት፣ ካሳ ሳይከፈል፣ መንግስት ለልማት  መውሰዱን ተከትሎ፣ ሰሞኑን በተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ ከፖሊስ ጋር ግጭት በመፈጠሩ፣ በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ፓርቲው ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡
ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ወጣቶችና የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች መታሰራቸውን የጠቆሙት የመኢአድ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ፤ የፓርቲያቸው የዞኑ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ብርሃን አንለይን ጨምሮ አምስት የአመራር አባላት እንደታሰሩባቸው አስታውቀዋል፡፡
መንግስት የእምነት ቦታዎችን ጉዳይ በጥንቃቄ ማስተናገድ እንዳለበት ያሳሰቡት አቶ ሙሉጌታ፤ እንዲህ ያሉ ውዝግቦች እየተበራከቱ መምጣታቸው መልካም አይደለም ብለዋል፡፡ ግጭት ባስከተለው የደብረ ታቦር የተቃውሞ ሰልፍ ላይ 2ሺ ያህል ሰዎች መሳተፋቸውን የጠቆሙት አቶ ሙሉጌታ፤ አባሎቻቸው እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡
የአማራ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን በበኩላቸው፤ ቦታው ለቴሌቪዥን ማሰራጫ ሳተላይት ግንባታ መፈለጉን ተከትሎ ከአካባቢው ህዝብና ከቤተ ክርስቲያኑ የሰበካ ጉባኤ አባላት ጋር ተደጋጋሚ ውይይት ተደርጎ፣ “ማሰራጫው ቢገነባ ለኛም ይጠቅማል” በሚል እምነት ህዝቡ ተስማምቶ፣ በቦታው ላይ ግንባታ እየተከናወነ እንጂ በሃይል የተወሰደ አንዳችም መሬት የለም በማለት አስተባብለዋል፡፡
ህዝቡና የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ተስማምተው ባሉበት ሁኔታ ጥቂት ግለሰቦች ግርግር ለመፍጠር መሞከራቸውንና የክልሉ መንግስትም ህግ የማስከበር ስራ መስራቱን አቶ ንጉሱ ጨምረው አስረድተዋል፡፡ ሆኖም ጉዳት የደረሰበት ማንም ሰው እንደሌለ ተናግረዋል - አቶ ንጉሱ፡፡

Read 4978 times