Saturday, 30 September 2017 14:43

የህጻናት ‘ፊፍቲ ሼድስ ኦፍ ግሬይ’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

“-- ይሄ ጉዳይ ልንገምተው ከምንችለው በላይ አሳሳቢ ነው፡፡ ጥያቄው “እውነት የሚያሳስበን አለን ወይ” ነው፡፡ የጥቂት
ባህሪያቸው የተበላሸ፣ በተለምዶ ‘ቀጪ፣ ቆንጣጭ’ የሌላቸው ምናምን የምንላቸው፣ ታዳጊዎችና ወጣቶች ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡
የትውልድ ጉዳይ ነው፡፡----”


እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ብቻቸውን በደሳሳ ቤት ውስጥ ከኑሮ ጋር ትግል የያዙ እናት ናቸው፡፡ አንድ ቀን ረፋድ ላይ የማያውቋቸው አንድ ወንድና ሴት ታዳጊዎች ቤታቸው ይመጣሉ፡፡
“እማማ፤  ጓዳዎ ጥናት እንድናጠና እንዲፈቅዱልን ነው፣” ይሏቸዋል፡፡ ሴትዮዋ ግራ ይገባቸዋል፡፡ እንግዲህ ልጆቹ ዘመድ አይደሉ፣ የሰፈር ልጆች አይደሉ! እንዴት ብለው ነው ለማያውቋቸው ልጆች ጓዳቸውን የሚፈቅዱት! እያመነቱ እያለ ልጅቱ መቶ ብር እጃቸው ላይ ታስቀምጥላቸዋለች፡፡ ግድቡ ፈረሰ፣ ፈቀዱላቸው፡፡
ሴትዮዋ አንድ ሁለት ሰዓት ያህል ቆይተው፣ እንደው ልጆቹ እንዴት እየሆኑ እንደሆነ ለማየት፣ ወደ መጋረጃነት የተለወጠችውን አሮጌ አንሶላ ገለጥ አድርገው ያያሉ፡፡ እንደዚያን ጊዜ በህይወታቸው ደንግጠው አያውቁም፡፡ ልጆቹ ጥናት እያጠኑ አልነበረም፣ ሌላ ነገር እያደረጉ እንጂ፡፡ ሴትዮዋም ይጮሁና መቶ ብራቸውን ወርውረውላቸው እያካለቡ ከቤት ያስወጧቸዋል፡፡
እኚህ እናት ምን ያህል ስሜታቸው እንደሚጎዳ፣ በፈጣሪ ፊት ምን ያህል ከባድ ሀጢአት እንደሠሩ አድርገው እንደሚጨነቁ መገመቱ ቀላል ነው፡፡ እድሜ ልካቸውን እየራባቸውም፣ እየጠማቸውም “ተመስገን!” እያሉ ሲጸልዩ የኖሩት ለዚህ አልነበረም። በገዛ ቤታቸው፣ በገዛ ጓዳቸው እንዲህ አይነት ነገር ሰፈጸም ለማየት አልነበረም፡፡ ግን ባላሰቡት፣ ባልገመቱት መንገድ ሆነ፡፡ እናላችሁ…
“እዚህም ተደርሷል እንዴ!”
“ይሄን ያህል ርቀን ሄደናል እንዴ!”
“ይሄ ሁሉ የሚደረገው እዚሁ በዓይናችን ስር ነው እንዴ!”
ከማስባልም አልፈዋል፡፡
የምንሰማቸው ነገሮች የሆነ የህጻናት ‘ፊፍቲ ሼድስ ኦፍ ግሬይ’ ነገር እየመሰሉንም ነው፡፡
የምር ግን… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…አዲስ አበባ እንደዚህ ሆናለች፡፡ ወላ ‘ገስት ሀውስ’ ብሎ በሚያማምሩ ፊደላት፣ መንገድ ዳር ብረት መስቀል የለ፣ ወላ “ሙቅ ሻወር ያለውና ቁርስ በነጻ” ምናምን ብሎ ማስታወቂያ ማስነገር የለ…ችግረኞች እናቶች የሚኖሩበት ደሳሳ ጎጆ ፈልጎ፣ “እማማ፣ ጓዳዎት ማጥናት ፈልገን ነው፣” ማለት ነው። እናማ…የከተማችን ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል ታዳጊዎች፣ ትምህርት ቤቶቻቸው አካባቢ ደከም ያሉ መንደሮች ውስጥ፣ ደከም ያሉ  ቤቶች ጓዳዎችን ‘እየተከራዩ’፣ ለአቅመ አዳም መድረሻውን እድሜ፣ በአስደናቂ ፍጥነት ወደ ታች እያወረዱት ነው፡፡
የምንሰማቸው ነገሮች የሆነ የህጻናት ‘ፊፍቲ ሼድስ ኦፍ ግሬይ’ ነገር እየመሰሉንም ነው፡፡
ታዲያላችሁ… ይሄ ጉዳይ ልንገምተው ከምንችለው በላይ አሳሳቢ ነው፡፡ ጥያቄው “እውነት የሚያሳስበን አለን ወይ” ነው፡፡ የጥቂት ባህሪያቸው የተበላሸ፣ በተለምዶ ‘ቀጪ፣ ቆንጣጭ’ የሌላቸው  ምናምን የምንላቸው፣ ታዳጊዎችና ወጣቶች ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የትውልድ ጉዳይ ነው። ‘የነገ የአገር ተረካቢዎች’ ጉዳይ ነው፡፡ (ይሄ ነገር ለምንድነው ከጊዜ ወደ ጊዜ ‘የተጻፈበትን ጨርቅ የማይለቅ መፈክር’ ብቻ እየመሰለን የመጣው! ለግንዛቤ ያህል ነው፡፡)
እናማ…መቼም ብዙ ህዝባችን ያለበት የኑሮ ችግር የታወቀ ነው፡፡ በተለይ ጧሪ፣ ረዳት የሌላቸው በእድሜ የገፉ ችግረኞች በራቸውን አንኳኩቶ የመጣ ትንሽም ፍራንክ መመለስ ማለት፣ በረሀብ ሲሰቃዩ ውሎ ማደር ስለሚሆነባቸው፣ ነገርዬውን ወደ ‘ቢዝነስነት’ እየለወጡት ነው፡፡ ምን ያድርጉ! ተሠርቶም እንኳን ረሀብ ማስታገስ አስቸጋሪ የሆነበት ዘመን ነው! በነገራችን ላይ ብዙዎቹ፣ጓዳዎቹን የሚፈልጓቸው ለ‘አዳምና ሔዋን የሀጢአት ጦስ’ ብቻ ሳይሆን፣ ባብዛኛው ለጫት መቃሚያና ለሺሻ ማጨሻም ነው ይባላል፡፡
የምንሰማቸው ነገሮች የሆነ የህጻናት ‘ፊፍቲ ሼድስ ኦፍ ግሬይ’ ነገር እየመሰሉንም ነው፡፡
  ፍሬው ያማረ ዘር እንዲበዛለት
  አባት ደስ ይለዋል ልጅ ሲወለድለት
ተብሏል፡፡ በእርግጥም እንደዛ ነው፡፡ ለማንኛውም ቤተሰብ፣ ልጅ ከመውለድ የበለጠ ጸጋ ሊኖር አይችልም፡፡ ዘመኑ ይህንን የዘመናት እውነት ጥላ እያጠላበት ነው እንጂ፡፡ ልጅ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ፣ ከአጭር ጊዜ ደስታ ጋር የረጅም ጊዜ ስጋትን ይዞ የሚመጣበት እየሆነ ነው፡፡ ልጅ ማሳደግ ከባድ ፈተና እየሆነ መጥቷልና፡፡ የወላጆች ጥንካሬና ጽናት ብቻ ሳይሆን ልጆች ወደ ትምህርት ቤትም ሆነ ወደ ሌላ ስፍራ ሲሄዱ የሚገጥሟቸው አብዛኞቹ ነገሮች፣ የህይወታቸውን መንገድ የሚያስቱ እየሆኑ ነው፡፡ ልጅን “ጎረቤት ያሳድገዋል፣” የሚባልበት ዘመን በአብዛኛው እያለፈ ነው፡፡
እናማ… በዚህ ሁሉ መሀል ‘ቄሱም ዝም፣ መጽሐፉም ዝም’ ሲሆን አሳዛኝ ነው፡፡  
እናማ… ዙሪያችንን እየሆኑ ያሉ ነገሮችን እያየን “ጉድ!” “ወይ ስምንተኛው ሺህ!” ምናምን አይነት የተለመዱ ነገሮችን ከመደጋገም አልፈን… አለ አይደል… “ይሄ ነገር መቆም አለበት!” ማለት ያቃተን ለምን እንደሆነ አንድዬ ይወቀው፡፡ … “ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች የተከለከለ” የሚለው ግዴታ ማስታወቂያዎች ላይ ብቻ ነው እንዴ የሚሰራው? ከተማው በአስራ ሦስትና በአስራ አራት ዓመት የልጅ ጣጤዎች ተሞልቶ እያየን ምነው… “እንዴት ሊሆን ቻለ! ማነው ህግ ጥሶ ለህጻናቱ መጠጥ የሸጠው!” ማለት አቃተን! ደንብ ተጥሶ የለም እንዴ! እና ማነው ይህኛውን ደንብ የሚያስከብረው!
የምንሰማቸው ነገሮች የሆነ የህጻናት ‘ፊፍቲ ሼድስ ኦፍ ግሬይ’ ነገር እየመሰሉን ነው፡፡
የአሥራ ሦስት ዓመት ታዳጊዎች፣ እንደ ሀያ ምናምን ዓመት ኮረዶች ሲሆኑ ማየት አያስጨበጭብም፡፡ “አደገች፣ አደገች በቀሚሷ ሞላች…” ለ‘አሼሼ ገዳሜ’ ጥሩ ይሆን ይሆናል። ከማለት የተሻለ አስተሳሰብ የሌላቸው ወላጆች መኖራቸውን ማወቁ ያሳዝናል፡፡
ልጆች ሀሳባቸው ከትምህርታቸው ላይ እየተሰረቀ ነው፡፡ ዘንድሮ “ትምህርት ምን ያደርጋል!” የሚሉት ‘አስገራሚ ፍልስፍና’ ተደጋግሞ በሚነሳበት ጊዜ፣ ልጆቹ ከትምህርት ክፍላቸው እየራቁ፣ በእነሱ መለኪያ ‘መዝናኛ’ የሚሏቸውን ጓዳዎች የሙጥኝ ሲሉ አገር ሊጨነቅ በተገባ ነበር፡፡  
ልጁ ለአባቱ… “አባዬ እድለኛ ነህ፣” ይለዋል፤ አባትየውም…
“እንዴት ነው እድለኛ የሆንኩት?” ሲለው ልጁ ምን ቢለው ጥሩ ነው፣
“ዘንድሮ ክፍል ስለደገምኩ መጽሐፍ እንደገና መግዛት አይኖርብህም፣” ብሎት አረፈ፡፡ ይህ ልጅ ከአምስቱ የትምህርት ቀናት ሁለቱን በመንደር ጓዳዎች ቢገኝ አይገርምም፡፡
የምንሰማቸው ነገሮች የሆነ የህጻናት ‘ፊፍቲ ሼድስ ኦፍ ግሬይ’ ነገር እየመሰሉንም ነው፡፡
በፊት በሰፈር የሚለይ ነበር፡፡ እንደ ልባቸው የሚሆኑት፣ ታዳጊ ሆነው እንደ ትልቅ የሚያደርጋቸው ልጆች፣ ኑሮ የደላቸው ናቸው ምናምን የሚል፣ ማን በምርምር እንደደረሰበት ያልታወቀ፣ ነገር ነበር፡፡ እናማ… ሲወለዱ ‘ጮማ በአፍንጫቸው ተንቆርቁሮላቸው’ ሁሉ ነገር ቢያሰኛቸው ምን ይገርማል ይባል ነበር፡፡ ዘንድሮ ሊያሳስብ የሚገባው ነገር ጮማ የመብላትና ያለመብላት፣ አይስክሪም የመላስና ያለመላስ ጉዳይ አይደለም፡፡ አይደለም ጮማ በዞረበት ሊዞሩ፣ ወላጆቻቸው በቀን ሁለቴ እንኳን እነሱን ለማብላት የሚቸግራቸው ልጆች ሁሉ እየሄዱበት ያለው መንገድ ሊያሳስበን ይገባል፡፡
የምንሰማቸው ነገሮች የሆነ የህጻናት ‘ፊፍቲ ሼድስ ኦፍ ግሬይ’ ነገር እየመሰሉን ነው፡፡
በጨርቅ ኳስ ‘የመራገጥና’ በቪዲዮ ጌም ‘የመዝናናት’ ጉዳይ አይደለም፡፡ በማንኛውም የእድሜ ክልል፣ በማንኛውም የኑሮ ደረጃ ያሉ ታዳጊዎቸ ሰለባ እየሆኑ ነው፡፡  (ለነገሩ እኮ፣ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የጨርቅ ኳስ መተካቱ ግን አስቸጋሪ ሳይሆን አይቀርም፡፡ አሮጌ ካልሲ የሚባል ነገር የለማ! አንድ ደህና ካልሲ ሰባና ሰማንያ ብር እየተሸጠ፣ አውራ ጣቱ ላይ ተበድሷል ተብሎ የሚጣል ካልሲ የለማ! ጫማ ለሚወለቅበት ለቦሌ ሽኝትና ቅበላ ከሆነም ልክ የክት ልብስ እንደምንለው፣አንድ የክት ካልሲ እናስቀምጣለን። ሰባና ሰማንያ ብር ሸላይ ጫማ የሚገዛበት ጊዜ፣ ይሄን ያህል እርቆናል እንዴ!)
እናማ…አዲሱ የትምህርት ዘመን ተጀምሯል። ‘ጥናት፣’ ‘ወርክሾፕ፣’ ‘ንቅናቄ’ ቅብጥርስዮ ብቻ ሳይሆን…  እንደ ጆከር ካርታ አይነት ያደረግነውን አባባል ለመጠቀም፣ ‘ውሀ የሚያነሳ’ ነገር ለማድረግ ያብቃን፡፡
የምንሰማቸው ነገሮች የሆነ የህጻናት ‘ፊፍቲ ሼድስ ኦፍ ግሬይ’ ነገር እየመሰሉን ነውና!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5330 times