Print this page
Saturday, 30 September 2017 14:44

ቅኔ፡- የፍልስፍና ላዕላይ ጥበብ

Written by  ካሣሁን ዓለሙ
Rate this item
(1 Vote)

‹ዕውቀት ቢወዳደር ድርሰት ቢፎካከር፣
ሁልጊዜ ቅኔ ናት የድርሰቱ ጀምበር፡፡›
(ከበደ ሚካኤል)

ባለፈው ሳምንት መስከረም 13 ቀን 2010 ዓ.ም. በወጣዉ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ፣ ብሩህ ዓለምነህ የተባለ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር፤ ‹ለመሆኑ ቅኔ ፍልስፍና መሆን ይችላል?› በሚል ርዕስ፣ በቅኔ ፍልስፍናነት ላይ ትችት አቅርቧል፡፡ ለመጻፍም ምክንያት የሆነው ‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና› የሚለውን መጽሐፉን፣ የቤተክርስቲያን ምሁራን ስለተቹበትና ‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና ቅኔ ነው› በማለት ስለሞገቱት መሆኑን ገልጽዋል፡፡ በእውነቱ ያነሳው ሐሳብ፣ ስለ ፍልስፍና ጥሩ አገራዊ የክርክር መነሳሳትና ዕይታን የሚፈጥር ስለሆነ፣ የበለጠ ትጋትንና የዕውቀት ብልፅግናን ያድልልን እላለሁ፡፡
እኔም በተነሳው ሐሳብ ላይ የራሴ የጥናት ጅማሮ ስላለኝ ምልከታዬን ላካፍል ወደድኩ። ይሁንና በጽሑፌ የብሩህን መጽሐፍ ለመተቸት አልተነሣሁም፤ የኢትዮጵያ ፍልስፍናን ይዘትም ማሳየት ማጠንጠኛዬ አይደለም፡፡ ይልቁንስ ቅኔን ከደረጃዋ አውርደን በአመድ ላይ እንዳናከባልላት፣ ከፍታዋን በመጠኑ ለማሳየትና ለመሞገት ነው- አነሣሤ፡፡ ባይሆን የብሩህ መጽሐፍን ለመሔስና የኢትዮጵያን ፍልስፍና ይዘት ለማሳየት በሌላ ጊዜ እመለሳለሁ፡፡
የብሩህ ክርክር ቀድሞ ባዘጋጀው ‹ቅኔ ፍልስፍና መሆን ይችላል/አይችልም› በሚል ሜዳ ውስጥ አስገብቶ በተማረው የፍልስፍና አመክንዮ ለመነረት አመቻችቶ የሚጠብቅ ይመስላል፡፡ እኔ ግን ወደዚህኛው መንቦጫረቅ ውስጥ ገብቶ ‹በግላዲያተርነት› መደባደብ አልፈለኩም፡፡ አንድ እውነት ግን ልመስክር፤ የብሩህ ክርክር ፍሰቱ ‹ይበል!› የሚያስብል ነው፤ ‹የኢትዮጵያን ፍልስፍና ከቅኔነት ውስጥ ማውጣት አይቻልም› የሚለው መደምደሚያም ከርዕሱ ጋር ይስማማል፤ ‹እንከን የለሽ ነው› ማለት ግን አይደለም፡፡ ከእንደ እኔ ዓይነቱ ሐሳብ ጋር አይስማማምና፡፡ ሆኖም የቅኔ ፍልስፍና በዩኒቨርስቲዎች አለመሰጠቱ እና ቀደም ብሎ መጽሐፉን ከማዘጋጀቱ በፊት የኢትዮጵያ ቅኔዎችን ከፍልስፍና አንጻር አለመመልከቱ ብሩህን የጎዳው ይመስለኛል፡፡ ያ አልፏል፤ አሁን የብሩህ ክርክር፣ ‹ወይ ፍንክች ያ አባ ቢላ ልጅ› ሊሆን እንደሚችል ለመገመት ‹ሕፃን መሆንም› በቂ ነው፡፡
የብሩህ ክርክር ማጠንጠኛም መቋጫም ‹በተለያዩ ቅኔዎች መካከል በየጊዜው የሚገነባ አንድ ወጥነት ያለው የሐሳብ ሥርዓት መዘርጋት ስለማይቻል፣ የኢትዮጵያን ፍልስፍና ከቅኔነት ውስጥ ማውጣት አይቻልም፡፡› የሚለው ነው። በዚህ መደምደሚያ ግን እኔ አልተስማማሁም፤ ባለመስማማት ካልተቀበልኩት ደግሞ የመንደርደሪያ ማስረጃዎቹን በመፈተሽ፣ ክርክሩ ያለበትን ችግር መለየትና ማረም ይኖርብኛል፡፡ ይህን ላድርግ ካልኩ ግን የብሩህ ሐሳብ ላይ እየተሽከረከርኩ መቅረቴ ነው፡፡ ያ እንዲሆን አልፈልግም፤ ስለዚህ የራሴን ክርክር በአዲስ መልክ በማዋቀር፣‹የኢትዮጵያ ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ ቅኔነት ነው› የሚል የአፀፋ መደምደሚያ ላይ ደርሻለሁ፤ በዚያውም የቅኔን ልዕለ-ፍልስፍናነት ለማሳየት ሞክሬያለሁ፡፡
አሁን የብሩህን ክርክር፣ መሠረታዊ ስህተት ነው የምለውን በማሳየት ልነሣ፡፡ ‹ችግሩ ያመለካከት ነው› እንዲል ካድሬ፣ ለእኔ የብሩህ ክርክር ዋና ስህተት ያለው በዕይታው ላይ ነው፤ ዕይታው ከማዶ ስለሆነ ወዲህ ማዶ ያለው በአግባቡ ዐልታይ ያለው ይመስላል፡፡ ማስተዋል የሚገባው ግን የአገራችን ፍልስፍና የዕይታ ማጠንጠኛው ልክ እንደ ፊደላችን፣ ከአውሮጳውያን ይለያል (ዘመናዊ ትምህርታችን አውሮጳዊ ቢሆንም)፡፡ ምን ማለቴ ነው?
ሁለቱ የግዕዝ ፊደላት እና የእንግሊዘኛ አልፋቤቶች፣ ተፈጥሮን በሥዕልነት በመወከል አቅማቸው፣ በአናባቢና በተነባቢ ተዋሕዷቸው፣ በቅርጻቸው፣ በድምፅ አወጣጣቸው፣… ይለያያሉ። ስለሆነም አንድ ሐሳብ ስንጽፍባቸውና ስናነብባቸው፣ ከተፈጥሯቸው ጋር የተገናዘበ ስሜትና ግንዛቤን ነው የሚሰጡን፡፡ የተጻፉ ጽሑፎችን ከማንበብ በፊትም ፊደላቱን/አልፋቤቱን ማወቅም ይቀድማል፡፡ ለምሳሌ የግዕዝን ፊደል ያላወቀ የእንግለዘኛ ሊቅ፤ በዚያ የተጻፈ ጽሑፍን ሊያነበውና ሊጽፍበት አይችልም፤ ስላልቻለ ቢተቸውም ትርጉም አይሠጥም፡፡ የኢትዮጵያ ፍልስፍናም ሆነ የቅኔ ፍልስፍናነት ተፈጥሮ ከፊደል ምሳሌ ጋር ይናበባል፡፡ ቅኔነት በኅብርነት፣ በዕምቅነትና በለዛዊነት የተሠራ ስለሆነ በደረቅና በነጠላ ሐሳብ ከሚገነባው እና የአሻሚነት ትርጉም ከማይስማማው የአመክንዮ ፍልስፍና ጋር አንድ አይደለም፤ ዕይታውም መንገዱም ይለያል፡፡ ስለዚህ የቅኔን ፍልስፍናነት የምናይበት እና ደረቁን የአውሮጳ ፍልስፍና የምናይበት ዕይታ ልዩነቱንና አመሠራረቱን መገንዘብ፣ የዕይታ አድማሳችንን ይቀርጸዋል፤ ሚዛናችንንም እንደዚሁ፡፡ አሁን እየተቸገርን ያለነው የግዕዝ ፊደል ባሕርይ የያዘውን የኢትዮጵያን ፍልስፍና፣ በእንግሊዘኛ አልፋቤት እያነበቡ የተረዱ ምሁራን ጋር መላተማችን ነው፡፡
እዚህ ላይ ‹የኢትዮጵያን ፍልስፍና› የምንገመግመው ከአምክንዮ መርህ አንጻር ከሆነም ‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና ከተጠየቅ ልጠየቅ ጥበብ› ጋር በማገናዘብ መከራከር ይቻላል፤ ተጠየቅ ልጠየቅ ራሱ ከቅኔ የፈለቀ የክርክር ጥበብ ነውና፤ ዋና ግን አይደለም፡፡ በብሩህ መከራከሪያ የማልስማማውም ቅኔን በፍልስፍና አወቃቀርና በሐሳብ ሥርዓታዊ ትሥሥር (ፍሰት) አንጻር ብቻ ስላየው ነው። የአገራችን የቅኔ ጥበብ ግን በዋናነት የሐሳብ ሥርዓትንና ትሥሥርን የሚፈጥረው በሰምና ወርቅነቱ እንጂ በአምክንዮአዊነቱ/በተጠየቃዊነቱ አይደለም፤ ለዘመናት ሊቃውንቱ የተለያዩ ስልቶችን በመፍጠርና በመጠቀም ሲማሩትና ሲያስተምሩት የኖሩት በኅብርነት ወይም በሰምና ወርቅ መነጽር ነውና፡፡ ይህን ብልም በተለመደውና በተማርነው መሠረት ስላልሆነ እንጂ ምክንያታዊ ትሥሥር የሌላቸው ቅኔዎች የሉም፡፡ ቅኔዎቹን ወደ አመክንዮአዊ ክርክር በመቀየርም የዐረፍተ ነገሮቹን ምክንያታዊ ትሥሥር እየተነተኑ ማሳየት ይቻል፤ ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ መሆኑ ግን አይታበልም፡፡ ይህ ነጥብ ይቆየን፤ አሁን እስቲ ቅኔን ፍልስፍና አድርገን እንድንወስድ የሚያደርገን ምን እንደሆነ ለማሳየት ልሞክር፡፡
ቅኔ በመደነቅ ላይ የተመሠረተ ጥበብ ነው፤ ማጠንጠኛውም ምሥጢር እየፈለቀቁ መገረም ነው፤ ፍልስፍናም እንደዚሁ አይደለም ወይ? የቅኔ ዓላማ የእውነትን ምሥጢር መግለጥ ነው (ወርቅ የሚለው ‹እውነት!› ሲል ነው)፤ ፍልስፍናም መዳረሻው እውነትን ማግኘት ነው (ማንም እውነተኛ የፍልስፍና ዐዋቂ ይህን አይክድም)፡፡ ፍልስፍና እና ቅኔን የምመዝነው በእነዚህ መሠረታዊ ዕሳቤዎች ላይ ተመሥርቼ እንጂ ከቅርንጫፉ ጀምሬ ወይም በመንገዳቸው ላይ እየተንገዳገድኩ አይደለም፡- በስልት ከሆነ አመክንዮ አንድ የፍልስፍና የአተዋወቅ ስልት ነው፤ ሰምና ወርቅነት ደግሞ የቅኔ፡፡ ስለዚህ ሁለቱ በአመሠራረታቸው ሳይሆን በአተዋወቅ ስልታቸውና በይዘታቸው ልዩነት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ መዳረሻቸውና አመሠረራታቸው ግን ያገናኛቸዋል፡፡
አዎ! የቅኔ ይዘት ሰምና ወርቅን ማዋደድ ሲሆን ዋና ስልቱም ሰምን ተጠቅሞ ወርቅን በማንጠር ምሥጢሩን ማግኘት ወይም የተደበቀውንና የተሠወረውን ማውጣትና ዕንቆቅልሹን መፍታት ነው፡፡ ቅኔ ተፈጥሮን በቅርብ ነው የሚያነባት፤ ምክንያቱም ተፈጥሮ የተሠራችው በኅብርነት፣ በዕምቅነት፣ በዜማና በውበት ነው፤ የቅኔም ሥሪትና ጠባይ እንደዚሁ ነው፡፡ ቅኔ ለተፈጥሮ ባላው ቅርበት የተነሣም በእውነት ዕንቆቅልሽ ላይ ይሽከረከራል፤ ለዚያም ነው የሰምና ወርቅ ሥሪት፣ የእውነት አመሠራረት፣ የማይፈታ የምሥጢር ቤት የሆነው። የቅኔ ፍልስፍናነትም የሚሸለቀቀው በዚህ መልኩ እንጂ የዕውቀት አወቃቀሩና ፍሰቱ ከፍልስፍና ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ አይደለም፡፡
ፍልስፍና፤ ‹የእውነትን፣ የዕውቀትንና የእሴትን› መስተጋብር በአምክንዮ መርሆዎች እያበጠረና እያዋደደ መጎርጎርና የእውነት መዳረሻን ማግኘት ነው፡- ማጠንጠኛው፤ (በምንፍቅና (Skeptic) ፍልስፍናን እንገምግም የሚሉትን እንተዋቸው፤ በግሌ አእምሯዊ ናቸውም ብዬ አላምንም (ተጠራጠርኩ እንዴ?)፡፡ ፍልስፍና አተዋወቁ በአመክንዮ መሆኑ ለዕውቀት እንዲያደላ፣ ከዕውቀት ተነሥቶ እውነትን ወደ መፈለግ እንዲያንጋጥጥ፣ የእውነትና የዕውቀት እሴቶችን ከአመሠራረታቸው ጋር ለማጣጣም እንዲተጋ፣ በዚህ የተነሣም እውነትን ቆፍሮና በዕውቀት አበጥሮ ለማውጣት ሲለፋ እንዲኖር አድርጎታል፡፡ በእውነቱ የቅኔነትን ጠባይ ከተረዳን ፍልስፍና በቅኔ የተቃኘ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ላብራራው!
የፍልስፍና መጠንጠኛዎች ‹እውነት፣ ዕውቀት እና እሴት› የሚሉ ፅንሳተ ሐሳባት መሆናቸውን ገልጫለሁ፤ እነዚህ ‹እውነት፣ ዕውቀትና እሴት› የሚባሉ ፅንሳተ ሐሳቦች በአመሠራረታቸው፣ በቅኔነት ተፈጥሮ የተቃኙ መሆናቸውንም እንደዚሁ፡፡ እውነት በምንነቷና በአተዋወቁዋ ዕንቆቅልሽ (ምሥጢር) እንደሆነች አለች፤ የሰው ልጅም እስከ ዛሬ ድረስ እየቆፈረ የኖረው የእውነትን ሰም እንጂ ዋና ምሥጢር የሆነችውን ዋናዋን ወርቅ አላገኛትም (የእውነት ምሥጢርነት ቢፈታ ኖሮም ፍልስፍና አይኖርም ነበር)፤ ይህም ነው እውነትን ቅኔ ያደረጋት፡፡ ዕውቀትም ቢሆን ከምንጯ፣ ከስፋቷ፣ ከጥልቀቷ፣ከመዋቅራዊ ሥርዓቷ አንጻር እስካሁን ምሥጢሯ ሊፈታ አልቻለም፤ ይህም ዕውቀትን ቅኔ ያደርጋታል፡፡ የእሴትም አንድምታ ተመሳሳይ ነው፤ የእውነትና የዕውቀት እሴቶች ጉዳይ፣ የዉበት፣ የግብረገብ (የሞራል)፣ የማኅበራዊ መስተጋብር እና የአኗኗር ሥርዓት ምሥጢሩ ያልተፈታ ዕንቆቅልሽ እንደሆነ አለ፤ የእሴት ቅኔ ማለት ይህ ነው፡፡ እነዚህ እውነት፣ ዕውቀትና እሴት ደግሞ ፍልስፍና የተሠራባቸው ናቸው ብለናል፤ ይህም ማለት ፍልስፍና ጥልቀቱና ምጥቀቱ የተመሠረተው በቅኔ ላይ ነው ማለት አይደለም ወይ? ስለዚህ ቅኔ ‹የእውነት፣ የዕውቀትና የዕሴት› ንጣፍ ላይ (ንጣፍ የምትለዋን ቃል ከብሩህ ነው የወሰድኳት) የሚሽከረከር የፍልስፍና ላዕላይ ክፍል ነው ብንልስ ---- ዐበልን ወይ?
የቅኔን ልዕለ-ፍልስፍናነት ለማስረዳት ከአገራችን ልውጣና፣ የአውሮጳ ታዋቂ ፈላስፎች (ምንም እንኳ ከአገራችን ቅኔ ቢለይም) ‹እጃችሁ ከምን?› ብዬ ልጋብዛቸው፤ ምን ላድርግ? ሙግቱ ሁሉ ‹በከመ ይቤ› ሆነብና! ባይሆን እንዳትሰለቹብኝ ሐሳቤን ቀለል አድርጌ በወዘና ለማቅረብ ልሞክር፡፡
በመጀመሪያ የግሪኮቹን ሶቅራጥስን፣ ፕላቶንና አርስቶትልን ልጋብዛቸው ስል፣ ሶቅራጥስ ‹መጀመሪያ ራስህን ዕወቅ› አለኝ፣ ፕላቶን ‹ይህን ቅኔ የሚባል የተረት አስተሳሰብ ይዘህ፣ መምህሬን ምን አድርግ ነው የምትለው?› ብሎ ሲያፈጥብኝ፣ አርስቶትል ግን በማስተዛዘን ‹ቅኔ እንደ ፍልስፍና ባይሆንም ከታሪክ የተሻለ ሐሳብ ነው› ብሎ ሸኘኝ፡፡ ምስክር ለማግኘት በማደርገው ጥረት ተስፋ አልቆረጥኩም፤ ግን አኳይነስ ጋር እስከምደርስ ድረስ የሮማውያኑም መልስ ከፕላቶንና ከሶቅራጥስ የተቀዳ ነበር፤ በተለይ አውጉስጢን የጣኦት ማምለኪያ ብሎ ነው ቅኔን ያንቋሸሸብኝ (የእነዚህን ፈላስፎች ክርክር ሰምቶ ከሆነ፣ የብሩህ ክርክር አጋዥ አለው)፡፡
አኳይነስ ሲያረጋጋኝ፤ ቪኮ የተባለው ኢጣሊያዊ ፈላስፋ የዕውቀት ምጥቀትና የፍልስፍና መሠረት ቅኔ መሆኑን ተከራከረልኝ፤ ከዚያማ አቶ ካንት፣ አቶ ሄግል፣ አቶ ኬርከጋርድ፣ አቶ ኒቼ፣ አቶ ሄደጌር፣… (ወይ! አቶ አልኩኝ፣ የፕሮፌሰሮቹን ፕሮፌሰሮች እኮ ነው!) ከፍልስፍና አልፈህ ወደ ቅኔ ልዕልና ከፍ ከፍ በል አሉኝ፡፡ ካንት ከአድማሱ ባሻገር (Noumenon) ያለው ዓለምን ለመረዳት የሚያበቃው ቅኔ እንጂ ምክንያት አቅሟ አይፈቅድም በሚል Critique of Jugdement የሚለውን መጽሐፉን ጋበዘኝ፤ ጥሩ ትዝብት አለው፡፡ ሄግል ተቀብሎ ‹የፍልስፍና ሁሉዓቀፋዊ ውህደት የሚገኘው በቅኔ ነው› በሚል በPhenomenology of Spirit መጽሐፉ ሞገተኝ። ቀጠለ ኬርከጋርድ፤ ፈላስፋ ሳይሆን ‹ባለቅኔ› ብለህ ጥራኝ አለኝ፤ በዚህም Absurdity የማለቱ ምሥጢር፣ የአመክንዮ ፍልስፍና የተፈጥሮን ዕንቆቅልሽ መፍታት እንደማትችል ስለተረዳ መሆኑን አብራራልኝ፡፡ ‹እሺ ከሐዲው ኒቼስ ምን ትላለህ?› ብዬ ልጠይቅ ስል፣ በሶቅራጥስ ‹እስጥአገባ› (Dialectic) ክርክር ሲበሣጭ አገኘሁት ‹ምነው?› ስለው፣ ‹በቅኔ ላይ በሠራው ወንጀል ሞት ሲያንሰው ነው› ብሎ መለሰልኝ፤ ኒቼ ደግሞ ከተበሳጨ እግዜርንም ከመግደል እንደማይመለስ ስለማውቅ፣ ቀዝቀዝ ብዬ ‹ይህንን የምትልበት እጅህ ከምን?› ስለው፣ The Birth of Tragedy የሚለውን መጽሐፉን Gay Science ከሚለው ጋር እያስማማ፣ ስለ ቅኔ ልዕልና ሞገተኝ፤ ‹ድንቅ ነው› ብዬ ተለየሁት። ወደ አገር ቤት ልመለስ ስል፣ ‹ሄደገር!› ከካንትና ከኒቼ የተቀበለውን እየተቸና እያሰፋ ‹ሥነ-ኩነትን› (Beingness) መግለጽ የሚችለው ቅኔ ስለሆነ ካድማሱ ባሻገር የተደበቀውን የኩነት ጥበብ ማሳያም መሆን ይችላል አለኝ፤ ለማረጋገጥ ‹ምክንያትስ?› ስለው፣ ልኳ አፍጥና አግጥን ማቀናበር ስለሆነ ከግድግዳው ወዲያ ማሰብም ማሳሰብም አትችልም አለኝ፡፡ ከዚህ በላይ የቅኔ ልዕልና ምስክርስ ከየት ላምጣ? ለካ! አመክንዮ፤ ፍልስፍናን ቅኝ ግዛት ይዛ፣ ብዙ ምሥጢር ደብቃብናለች እያልኩ ወደ አገር ቤት!፡፡
ወደ አገር ቤት ስመለስ አገናኝ ድልድይ ፈለኩ፤ ማንን አገኘሁ? እጓለ ገ/ዮሐንስን፡፡ እሱም ‹ቅኔ ስንል… ጨርሶ ሌላ ነገር ነው፡፡ ከባድ ነው፡፡ ምሥጢር የተመላ፣ የረቀቀ ፍልስፍና የተከማቸበት ማለት ነው፡፡ ባለቅኔውም ሰሚውም በሕሊና ርቀት የተራመዱ ናቸው፡፡ ሁለቱ ሲገናኙ አንደኛው ገና ከመጀመሩ ኹለተኛው ይበል! ይበል! እያለ በቃሉ ተማርኮ ነው፡፡ የሕሊና ርቀትና የቃል አንደበት ጉልበት በቅኔ ትምህርት በጣም ተስፋፍቶ ይታያል።› አለኝ (እጓለ ገብረ ዮሐንስ (2003 ዓ.ም፣ 2ኛ እትም)፣ የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ፣ ገጽ 71)፡፡
ከዚያም የአገራችን ባለቅኔዎች ‹ቅኔን እንዴት ነው የሚያዩት?› የሚል ጥያቄ ይዤ፣ ወደ እማሆይ ገላነሽ ስጠጋ፣ ‹ቅኔን ይቀኙታል እንጂ ዐያዩትም!› ሲሉኝ ጥያቄው ራሱ ጠፋብኝ፡፡ ሊቁ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ግን ‹ቅኔ ሕሊናን (አእምሮን) ለምሥጢር የማስገዛት ጥበብ ነው› ብለው እጥር ምጥን አድርገው አስቀመጡት፤ ‹ማብራሪያ!› እንዳልል ‹ጨዋ!› ይሉኛል ብዬ ‹ሕሊና›፣ ‹ምሥጢር›፣ ‹ማስገዛት› የሚሉትን ቃላት እያብሰለሰልኩ አለሁ፡፡ እስቲ አብረን እናስብ፤ ሕሊናን ለምሥጢር ከማስገዛት በላይ ምን ጥበብ ይገኛል ትላላችሁ?
እንደ ጉርሻ ጠቅለል ሳደርገው፣ የቅኔ ጥበብ ተግባር የዕንቆቅልሹን ዓለም ምሥጢር መፍታት በመሆኑ ከፍልስፍናም በላይ ልዕልና ያለው እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ቅኔን ፍልስፍና የምናደርገውም በሐሳቡ ስፋት፣ ምጥቀት፣ ጥልቀትና ድንቀት፣ እንዲሁም ዕንቆቅልሽዋን እውነት መመርመሪያ ልዩ ጥበብ ስለሆነ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ አእምሯችንን ከፍ ከፍ በማድረግ፣ የፍልስፍና ዘውጎች መሠረት ወይም ንጣፍ የሆነውን ቅኔነትን ወደ መረዳት እንደግ፡፡ አይበቃኝም? (ኧረ! አራት ነጥብ ወዴት ነሽ? ሰውየው ይዘውሽ ሄዱ እንዴ?)

Read 3122 times