Saturday, 30 September 2017 14:47

የባህልና ትውፊት ተቋምን ያገለለው፣ ”የህዳሴ ፕሮጀክት”

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ፣ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(1 Vote)

   መቼም በዚህ ርዕስ የመጣሁት ሀገራችን የተለያዩ ሃይማኖቶች መኖሪያ መሆኗን ዘንግቼው ሳይሆን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፤ ለአሁኑ ሀገራዊ እሴቶችና ማንነት መፈጠር ያላት ታሪካዊ አበርክቶትና አሁንም ድረስ 50 ሚሊዮን በሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ያላት ተሰሚነት ከፍተኛ በመሆኑ እንጂ፡፡
እኔ “የኢትዮጵያ ህዳሴ” የሚባለው አካሄድ ላይ ከፍተኛ ስጋት አለኝ፡፡ የአውሮፓውያኑን የህዳሴ አካሄድ ለመድገም ከሆነ በጣም ተሳስተናል። ፈረንጆች ለምንድን ነው የሀገራችንን ባህልና ሃይማኖታዊ በዓላት ለማየት ብዙ ሺ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት? የእነሱ የህዳሴ አካሄድ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻቸውን ስላወደመባቸው ነው፡፡ ይሄ የሆነው ደግሞ ካቶሊክ ቤ/ክ በህዳሴያቸው ፕሮጀክት ውስጥ ከመካተት ይልቅ ጭራሽ የህዳሴያቸው ተፃራሪ ሆና በመገኘቷ ነው፡፡ እናም የምዕራባውያን ህዳሴና አብርሆት በመሰረቱ የነባር ትውፊታዊና ባህላዊ እሴቶቻቸው ተፃራሪ ሆኖ ነው የወጣው፡፡ ይሄ ነገር በእኛም ሀገር እንዳይደገም ከፍተኛ ስጋት አለኝ፡፡ ፍንጮች ግን ታይተዋል፤ በ1966ቱ አብዮት ወቅት የጥንቱን ትውፊትና ባህላዊ እሴት አምርሮ የሚጠላ ትውልድ መፈጠሩን አይተናል፡፡ ህዳሴ አያስፈልግም እያልኩ ግን አይደለም፤ የኔ ስጋት አካሄዱ ላይ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም “የከሸፉት 4ቱ የነገስታቱ የዘመናዊነት ፕሮጀክቶች” በሚል ርዕስ በተከታታይ ሁለት መጣጥፎችን እንዳስነበብኳችሁ ይታወሳል። ኢትዮጵያን ወደ ቀድሞ የገናናነት ሥልጣኔዋ ለመመለስ ከዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ጀምሮ ላለፉት 160 ዓመታት በተለያየ መንገድ ሞክረን አልተሳካልንም፡፡ አውሮፓውያን ለህዳሴ የፈጀባቸው ጊዜ 300 ዓመታት ቢሆንም፣ የህዳሴያቸው ንቅናቄ እንደ ዳቬንቺና ኮፐርኒከስ ያሉ ፍሬዎችን ማፍራት የጀመረው ግን ገና በመጀመሪያዎቹ 100 ዓመታት ውስጥ ነበር፡፡ እኛ የእነሱን አጠቃላይ የህዳሴ ዘመን ግማሹን ቀርጥፈን የበላነው ቢሆንም ጉዟችን ግን ጭራሽ ወደ ኋላ ተንሸራቶ፣ ዛሬ ላይ ህዳሴ የሚለው ፅንሰ ሐሳብ ተረስቶ፣ ጭንቀታችን ስለ ሀገራዊ ህልውና ሆኗል፡፡
ከአረቦችና ከደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገሮች የእድገት ፍጥነት አንፃር ካየነው ደግሞ የእኛ ሀገር የ160 ዓመታት ጉዞ እጅግ ቀርፋፋና አናዳጅ ነው። ይበልጥ የሚያስቆጨው ደግሞ በእነዚህ ረጅም ዓመታት ውስጥ ርዕያችንን እስከ አሁን ድረስ ማሳካት አለመቻላችን ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ገና ብዙ እንደሚቀረን ወቅታዊው የሀገራችን የብሄር ፖለቲካ ትኩሳት እያሳየን መሆኑ ነው፡፡
ከዚህ ሁሉ ድካም በኋላ የተመኘነውን አለማሳካታችን የሚነግረን ነገር ቢኖር፣ በ160 ዓመታት የህዳሴ ፕሮጀክታችን ውስጥ አንድ ወሳኝ የሆነ ነገር መዘንጋታችንን ነው፡፡ የዚህ ፅሁፍ ዋነኛ ጭብጥም “እስከ ዛሬ ድረስ የኢትዮጵያን ህዳሴ ለማምጣት ያልተቻለው፣ ህዳሴን የፖለቲካችን ፕሮጀክት ብቻ በማድረጋችንና በዚህም ወሳኝ የሆነችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክንን የፕሮጀክቱ ባለቤት ባለማድረጋችን የተነሳ ነው” የሚል ነው፡፡
ህዳሴ የሚለው ቃል መታደስ፣ ዳግም ልደት፣ ትንሳዔ፣ እንደገና መነሳሳት የሚል ትርጓሜ ሲኖረው፤ የእንግሊዝኛው አቻ ቃሉ ደግሞ Renaissance የሚለው ነው፡፡ ህዳሴ የሚለው ቃል ጥቅም ላይ የዋለው አውሮፓውያን፣ ሃይማኖታዊ ከሆነው መካከለኛው ዘመን ፍፁም ቁሳዊ ወደ ሆነው ዘመናዊ ታሪክ የተሸጋገሩበትን የሽግግር ወቅት የሚያመላክት ሲሆን፤ ይሄም የሽግግር ወቅት ከ14ኛው-17ኛው መቶ ክ/ዘ አጋማሽ ድረስ ለ300 ዓመታት የቆየ ነው፡፡
ህዳሴ ናፍቆት ነው፤ የጥንት አያቶችን ባህል መናፈቅ ነው!! በእኛ ሀገር ግን የድሮውን መናፈቅ ያሰድባል - “የድሮ ሥርዓት ናፋቂ” ተብለህ ትሰደባለህ፡፡ የ14ኛው ክ/ዘ አውሮፓውያን ግን ህዳሴ ሲሉ የጥንት ግሪካውያንና ሮማውያን ባህል ናፍቆት ጠንቶባቸው ነው፡፡ ዓላማቸውም የጥንት ግሪኮ ሮማውያን ስራዎችን በመተርጎም፣ በአርትዖና በድጋሚ በመጠቀም የሰውን ልጅ ምናብ፣ ነፃነትና መንፈስ በመኮትኮትና በማበልፀግ፣ ለአዳዲስ ፈጠራዎች እንዲነሳሳ ማድረግ ነው፡፡ አውሮፓውያኑ የድሮው ናፍቆት እንዲበረታባቸው የሆነው ደግሞ የመካከለኛው ዘመን ያሳረፈባቸው ጠባሳ ነው፡፡ ለ1000 ዓመታት ሃይማኖትን ብቻ ማዕከል ባደረገው መንፈሳዊ ህይወት ውስጥ የሰው ልጅ ህይወቱ፣ ኑሮው፣ ችሎታው፣ ኃይሉና ታሪኩ የተረሳ ነበር፡፡ ይሄም የፈጠራ ምናቡ እንዳይዳብር አድርጎት ቆይቷል፡፡ በመሆኑም፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ የሰው ልጅ ለምድራዊ ህይወቱ ያበረከተው አንድም ተጠቃሽ ስኬት አልነበረም፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የጥንት ግሪካውያን በኪነጥበብ፣ በሥነ ፅሁፍ፣ በፍልስፍና በሳይንስ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሰው ነበር፡፡ ይሄ እንዴት ሊሆን ቻለ? ወደ ኋላ መንሸራተቱን ምን አመጣው? የመካከለኛው ዘመን አውሮፓውያን፣ ለዚህ እንቆቅልሽ መልስ ሲያፈላልጉ፣ አንድ መደምደሚያ ላይ ደረሱ - የስነ ሰብዕ ትምህርቶች ኃያልነት ላይ፡፡
በጥንት ግሪካውያን ባህል ውስጥ የሰውን ልጅ መንፈስና የፈጠራ ምናብ  የሚያበለፅግ አንድ ወሳኝ የሆነ ቅመም እንደነበረም ደረሱበት - እሱም ስነ ሰብዕ (humanities) ነው፡፡ የጥንት ግሪኮ ሮማውያን በኪነጥበብ፣ በሥነ ፅሁፍ፣ በፍልስፍናና በሳይንስ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረስ የቻሉት ስነ ሰብዕን ማዕከል ያደረገ ባህል ስለነበራቸው ነው። ስነ ሰብዕ ማለት ደግሞ የሰውን ልጅ ህይወት ማዕከል ያደረገ ትምህርትና ባህል ነው፤ “ሰው — ሰው” የሚሸት፣ የሰውን ልጅ ጥረቱን፣ ስነ ልቦናን፣ ስኬቱን፣ ውድቀቱን … ባጠቃላይ ህይወቱንና ባህሉን የሚያንፀባርቅ፣ የሚገመግም፣ የሚመረምርና የሚተች፤ የሰውን ልጅ መንፈስና ባህሪ ዓለማዊ በሆነው ህይወቱ የሚያንፅ ባህልና ትምህርት ነው ስነ ሰብዕ፡፡ የአውሮፓውያን ህዳሴ የስነ ሰብዕ ባህል ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በመሆኑም ህዳሴ የስነ ሰብዕ ፕሮጀክት እንጂ የኢኮኖሚም ሆነ የፖለቲካ ፅንሰ ሐሳብ አይደለም፡፡
በእኛ ሀገር ታሪክ ውስጥ “ህዳሴ” የሚለውን ቃል በጣም አጉልቶ እየተጠቀመ ያለው ኢህአዴግ ቢሆንም፣ የፅንሰ ሐሳቡ አጠቃቀም ላይ ግን ሁለት ችግሮች አሉበት፡፡ የመጀመሪያው፣ ህዳሴ የጥንት አያቶች ባህል ናፍቆት በመሆኑ፣ የታሪክ ሸክም የሌለበት መሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም “ከብሄር የታሪክ ቅራኔ ተወለድኩ” የሚለው ኢህአዴግ፤ የታሪክ ሸክም ስላለበት (እሱ ራሱ የቅራኔው አካል ስለሆነ) እዚህ የታሪክ ቅራኔ ላይ ቆሞ ህዳሴን ለማምጣት መሞከር ራስን እንደመቃረን ይቆጠራል፡፡
ሁለተኛ፣ ኢህአዴግ ህዳሴን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፅንሰ ሐሳብ ማድረጉ ነው፡፡ ለዚህም ነው ፋብሪካ መገንባትንና የኢኮኖሚ ዕድገትን የህዳሴ መገለጫ አድርጎ የሚያቀርበው፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው ግን፣ ህዳሴ የባህል ንቅናቄ በመሆኑ የፕሮጀክቱ ባለቤት መሆን ያለበት ባህሉን በመፍጠርና በመቅረፅ ትልቅ አበርክቶት ያለው ተቋም ነው፡፡ ይሄም ተቋም የኦርቶዶክስ ቤ/ክ ነች፡፡ በመሆኑም፣ የኢትዮጵያን ህዳሴ ማምጣት የምትችለውና የፕሮጀክቱም ባለቤት መሆን ያለባት በዋነኛነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ነች፡፡
ሆኖም ግን፣ ኢትዮጵያን ወደ ቀድሞው ገናናነቷ ለመመለስ በተደረገው የ160 ዓመታት ጥረት ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ እንድትካተት አልተደረገችም፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ የዘመናዊነት ፕሮጀክት ትልቅ ተቃውሞ የገጠመው በዋነኛነት ከኦርቶዶክስ ቤ/ክ ነው፡፡ አፄ ምኒሊክ የአውሮፓን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ሲያስገቡ ከካህናቱና ከህዝቡ በርካታ ተቃውሞ ነበረባቸው፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ  ዘመን ትውፊታዊውን እውቀት ከዘመናዊው ትምህርት ጋር የማዋኻድ ፍላጎት የነበረ ቢሆንም፣ ለምዕራባዊው ትምህርት ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱ ግን ኦርቶዶክስ ቤ/ክ የዘመናዊነት ፕሮጀክቱ አካል እንዳትሆን አደርጓታል፡፡ በአብዮቱ (በደርግና በኢህአዴግ) የዘመናዊነት ፕሮጀክት ውስጥም ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ገለልተኛ እንድትሆን ተደርጋለች፡፡ ባጠቃላይ ባለፉት 160 ዓመታት ውስጥ በ5 መንግስታት በተሞከረው የዘመናዊነት (የህዳሴ) ፕሮጀክት ውስጥ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ስላልተሳተፈችበት ሁሉም ሊሳኩ አልቻሉም፡፡
ከላይ በጠቀስነው ምክንያት ህዳሴ የስነ ሰብዕ (የባህል) ፕሮጀክት በመሆኑ የፕሮጀክቱ ባለቤት መሆን ያለባት የኦርቶዶክስ ቤ/ክ ነች። በዚህ ፕሮጀክት ውስጥ መንግስት አጋዥ ኃይል ነው መሆን ያለበት፡፡ የኦርቶዶክስ ቤ/ክ ይሄንን የህዳሴ ፕሮጀክት በባለቤትነት የምታስፈፅመውም ምዕመኑን ለማስተማር የምትጠቀምባቸውን ትምህርቶች፣ ገድላትና ታሪኮች የስነ ሰብዕ ይዘታቸውን ከፍ አድርጎ በመከለስ ነው፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ያሬድን የሚመለከቱ መለኮታዊና ሰውኛ የሆኑ ሁለት አተራረኮችን በንፅፅር እንመልከት፡፡   
ቅዱስ ያሬድ ዜማውን ሊደርስ የቻለው ሃይማኖታዊ መፃህፍትን መሰረት በማድረግ ንባቡን ለዜማው እንዲስማማ በማቃናትና መሰረተ ሐሳቡን ሳይለቅ ንባቡ ከእነ ሚሥጥሩ በመንፈስ ቅዱስ ተገልፆለት እንጂ እንዲሁ በዘፈቀደ ከልቡ አንቅቶ፣  ከአፉ አውጥቶ አልተናገረውም፡፡
በዚህ የቅዱስ ያሬድ መለኮታዊ አተራረክ ውስጥ የያሬድ የሰውኛ ጥረቱና ፅናቱ፣ ድካሙና እንግልቱ፣ ችሎታውና ዕውቀቱ የተዘነጋ ነው፡፡ ሃይማኖታዊው አተራረክ ሰብዓዊ ይዘቶችን በመሸፈን አሊያም በማኮሰስ መለኮታዊ ይዘቱን ብቻ ያጎላዋል። ባህላችን ውስጥ እንደነዚህ ዓይነት ሃይማኖትን ማዕከል አድርገው፣ የሰውን ልጅ ህይወት ግን ወደ ጠርዝ የገፉ አስተሳሰቦች፣ ትምህርቶችና አፈ ታሪኮች አሁንም ድረስ በብዛት አሉ፡፡ የሀገራችን ህዝብ ለሰው ልጅ ዕውቀትና ችሎታ ዕውቅናና ክብር ከመስጠት ይልቅ መለኮታዊ ተዓምራትን ማመን ደስ ይለዋል፡፡ ነጋድራስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ፣ እንደዚህ ዓይነቱን የታሪክ አተራረክ እንዲህ በማለት ይሳለቁበታል፣
እንደ ኢትዮጵያችን ነገስታትና ገዥዎች ብዙ የቅዱሳንና የአጋንንት እርዳታ የሚያስፈልገው ሰው በዓለሙ ታሪክ ከቶ አልተሰማም፡፡
ዶ/ር እጓለ ገ/ዮሐንስም ከዚህ የነጋድራስ ገብረ ህይወት ትችት ጋር ይስማማሉ፣
በማናቸውም በኩል ብንመለከተው የኢትዮጵያ ህዝብ በዘመናት መካከል ያደረገው የታሪክ ጉዞ፣ በሊቃውንቱ ጥረት የተከማቸው የመንፈስ ውጤት ሁሉ መሠረቱን ስናየው፣ በሃይማኖት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የማናቸውም ነገር ማዕከል እግዚአብሔር ነው፡፡ አነሳስቶ የሚያስጀምር፣ ረድቶም የሚያስጨርስ፣ የነገሮች ሁሉ ጥንተ ተፍፃሜት አምላክ ነው፡፡ እንዲያውም፣ ሃይማኖት የነገሮችን ሁሉ ባህሪ መመልከቻ መነፅር ነው ማለት ይቻላል፡፡
የጥንቱ፣ የመካከለኛውና አሁን ላይ ያለው የሰሜኑ ባህልና ስነ ልቦና በእንደዚህ ዓይነት የስነ ሰብዕ ይዘቶችን በተነፈጉ ታሪኮችና ሃይማኖታዊ ትምህርቶች የተሞላ ነው፡፡  እንደዚህ ዓይነቱ ባህል ዋነኛ ችግሩ የሰውን የፈጠራ ምናብ በማቀጨጭ ለለውጥ ያለውን ተነሳሽነት ይገድልበታል። የህዳሴ ፕሮጀክት መጀመር ያለበት ለህዝቡ በየዕለቱ በሚነገሩ በእነዚህ ታሪኮችና ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ውስጥ ያለውን የስነ ሰብዕ ይዘት በመጨመር ነው፤ ወይም ደግሞ የመንፈሳዊና የሰብዓዊ ይዘታቸውን በማመጣጠን ነው፡፡ ይሄንን ማድረግ የምትችለው ደግሞ የትውፊቱ ባለቤት የሆነችው ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ናት፡፡ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ የተመሰረተችበትን ቀኖና ሳትነካ ይሄንን ማድረግ ትችላለች፡፡  ከላይ የቅዱስ ያሬድን አነሳስ በተመለከተ ሰብዓዊ ይዘት የተነፈገውን መለኮታዊ አተራረክ ተመልክተናል፡፡ አሁን ደግሞ የአለቃ ተክለየሱስ ዋቅጅራን አተራረክ እንመልከት፡-
በአፄ ካሌብና በልጁ በአፄ ገብረ መስቀል ዘመን የዛር ዘፈን ተስፋፍቶ ነበር፤ በቤ/ክ እስኪዘፈን ድረስ። በዚያም ዘመን አንድ ድምፀ መልካም ደብተራ ተነሳ፤ በግዕዝ ቋንቋ የሚዘፍን ማኅሌታይ — ስሙ ያሬድ የሚባል፡፡ … ያሬድ ሚስቱ በላዩ ላይ ሌላ ወንድ ስለደረበችበት፣ በዚያ ተበሳጭቶ ወደ በርሃ ገባ፡፡ በዚያም እየተመላለሰ ተራራ ለተራራ እየጮኸ ሦስት ዓመት በትግሬ ምድር ዞረ፡፡ የሰሙትም ሰዎች “ዛር ፈልቆበታልን?” ይሉ ነበር፡፡ ነገር ግን እሱ ዜማውን በ3 ዓይነት አዚሞታል — በግዕዝ፣ በዕዝልና በዓራራይ፡፡ ሆኖም ግን ድርሰቱ ከቅዱስ መፃህፍት ስለነበረ ሊቃውንቱ ተቀብለውታል፡፡
የሰውን ልጅ ማዕከል ያደረገ አገላለፅ ማለት ይሄ ነው፡፡ ያሬድ ሰው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ እንደ ሰውነቱ ስሜት፣ ስነልቦናና ማህበራዊ ህይወት አለው፡፡ ያሬድን ከመለኮታዊ ፀጋ ተቀባይነቱ አንፃር ብቻ ከመተረክ ይልቅ፣ ከሰብዓዊ ባህሪው አንፃርም ቢተረክ ይሄንን የሚማሩ የአብነት ተማሪዎች ስለ ሰው ልጅ ያላቸው ግንዛቤ ይለወጣል፡፡ አሁን ባለው ሃይማኖታዊ አተራረክ ግን የሰው ልጅ መለኮታዊ ፀጋ ካልተሰጠው በራሱ ችሎታ ምንም ነገር ማድረግ የማይችል ደካማ፣ አቅመ ቢስና እንደ ሸክላ በቀላሉ ተሰባሪ ተደርጎ ነው እየቀረበ ያለው፡፡ ከዚህ ይልቅ፣ በሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች የሰው ልጅ ችሎታ፣ ኃይልና ጥንካሬ ጎላ ተደርጎ ቢቀርብና እግዚአብሔርም መለኮታዊ ፀጋውን የሚሰጠው ለእንደዚህ ዓይነት ጠንካራና ብርቱ ሰዎች መሆኑን ቢነገር፣ ማህበረሰቡ ውስጥ አዲስ ዓይነት የለውጥ ንቅናቄ መፍጠር ይቻላል፡፡
አለቃ ተክለ እየሱስም ያሬድን የተረኩበት መንገድ ይሄው ነው፡፡ አተራረካቸው ሰው - ሰው የሚሸት ነው፡፡ የያሬድ ዜማ ድንገት ከመለኮታዊ ፀጋ የወረደ ተአምር ሳይሆን ራሱን የቻለ የባህል መሰረት ያለው ነው፡፡ አለቃ ተክለ እየሱስ ”በዚያን ዘመን ዘፈንና ሙዚቃ ተስፋፍቶ ነበር” ማለታቸው የያሬድ አነሳስ ድንገተኛ መለኮታዊ ክስተት ሳይሆን በወቅቱ የነበረው ባህል ቅጥያ መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡
በሌላ በኩል አለቃ ተክለ እየሱስ ”ያሬድ ለ3 ዓመታት ተራራ ለተራራ እየጮኸ ቆየ” ማለታቸው የያሬድን ጥረት፣ ልምምድና አዲስ ዜማን ለማፍለቅ የከፈለውን ሰውኛ መስዋዕትነት በግልፅ ያሳየናል፡፡ ከመለኮታዊ አተራረኮች ይልቅ እንደዚህ ዓይነት ሰውኛ አገላለፆች ናቸው፣ የሰውን ልጅ በስራ እንዲተጋና ህይወቱን እንዲያሻሽል እገዛ የሚያደርጉት፡፡
በገዳማቱ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ከንባብ ቤት ቀጥሎ ያለው የዜማ ቤት ነው፡፡ የዜማ ቤት ትምህርት የሚጀምረው ደግሞ ቅዱስ ያሬድ ባዘጋጀው ድጓ (ፆመ ድጓ) ነው፡፡ የአብነት ተማሪዎች ስለ ቅዱስ ያሬድ ሲማሩ፣ የአለቃ ተክለ እየሱስ ዋቅጅራ የአተራረክ ስልት ቢጨመርበት ተማሪዎች እግረ መንገዳቸውን የሰው ልጅ በድካም፣ በጥረትና በፅናት ለውጤት እንደሚበቃ ይማሩበታል። ሃይማኖታዊ መፃህፍት፣ ስብከቶች፣ ታሪኮችና ገድላት ሁሉ በዚህ መልኩ ሰብዓዊ ይዘታቸው ከፍ ተደርጎ ቢከለሱ፣ህዝቡን በቀላሉ ለሚፈለገው ለውጥ ዝግጁ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይሄ ለሁሉም ሃይማኖቶች ይሰራል፡፡
ኦርቶዶክስ ይሄንን የህዳሴ ፕሮጀክት በዚህ መልኩ በባለቤትነት ማስፈፀሟ ሁለት ጥቅም አለው፡፡ የመጀመሪያው፣ እስከ ዛሬ ድረስ ሀገር በቀል እውቀትንና ዘመናዊው ትምህርትን ለማስታረቅ ተሞክሮ ያልተሳካውን ፕሮጀክት ለማሳካት ይረዳናል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፣ አውሮፓውያን በአብርሆት ዘመን ላይ የገጠማቸው ዓይነት ችግር በእኛም ሀገር እንዳይከሰት ይረዳናል፡፡
የ18ኛው ክ/ዘ የአውሮፓውያን አብርሆት፣በባህልና በሃይማኖት ጥላቻ ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ ለዚህም ያበቃቸው ከ14ኛው እስከ 17ኛው መቶ ክ/ዘ በቆየው የህዳሴያቸው ፕሮጀክት ውስጥ የካቶሊክ ቤ/ክ ባለመሳተፏ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የአውሮፓውያን አብርሆትና ዘመናዊነት በዋነኛነት ከካቶሊክ አስተምህሮ ተፃራሪ ሆኖ ነው የበቀለው፡፡ ለዚህም ዋጋ ከፍለውበታል፤ በገነገነ ግለሰባዊነት፣ በብቸኝነት፣ በድብርት፣ በፍርሃት፣ በተስፋ መቁረጥና በህይወት ትርጉም ማጣት … ችግሮች የተተበተበ ማህበረሰብን ፈጠሩ። ስኮትላንዳዊው ፈላስፋ ማካንታየር (MacIntyre) ለዚህ ችግር እንደ መፍትሄ ያቀረበው ነገር በካቶሊክ ቤ/ክ አማካኝነት ከመካከለኛው ዘመን ባህልና ትውፊት ጋር አዲስ ዓይነት ትስስር መፍጠርን ነው። ሆኖም ግን አውሮፓውያን ይሄንን ለማድረግ እረፍዶባቸዋል፡፡ ምክንያቱም የእነሱ ህዳሴ፣ አብርሆትና ዘመናዊነት ባህላዊውን እሴቶቻቸውን አጥፍቶና ትውፊታዊ ትስስራቸውንም በጣጥሶ፣ በስተመጨረሻ ማሽኖችንና ህንፃዎችን አስታቅፏቸው ሄዷል፡፡
ለ160 ዓመታት ኦርቶዶክስ ቤ/ክንን ያገለለው የእኛም የህዳሴ ፕሮጀክት በስተመጨረሻ የአውሮፓውያንን ዓይነት ፀረ ባህልና ፀረ ትውፊት የሆነ ትውልድ መፍጠር መጀመሩን የ1966ቱ አብዮት አሳይቶናል፡፡ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ የሀገሪቱ የህዳሴ ፕሮጀክት ውስጥ የማትሳተፍ ከሆነ፣ ልክ እንደ አውሮፓውያን ሁሉ የኢትዮጵያም ህዳሴ ኦርቶዶክሳዊ የሆኑትን ትውፊቶችና እሴቶች በመደምሰስ እንዳይቋጭ ያሰጋል፡፡
የአዘጋጁ ማስታወሻ፡- (ጸሃፊው፤ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህርና “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” መፅሐፍ ደራሲ ሲሆን በኢ-ሜይል አድራሻው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል)

Read 2998 times