Saturday, 30 September 2017 14:49

“ማረሻ ብቻውን አያርስም”

Written by  ጋሻው ሙሉ
Rate this item
(6 votes)

ማረሻ ብቻውን አያርስም፡፡ ለማረሻ እርፍ ያስፈልገዋል፡፡ እርፍና ማረሻውን አዋዶ ለመያዝ ድግር ያስፈልገዋል፡፡ ድግርን ለማዋደድ ቅቅርት ያስፈልጋል። ድግሩን፣ እርፉን፣ ማረሻውንና ቅቅርቱን አዋዶ አንድ ለማድረግ ወገል ያስፈልጋል፡፡ ይህን ሁሉ በአንድ ለማሰር መርገጥ መኖር አለበት፡፡ ግን ይህን ሁሉ ሰብስቦ የሚይዘው ሞፈር ነው፡፡ ሞፈርም ቀንበር ከሌለ ብቻውን አይሆንም፡፡ ሞፈርንና ቀንበርን አንድ ለማድረግ ደግሞ ግድ ምናር ያስፈልጋል፡፡ ምናር የሁሉም መጠቅለያ ነው፡፡ ከእነዚህ ሁሉ አንዱ ቢጎድል፣ ገበሬው ስራ ፈትቶ ስድ ይውላል፡፡
ታሪክና ባህልም እንደዚሁ ነው፡፡ የተማረው ክፍል ለጥናትና ምርምር ሲነሳ፣ “እገሌ እንዳለውና እንደፃፈው፣” በማለት ብቻ ሳይሆን እንደ ሞፈርና ቀንበር፣ አንዱ በአንዱ መደጋገፍ አለበት፡፡ የተፃፈን ብቻ መረጃ አድርጎ እርግጠኛ ከመሆን በፊት የአካባቢውን ሰው መጠየቅ ታሪኩን የበለጠ ሙሉ ያደርገዋል። ምክንያቱም “ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ” ስለሚባል፡፡ ከዚህ በፊት ስለ “አድዋ” ጦርነት፣ የጥናት ዳሰሳ ተደርጎ የቀረበ ጽሑፍ ላይ፣ብዙ ስህተቶችን ሰምቻለሁ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ስህተት የሚፈጸመው ጥቂት ጽሁፎችን ብቻ በማንበብና ከአካባቢው ህዝብና ከሀገራችን ጽሁፎች ይልቅ በውጭ ፀሐፍት ላይ ሲበዛ በመተማመናችን ነው፡፡ እውነተኛውን ነገር ወደ ጎን ትተን፣ በባዶ እየሸመጠጥን ያለን ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ቆም ብለን ማሰብ ሳያስፈልገን አይቀርም፡፡
የአንድ አካባቢ ማህበረሰብ፣ወግና ባህሉ ሲጠናም ሆነ መረጃ ሲሰበሰብ፣ከቦታው ተገኝቶ ትልልቅ አባቶችና እናቶች ቢጠየቁ መረጃውን ሙሉ ያደርገዋል፡፡ ብዙ ጊዜ “እገሌ እንዳለው” እየተባለ ብዙ የታሪክ ክፍተቶች እየታዩ ነው፡፡
ባለፈው መስከረም 13 ቀን 2010 ዓ.ም በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ፣ “አበባየ’ሽ ወይ” … የልጃገረዶች ጨዋታ” በሚል ርዕስ፣ ሠርጸ ፍሬ ስብሃት አንድ ጽሁፍ አስነብቦናል፡፡ ጸሃፊው ገና ሲጀምር፣ የዓመት መለወጥ ለምን እንደሚያስፈልግ በሚገባ ያብራራል፡፡ ነገር ግን ስለ “አበባየ’ሽ ወይ” ግጥም ያስነበበን፣ የፋሲካ ዕለት ልጃገረዶች ተሰብስበው፣ ከእሁድ እስከ እሁድ፣ ለአንድ ሳምንት የሚጫወቱትን ጨዋታ ነው፡፡ የአስቴር አወቀ “አበባየሁሽ” የሚል ዘፈን ላይ እንዲሁ ተመሳሳይ ነገር አስተውያለሁ፡፡ “አበባየሁሽ ለምለም” ብላ እያዜመች፣ “ከጎኔም ጎኔን” የሚለውን የፋሲካን የበዓል ጨዋታ “ለአበባየሁሽ” ትጫወተዋለች።
ይሄ ዜማና ግጥም እንዴት ለፋሲካ ሊሆን ይችላል? የሚል ጥያቄ እንደሚነሳ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ልክ እንደ ሆያ ሆዬ፣ አሸንዳ እና እንቁጣጣሽ ሁሉ ልጃገረዶችና ወጣት ወንዶች ተሰብስበው፣ ወንዶች “ጊጤ” ሲጫወቱ፣ ሴቶች ደግሞ “እሽው ላሌ (ሶለላዬ)” ይጫወታሉ፡፡ ለዚያውም ሳያቋርጡ ለአንድ ሳምንት፣ ሴቶች ትልቅ ዛፍ ላይ መጫኛ ያስሩና ከፍ ብለው እየሰገሩ፣ከኋላ ሁለትና ሦስት ልጃገረዶች ቆመው፣ መጫኛው ላይ ተቀምጣ ያለችው ከፍ ብላ ሰግራ፣ ደርሳ ስትመለስ መልሰው ይገፏታል፡፡ እሷም ስትመላለስ በዜማ ነው፡፡
“የአቡዬ ሶለላዬ” ስትል ተቀባዮቹም
“የአቡዬ ሶለላዬ” በማለት ይመልሳሉ
“የሶለላው ጊዜ የተገዛው በሬ
ከመንገድ ዳር ቆሞ ይጠይቃል ወሬ”
“የአቡዬ ሶለላዬ
እሽው እያልኩኝ በየዱሩ
ባልንጀሮቼ ወልደው ዳሩ”
--ትልና ከዚያም ቀጥላ ዜማውንና ግጥሙን ትቀይራለች፡፡
“እንድልቅዬ” ስትል፣ ተቀባዮቹም “እንድልቅ” እያሉ ይቀበላሉ፡፡
“እንድልቅዬ”
“እንድልቅ”
“ንፍሮ ቀቅዬ ብላ ብለው
ጉልቻ አንስቶ ጎኔን አለው
ከጎኔም ጎኔ ኩላሊቴን
እናቴን ጥሯት መድኃኒቴን
እሷን ብታጡ መቀነቷን”
“እንድልቅዬ”
“እንጨት ለቅሜ ስገባ ቤቴ
ትቆጣኛለች የእንጀራ እናቴ”
--አሁንም ትቆይና ዜማውንና ግጥሙን ትቀይራለች፡፡
“እዮም-እዮሜ” ስትል፣ ተቀባዮቹም ያለችውን መልሰው ይደግማሉ፡፡
“እዮሜ”
“እዮሜ ሰላ ከወዴት መጡ?”
“ከላሊበላ”
“ምን እየበሉ?”
“ሳር እንደ እንጀራ”
“ምን እየጠጡ?”
“ደም እንደ አተላ”
“እዮም-እዮሜ ሰላ”
---እያለች ታዜማለች፡፡ አሁንም ዜማቸውን በመቀየር ተሰብስበው ክብ ይሰሩና …
“እንደር - እንደሬ”
“እንደሬ”
“እንደር - ማርዬ”
ይላሉ፡፡ እንደር ማርዬ ማለት፣ በዓመት አንድ ጊዜ የምትመጣ፣ ድምጿም መልኳም በጣም የሚያምር ትንሽዬ ወፍ ናት፡፡ የእሷ ድምጽ ከተሰማ የአካባቢው ማህበረሰብ፣ “ዘንድሮ ጥሩ ጊዜ” ይሆናል በማለት ይፈነጥዛሉ፡፡ እኔም ድምጿን ስሰማ በጣም ነበር የምደሰተው፡፡ በዚህ ጨዋታ ያገቡ ሴቶችም ይሳተፋሉ።  
ወንዶች ደግሞ “ጊጤ” የሚባለውን ጨዋታ በቡድን ይሆኑና ዳኛ መርጠው ከ10 ሜትር በላይ ባለው እርቀት እርጥብ፣ ጠንካራ ያልሆነ ግንድ ይተክላሉ፡፡ ከተቧደኑ በኋላ ሁሉም በተራ ጦር ይወረውራሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ከቡድኑ 5 ሰው ቢኖር፣ ከ5ቱ 2ቱ ቢስት፣ የሌላኛው ቡድን ደግሞ አንዱ ቢስት፣ ሁለት የሳተው ቡድን ይጋለባል፡፡ በዚህ ጊዜ ያለው ሽኩቻና ተረብ፣ የዳኛውና የጋላቢዎች ሸፍጥ፣ የተጋላቢዎች ብስጭትና ንጭንጭ ተመልካቹን በጣም ያዝናናል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የሴቶችና የወንዶች ጨዋታ ጎን ለጎን ስለሚሆን ሚስት፣ ባሏ ወይም እጮኛዋ ተጋልቦ ልታየው ትችላለች፡፡ ግን ጨዋታ ስለሆነ ማፈር የለም፡፡
ጋላቢዎች ጦሩን እየሰበቁ ቶሎ አይወረውሩም፤ የተጋለበው ከብዶት ከተቁነጠነጠ “ዳኛ፤ አየኸው ሊያስፎርሸኝ ነው አልወረውርም” በማለት ጋላቢውን አውቆ ጊዜ ይፈጃል፡፡ ወርውሮ ግንዱን ከወጋም ጦሩን የሚነቅለው አውቆ፣ “አልነቀል አለ” በማለት ጦሩን ከዛው ይዞ ይቆያል፡፡ ጦሩ ከመጣም በኋላ ጋላቢው፤ “ቆይ ለፈረሴ ጥሬ ይሰጠው” በማለት ከዳኛ ጋር ሸፍጥ ይይዛል፡፡ ጨዋታ ስለሆነ ማንም አይጣላም፡፡ ብሽሽቁ ግን ጨርቅ ያስጥላል፡፡ ይህ ሁሉ ጨዋታ የሚሆነው በፋሲካ ነው፡፡
“አሸንዳ ሙሴ
ፈሰስ በይ በቀሚሴ” (ለአሸንዳ ጊዜ)
“እንቁጣጣሽ እንኳን መጣሽ
በአበቦች መሀል እንምነሽነሽ” (ለእንቁጣጣሽ)
“እሽው እያልኩኝ በየዱሩ
ባልንጀሮቼ ወልደው ዳሩ”
“እንድልቅ እዬ”
“እንድልቅ”
“ንፍሮ ቀቅዬ ብላ ብለው
ጉልቻ አንስቶ ጎኔን አለው” (ለፋሲካ)--- ጨዋታ ይዜማሉ፡፡
እነዚህ ሁሉ ዜማቸው የተለያዩ ናቸው። በዚህ አጋጣሚ ሠርጸ ፍሬ ስብሐት የፃፈውን ለእናቴ አነበብኩላትና፤ “ለፋሲካ ነው ለእንቁጣጣሽ የሚዜመው?” ስላት፣ “ምን አልባት የአዲስ አበባ ባህል ሊለይ ይችላል፤ በእኛ ግን ይህን ‹በሽውላሌ (ሶለላዬ)› ጊዜ ነው የምንለው” በማለት ሀሳቤን ሙሉ አድርጋልኛልች፡፡ እናቴ እንዳለችው፤ በየአካባቢው ጨዋታውና ዜማው ስለሚለያይ፣ አጥርቶ ማወቁ አይከፋም፡፡ “ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ” ነውና። ማረሻ ብቻውን እንደማያርሰው ሁሉ ባህልና ትውፊትንም የጎደለውን እየሞላን መሄዱ መልካም ነው የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡
ሠርጸ ፍሬ ስብሐት፤ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ነውና “በርታልን!” እለዋለሁ። በእንዲህ ያለው ባህልና ትውፊት ላይ ግን የአካባቢውን ተወላጆች መጠየቅ፣ ትክክለኛውን መረጃ ለማግኘት ያግዛል ብዬ አስባለሁ፡፡ አንዱ የዘነጋውን ሌላው ሊያስታውሰው ይችላልና፡፡ ማረሻ ብቻውን አያርስምና ባህላችንና ትውፊታችን በስርአቱ እንዲቀጥል ሁላችንም ኃላፊነታችንን እንወጣ፡፡   Read 3892 times