Saturday, 30 September 2017 14:52

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

“ባልና ሚስት ከአንድ ወንዝ ይቀዳሉ”

“ምን ታደርጋለህ?”
“እየጠበቅሁት ነው”
“ማንን?”
“ጎዶትን”
ጠያቂው ቆይቶ ሲመጣ፣ እዛው ቦታ ቁጭ ብሎ ሲጠብቅ አገኘውና …
“አሁንም ጎዶትን እየጠበቅህ ነው?”
“አዎን”
“ጎዶት ማነው?”
“እኔ እንጃ!”
 (Samuel Bucket)
ወዳጄ፤ አንዳንዴ ስታስብ የጎደለህ ነገር ያለ፤ አይመስልህም? … የምንጠብቀው፣ አንድ ቀን መጥቶ “ሙሉ” የሚያደርገን የሚመስለን ‹ነገር›፡፡ (vague expectation) … እንደሚሉት፡፡
በቃላት የማንገልፃቸው ስሜቶች አሉ፡፡ … ህይወታችን ውስጥ ብቅ፣ ጥልቅ የሚሉ፡፡ ብቻችንን ስንሆን ወረር የሚያደርገን ወይ አጠገባችን ያለ የሚመስል፡፡ አልፎ፣ አልፎ ደግሞ በተኛንበት በሩን ከፍቶ ሲገባ የሚታወቀን ዓይነት፡፡ (proximity sense እንደሚባለው) አንዳንዴ ምቾችና ደስታ፣ አንዳንዴ ፍርሃት የሚለቅብን “መንፈስ” እንበለው፡፡
ባለሙያዎች፤ይህንን ዓይነት ስሜት mental events ከሚሏቸው (hallucination, hounting, hypnotization etc) ስነ አዕምሯዊ ውዝግቦች (higher abstractions) ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሲያዛምዷቸው፣ ሌሎች ከ ‹አምልኮት› ጋር ያገናኙታል፡፡ ከመጀመሪያዎቹ ጋር በቀረበ መልኩ ደግሞ በሌላኛው የአእምሮአችን ክፍል (sub conscious mind) የሚፈጠር የግንኙነት (relationship) ቀውስ (ናፍቆት፣ ብቸኝነት ወዘተ) ጋር የተያያዘ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ሁለተኛዎቹ በጎ፣ በጎውን ከእግዜር (Gods presense)፣ በህይወት ከሌሉ ወዳጆች መንፈስ (ghost) ጋር ሲያቀራርቡት፣ በጎ ያልሆነውን ደግሞ በተቃራኒው ይመድቡታል፡፡ (evil spirit … እንደሚሉት፡፡)
ይህንን ያነሳነው relationship (ትዳር፣ ፍቅር፣ ናፍቆት) መቼና እንዴት ተጀመረ ለሚለው ቀጣይ ጨዋታችን ለመንደርደሪያ ብቻ ነው፡፡
እናም ወዳጄ፤ የዚህ ዓይነት ስሜት ኖሮህ ያውቃል? … ከሌለህ በጣም ጥሩ፡፡ … ያላቸው ሰዎች ስለሚኖሩ እስኪ ወደ ኋላ ሄደን ፕሌቶ የፃፈልንን እንመልከት፡፡
“ሰው ግማሽ አካሉን ባገኘ ጊዜ ደስታው ወደር የለውም፡፡ በፍቅር ጥሞና፣ በናፍቆት የተኮማተረ ገላ የጠፋበትን ወይም የራቀውን ግማሽ አካሉን አግኝቶ፣ ሙሉ ሲሆን ተዓምር ይፈጠራል፡፡ ከዛ በኋላ መለያየት የለም፡፡ …. ለአፍታ እንኳ ቢሆን። (And so, when a person meets the half that is his very own, … then something wonderful happens: the two are struck from their senses by love, by a sense of belonging to one another, and by disire, and they don’t want to be separated from one another, not even for a moment.)
ፕሌቶ በዚሁ “ዘ ሲምፖዚየም” በተሰኘው ዲያሎጉ፣ ተውኔት ፀሐፊው አርስቶፌንስ በደረሰው ጭውውት፤ “… ሰው መጀመሪያ ሲፈጠር ማወቅና አለማወቅን (hubris) ጨምሮ የሰውነት አካላቱ (body parts) አሁን ካለው ‹ሰው› እጥፍ ነበር። … ነገር ግን በጥፋቱ የተነሳ የአማልክቶች ንጉስ የነበረው ዚየስ እንደ አፕል ፍሬ ሁለት ቦታ ሰነጠቀው፡፡ … እንዲቀጣ!! … ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሰው ልጆች በየበኩላቸወ ግማሽ አካላቸውን ፍለጋ ይንከራተታሉ፡፡ … ፍቅር የጀመረው የዚያን ጊዜ ነው፡፡ … that is the origin of love … ይለናል፡፡
እና ወዳጄ፤ ስታያት የምትደነግጥላት፣ ስታይህ ክው የምትል አካልህ የት ሰፈር፣ የትኛው ከተማ፣ የትኛው ክልል፣ የትኛው አገር፣ የትኛው አህጉር ትኖር ይሆን? አንተ እንደምታስባት፣ እንደምትጠብቃት፣ እሷም እያሰበችህ፣ እየጠበቀችህ ይሆናል … ይህን ጊዜ!
ትመጪያለሽ ብዬ
ስጠብቅ ፣ ስጠብቅ፣
አገኝሽ እንደሆን
ስፈልግ ፣ ስፈልግ፣
ዓመታቶች መጥተው
ዓመታቶች ሄዱ፣
አንቺ ግን የለሽም
ትመጪያለሽ ብዬ
ዛሬም ጠብቃለሁ፣
ባይኔ ልማትርሽ
መንገድ ዳር ቆሜአለሁ
ምንም ይሁን ምንም
ተስፋ አልቆርጥም ከቶ፣
እኔ ራሴ እስከማስበው
እንኳን ጊዜው ቀርቶ፡፡ … እንዳለው ገጣሚ፡፡
ወዳጄ፤ የሚወዱትን መለየት፣ የሚወዱትን ማጣት ወይ መናፈቅ ያለ ነው፤እኔን የሚከነክነኝ በአንድ ታዛ ስር አብረው መኖር የጀመሩ ወዳጆች፣ ፍቅራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀዛቀዘ መምጣቱ ነው፡፡ … በጥናት የተረጋገጠውን እንኳ ማመን በእጅጉ ያስቸግራል፡፡
“… እንኳን ያንቺ ፍቅር … የትናትናው፣
አራዳ እንኳ ፈርሷል ጣሊያን የሰራው፡፡”
…እየተባለ ጠብ ሲነግስ፣ ጎጆ ሲፈርስ … አልፎም ህይወት ሲቀጠፍ ይታያል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ፣ ቅድም እንዳልነው፣ በአብዛኛው የስጋና የመንፈስ አካልን ፈልጎና ጠብቆ ማግኘት አለመቻል፣ ትዕግስት ማጣት፣ በድህነት አስገዳጅነት፣ በድንቁርናና በጥቅም መነሁለል፣ የእህል ውሃ ነገር እንደሚባለው ሆኖ ወይ የልጆች ስሜት እንዳይጎዳ፣ ‹አንዴ ሆኗል› በማለት ሊሆን ይችላል፡፡ … ምክንያቶቹን ለባለቤቶቹ እንተውላቸው፡፡
ወዳጄ ልቤ ፡- ‹እናታችን› ሄዋን የተሰራችው ከአዳም የግራ ጎን አጥንት ነው ተብሎ ተፅፎአል። … ሁለቱ አንሴስተሮቻችን ፆታቸው ተለያየ እንጂ ሥነ ፍጥረታዊ ባህሪያቸው አንድ ነው፡፡ … ከአንድ ህዋስ ነዋ የተሰሩት!! … “ባልና ሚስት ከአንድ ወንዝ ይቀዳሉ” የሚባለው እነሱ ላይ ልክ ይመስላል፡፡ አንዱ ለሌላኛው (made to each other) ሳይሆን አንዱ ከሌላኛው (made from the other) እንደሚባለው ማለት ነው፡፡ … ቀለል ስናደርገው ደግሞ perfect couple እንደሚሉት ይሆናል። ፍቅር የተጀመረው ‹እዚህ ጋ› ነው፡፡ … ለኛ፡፡ … ጣይቱ ባራኺ እንደዘፈነችው፡፡
በዘመናዊ ሳይንስ ከአንድ እንስሳ (ሰውን ጨምሮ) ወይም ዕፀዋት አካል… በዓይናችን እንኳ ለማየት ከማንችለው ህዋስ (cell) በመቆንጠር፣ ተመሳሳዩን እንስሳ ወይ ዕፅዋት መስራት እንደሚቻል ተረጋግጧል፡፡ … Cloning ይሉታል፡፡ በሰው ላይ እንዳይሞከር ‹ኢሞራላዊ› ተብሎ ተወግዟል፡፡
ይሁን እንጂ የጋብቻ “ቅጥ” ማጣት ያሰባሰባቸው አንዳንድ ተመራማሪዎች ታዲያ እንደ ‹አባታችን› አዳምና እናታችን ‹ሄዋን› ጥሩ ቤተሰብ እንድንሆን፣ሚስቶቻችን ወይ ባሎቻችን በዚሁ ቴክኖሎጂ (genetic engineering) ከህዋሳችን ቢሰሩ፣ ዓለም የመልካም ቤተሰቦች ‹ቤት› ስለምትሆን ጦርነትና ስጋት አይኖርም፣ ድህነት ይጠፋል የሚል አዝማሚያ አሳይተው ነበር፡፡ የኋላ ኋላ ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚበዛ በማረጋገጣቸው ትተውታል፡፡ ምክንያቱም ሰው ሁሉ ተመሳሳይ ይሆንና፣ እንደኛ አገር ‹ኋላ ቀሮች› አንዱን ከአንዱ ለመለየት ፈተና እንዳይሆንባቸው ሳይሰጉ አልቀሩም፡፡  
እና ወዳጄ፤ ወደ ቁም ነገሩ ስመለስ፣ ደጅ ደጁን እያየን፡-
“እንደ ፀደይ ወራት
እንደ ዐደይ አበባ፣
እጠብቅሻለሁ
መስከረም ሲጠባ፡፡”
-- እያልን ቢጤአችንን እንጠብቅ? … (ብትመጣም ባትመጣም) ወይስ በ ‹እህል ውሃ› ሰበብ ለባርነት እጅ እንስጥ?
ሠላም!



Read 2015 times