Saturday, 30 September 2017 14:54

መፍጠርም መኮረጅም እንዴት ይሳነናል?

Written by  ትዕግስቱ በለጠ
Rate this item
(5 votes)

አሁንም “ቃና” ይዘጋልን የሚለው ዘመቻ አልቆመም!

   በየበዓሉ ተሰናድተው ለተመልካች የሚቀርቡ ልዩ የቴሌቪዥን ፕሮግራማቾች፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሰልቺና አታካች እየሆኑ መምጣታቸው፣ በጉጉት እንዳንጠብቃቸው ያደረገን ይመስለኛል፡፡ በአንድ ኩባንያ ውስጥ በማርኬቲንግ ሃላፊነት የሚሰራ አንድ ግለሰብ እንዳጫወተኝ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለኩባንያቸው ከሚላኩላቸው በርካታ የአውዳመት የቴሌቪዥን ፕሮግራም ፕሮፖዛሎች መካከል አብዛኞቹን አይመለከቷቸውም፡፡ ለምን ቢባል፣ተመሳሳይ፣ አሰልቺና እንኳን ሊያዝናኑ ጭራሽየሚያበሳጩ በመሆናቸው ነው ብሎኛል - የማርኬቲንግ ባለሙያው፡፡ እስካሁን በእሱ ዓይነት ቦታ ሆኜ ፕሮፖዛሎችን የመገምገም ዕድል ባላገኝም እንደ ተመልካች ግን በሱ አስተያየት ከሞላ ጎደል እስማማለሁ፡፡ በዚህም የተነሳ የዓመት በዓል ዝግጅቶችን መመልከት ሁሉ ትቻለሁ፡፡
ዕድሜ ለጓደኛዬ! ከዘንድሮ የዓውዳመት የቴሌቪዥን ዝግጅቶች መካከል፣ በኤልቲቪ የቀረበውን “ከታክሲው ተራ…” የሚል ዝግጅት ተመልክቻለሁ፤ በቲቪ ሳይሆን በኮምፒውተሬ ላይ፡፡ በዓሉ ካለፈ ከሳምንት በኋላ ነው፣“ማየት አለብህ” ብሎ ከዩቲዩብ አውርዶ የሰጠኝ፡፡እግዜር ይስጠው! ዝግጅቱ በደንብ ታቅዷል፡፡በደንብ ታስቦበታል፡፡ (ዋና ችግራችን ማሰብ እኮ ነው!) በደንብ ተለፍቶበታል፡፡ ግን ለምንድን ነው፣ አብዛኞቹ እንዲህ ያሉ ዝግጅቶች፣ አሰልቺና የማይስቡ የሚሆኑት?
ወደ ዝግጅቱ እንሂድ፡፡ የታክሲ ሹፌሮችና ረዳቶች በዕለት ተዕለት ሥራቸው፤ ከተሳፋሪዎች ጋር የሚገጥማቸውን ተግዳሮትና በታክሲ ሥራ ዙሪያ ያለውን የተሳሳተና የተዛባ አስተሳሰብ የሚቃኝ … የሚያነቃቃ … ግንዛቤ የሚያስጨብጥ እንዲሁም እውነታውን ህብረተሰቡ እንዲረዳ ለማድረግ የተጣረበት ዝግጅት ነው፡፡ በእርግጥ በአንድ የቲቪ ዝግጅት ሥር የሰደደ አመለካከትን ወይም ግንዛቤን መቀየር ያዳግታል፡፡
ራሱን፤ “ኮሜዲያን፣ ዶክተር፣ ኢንጂነር ደምሴ ፈቃዱ” በሚል የሚያስተዋውቀን አርቲስት(ኮሜዲያኑ ማለት ነው) የዝግጅቱ መሪ ነው፡፡ ፕሮግራሙ ሲጀምር፤ የታክሲ ሹፌሮችና ረዳቶች ተሞክሯቸውን በአጭር በአጭሩ ያጋራሉ፡፡ ምሬትና ወቀሳ ይሰነዝራሉ። አጋጥሞናል የሚሉትን፡፡ “ሰውን የሚያክል ክቡር ፍጡር እያመላለስን እንዴት ምስጋና አይኖረንም”፣“ህዝቡ ለኛ ያለውን አመለካከት ቢለወጥ ጥሩ ነው”፣ “ትራፊክ ፖሊሶች  እንደ ሰው አያዩንም”ወዘተ---የሚሉ ቅሬታዎችን አቅርበዋል፡፡
የዝግጅቱ አስኳል ግን ይሄ አይደለም።  በርካታ ታዋቂና ተወዳጅ አርቲስቶች የተሳተፉብት ነው፡፡ አርቲስቶቹ በታክሲ ሹፌርነትና ረዳትነት ተመድበው፣ ህዝቡ እንዳያውቃቸው በሜክአፕ አርቲስት ተሰርተው፣ በመዲናዋ ለአንድ ቀን አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ “የእውነት እየኖሩ መተወን” የሚባል ነገር ይኖር ይሆን?(“ተሳፋሪውን ፕራንክ ያደርጉታል”እንደ ማለት) በሹፌርነት ከተመረጡት መካከል፡- አርቲስት ሸዊት ከበደ፣ አርቲስት ትዕግስት ግርማ፣ አርቲስት ይገረም ደጀኔ … ይገኙበታል። በረዳትነት ከተመደቡት ውስጥ ደግሞ አርቲስት ኢዮብ ዳዊት (ልጅ ተዋናዩ) እና ልጅ ያሬድ (ኮሜዲያኑ) ይጠቀሳሉ፡፡ የሚገርመው ደግሞ አርቲስቶቹን ፕራንክ የሚያደርጉ ሌሎች ሰዎች ተመድበዋል፡፡ (በፕራንክ ውስጥ ሌላ ፕራንክ በሉት!) አንደኛዋ ለምሳሌ፡- “የ100 ብር መልሴን ስጠኝ” ብላ የምትሟገትና የምትሳደብ ናት፡፡ (ግን እያጭበረበረች ነው) የተሰጣት ሚና የአጭበርባሪ ተሳፋሪ ነው፡፡ ሹፌሩም ሆነ ረዳቱ ይሄን አለማወቃቸው ነው፣ ነገርየውን ማራኪ የሚያደርገው፡፡ ሌላኛው ደግሞ ሰካራም ተሳፋሪ ነው፡፡ ሰክሮ “የማስመልስበት ፌስታል ውለዱ” ይላል፡፡ሆን ብለው መኪና ስር በመውደቅ፣ “ተጋጨን” የሚሉም አሉ። ከዚያም ገንዘብ ለመደራደር ይሞክራሉ፡፡ እነዚህ እነዚህ ---ለሹፌሮቹና ረዳቶቹ ከባድ ፈተና ይደቅኑባቸዋል፡፡ የዓመት በዓል ዝግጅት በመሆኑ፣ ማዝናናትምይጠበቅበታል፡፡ ስለዚህ በታክሲ ሾፌሮቹ መካከል (በአርቲስቶቹ ማለት ነው) ውድድር ይካሄዳል፡፡ የታክሲ አገልግሎት እየሰጡ ይወዳደራሉ፡፡ ተሳፋሪውን ማዝናናት፣ የትራፊክ ህግ ማክበር፣ የታክሲዎች አቋቋምና አጫጫን፣ ያስገቡት የሂሳብ መጠን … ወዘተ የውድድሩ መስፈርቶች ነበሩ፡፡ ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡና የተራ አስጠባቂዎች ኃላፊ፣ ዳኝነት ሰጥተዋል፡፡ በመጨረሻም የአርቲስት ትግስት ግርማ ቡድን አሸናፊ ሆኖ ሙክት ተሸልሟል፡፡
ትኩረት ያልተሰጠው አብይ ማህበራዊ ችግርን የዳሰሰ፣ የታክሲ ስራ አስቸጋሪነትን ለማሳየት የሞከረ፣ አዝናኝናአዲስ (ያልተሰለቸ) እንዲሁም ቀልጠፍ ያለ፣ ግሩም የአዲስ ዓመት ልዩ የቴሌቪዥን ዝግጅት ነበር፡፡ (ኤዲቲንጉንም ሳያደንቁ ማለፍ አይቻልም!) ብራቮ የሃሳቡ አፍላቂዎች! ብራቮ አርቲስቶች! ብራቮ ኤልቲቪ!
እንግዲህ … “ለማሰብ” እየሰነፍን እንጂ ምርጥ የዓመት በዓል የቴሌቪዥን ዝግጅት ማሰናዳት ጨርሶ የማይሞከር አይደለም - ይቻላል፡፡ (አዘጋጆቹን “ይቻላል” ይበላቸው!) የአውዳመት ልዩ የቴሌቪዥን ዝግጅት ብቻ ግን አይደለም፡፡ የአዘቦት ቀናት ምርጥ የቲቪ ፕሮግራሞች ብናገኝ አንጠላም፡፡ ከአንዱ ጣቢያ እርስ በርስ “ኮፒ ፔስት”እየተደራረጉ ግን አይደለም፡፡ ሃሳብ ነጥፎ ካስቸገረን …ቢያንስ ከውጭ ቻናሎች ምርጡን ቀድቶ፣በቅጡ ወደ ሃበሽኛ (“ኢትዮጵያናይዝድ”!) ማዛመድ ቀላል ስራ እንዳይመስላችሁ  - ትልቅ አቅም ይጠይቃል፡፡ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር (ነፍሳቸውን ይማረውና!) “ጥሩ ኮራጅ መሆን ችግር የለውም” ማለታቸው ትዝ ይለኛል፡፡ እኛ‘ኮ መፍጠርም … መኮረጅም ነው የተሳነን። (ብንኮርጅ ደግሞ ቀሽም ቀሽሙን!) ወይም ደግሞ ምርጡን፣ ቀሽም አድርገን እንኮርጃለን። አለመታደል ነው፡፡
 ከዚህም ግን የሚብስ አለ፡፡ በጣም አደገኛ። ምን መሰላችሁ? ተወዳድረን የማናሸንፈው የመሰለንን “ግዙፍ” ተፎካካሪ (በሙያ … በፖለቲካ … በሃብት … በጥበብ ወዘተ ለማጥፋት … ለማውደም --- መሯሯጥ፣ የክፋት ሁሉ መጨረሻ ነው፡፡
ሥልጣኑ በመንግስት እጅ ከሆነ ደግሞ ቁጭ ብሎ የክፋት ፕሮፖዛል መፃፍ .. የውንጀላ ረቂቅ ማዘጋጀት … ከዚያበልኩ የፈጠርንለትን ሃጢዓት እየነቀስን፣ መንግስት እንዲዘጋው---ከሀገር እንዲያባርረው … ከኛ እንዲያርቀው… እንዲያግደው … ዘመቻ  ማወጅ፡፡ ክፉ ባህል፡፡
የ “ቃና” ቴሌቪዥን መምጣት ለተመልካች … እፎይታና ሰፊ ምርጫን አጎናፅፎናል፡፡ ለፊልም ባለሙያዎች (በተለይ ማደግና መፎካከር አንችልም ብለው ለተፈጠሙቱ!) የእንጀራ ገመድ እንደመበጠስ የሚቆጠር ነው የቃና መምጣት፡፡ (ቢያንስ እነሱ የሚያስቡት እንዲያ ነው!) ግን በግልጽ አይናገሩትም፡፡ “ተመልካች አሸፈተብን”፣ “ገበያ ወሰደብን”… “የተመልካች የፊልም ግንዛቤን ሰቀለብን” -- ወዘተ ብሎ  ሃቁን መናገር የአባት ነው፡፡
መፍትሄ አይጠፋም (…መወያየትም ይቻላል!) ሆኖም“የባህል ጠበቃ” … “የግብረ ገብ ፖሊስ” … “የህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ተቆርቋሪ ….” መስሎ መቅረብ ግን አሳሳች ነው። (ባህልም ሆነ ህፃናትና ወጣቶች፤ በሚኒስትር ደረጃ የተቋቋመላቸውየሚኒስቴር መ/ቤቶች አላቸው!) ቤት ውስጥ ደግሞ ከማንም የበለጠ የሚያስቡላቸው ብቻ ሳይሆን የሚሳሱላቸው ወላጆችና ቤተሰቦች አላቸው - ህፃናትና ወጣቶቹ፡፡ ስለዚህ አያስኬድም፡፡
የሆኖ ሆኖ በተደጋጋሚ “ቃና” እንዲዘጋ የሚቀርበው ጥያቄ በጣም ያሳፍራል፡፡ ከመንግስት ቢመጣ  እንኳን መቃወም ያለብንን የክልከላ አባዜ፣ ከሚዲያ ሰዎችና ከአርቲስቶች (ያውም የፊልም ባለሙያዎች) መስማት ያሳዝናል፤ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡
የነፃነት ጠላት መሆን ነው፡፡ ነገ መንግስት ተነስቶ አንዱን የቴሌቪዥን ጣቢያ ወይም ጋዜጣ፤ “ፀረ ሰላም፣ ፀረ ልማት፣ ፀረ ዲሞክራሲ” ወዘተ የሚል ታፔላ ለጥፎለት፣ ቢዘጋው ወይም ቢያግደው … የመብትና የነፃነት ታጋይ መስለው እርምጃውን የሚኮንኑት፣ ዛሬ “ቃና” እንዲዘጋ፣ ቀበቶአቸውን አጥብቀውየዘመቱ ወገኖች ናቸው፡፡
(ወደ ጨለማና አፈና ዘመን ለመመለስ ለምን ቸኮልን?!) ለመሆኑ የሚዲያ ነፃነት ይከበር ወይስ “ቃና” ይዘጋ?! የሚል ጥያቄ ቢቀርብልን፣ መልሳችን ሁለተኛው እንደሚሆን ግልፅ ነው፡፡
አያችሁልኝ … የፊልም አይዲያዎችን ያፈልቅ የነበር ድንቅ አዕምሮ… በከንቱ ሃሳብና በአሉታዊ መንፈስ (negative attitude) ተጠቅጥቆ …. ምን ያህል ሜጋባይት ኢነርጂ እንደሚያባክን! (“ለማንኛውም ቃና ውስጤ ነው!”)
በነገራችን ላይ መንግስት አምና ከግል ሚዲያ አባላት ጋር ባደረገው ውይይት ላይ “ቃና” እንዲዘጋ ወይም እንዲታገድ ከጋዜጠኞች ለቀረበው መረር ከረር ያለ ጥያቄ፤ (“ሚዲያዬን ወይም ጋዜጣዬን ዝጋው” እንደ ማለት እኮ ነው!)፤ መንግስት ቃናን ለመዝጋት የሚያስችል “የህግ ማዕቀፍ” እንደሌለው ጠቁሞ፤ ስጋታቸውን ግን እንደሚጋራ ገልፆላቸው ነበር፡፡ (“የባህል ወረራ” ምናምን ያሉትን ማለት ነው!)
አሁን የምፈራው ምን መሰላችሁ … እኒህ “የባህል ጠበቃ ነን” ባዮች .. “ቃና” እንዲዘጋ የሚያስችለውን የህግ ማዕቀፍአዘጋጅተው እንዳያቀርቡ ነው፡፡  “ቃናንማሸነፊያው ብቸኛው መንገድ፣ ማዘጋት ብቻ ነው የሚመስላቸው፡፡ (እነዚህ መንግስት ቢሆኑ አስቡት?!)



Read 1744 times