Saturday, 30 September 2017 15:04

የመስቀል ደመራ - ከምኒልክ እስከ ኢህአዴግ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

• “መስቀል፤ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም በዓል ሆኗል”
• ”የገቢ ምንጫችን መስቀል መስቀል” መባል አለበት
• ”ጥምቀት በዩኔስኮ ለመመዝገብ በሂደት ላይ ነው”


በዘንድሮው የመስቀል በዓል ምን ዝግጅቶች ተካሄዱ?
በጣም ደስ የሚል ነበር፤ እኛ እንደ ቢሯችን ፕሮግራሙን የያዝነው በስፋት ጉብኝት ላይ አተኩረን ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የአገር ውስጥ ጉብኝት ላይ ብዙ ወደ ኋላ የቀረን በመሆኑ፣ ይህን ለማስተካከልና የአገር ውስጥ ጉብኝት እንዲያድግ ለማድረግ ነው፡፡ በዚህ ረገድም በጣም የተሳካ ስራ ሰርተናል ማለት እችላለሁ፡፡
በጉብኝቱ ማን ተሳተፈ? የጉብኝት  ቦታዎቹስ ?
ጉብኝቱ ይመለከታቸዋል ያልናቸውን ግለሰቦችም ሆነ ተቋማት ያካተተ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ት/ቤቶች፣ የልማት ማህበራት፣ ሆቴሎች፣ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ የታክሲ ማህበራት፣ የአገርህን እወቅ ክበባት፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ሌሎችም በጉብኝቱ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ የተጎበኙት ሙዚየሞች ናቸው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ 22 ያህል ሙዚየሞች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ኤትኖግራፊክ ሙዚየም፣ መንበረ ፓትርያርክ ሙዚየም፣ አራዳ ጊዮርጊስ ሙዚየም፣ ባዕታ ሙዚየም፣ የቀይ ሽብር ሰማዕታት ሙዚየም፣ አዲስ አበባ ሙዚየም፣ ብሔራዊ ሙዚየምና ሌሎችም ተጎብኝተዋል፡፡ በትላንትናው ዕለት ደግሞ  ከአሥሩም ክፍለ ከተማ የተውጣጡ ነዋሪዎችና ወጣቶች ጎብኝተዋል፡፡ ለእያንዳንዱ ክ/ከተማ አራት አውቶቡስ፣ የጉብኝት መግቢያ ክፍያ፣ ውሃና ሌሎች ወጪዎችን ቢሯችን ሸፍኖ ጉብኝቱ ተካሂዷል፡፡ እነዚህ ሙዚየሞች የተለያየ ታሪክና ቅርስ የያዙ፣ ትልቅ የአገራችን ሀብት ቢሆኑም አብዛኛው ነዋሪ፣እንኳንስ ሥራዬ ብሎ አምስትና አስር ብር ከፍሎ መጎብኘት ቀርቶ ትዝም አይሉትም፡፡ ይሄ መለወጥ አለበት፡፡ ነዋሪው በዙሪያው ያሉትን ቅርሶች መጎብኘት፣ ታሪኩንና ማንነቱን ማወቅ ይኖርበታል፡፡ ስለዚህም ቢሯችን ተነሳሽነቱን ወስዶና በጀት መድቦ ጉብኝቱን አካሂዷል፡፡ መስቀልን እንዲህ ነው ያሳለፍነው፡፡
የደመራና የመስቀል በዓል አከባበር ታሪካዊ ዳራ ይታወቃል፤ ግን አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡ ደመራ ከበራ በኋላ የሚወድቅበት አቅጣጫ፣ የመጪውን ጊዜ እጣ ፈንታ የሚወስን ነው ይባላል፡፡ ይሄ ነገር  ሀይማኖታዊ መሰረት አለው ወይስ ?
በግራ የሚቆሙ ሀጢያን፣ በቀኝ የሚቆሙ ፃድቃን ናቸው የሚለው በ”ዕለተ ምፅዓት” ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ደመራው ከሚወድቅበት አቅጣጫ ጋር በተያያዘ የሚሰጠው ትርጉም ግን ምንም ሀይማኖታዊ ይዘት የለውም፤ ትክክልም አይደለም። ሀይማኖታዊም ሆነ የእምነት መሰረት የለውም። ለምሳሌ እኔ ባደግኩበት የገጠር አካባቢ፣ በሬ ሲታረድ በግራ በኩል ከወደቀ፣ የጥሩ ጊዜ ምልክት አይደለም፡፡ “በግራ ወድቋል በቃ ስራችንም ኑሯችንም ግራ ይሆናል፤ ስለዚህ ወደ ቀኝ ይዙር” ተብሎ ወደ ቀኝ ይዞራል፡፡ ሌላው ቀርቶ ነብር ራሱ የገደለው እንስሳ፣ በቀኝ ካልወደቀ በስተቀር አይበላውም ይባላል፡፡ ስለዚህ የጣለው እንስሳ ነፍሱ ከመውጣቱ በፊት ወደ ቀኝ ያዞረዋል ይባላል፡፡ ይሄ እንግዲህ የእነሱ የተፈጥሮ ስርዓት ሊሆን ይችላል። የደመራ ግን ከእዚህ ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ የደመራው አተካከልና አቋቋም፣ የመውደቂያውን አቅጣጫ ይወስነዋል፡፡ ለምሳሌ ሲተከል በአንድ በኩል በደንብ ተተክሎ፣ በአንድ በኩል ካልጠበቀ፣ ሲቀጣጠል በደንብ ወዳልተተከለው አቅጣጫ ይወድቃል፡፡ በሌላ በኩል ደመራው ሲለኮስ፣ ነፋስ ወደሚነድበት አቅጣጫ በሀይል ከነፈሰ፣ ነፋሱም እሳቱም ተባብረው ደመራውን ይገፉትና ይወድቃል። ደመራው ወደየትኛውም አቅጣጫ ቢወድቅ ግን ከአፈ ታሪክነት የዘለለ ትርጉም የለውም፡፡ ስለዚህ “በግራ ከወደቀ፣ ይሄ መንግስት ይወድቃል፣ በቀኝ ከወደቀ ይቀጥላል፣” “በቀኝ ከወደቀ ዘመኑ ጥሩ ነው፣ በግራ ከወደቀ ዘመኑ በችግር የተሞላ ነው፣” የሚለው ትርጉም መሰረት የለውም፡፡  
የመስቀል ደመራ፣ በ2006 ዓ.ም በዩኔስኮ፣ በዓለም ቅርስነት ከተመዘገበ ወዲህ ለአገሪቱና ለህዝቧ ምን ለውጥ መጥቷል?
በርካታ ለውጦች መጥተዋል፡፡ አንደኛ ቀደም ሲል የመስቀል ደመራ፣ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በዓል ብቻ ነበር፡፡ ከዚህ ሀይማኖት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ብቻ፣ በየቤተ ክርስቲያኑ በየሰፈሩ ያከብሩታል፡፡ በየገጠሩም አደባባይ ተመቻችቶ ይከበራል፡፡ ነገር ግን በዩኔስኮ ከተመዘገበ በኋላ የዓለም ቅርስና ሀብት ነው፡፡ ዓለም ራሱ የገቢ ምንጭ የሚፈጥርበት ነው፡፡ ዓለም ራሱ የተለያዩ ቱሪስቶችን ይዞ የሚመጣበት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን አስጎብኚዎች ደግሞ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከሚገኙ አስጎብኚ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ ቱሪስቶችን እያመጡ፣ ራሳቸውንም አገራቸውንም መጥቀም የቻሉበት ነው፡፡ ቱሪስቶች መስቀልን ለመጎብኘት ሲመጡ ሆቴሎች፣ አስጎብኚዎች፣ መኪና አከራዮች፣ በዕደ ጥበብ ሥራ የተሰማሩት፣ ቱር ጋይዶች--- ሁሉም ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ከዚህ ሁሉ ደግሞ አገራችንም ተጠቃሚ ናት፡፡ መስቀል ልክ “የገቢ ምንጫችን ቡና ቡና” እንደሚባለው ሁሉ፣ “የገቢ ምንጫችን መስቀል መስቀል” መባል አለበት፡፡ በሌላ በኩል ለመስቀል በዓል መቀጠልና መድመቅ ጥበቃ የምናደርገው እኛ ብቻ ሳንሆን ዓለምም ጭምር ነው፡፡ መስቀል፤ የኦሮቶዶክስ ብቻ ሳይሆን የዓለም በዓል ነው፡፡  ይሄ ራሱ ትልቅ ነገር ነው፤ ትልቅ ለውጥ አለው፡፡
እስኪ ወደ ታሪኩ እንምጣ፡፡ በአገራችን የመስቀል ደመራ መከበር የጀመረው መቼ ነው?
የመስቀል ደመራ ማክበር የተጀመረው፣ በ1898 ዓ.ም በአፄ ምኒሊክ ዘመን ሲሆን የሚከበረውም በጃንሜዳ ነበር፡፡ ያን ጊዜ ጃንሜዳ ለሰልፍ፣ ለስብሰባ፣ ለስፖርት ተብሎ የተቋቋመ ሲሆን ደመራም እዚያው ነበር የሚከበረው፡፡ ከዚያ በልጅ እያሱ ጊዜ፣ መስከረም 16 ቀን 1908 ዓ.ም በዚያው  በጃንሜዳ ደማቅ የደመራና የመስቀል በዓል እንደተከበረ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በወቅቱ በትልቅ ወታደራዊ ትርኢት እንዳከበሩት ይነገራል፡፡ ሌላው ቀርቶ ደመራው ሲከበር፤ የልጅ እያሱ ልብስ ቀይ ከፋይ ባለወርቅ ሰገባ፣ ባለወርቅ ካባ ደርቦ፣ በወርቅ ኮርቻና መጣምር ባጌጠ፣ “ጤና” በተባለ ፈረሱ ላይ ተቀምጦ፣ በፈረስ ታጅቦ፣ ጃንሜዳ ደመራው ቦታ ሲደርስ፣ አሽከሮቹ ከወርቅና ከብር በተሰራ ልዩ ልዩ ጌጥ አጊጤው ተቀብለውታል፤ ይላል መረጃው፡፡
ከልጅ እያሱ በኋላ ግን የመስቀል ደመራ በጃንሜዳ አልቀጠለም ----
እውነት ነው፡፡ በልጅ እያሱ ላይ ተቃውሞ መነሳት በመጀመሩ የመስቀል ደመራው እዚያ መከበሩ አልቀጠለም፡፡ ቦታው ከዚያ በኋላ አዋጅ ማወጃ ሆነ፡፡ “ልጅ እያሱ አይቀጥልም፤ ይውረድ” የሚሉ ተቃውሞዎች መግለጫ ቦታ ሆነ፡፡ አዋጅ መንገሪያ፣ ጉባኤ ማካሄጃና መሰብሰቢያ ሆነ። ከዚያ ደመራ፣ ፍልውሃ ሜዳ መከበር ጀመረ። የ1918 ዓ.ም መረጃ እንደሚያሳየን፤ በዚያ ወቅት እጨጌ ገብረ መንፈስ ቅዱስ 58ኛው የተባሉ የደብረ ሊባኖስ እጨጌና ራሳቸው ጃንሆይ በተገኙበት፣ የአራዳና የክብር ዘበኞች በዘመናዊ ስርዓትና በኮት ተሰልፈው፣ ልዩ ትርኢት በደመራ ጊዜ ያሳዩ ነበር። በሌላ በኩል ፀሀፌ ትዕዛዝ ወ/መስቀል ታሪኩ፤ ጭፍሮቻቸውንና የፖስታ ቤት ሰራተኞቻቸውን አሰልፈው፣ አርባ ያህል የአርመን ሙዚቀኞች በሙዚቃ ታጅበው ትርኢት ያቀርቡ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ፡፡
ከፍል ውሃ ሜዳ ወደ እስጢፋኖስ ሜዳ ተዛውሮም ይከበር ነበር ይባላል፡፡ እንዴት እስጢፋኖስ ተጀመረ?
ወደ እስጢፋኖስ ሜዳ ከመሄዱ በፊት አራዳ ጊዮርጊስ ሜዳ መከበር ጀምሮ ነበር፡፡ ይሄ እንግዲህ ከ1920 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ ከዚያ የበዓሉ አከባበር እየደመቀ፣ ሰው እየበዛ ሲሄድ፣ አራዳ ጊዮርጊስ ሜዳ በመጥበቡ አሁን አፄ ምኒልክ ሀውልት የቆመበት ትልቁ ሜዳ ላይ መከበር ጀመረ፡፡ ያን ጊዜ እንደውም በበዓሉ ዕለት ሦስት አውሮፕላኖች እያንዣበቡ በመገለባበጥ ትርኢት እንደሚያሳዩ፣ የወረቀት አበባና የግጥም ፅሁፎችን ይበትኑ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በጣም የተለየ አከባበር ነበረው፡፡ በጣም የሚገርመው ግጥሞች ሁሉ ነበሩ፡፡
የሚያስታውሷቸወ ግጥሞች ይኖራሉ?
“የመስቀል በዓል ምንኛ ገነነ
ከአምናም ዘንድሮ የበለጠ ሆነ
ንግስትና ንጉስ በዙፋን ላይ ሆነው
ጀግናው ተሰልፎ መኳንንቱ ከበው
በግራና በቀኝ በራስጌ በግርጌ
አምስት ጳጳሳት ስድስተኛ እጨጌ
ደግሞም ተንዣበበ በስተላይ ባየር
ከጓደኞቹ ጋር የተፈሪ ንስር” -- ይላል፡፡
 “ንስረ ተፈሪ” እንግዲህ በዚያን ወቅት የአውሮፕላኑ ስም መሆኑን ልብ በይ፡፡
“አበባ አበባ ሊነሳ በዓሉን ሊያከብር
በዘንድሮ በዓል እስኪ ደስ ይበለን እልል እንበል
ብርሀንን እንልበስ ሰላምን እንውደድ
ንስረ ተፈሪ ነው በጨለማ እንሂድ
በአየር ላይ ሆኖ አበባን ሲሰራ
ከተከታዮቹ ከመላዕክት ጋራ
እንቁጣጣሽ ይላል የተፈሪ አሞራ”፡፡-- ይላል፡፡
 በወቅቱ በመስቀል ደመራ ክብረ በዓል ላይ ከአውሮፕላን የሚበተነው ግጥም ነው፡፡ የተፈሪ አሞራም አውሮፕላኑ ነው፡፡ እና ከዚያ በኋላ አሁንም ህዝቡ እየበዛ ሲሄድ፣ ክብረ በዓሉ እስጢፋኖስ ቤተ-ክርስቲያን ፊት ለፊት ያለው ሜዳ ላይ መካሄድ ጀመረ፡፡ አንድም ምኒልክ አደባባይ በመጥበቡ፣ ሁለተኛም እስጢፋኖስ በ17 የሚከበር በመሆኑ፣ እስጢፋኖስ ፊት ለፊት ሲከበር ቆይቶ፣ ሰፊ ቦታ በማስፈለጉ ወደ መስቀል አደባባይ ተዛወረ፡፡ እስከ ጃንሆይ ውድቀት፣ 1967 ዓ.ም  ድረስ መስቀል አደባባይ ይከበር ነበር፡፡
በደርግ ዘመን የቦታው ስም  “አብዮት አደባባይ” በተባለበት ወቅት ደመራ የት ይከበር ነበር?
ደርግ ቦታውን በከለከለበት ወቅት የመስቀል ደመራ ተመልሶ ወደ ምኒልክ አደባባይ መጣና መከበር ጀመረ፡፡ በየሰፈሩም ህዝቡ ማክበሩን ቀጠለና ኢህአዴግ በ1983 ዓ.ም አገሪቱን ሲቆጣጠር፣ መስቀል  አደባባይ በቀደመ ግርማ ሞገሱ መከበር ጀመረ፡፡ በ1987 ዓ.ም የሀይማኖት ነፃነት በህገ- መንግስቱ ሲፀድቅ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመላው አደባባይ እያሸበረቀ፣ የሀይማኖት አባቶችና ከፍተኛ ባለስልጣናት እየተጋበዙ መከበሩን ቀጠለ፡፡ አሁን ከኦርቶዶክስ ሀይማኖትና ከኢትዮጵያ ሀብትነት አልፎ የአለም ቅርስ ሆኖ ተመዘገበ፡፡ ይህን ሂደትና ውጣ ውረድ አልፎ፣ ለዚህ መብቃቱ በእውነት የሚደንቅ በመሆኑ አሁንም የበለጠ ልናሳድገውና ልንንከባከበው ይገባል፡፡ ምክንያቱም መስቀል በዓለም ቅርስነት ሲመዘገብ ደመራው ብቻ ሳይሆን የህዝቡም ባህል አብሮ ነው የተመዘገበው፡፡
መስቀል በልዩ ሁኔታና በዝግጅት የሚከበርባቸው የአገራችን ክፍሎች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ጉራጌ ዞን፣ ወላይታ፣ ጋሞ ጎፋ፣ ትግራይ፣ አማራና ሌሎችም አካባቢዎች የሚደረገው ዝግጅትና የህዝቡም ባህል ተጠንቷል፡፡ የዓለም የታሪክና የባህል ተመራማሪዎች፣ አጥንተውት ነው የተመዘገበው፡፡ ይሄ ትልቅ እድል ነው፡፡ ለዚህ ነው ቀደም ብዬ “የገቢ ምንጫችን መስቀል መስቀል” መባል አለበት ያልኩሽ፡፡ በነገራችን ላይ ደመራ ከአክሱም ስልጣኔ በፊትም እንደ ዘመን መቀበያ ተደርጎ ይከበር ነበር፡፡ ከክርስትና ጋር ተያይዞ ግማደ መስቀሉ ሲመጣ፣ ዘመን መለወጫ መስከረም 1፣ ደመራ በ16 ሆነ፡፡ ክርስትና በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ወደ አገራችን ከመጣና ንግስት እሌኒ ግማደ መስቀሉን አስቆፍራ ካስወጣች በኋላ ነው፣ ዘመን መለወጫና ደመራ የተለያዩት፡፡ ከዚያ በፊት ደመራ እንደ ዘመን መለወጫ ነበር የሚከበረው፡፡
የዘንድሮው የመስቀል ደመራ የህንድ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ በተገኙበት ነው የተከበረው፡፡ የመስቀል አከባበራችን ከህንዶች ጋር የሚያመሳስለው ነገር አለ?
በጣም ጥሩ፡፡ አምስት እህት አብያተ ክርስቲያናት የሚባሉ አሉ፡፡ እነዚህም ህንድ፣ ሶሪያ፣ አርመን፣ ግብፅና ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እነዚህ አምስቱ አንድ አይነት አምልኮ ነው ያላቸው፤ ነገር ግን በቀዳማዊ ምኒልክ ጊዜ ታቦተ ፅዮን ወደ አገራችን ስለገባች፣ እኛ የጥንቱን ተከትለን ታቦት እናወጣለን፤ ቀሪዎቹ አራቱ ይህን ስርአት አይከተሉም፡፡ ስሙ የተፃፈበት ታቦት በየቤተክርስቲያኑ አላቸው፤ ነገር ግን እንደኛ ወጥቶ የሚንቀሳቀስና የሚዘዋወር ታቦት የላቸውም፡፡ ታቦተ ፅዮንን የተቀብልን እኛ ብቻ ነን። ታቦቱን እናከብራለን፡፡ ያሬድ ዜማ ሰርቶላቸዋል፤ ያንን እናከብራለን፡፡ የጥናት መፅሐፍ ፅፎላቸዋል። ይሄ ሌላው ዓለም የለም፡፡ እኛ በዚህ ምክንያት ደመራን እናከብራለን፡፡ ነገር ግን ከህንዶች ጋር አንድ አይነት ሀይማኖት ነው ያለን፡፡ በዚያ ላይ መስቀል የዓለም ቅርስ በመሆኑ፣ የህንድ ኦርቶዶክስ ፓትሪያርክ በበዓሉ ላይ ታድመዋል፡፡
ወደፊት በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እቅድ የታየዘለት ቅርስ አለ?
እንደ አገር እንግዲህ ጥምቀት የሆነ ሂደት ላይ እንዳለ አውቃለሁ፡፡ የጥምቀት በዓል አከባበርና ድምቀቱን የምታውቂው ነው፡፡ እንደውም እኔ ከመስቀል ቀድሞ መመዝገብ ነበረበት ባይ ነኝ። በቅርስ በኩል ብዙ ሊመዘገቡ የሚችሉ ሀብቶች አሉን፤ ጥረት ይጠይቃል፤ በጣም መስራት መድከም ያስፈልጋል፡፡
የመስቀል ወፍና የመስቀል አበባ (አደይ አበባ) ከመስቀል ጋር የሚያገናኛቸው ምንድን ነው?
የአደይ አበባ በመስከረም ወር የሚታይ፣ ዝርያው በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ ልዩ የሆነ አበባ ነው፡፡ ብዙ ተመራማሪዎችም የሚሉት ይህንኑ ነው፡፡ አበባው ከመስከረም በኋላ ከስሞ ይጠፋል። የመስቀል ወፍም የመራቢያዋ ጊዜ ስለሆነ ብቅ የምትለው በመስከረም ወር አጋማሽ መስቀል ላይ ነው፡፡ ይህን አስመልክቶ አብዬ ለማ ምን አሉ?
የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ
ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ
ማን ያውቃል?
በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ወፏ መራባት የምትችለው በዚህ ወር ነው፡፡ ይህቺ የመስቀል ወፍ ዝርያዋ አስር አይነት እንደሆነ ተመራማሪዎች ይናገራሉ፡፡ በዚህ የመራቢያዋ ወቅት ብቅ ይላሉ፡፡ ወንዶቹ ወፎች ሙዚቃ እያሰሙ እየተሽኮረመሙ፣ ቀለማቸውን ቀይረው፣ ሴቷን የመስቀል ወፍ ያማልላሉ፡፡ አንገቷ አካባቢ የአደይ አበባ ቀለም ያላት፣ አብረቅራቂና ጅራተ ረጅም ቆንጆ ወፍ ናት፡፡ ከመስቀል ጋር ተያይዞ ስሟ የሚነሳውና ስያሜዋንም ያገኘችው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

Read 5701 times