Saturday, 07 October 2017 14:25

የኤድስ ወረርሽኝ ሥርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(7 votes)


-    በየዓመቱ 21ሺ የሚሆኑ ሰዎች በቫይረሱ ይያዛሉ፡፡ 60 በመቶ ያህሉ ሴቶች ናቸው
-    ዓምና ብቻ 20 ሺ የሚጠጉ ሰዎች በበሽታው ህይወታቸውን ማጣታቸው ይገመታል
-    በአዲስ አበባ ብቻ በየዓመቱ 4ሺ243 አዳዲስ ሰዎች በኤችይቪ ይያዛሉ
-    718ሺ500  ሰዎች ከቫይረሱ ጋር ይኖራሉ
በኢትዮጵያ የኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መሄዱና አገሪቱ በበሽታው ወረርሽኝ ውስጥ እንደምትገኝ ተጠቆመ፡፡ የፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ከበደ ወርቁ፣ ከትናንት በስቲያ፣ በባለድርሻ አካላት መካከል በተደረገው የምክክር ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት፤ የኤችአይቪ/ኤድስ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በአሁኑ ወቅት 718ሺ500 የሚሆኑ ዜጎች ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሲሆን መድኃኒቱን የሚወስዱት ግን ከ400 ሺ አይበልጡም፡፡ በቫይረሱ ከተያዙት ዜጎች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው ተብሏል፡፡
 በወሲብ ንግድ ሥራ ላይ ከተሰማሩት ሴቶች መካከል 25 በመቶ ያህሉ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንደሚገኝ የገለፁት ዶ/ር ከበደ፤አራት በመቶ የሚሆኑት በአገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚሰሩ ሾፌሮች የቫይረሱ ተጠቂዎች እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡ በየዓመቱ 21 ሺ አዳዲስ ሰዎች በቫይረሱ እንደሚያዙ የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፤ከእነዚህ መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውንና ከ15 እስከ 24 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙም ተናግረዋል፡፡ ለበሽታው ይሰጥ የነበረው ትኩረት በመቀዛቀዙ፣ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ወገኖች የፀረ ኤችአይቪ መድሃኒት ተጠቃሚ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ፣ከተወሰኑ አመታት በፊት ሲታይ የነበረው ከኤድስ ጋር የተያያዘው ህመምና ሞት በከፍተኛ ደረጃ በመቀነሱ ምክንያት፣ህብረተሰቡ ለበሽታው ይወስድ የነበረው ጥንቃቄ በመቀነሱ፣የቫይረሱ ስርጭት እንዲያገረሽ ምክንያት መሆኑን ዶ/ር ከበደ ገልፀዋል፡፡ ሁኔታው አሣሣቢ ደረጃ ላይ የደረሰ በመሆኑም ህብረተሰቡ፣በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
በፌደራል ኤችአይቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽ/ቤት፣ የዘርፈ ብዙ ምላሽ ማስተባበር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ክፍሌ ምትኩ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ በሽታው በአሁኑ ወቅት አሳሳቢ ከሚባል ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቁመው፣ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ይደረጉ የነበሩት የተለያዩ የውጪ ድርጅቶች እርዳታና ድጋፍ በመቋረጡ ምክንያት ስራው ተቀዛቅዞ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገው የውጪ እርዳታ መቋረጡን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ለመድኃኒት ግዥ የሚውለውም እርዳታ እየቀነሰ በመምጣቱ መጪውን ጊዜ እጅግ አሳሳቢ እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ ከቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፎች አብዛኛዎቹ በሽታው በአሁኑ ወቅት ያለበትን አሳሳቢ ደረጃ የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ በአገሪቱ ካሉት ክልሎች ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ ክልልና አዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው፣ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ወገኖች የሚኖሩባቸው ክልሎች መሆናቸውን ያመለከቱት ጥናቶቹ፤ በአራቱ ክልሎች ብቻ የሚገኙት የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ወገኖች በአጠቃላይ በአገሪቱ የሚገኙትን ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ወገኖች 82 በመቶ ያህሉን እንደሚሸፍኑ ጠቁመዋል፡፡  
በ2009 ዓ.ም ብቻ ከአጠቃላይ 19ሺ743 ሰዎች በኤድስ ሳቢያ እንደሞቱ እንደሚገመት የገለፀው ጥናቱ፤ ከእነዚህ መካከል 58 በመቶ ያህሉ ሴቶች መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም 3ሺ173 የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ0-14 ዓመት የሆናቸው ህፃናት መሆናቸውን በምክክር መድረኩ ላይ የቀረበው ጥናት ያመለክታል፡፡
በተለያዩ የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ለበሽታው ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ መሆኑን የጠቆሙት እነዚሁ ጥናቶች፤ የኤችአይቪ ስርጭቱም በዛው መጠን እየጨመረ መምጣቱ ተገልጿል፡፡ በሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች ላይ በተካሄደ ጥናት፤ከአንድ ሺ ሴት ተማሪዎች ስልሣ አምስት (65) ያህሉ  ውርጃ መፈጸማቸውንና ይህም የበሽታው ስርጭት እጅግ አሣሣቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አመላካች መሆኑ ተገልጿል፡፡ ለአብነትም በአንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ላይ በተካሄደ ጥናት፤አማካይ የስርጭት መጠኑ 3.8 በመቶ (በሴቶች 5.6%፣ በወንዶች 3%) መሆኑ ተገልጿል፡፡
ትላልቅ የልማት ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ዜጎች፤ለበሽታው ተጋላጭ መሆናቸው እየጨመረ መምጣቱን ያመለከቱት ጥናቶች፤ በአበባ እርሻ ልማት ውስጥ የሚሰሩ ሴቶች፣ ጥንቃቄ ለጎደለው የግብረ ስጋ ግንኙነት በመጋለጣቸው፣25.6 በመቶ ውርጃ መፈጸማቸውን ጠቁመዋል፡፡  
በፌደራል ኤችአይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ፅ/ቤትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት መካከል ሲካሄድ የዋለው የምክክር መድረክ፤ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባና ህብረተሰቡ ለበሽታው ያለውን ግንዛቤ በማሳደጉ ረገድ ከፍተኛ ጥረት መደረግ እንዳለበት አቋም ተይዞ ተጠናቋል፡፡
በዓለማችን እስካሁን ከ70 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በበሽታው መያዛቸውና 35 ሚሊዮን የሚሆኑት በዚሁ በሽታ ሣቢያ ህይወታቸውን ማጣታቸው ይታወቃል፡፡



Read 4925 times