Saturday, 07 October 2017 14:27

የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ፤ ለኢትዮ - ኤርትራ ግጭት መፍትሄ አፈላልጋለሁ አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(11 votes)

  ሰሞኑን በኤርትራ ጉብኝት ያደረጉ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ አመራሮችና አባላት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለው ቅራኔ የሚፈታበትን መንገድ እንደሚያፈላልጉ አስታወቁ።
የጉባኤው አመራሮች፣ በኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አቀባበልና መስተንግዶ የተደረገላቸው ሲሆን ከአስከፊው ጦርነት በኋላ ላለፉት አሥራ ሰባት አመታት በቅራኔ ውስጥ የቆዩት የኤርትራና የኢትዮጵያ መንግስታት ጉዳይ አሳሳቢ እንደሆነባቸው በውይይታቸው ወቅት ማንሳታቸው የዜና ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የሃይማኖት አባቶቹ በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰላም ሰፍኖ፣ ወንድማማችነት እንዲጠናከር ለፈጣሪ ፀሎት እንደሚያደርጉና የረጅም ጊዜ የድንበር ውዝግቡ የሚፈታበትንም መፍትሄ በማፈላለጉ ረገድ የራሳቸውን ድርሻ እንደሚወጡና ለእርቅ እንደሚንቀሳቀሱ አስታውቀዋል፡፡
በግጭቱና በተለያዩ ምክንያቶች ላለፉት አስር አመታት፣ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከዓለም ተገልላ መቆየቷን ያወሱት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ፣ የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ ዶ/ር ንጉሴ ለገሰ፣ በአስመራ አየር ማረፊያ ደማቅ አቀባበል እንደተደረገላቸው ለአፍሪካን ኒውስ ዶትኮም ገልፀዋል፡፡
በቆይታቸውም ከሃይማኖት አባቶችና ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን ዶ/ር ንጉሴ ጠቁመው፣ ስለ ውይይቱ በዝርዝር ከመግለፅ በመቆጠብ ውይይቱ ግን ገንቢ ነበር ብለዋል፡፡
የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ኤርትራ ከኢትዮጵያ መገንጠሏን ተከትሎ ራሷን የቻለች ሲሆን በአሁን ወቅት ወደ 2.5 ሚሊዮን ተከታይና ከ15 ሺህ በላይ ካህናት እንዳሏት ተጠቁሟል፡፡ ከ17 አመት በፊት የተከሰተው የኢትዮ - ኤርትራ ጦርነት፣ ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች ያለቁበት መሆኑ ይታወቃል፡፡

Read 3735 times