Saturday, 07 October 2017 14:27

“ሰማያዊ” ፓርቲ፤ ለጠ/ሚኒስትሩ አቤቱታ አቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(14 votes)

· “ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ህገ መንስታዊ መብቴ ተጥሷል”
· በአስተዳደሩ ላይ ክስ መስርቻለሁ ብሏል
     በነገው ዕለት በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ አቅዶ የነበረው “ሰማያዊ” ፓርቲ፤ ለሰልፉ እውቅና መከልከሉን ተከትሎ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አቤቱታ ያቀረበ ሲሆን ለተፈፀመብኝ የህግ ጥሰትና እንግልትም በጠቅላይ ፍ/ቤት ክስ መስርቻለሁ ብሏል፡፡
ፓርቲው የሰላማዊ ሰልፍ እውቅና መከልከሉን አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ለአፈጉባኤ አባ ዱላ ገመዳ፣ ለፌዴሬሽን ም/ቤት አፈጉባኤ አቶ ያለው አባተና ለከንቲባ ድሪባ ኩማ በየአድራሻቸው በፃፈው የአቤቱታ ደብዳቤው፤ “ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ህገ መንግስታዊ መብቴ ተጥሷል፤ የመድብለ ፓርቲ ስርአቱም አደጋ ላይ ወድቋል” ብሏል፡፡
በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ያቀደው መስከረም 14 ቀን 2010 ዓ.ም የነበረ ቢሆንም በኢሬቻ እና በመስቀል በዓል ምክንያት ቀን እንዲለውጥ ከእውቅና ሰጪ አካሉ በቀረበለት ሃሳብ መሰረት፤ ቀኑን ለውጦ ለነገ መስከረም 28 ሰልፉን ለማካሄድ ዕቅድ መያዙን የጠቆመው “ሰማያዊ”፤ ግልፅ ባልሆነ ምክንያት ከአስተዳደሩ እውቅና ሊሰጠው እንዳልቻለ አመልክቷል፡፡
ፓርቲው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በፃፈው ደብዳቤ፤ “መንግስትዎ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ህገ መንግስታዊ መብታችንን እየገፈፈን ነው” ሲል አማሯል፡፡ “ህዝብ ውስጥ ገብቶ የፖለቲካ ስራ እንዳይሰራም የሰላማዊ ትግል በሮች በሙሉ እየተዘጉ፣ አላንቀሳቅስ ብለውኛል” ሲል እንዳሉት ፓርቲው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በፃፈው አቤቱታ ላይ ጠቅሷል፡፡
“የህዝቡን ብሶት አደባባይ ይዘን ለመውጣት፣ ለአዲስ አበባ መስተዳደር የምናቀርበው የእውቅና ጥያቄ አይቋረጥም” ያለው ፓርቲው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በጉዳዩ ጣልቃ ገብተው ህገ መንግስቱን እንዲያስከብሩ ጠይቋል፡፡
በተመሳሳይ “ሰማያዊ” ለፓርላማው አፈጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ በፃፈው የአቤቱታ ደብዳቤ፤ በህገ መንግስቱ የተቀመጠውን ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት ድንጋጌ በመጣስ፣ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን እያጠበበ መሆኑን በመጥቀስ፣ በፓርላማው በተሰጣቸው ኃላፊነት ተጠቅመው፣ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ እንዲገቡ ጠይቋል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት፤ ህገ መንግስቱን የመተርጎምና የማስከበር ኃላፊነት ስላለበት የም/ቤቱ አፈጉባኤ አቶ ያለው አባተም በጉዳዩ ጣልቃ ገብተው ህግ እንዲያስከብሩ ከፓርቲው ተጠይቀዋል፡፡
“በሰማያዊ ፓርቲ የትግል እንቅስቃሴ ላይ የሰሞኑን የአዲስ አበባ መስተዳደር ተፅዕኖ እጅግ የከፋ ሆኖ አግኝቼዋለሁ” ያለው ፓርቲው፤ የመስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ጉዳዩን በጥልቀት እንዲያጤኑትና ለሰላማዊ ሰልፉ ጥያቄም ተገቢውን አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጡ በፃፈው ደብዳቤ ጠይቋል፡፡ ችግሩን በንግግርና በውይይት ለመፍታትም ከንቲባው ቀጠሮ እንዲሰጧቸው ተማፅነዋል - የፓርቲው አመራሮች፡፡
ለአራቱ የመንግስት አካላት ከተፃፉት የአቤቱታ ደብዳቤዎች ጋር የሰላማዊ ሰልፉን እውቅና ጥያቄ አስመልክቶ የተፃፃፏቸው አምስት ያህል ደብዳቤዎች፣ በአባሪነት መያያዛቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ፓርቲው እስካሁን ለተፈፀመበት የህግ ጥሰትና እንግልትም ከሰሞኑ በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት፣ በአስተዳደሩ ላይ ክስ መመስረቱን አስታውቋል፡፡
ፓርቲው በሰላማዊ ሰልፉ፤ የኑሮ ውድነትን፣ የዜጎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው መፈናቀል ጉዳይንና በሀገሪቱ የሚስተዋሉ ፖለቲካዊ ችግሮችን በተመለከተ ድምፅ ለማሰማት አቅዶ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡ “ሰማያዊ” የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመነሳቱ አንድ ሳምንት በፊት አንስቶ አዋጁ ከተነሳ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርግ መግለፁ ይታወሳል፡፡


Read 5538 times