Saturday, 07 October 2017 14:30

የኦሮሚያ - ሶማሌ አዋሳኝ ግጭት ምርት ወደ ውጪ እንዳይላክ እክል ፈጥሯል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(54 votes)

· “ግጭቱን የሚያባብሱና ህዝብን የሚያጋጩ ህጋዊ እርምጃ ይወሰድባቸዋል”
· የሶማሌ ክልል፤ ከኦሮሚያ ጋር ለተፈጠረው ግጭት “መንስኤዎችን” ለየሁ አለ
· “ግጭቱ ሙሉ ለሙሉ እንዲቆም የማረጋጋትና ሰላም የማስፈን ስራዎች
• ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው” ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ
· የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የምርመራ ሪፖርት ሰሞኑን ይቀርባል

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና ሌሎች የፌደራል ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፤ የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልል ባለስልጣናትንና የሀገር ሽማግሌዎችን በግጭቱ ዙሪያ ሰሞኑን በድጋሚ ያወያዩ ሲሆን ግጭቱ የሀገሪቱን ምርት ወደውጪ በመላክ ላይ ጭምር እክል መፍጠሩን በመጠቆም፣ ሰላምና መረጋጋት በአፋጣኝ እንዲሰፍን አሳስበዋል።
ከትናንት በስቲያ የጠ/ሚኒስትር ፅ/ቤት ባወጣው መግለጫ፤ በግጭቱ ወቅት የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈፀሙ አካላትን ወደ ህግ በማቅረብ በኩል የፌደራል መንግስቱ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ጠ/ሚኒስትሩ መናገራቸውን ጠቁሞ በግጭቱ የተፈናቀሉ ዜጎች ተመልሰው እንዲቋቋሙና የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችን የመምከርና የማስታረቅ ስራ መስራት እንዳለባቸው ማሳሰባቸውንም አመልክቷል፡፡
ውይይቱን የተከታተሉት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው፤ ግጭቱ አሁን ያለበትን ደረጃ የሚያሳይ ሪፖርት በውይይት መድረኩ ላይ መቅረቡን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡ በግጭቱ አካባቢዎች በሚገኙ ኬላዎች ተሽከርካሪዎች እንዳያልፉ መደረጉን ተከትሎ፣ የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ ችግር መፈጠሩ  መታወቁን የጠቆሙት ዶ/ር ነገሪ፤ ከዚህ በኋላ የየትኛውም ክልል የፀጥታ አካል ኬላ አቁሞ እንዳይፈተሽ ትዕዛዝ መተላለፉን ተናግረዋል፤ ይህን ስራ የመቆጣጠር ተግባርም የፌደራል የፀጥታ አካላት መሆኑንም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡ በዚሁ የውይይት መድረክ ላይ በግጭቱ የተፈናቀሉ ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ፣ የተዘረፈ ንብረታቸው እንዲመለስ፣ ያለዚያም ካሳ እንዲከፈላቸው እንደሚደረግም ዶ/ር ነገሪ አስታውቀዋል፡፡  የተፈናቀሉትን መልሶ የማቋቋምና አስፈላጊውን ከለላ የመስጠት ኃላፊነቱም ዜጎች የተፈናቀሉባቸው ክልሎች እንዲሆን መወሰኑንና የየክልሎቹን አመራሮችም ይህን ለመፈፀም ቃል መግባታቸውን ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም እንደ ማንኛውም ዜጋ ጥበቃ ስለሚደረግላቸው ለደህንነታቸው ሳይሰጉ ወደየተመደቡበት ዩኒቨርሲቲዎች ገብተው እንዲማሩ ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡
የሁለቱም ክልሎች አመራር አባላት፣ ለግጭቱ መንስኤ የሆኑ አካላትን በማጋለጥ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ያሉት ዶ/ር ነገሪ፤ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች የሚመሯቸውና የሁለቱም ክልል ህዝቦች የሚሳተፉባቸው ህዝባዊ ጉባኤዎች በተከታታይ እንደሚደረጉም አውስተዋል፡፡   
በሌላ በኩል የሶማሌ ክልላዊ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ባወጣው መግለጫ፣ የክልሉ አስተዳደሮችና የሀገር ሽማግሌዎች በጋራ ባካሄዱት ስብሰባ ለግጭቱ መነሻ ናቸው ያሏቸውን ሶስት ጉዳዮች ተለይተዋል ብሏል፡፡
በመግለጫው መንስኤ ተብለው ከተጠቀሱት መካከልም መሬትን በኃይል የመውሰድ ፍላጎት፣ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ የማስገባት ፍላጎትና የፌደራል ስርአቱን የማፈራረስና የደርግ ስርአትን የመመለስ ፍላጎት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በኩል በመኖሩ ነው ይላል፡፡
የመንግስት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው፤ በአሁን ወቅት ግጭቱን የሚያባብስና ህዝብን የሚያጋጭ መረጃ በማንኛውም መገናኛ ብዙሃንም ሆነ ግለሰብ እንዳይተላለፍ አቅጣጫ መቀመጡን አስታውቀው፣ መመሪያውን ተላልፈው ግጭቱን የብሄር ግጭት አስመስለው የሚያናፍሱ የኮሚኒኬሽን አካላትና መገናኛ ብዙኃን ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ በድጋሚ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በበኩሉ፤ በሁለቱ ክልል አዋሳኝ አካባቢ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ፣ የምርመራ ቡድን ወደ ስፍራው ልኮ፣ የግጭቱን መንስኤና የደረሰውን ጉዳት ሲያጣራ መሰንበቱን የገለጸ ሲሆን ምርመራውን እያጠናቀቀ በመሆኑ፣ ውጤቱን በጥቂት ቀናት ውስጥ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት እንደሚያቀርብ፣ የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደምሰው በንቲ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡



Read 6331 times